ምዕራፍ 15
ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት መገዛት የሚያስገኘው ጥቅም
የይሖዋን ፈቃድ በተደራጀ ሁኔታ ማከናወን እንድንችል የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ለሆነው አምላክ መገዛት ይኖርብናል። የአምላክ ልጅ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደሆነ የምንገነዘብ ከመሆኑም ሌላ በሌሎች የሕይወታችን ዘርፎችም የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት ለማክበር ጥረት እናደርጋለን። ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት መገዛት ለሁላችንም ጥቅም ያስገኛል።
2 ለተገቢው አካል መገዛትን የሚመለከት መመሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰው ልጅ የተሰጠው በኤደን ገነት ውስጥ ነው። ይህ መመሪያ በዘፍጥረት 1:28 እና 2:16, 17 ላይ በሚገኙት የአምላክ ትእዛዛት ውስጥ ተካትቶ ይገኛል። እንስሳት ለሰዎች መገዛት የነበረባቸው ሲሆን አዳምና ሔዋን ደግሞ ለአምላክ ፈቃድና ሥልጣን መገዛት ነበረባቸው። ለአምላክ ሥልጣን መገዛት ሰላምና ሥርዓት እንዲሰፍን ያደርጋል። የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት ከጊዜ በኋላ በ1 ቆሮንቶስ 11:3 ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ” ሲል ጽፏል። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ከይሖዋ በቀር ለራስነት ሥልጣን መገዛት የማያስፈልገው አካል የለም።
3 በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት አይቀበሉም ወይም አያከብሩም። ለምን? ይህ ችግር የጀመረው የሰው ዘር ወላጆች በኤደን ገነት ውስጥ ሉዓላዊ ለሆነው አምላክ የራስነት ሥልጣን ለመገዛት አሻፈረን ባሉ ጊዜ ነው። (ዘፍ. 3:4, 5) ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጋቸው የተሻለ ነፃነት አላስገኘላቸውም። ከዚህ ይልቅ የአንድ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ይኸውም የሰይጣን ዲያብሎስ ተገዢዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የመጀመሪያው ዓመፅ የሰው ዘር ከአምላክ እንዲርቅ አድርጓል። (ቆላ. 1:21) በዚህም የተነሳ በዛሬው ጊዜ አብዛኛው የሰው ዘር በክፉው ቁጥጥር ሥር ይገኛል።—1 ዮሐ. 5:19
4 እኛ ግን የአምላክን ቃል እውነት በመማራችንና የተማርነውን ተግባራዊ በማድረጋችን ከሰይጣን ተጽዕኖ መላቀቅ ችለናል። ራሳችንን የወሰንንና የተጠመቅን የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት እንቀበላለን። “ከሁሉም በላይ ከፍ ከፍ ያልክ ራስ ነህ” በማለት ስለ ይሖዋ የተናገረውን የንጉሥ ዳዊትን ሐሳብ እንጋራለን። (1 ዜና 29:11) አዎ፣ በትሕትና እንደሚከተለው ብለን እንናገራለን፦ “ይሖዋ፣ አምላክ መሆኑን እወቁ። የሠራን እሱ ነው፤ እኛም የእሱ ንብረት ነን። እኛ ሕዝቡና የማሰማሪያው በጎች ነን።” (መዝ. 100:3) ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ይሖዋ ታላቅ እንደሆነና ለእሱ ሙሉ በሙሉ ልንገዛለት እንደሚገባ እንገነዘባለን። (ራእይ 4:11) የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለአምላክ በመገዛት ረገድ ፍጹም ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተላለን።
5 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ከደረሰበት መከራ ምን ተምሯል? ዕብራውያን 5:8 “ልጅ ቢሆንም እንኳ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። አዎ፣ ኢየሱስ መከራ ቢደርስበትም በሰማይ ለሚኖረው አባቱ በታማኝነት ተገዝቷል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ፣ በራሱ ተነሳስቶ ያደረገው አንዳች ነገር የለም። ምንም ነገር ከራሱ አመንጭቶ አልተናገረም፤ እንዲሁም ለራሱ ክብር ለማግኘት አልሞከረም። (ዮሐ. 5:19, 30፤ 6:38፤ 7:16-18) ኢየሱስ ያከናወነው አገልግሎት ተቃውሞና ስደት ቢያስከትልበትም የአባቱን ፈቃድ በመፈጸሙ ደስታ አግኝቷል። (ዮሐ. 15:20) ኢየሱስ ለአምላክ መገዛትን የመረጠ ሲሆን “ራሱን ዝቅ በማድረግ . . . በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል።” ራሱን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ማስገዛቱ ብዙ በረከት አምጥቷል፤ የሰው ልጆች የዘላለም መዳን እንዲያገኙና አባቱ ክብር እንዲጎናጸፍ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ለእሱም ከፍ ያለ ቦታ አስገኝቶለታል።—ፊልጵ. 2:5-11፤ ዕብ. 5:9
ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት ተገዢ መሆናችንን የምናሳይባቸው መስኮች
6 የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ለእሱ ስንገዛ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ከሚያጋጥማቸው ጭንቀትና ግራ መጋባት እንጠበቃለን። ጠላታችን ዲያብሎስ ምንጊዜም እኛን የሚውጥበት አጋጣሚ ይፈልጋል። ሰይጣንን ከተቃወምንና ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለይሖዋ በፈቃደኝነት ከተገዛን ከክፉው እጅ እንድናለን።—ማቴ. 6:10, 13፤ 1 ጴጥ. 5:6-9
7 ክርስቶስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደሆነና ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ ሥልጣን እንደሰጠው አምነን እንቀበላለን። ይህ ደግሞ አንዳችን ለሌላው በሚኖረን አመለካከትና በምናሳየው ምግባር ላይ ለውጥ ያመጣል። አምላክ በጉባኤ ውስጥ ላቋቋመው ሥልጣን መገዛታችን በሁሉም የአምልኳችን ዘርፍ ለአምላክ ቃል ታዛዥ እንድንሆን ይገፋፋናል። ይህ ታዛዥነት በአገልግሎት መካፈልን፣ ስብሰባ ላይ መገኘትንና ተሳትፎ ማድረግን፣ ከሽማግሌዎች ጋር ተባብሮ መሥራትን እንዲሁም ለድርጅታዊ አሠራሮች ታዛዥ መሆንን ይጨምራል።—ማቴ. 24:45-47፤ 28:19, 20፤ ዕብ. 10:24, 25፤ 13:7, 17
8 ለአምላክ መገዛታችን የክርስቲያን ጉባኤ ሰላም የሰፈነበት፣ በሥርዓት የተደራጀና የተረጋጋ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። የይሖዋ አገልጋዮች የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 14:33, 40) በግለሰብ ደረጃ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የተመለከትነው ነገር ንጉሥ ዳዊት የተሰማው ዓይነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። ዳዊት በይሖዋ አገልጋዮችና በክፉዎች መካከል ያለውን ጉልህ ልዩነት ከተመለከተ በኋላ “አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” ሲል በአድናቆት ተናግሯል።—መዝ. 144:15
9 በትዳርና በቤተሰብ ተቋም ውስጥ ‘የሴት ራስ ወንድ ነው።’ ወንዶች ለክርስቶስ መገዛት ያለባቸው ሲሆን የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ ነው። (1 ቆሮ. 11:3) ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲሁም ልጆች ለወላጆቻቸው መገዛት ይጠበቅባቸዋል። (ኤፌ. 5:22-24፤ 6:1) እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት ሲያከብር ቤቱ ሰላም የሰፈነበት ይሆናል።
10 አንድ ባል የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል የራስነት ሥልጣኑን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ሊጠቀምበት ይገባል። (ኤፌ. 5:25-29) የራስነት ሥልጣኑን አላግባብ ከመጠቀም ወይም ይህን ኃላፊነቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚቆጠብ ከሆነ ሚስቱና ልጆቹ በደስታ ይገዙለታል። የሚስት ሚና ረዳት ወይም ማሟያ መሆን ነው። (ዘፍ. 2:18) አንዲት ሚስት፣ ባሏን በትዕግሥት የምትደግፍና የምታከብር ከሆነ በባሏ ዘንድ ሞገስ ታገኛለች፤ እንዲሁም አምላክ እንዲወደስ ታደርጋለች። (1 ጴጥ. 3:1-4) ባለትዳሮች መጽሐፍ ቅዱስ የራስነት ሥልጣንን አስመልክቶ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ሲያደርጉ ለአምላክ በመገዛት ረገድ ለልጆቻቸው ምሳሌ ይሆናሉ።
ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት መገዛት መላ ሕይወታችንን የሚነካ ጉዳይ ነው
11 ለአምላክ መገዛታችን ‘አንጻራዊ ቦታቸውን ከአምላክ ላገኙት የበላይ ባለሥልጣናት’ በሚኖረን አመለካከት ላይም ለውጥ ያመጣል። (ሮም 13:1-7) ክርስቲያኖች ሕግ አክባሪ ዜጎች ስለሆኑ የሚጠበቅባቸውን ግብር ይከፍላሉ፤ በዚህ መንገድ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ” ይሰጣሉ። (ማቴ. 22:21) በተጨማሪም የአገልግሎት ክልሎችን ለመሸፈን የሚያደርጉት ዝግጅት ለአካባቢው ከሚሠሩ የመረጃ ጥበቃ ሕጎች ጋር ይስማማል። ከይሖዋ የጽድቅ ሕግ ጋር የሚጋጭ ሕግ እስካላወጡ ድረስ ሥልጣን ለተሰጣቸው አካላት በሁሉም ነገር መገዛታችንና መታዘዛችን ትኩረታችንን በስብከቱ ሥራ ላይ እንድናደርግና ኃይላችንን ለዚህ ሥራ እንድናውል ያስችለናል።—ማር. 13:10፤ ሥራ 5:29
12 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት መገዛት መላ ሕይወታችንን የሚነካ ጉዳይ ነው። ወደፊት የሰው ልጆች በሙሉ ለይሖዋ አምላክ የሚገዙበትን ቀን በእምነት ዓይናችን እናያለን። (1 ቆሮ. 15:27, 28) የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት በደስታ የሚቀበሉና ለዘላለም ለእሱ የሚገዙ ሰዎች እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ያገኛሉ!