አምላካዊ ተገዥነት ምን ይፈልግብናል?
“እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ።” — ያዕቆብ 4:7
1. የምናመልከው አምላክ ምን ዓይነት ስለመሆኑ ምን ሊባል ይቻላል?
ይሖዋ እንዴት ያለ አስደናቂ አምላክ ነው! አቻ፣ ተወዳዳሪና እኩያ የሌለው፣ በብዙ መንገዶችም ልዩ የሆነ አምላክ ነው። እርሱ የሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነ ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ነው። ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር ከመሆኑም በላይ ታላቅ ግርማ የተጎናጸፈ ስለሆነ ማንም ሰው አይቶት በሕይወት ሊኖር አይችልም። (ዘጸአት 33:20፤ ሮሜ 16:26) ፍርዱ ፍጹም የሆነ፣ ፍቅርን የተላበሰና ለጥበቡና ለኃይሉ ዳርቻ የሌለው አምላክ ነው። እርሱ ፈጣሪያችን፣ ፈራጃችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ንጉሣችን ነው። መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእርሱ ይመጣል። — መዝሙር 100:3፤ ኢሳይያስ 33:22፤ ያዕቆብ 1:17
2. አምላካዊ ተገዥነት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?
2 እነዚህን ሁሉ ማስረጃዎች ስንመለከት ለእርሱ የመገዛት ግዴታ ያለብን ስለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ይህስ ምን ማድረግ አለብን ማለት ነው? በርካታ ነገሮችን። ይሖዋ አምላክን በዓይናችን ልናየው ስለማንችል አንድ ሰው ለእርሱ መገዛቱ የሠለጠነ ሕሊናው የሚነግረውን መስማትን፣ ከአምላክ ምድራዊ ድርጅት ጋር መተባበርን፣ የዓለማዊ ባለሥልጣኖችን ሥልጣን መቀበልንና በቤተሰብ ክልል ውስጥም የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት ማክበርን ይጠይቅብናል።
ሁል ጊዜ ጥሩ ሕሊና መያዝ
3. ጥሩ ኅሊና እንዲኖረን ለምን ዓይነት እገዳዎች መታዘዝ አለብን?
3 ጥሩ ሕሊና ይዘን ለመኖር ሰብአዊ ሕግ አስከባሪዎች ሊያስከብሩ ለማይችሉአቸው ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መገዛት አለብን። ለምሳሌ ያህል መመኘትን የሚከለክለው የአሥርቱ ትዕዛዛት አሥረኛ ትዕዛዝ በሰብአዊ ባለሥልጣኖች ሕግ አስከባሪነት ሊፈጸም አይችልም ነበር። ማንም ሰብአዊ ሕግ አውጪ ህጉ ቢጣስ ቅጣት ሊበይን የማይችልበትን ሕግ ስለማያወጣ ይህ ሕግ ራሱ አሥርቱ ትእዛዛት ከአምላክ የመነጩ ለመሆናቸው ምስክር ነው። እያንዳንዱ እሥራኤላዊ ጥሩ ሕሊና እንዲኖረው ከፈለገ በዚህ ሕግ አማካኝነት የራሱ ፖሊስ የመሆንን ኃላፊነት ይሖዋ አምላክ ሰጥቶታል። (ዘጸአት 20:17) በተመሳሳይም አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት እንዳይወርስ ከሚከለክሉት የሥጋ ሥራዎች መካከል ሰብአዊ ዳኞች ቅጣት ሊያስፈጽሙ የማይችሉባቸው ስሜቶች ይኸውም “ምቀኝነት እና “ቅናት” ይገኙባቸዋል። (ገላትያ 5:19–21) እኛ ግን ጥሩ ሕሊና ይዘን ለመኖር እነዚህን ማስወገድ አለብን።
4. ጥሩ ኅሊና ይዘን ለመኖር በየትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እየተመራን መኖር አለብን?
4 አዎ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተመራን መኖር አለብን። እነዚህም መሠረታዊ ሥርዓቶች ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙሴ ሕግ ውስጥ የትኛው እንደሚበልጥ ተጠይቆ በሰጠው መልስ ላይ በተናገራቸው ሁለት ትዕዛዞች ሊጠቃለሉ ይችላሉ። “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። . . . ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:36–40) ከእነዚህ ትዕዛዛት በሁለተኛው ትዕዛዝ ውስጥ የተካተቱትን ሊያጠቃልሉ የሚችሉት በማቴዎስ 7:12 ላይ የተመዘገቡት “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ናቸው።
5. ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን ለመቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
5 ሰዎች ቢያዩንም ባያዩንም ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር ማድረግና ስህተት እንደሆነ ከምናውቀው ነገር መራቅ አለብን። ይህም ማድረግ የሚገባንን ነገር ሳናደርግ ቀርተንም ሆነ ማድረግ የሌለብንን ነገር አድርገን በሰዎች ተጠያቂ ከመሆን ልናመልጥ ብንችልም እንኳን ተፈጻሚነት ያለው ነው። ይህ ማለትም ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 4:13 ላይ “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” በማለት የገለጸውን ማስጠንቀቂያ በማስታወስ ከሰማያዊ አባታችን ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን መቀጠል ማለት ነው። ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ መጽናታችን የዲያብሎስን የተንኮል ዘዴዎች ለመዋጋት፣ የዓለምን ተጽእኖ ለመቋቋምና ከወረስነው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ጋር ለመዋጋት ያስችለናል። — ከኤፌሶን 6:11 ጋር አወዳድር።
ለአምላክ ድርጅት መገዛት
6. ይሖዋ ከክርስትና ዘመን በፊት በነበሩት ዘመናት ምን የሐሳብ መገናኛ መሥመሮችን ተጠቅሞአል?
6 ይሖዋ አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን እንዴት አድርገን ልንሠራባቸው እንደምንችል በግላችን የመወሰንን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ለእኛ አልተወውም። ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ጀምሮ አምላክ ሰዎችን የሐሳብ መገናኛ መሥመር አድርጎ ሲጠቀም ቆይቷል። አዳም ለሔዋን የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ሠርቷል። ከተከለከለው ዛፍ አትብሉ የሚለው ትዕዛዝ ለአዳም የተሰጠው ሔዋን ከመፈጠሯ በፊት ነበር። ስለዚህ አምላክ ምን ፈቃድ እንዳለው አዳም ለሔዋን ነግሯት መሆን አለበት። (ዘፍጥረት 2:16–23) ኖኅ ለቤተሰቡና የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት ለነበረው ዓለም የአምላክ ነቢይ ነበር። (ዘፍጥረት 6:13፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) አብርሃም ለቤተሰቡ የአምላክ ቃል አቀባይ ነበር። (ዘፍጥረት 18:19) ለእሥራኤል ሕዝብ የአምላክ ነቢይና የሐሳብ ማስተላለፊያ መሥመር የነበረው ሙሴ ነበር። (ዘጸአት 3:15, 16፤ 19:3, 7) ከእርሱ በኋላ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ አምላክ ከሕዝቡ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ በብዙ ነቢያት፣ ካህናትና ነገሥታት ተጠቅሞአል።
7, 8. (ሀ) መሢሑ ከመጣ በኋላ የአምላክ ቃል አቀባይ በመሆን ያገለገሉት እነማን ነበሩ? (ለ) በዛሬው ጊዜ አምላካዊ ተገዥነት ከይሖዋ ምስክሮች ምን ይጠይቅባቸዋል?
7 መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ አምላክ እርሱንና እርሱን ይከተሉ የነበሩትን ሐዋርያትና ታማኝ ደቀ መዛሙርትን በቃል አቀባይነት እንዲያገለግሉት ተጠቅሞባቸዋል። በኋላም የኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡአን ታማኝ ተከታዮች የይሖዋ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው እንዴት ሊሠሩባቸው እንደሚገባ የአምላክን ሐሳብ ለማስተላለፍ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመሆን ማገልገል ነበረባቸው። አምላካዊ ተገዥነት ይሖዋ አምላክ እየተጠቀመበት የነበረውን የሐሳብ ማስተላለፊያ መሣሪያ መቀበልን የሚጠይቅ ነው። — ማቴዎስ 24:45–47፤ ኤፌሶን 4:11–14
8 በአሁኑ ጊዜ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ግንኙነት የሚያደርግና በእነዚህ ምስክሮች የአስተዳደር አካል የተወከለ መሆኑን ተጨባጩ ሁኔታ ያሳያል። ይህ አካል በአካባቢ ደረጃ ለሥራው አመራር እንዲሰጡ የተለያየ ማዕረግ ያላቸውን የበላይ ተመልካቾች ይኸውም ሽማግሌዎችና ተጓዥ ተወካዮች የመሳሰሉትን ይሾማል። አምላካዊ ተገዥነት ሕይወቱን ለአምላክ የወሰነ እያንዳንዱ ምስክር “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ” ከሚለው በዕብራውያን 13:17 ላይ ከሚገኘው መመሪያ ጋር በመስማማት ለእነዚህ የበላይ ተመልካቾች እንዲገዛ ይጠይቅበታል።
ተግሳጽን መቀበል
9. አምላካዊ ተገዥነት ብዙውን ጊዜ ምን ማድረግን ይጠይቃል?
9 አምላካዊ ተገዥነት ብዙውን ጊዜ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ከሚያገለግሉት የሚሰጠውን ተግሳጽ መቀበልን ይጠይቃል። ለራሳችን የሚያስፈልገንን ተግሳጽ ሁልጊዜ ራሳችን የማንሰጥ ከሆነ እኛን ለመምከርና ለመገሰጽ ተሞክሮና ሥልጣን ባላቸው ሰዎች ምክርና ተግሳጽ እንዲሰጠን ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነቱን ተግሳጽ መቀበል የጥበብ መንገድ ነው። — ምሳሌ 12:15፤ 19:20
10. ተግሳጽ የሚሰጡ ሽማግሌዎች ምን ግዴታ አለባቸው?
10 ተግሳጽ የሚሰጡ ሽማግሌዎች ራሳቸው የአምላካዊ ተገዥነት ምሳሌ መሆን እንዳለባቸው ግልጽ ነው። እንዴት? በገላትያ 6:1 መሠረት ጥሩ የምክር አሰጣጥ ዘዴ ሊኖራቸው የሚገባ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ምሳሌ መሆንም ይኖርባቸዋል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ [የተሳሳተ እርምጃ ቢወስድ አዓት] መንፈሳውያን የሆናችሁ [መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ አዓት] እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።” በሌላ አነጋገር የሽማግሌው ምክር ከራሱ ምሳሌነት ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት። ይህም በ2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25 እና በቲቶ 1:9 ላይ ከተሰጠው ምክር ጋር የሚስማማ ነው። አዎ፣ ተግሳጽ ወይም እርማት የሚሰጡ ሰዎች ሸካራ እንዳይሆኑ በጣም መጠንቀቅ አለባቸው። ሁልጊዜ በአያያዛቸው የማያስጨንቁና ደጎች መሆን ቢኖርባቸውም የአምላክን ቃል የሚያስከብሩ መሆን ይኖርባቸዋል። የደካሞችንና ሸክማቸው የከበደባቸውን ሰዎች መንፈስ የሚያነቃቁና የማያዳሉ አድማጮች መሆን ይኖርባቸዋል። — ከማቴዎስ 11:28–30 ጋር አወዳድር።
ለበላይ ባለሥልጣኖች መገዛት
11. ክርስቲያኖች ከዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ምን ይፈለግባቸዋል?
11 አምላካዊ ተገዥነት ለዓለማዊ ባለ ሥልጣኖችም እንድንታዘዝ ይጠይቅብናል። በሮሜ 13:1 ላይ “ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” በማለት ተመክረናል። እነዚህ ቃሎች ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 13:7 ላይ እንደገለጸው የትራፊክ ሕጎችን እንድንታዘዝና ግብርና ቀረጥን በመክፈል ረገድ ትጉዎች እንድንሆንም ይጠይቁብናል።
12. ለቄሣር መገዛታችን ገደብ ያለው የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
12 ለቄሣር የምናደርገው እንዲህ ዓይነቱ ተገዥነት ገደብ ያለው መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 22:21 ላይ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት የገለጸውን መሠረታዊ ሥርዓት ምን ጊዜም ማስታወስ አለብን። በኦክስፎርድ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን እስኮፌልድ ስታዲ ባይብል ላይ የሮሜ 13:1 የግርጌ ማስታወሻ “ይህ ማለት ክርስቲያኑ ብልግና ያለባቸውን ወይም ጸረ ክርስቲያን የሆኑ ደንቦችን ይታዘዛል ማለት አይደለም። በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ ከሰዎች ይልቅ ለአምላክ መታዘዝ የክርስቲያኑ ግዴታ ነው (ሥራ 5:29፤ ከዳንኤል 3:16–18 እና 6:10 ጋር አወዳድር)” በማለት ይገልጻል።
አምላካዊ ተገዥነት በቤተሰብ ክልል
13. አምላካዊ ተገዥነት በቤተሰብ ክልል ውስጥ ከአባሎቹ ምን ማድረግን ይጠይቅባቸዋል?
13 በቤተሰብ ክልል ውስጥ ባልና አባት የሆነው ወንድ በራስነት ያገለግላል። ይህም ሚስቶች በኤፌሶን 5:22, 23 ላይ የተሰጠውን “ሚስቶች ሆይ፣ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ . . . ባል የሚስት ራስ ነውና” የሚል ምክር እንዲቀበሉ ይጠይቅባቸዋል።a ልጆችም ጳውሎስ በኤፌሶን 6:1–3 ላይ “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት” በማለት እንደገለጸው ለአባታቸውና ለእናታቸው አምላካዊ ተገዥነትን ያሳያሉ እንጂ የራሳቸውን ሕግ አያወጡም።
14. አምላካዊ ተገዥነት የቤተሰብ ራሶች ምን እንዲያደርጉ ይጠይቅባቸዋል?
14 እርግጥ ባሎችና አባቶች ራሳቸው አምላካዊ ተገዥነትን የሚያሳዩ ሲሆኑ ሚስቶችና ልጆች እንዲህ ዓይነቱን አምላካዊ ተገዥነት በሥራ ለማዋል ቀላል ይሆንላቸዋል። ባሎችና አባቶች ይህን አምላካዊ ተገዥነት የሚያሳዩት በኤፌሶን 5:28, 29፤ 6:4 ላይ “እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና . . . እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሳጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” በማለት እንደተገለጸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በመስማማት የራስነት ሥልጣናቸውን ሲሠሩበት ነው።
አምላካዊ ተገዥነትን ለማሳየት የሚረዱን ነገሮች
15. አምላካዊ ተገዥነትን እንድናሳይ የሚረዳን የትኛው የመንፈስ ፍሬ ነው?
15 በእነዚህ ልዩ ልዩ መስኮች አምላካዊ ተገዥነትን እንድናሳይ የሚረዳን ምንድን ነው? አንደኛው ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ነው። ለይሖዋ አምላክና የበላይ አድርጎ ላስቀመጣቸው ሰዎች የምናሳየው ፍቅር ነው። በ1 ዮሐንስ 5:3 ላይ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” ተብሎ ተነግሮናል። ኢየሱስ በዮሐንስ 14:15 ላይ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” በማለት ይህንኑ ቁም ነገር ተናግሯል። በእርግጥም ፍቅር ይሖዋ ለእኛ ያደረገልንን ሁሉ እንድናደንቅና አምላካዊ ተገዥነትን እንድናሳይ ይረዳናል። — ገላትያ 5:22
16. አምላካዊ ተገዥነትን ለማሳየት አምላካዊ ፍርሃት ምን እርዳታ ይሰጣል?
16 ሁለተኛው፣ አምላካዊ ፍርሃት ወይም ፈሪሃ አምላክ ነው። ይሖዋ አምላክን ላለማሳዘን መፍራት ‘ክፋትን መጥላት ማለት ስለሆነ’ ይረዳናል። (ምሳሌ 8:13) ይሖዋን ላለማሳዘን መፍራታችን ሰውን በመፍራት አቋማችንን እንዳናላላ እንደሚጠብቀን አያጠራጥርም። በተጨማሪም ምንም ዓይነት ችግር ቢደርስብንም የአምላክን መመሪያ እንድንታዘዝ ይረዳናል። በተጨማሪም ኃጢአት የሆነውን ነገር እንድንሠራ ለሚፈታተነን ዝንባሌ እንዳንሸነፍ ይጠብቀናል። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማረድ እንዲቃጣ ያስቻለው ይሖዋን መፍራት እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች ይገልጻሉ። ዮሴፍም የጶጢፋር ሚስት ያመጣችበትን የብልግና ግፊት በተሳካ ሁኔታ እንዲቋቋም ያስቻለው ይሖዋን እንዳያሳዝን የነበረው ፍርሃት ነበር። — ዘፍጥረት 22:12፤ 39:9
17. አምላካዊ ተገዥነትን በማሳየት ረገድ እምነት ምን ሚና ሊጫወት ይችላል?
17 በዚህ ረገድ የሚረዳን ሦስተኛው ነገር በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ነው። እምነት በምሳሌ 3:5, 6 ላይ የተሰጠውን “በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን ምክር ለመከተል ያስችለናል። በተለይም በደል የተፈጸመብን ሲመስለን፣ ወይም በዘራችን ወይም በብሔራችን ወይም በግል አለመግባባት ምክንያት ልዩነት የተደረግብን መስሎ ሲሰማን እምነት ይረዳናል። አንዳንዶች ደግሞ ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ሆነው እንዲሾሙ ለማህበሩ የድጋፍ ሐሳብ ሳይላክላቸው ሲቀር ችላ እንደተባሉ ይሰማቸው ይሆናል። እምነት ካለን ይሖዋ ራሱ በወሰነው ጊዜ ነገሮችን እስኪያስተካክል ድረስ እንጠብቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን ትዕግስትን እየኮተኮትን መጽናት ሊያስፈልገን ይችላል። — ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26
18. አምላካዊ ተገዥነትን እንድናሳይ የሚረዳን አራተኛ ነገር ምንድን ነው?
18 አራተኛው የሚረዳን ነገር ትሕትና ነው። ትሑት ሰው ራሱን ዝቅ በማድረግ ‘ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ስለሚቆጥር’ አምላካዊ ተገዥነትን ለማሳየት አይቸገርም። ትሑት ሰው ‘የሌላው የበታች’ ለመሆን ፈቃደኛ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:2–4፤ ሉቃስ 9:48) ኩሩ ሰው ግን መገዛትን ስለማይወድ ይናደዳል። ኩሩ ሰው እርማት ተቀብሎ ሕይወቱን ከሚያድን ይልቅ ውዳሴ አግኝቶ ቢሞት ይመርጣል ተብሎ ይነገራል።
19. የቀድሞው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ምን የትሕትና ምሳሌ አሳይቷል?
19 የመጠበቂያ ግንብ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ሁለተኛ ፕሬዘዳንት የነበረው ጆሴፍ ራዘርፎርድ የትሕትናና የአምላካዊ ተገዥነት ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ሂትለር በጀርመን የይሖዋ ምስክሮችን ሥራ ባገደበት ጊዜ በዚያ አገር የነበሩት ወንድሞች ስብሰባዎቻቸውና የስብከት ሥራቸው ስለታገዱ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በመጠየቅ ደብዳቤ ጻፉለት። ለቤቴል ወንድሞች ይህንን ጥያቄያቸውን ካነበበላቸው በኋላ በእገዳው ምክንያት የጀርመን መንግሥት በጀርመን ወንድሞች ላይ ሊያመጣባቸው ከሚችለው ከፍተኛ ቅጣት አንጻር ምን እንደሚላቸው እንደማያውቅ ሳይሸሽግ ነገራቸው። የጀርመን ወንድሞች ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሚያውቅ ሰው ካለ ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑን ተናገረ። እንዴት ያለ የትሕትና መንፈስ ነበር!b
አምላካዊ ተገዥነትን ከማሳየት የሚመጡ ጥቅሞች
20. አምላካዊ ተገዥነትን ከማሳየት የሚመጡ በረከቶች ምንድን ናቸው?
20 አምላካዊ ተገዥነትን ከማሳየት የሚመጡ ጥቅሞች ምንድን ናቸው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ጥቅሞቹ በእርግጥ ብዙ ናቸው። በራሳቸው መንገድ በመመራት የሚኖሩ ሰዎች ከሚያጋጥማቸው ጭንቀትና ብስጭት እንድናለን። ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እናገኛለን። ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ኅብረት ይኖረናል። በተጨማሪም ሕግ አክባሪ በመሆናችን ከመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ጋር የማያስፈልግ ግጭት ከመፍጠር እንድናለን። በባልነትና በሚስትነት፣ በወላጅነትና በልጅነት ቦታችን ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ ይኖረናል። ከዚህም በላይ አምላካዊ ተገዥነትን እያሳየን ስንኖር በምሳሌ 27:11 ላይ ከተሰጠው “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው” ከሚለው ምክር ጋር ተስማምተን እንኖራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ አቅኚ አገልጋይ ስለሚስቱ አክባሪነት እርሷ ስለምታደርግለት ፍቃራዊ ድጋፍ በማመስገን ለአንድ ያላገባ አቅኚ ይናገራል። ነጠላው አቅኚ ስለሌሎች ጠባዮቿስ ለምን አልተናገረም ብሎ በልቡ አሰበ። አያሌ ዓመታት አልፈው ነጠላ የነበረው አቅኚ ራሱ ካገባ በኋላ ግን ሚስት የምትሰጠው ፍቅራዊ ድጋፍ በትዳር ውስጥ ለሚገኝ ደስታ የቱን ያህል አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተገነዘበ።
b ከብዙ ጸሎትና ከብዙ የአምላክ ቃል ጥናት በኋላ ጆሴፍ ራዘርፎርድ በጀርመን ላሉት ወንድሞች ምን ብሎ መልስ እንደሚሰጣቸው በግልጽ ተገነዘበ። ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው የሚነግራቸው እርሱ አለመሆኑን አወቀ። በስብሰባና በመመስከር ረገድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በግልጽ የሚነግራቸው የአምላክ ቃል ነው። ስለዚህ የጀርመን ወንድሞች በድብቅ ለመሥራት ተገደዱ። አንድ ላይ መሰብሰብንና ስለ ይሖዋ ስምና ስለ መንግሥቱ መመስከርን በሚመለከት የይሖዋን ትእዛዝ መታዘዛቸውን ቀጠሉ።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ አምላክ የሐሳብ መገናኛ መስመሮች አድርጎ የተጠቀመው በየትኞቹ ሰዎች ነው? አገልጋዮቹስ ምን ሊያሳዩአቸው ይገባ ነበር?
◻ አምላካዊ ተገዥነት በሥራ ላይ የሚውለው በምን የተለያዩ የግንኙነት መስኮች ነው?
◻ አምላካዊ ተገዥነትን እንድናሳይ የሚረዱን የትኞቹ ጠባዮች ናቸው?
◻ አምላካዊ ተገዥነት ምን በረከቶችን ያስገኛል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ከሕዝቡ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ በኢየሩሳሌም የቤተ መቅደስ ድርጅት ተጠቅሞአል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላካዊ ተገዥነትን ልናሳይ የምንችልባቸው መስኮች