አምላካዊ ተገዥነት—ለምንና በእነማን?
“አቤቱ [ይሖዋ ሆይ ] የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” — ኤርምያስ 10:23
1. በብዙ ቦታዎች ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ለምን ዓይነት ነፃነቶች ነው?
እጅግ በጣም ከታወቁት ሰብአዊ ሰነዶች አንዱ 13ቱ የሰሜን አሜሪካ የብሪታንያ ቅኝ ግዛቶች በ18ኛው መቶ ዘመን ከእናት አገራቸው ከብሪታንያ መገንጠላቸውን ያወጁበት የነፃነት አዋጅ ነው። ነፃነትንና ከውጭ ተጽዕኖ ተላቀው በራሳቸው መመራትን ፈልገው ነበር። በራስ መመራትና ነፃነት ደግሞ ጎን ለጎን የሚሄዱ ነገሮች ናቸው። ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል። በቅርብ ጊዜያት አንዳንድ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ፖለቲካዊ ነፃነት አግኝተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አገሮች ያገኙት ነፃነት ብዙ አሳሳቢ ችግሮችንም ይዞ እንደመጣ ሊካድ አይገባም።
2, 3. (ሀ) ሊያምረን የማይገባ ምን ዓይነት ነፃነት ነው? (ለ) ይህ ሐቅ በመጀመሪያ ጠንከር ተደርጎ የተገለጸው እንዴት ነው?
2 ልዩ ልዩ የነፃነት ዓይነቶች ማራኪ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ልንመኘው የማይገባን አንድ ዓይነት ነፃነት አለ። እርሱ ምንድን ነው? የሰው ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ነፃ መሆን ነው። ከይሖዋ አምላክ ነፃ መሆን በረከት ሳይሆን እርግማን ነው። ለምን? ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሱት የነቢዩ ኤርምያስ ቃላት በግልጽ እንደሚያሳዩት ሰው ከፈጣሪው ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ራሱን ችሎ እንዲኖር ስላልተፈጠረ ነው። በሌላ አነጋገር ሰው ለፈጣሪው እየተገዛ እንዲኖር የተፈጠረ ነው። ለፈጣሪያችን መገዛት ማለት ለእርሱ ታዛዥ መሆን ማለት ነው።
3 ይህ ሐቅ በዘፍጥረት 2:16, 17 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ለመጀመሪያዎቹ ሰብአውያን ባልና ሚስት በተሰጣቸው የይሖዋ ትዕዛዝ ላይ ጠንከር ተደርጎ ተገልጿል:- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” አዳም ለፈጣሪው ለመገዛት እምቢተኛ መሆኑ ለራሱና ለዘሮቹ ኃጢአትን፣ ስቃይንና ሞትን አመጣባቸው። — ዘፍጥረት 3:19፤ ሮሜ 5:12
4, 5. (ሀ) ሰዎች ለአምላክ ለመገዛት እምቢተኛ መሆናቸው ያስገኘው ውጤት ምንድን ነው? (ለ) ማምለጥ የማይቻለው የትኛውን የሥነ ምግባር ሕግ ነው?
4 ሰዎች ለፈጣሪያቸው ለመገዛት እምቢተኛ መሆናቸው ጥበብ የጎደለውና ከሥነ ምግባር አንፃርም ስህተት ነው። ይህም አድራጎት በዓለም ላይ ሕገ ወጥነትን፣ ወንጀልን፣ ዓመፅንና የፆታ ብልግናን ከነፍሬዎቹ ማለትም በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን አስከትሎአል። በተጨማሪም ተስፋፍቶ የሚገኘው የወጣቶች ወንጀል በአብዛኛው ሊመጣ የቻለው ወጣቶች ለይሖዋ፣ ለወላጆቻቸውና ለአገራቸው ሕግ ለመታዘዝ እምቢተኞች በመሆናቸው ምክንያት አይደለምን? ይህ በራስ የመመራት መንፈስ ብዙ ሰዎች በሚከተሉት እንግዳ በሆነና ደስ በማይል አለባበስ እንዲሁም ጸያፍ በሆነው አነጋገራቸው ይገለጻል።
5 ይሁን እንጂ “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና” ከሚለው ከማይሻረው የፈጣሪ የሥነ ምግባር ሕግ ማንም ሊያመልጥ አይችልም። — ገላትያ 6:7,8
6, 7. ለመገዛት አሻፈረኝ ማለትን የሚያመጣው መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ይህስ በምን ምሳሌዎች ታይቷል?
6 ለዚህ ሁሉ የመገዛት እምቢተኝነት ሥረ መሠረት የሆነው ምክንያት ምንድን ነው? በቀላል አነጋገር ራስ ወዳድነትና ኩራት ነው። የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን በእባቡ ለመታለል የፈቀደችውና ከተከለከለው ፍሬ ለመብላት የቻለችው ለዚህ ነው። ቦታዋንና አቅሟን የምታውቅና ትሑት ብትሆን ኖሮ መልካምና ክፉ ምን እንደሆነ ለራሷ በመወሰን እንደ አምላክ እንድትሆን የቀረበላት ፈተና ባልማረካት ነበር። ከዚህ ሌላ ራስ ወዳድ ባትሆን ኖሮ ፈጣሪዋ በሆነው በይሖዋ አምላክ በግልጽ የተከለከለውን ነገር ባልፈለገች ነበር። — ዘፍጥረት 2:16, 17
7 ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት ብዙም ሳይቆይ ኩራትና ራስ ወዳድነት ቃየን ወንድሙን አቤልን እንዲገድለው አድርጎታል። በተጨማሪም አንዳንድ መላእክት በራሳቸው ፈቃድ በመመራት የመጀመሪያ ሥልጣናቸውን ትተው ስሜታዊ ደስታን ለማግኘት ሥጋ እንዲለብሱ ያደረጋቸው ራስ ወዳድነት ነበር። ናምሩድን ያነሳሳው ኩራትና ራስ ወዳድነት ሲሆን ይህ ጠባይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተነሱት አብዛኞቹ የዓለም መሪዎች ዓይነተኛ ባሕርይ ሆኗል። — ዘፍጥረት 3:6, 7፤ 4:6–8፤ 1 ዮሐንስ 3:12፤ ይሁዳ 6
ለይሖዋ አምላክ የመገዛት ግዴታ ያለብን ለምንድን ነው?
8-11. አምላካዊ ተገዥነትን የምናሳይባቸው አራት ኃይለኛ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
8 ለፈጣሪያችን ለይሖዋ አምላክ የመገዛት ግዴታ ያለብን ለምንድን ነው? በመጀመሪያ እርሱ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ስለሆነ ነው። የሥልጣን ሁሉ ሕጋዊ ባለመብትነትን የጨበጠው እርሱ ነው። ፈራጃችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ንጉሣችን ነው። (ኢሳይያስ 33:22) ስለ እርሱ “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ተብሎ በትክክል ተገልጿል። — ዕብራውያን 4:13
9 ከዚህም በላይ ፈጣሪያችን ሁሉን ማድረግ የሚችል ስለሆነ እርሱን በመቃወም የሚሳካለት ፍጡር የለም፤ ለእርሱ ለመገዛት ያለበትን ግዴታ ችላ ለማለት የሚችል ፍጡር የለም። በጥንት ዘመን በነበረው ፈርዖን ላይ እንደደረሰበትና ወደፊትም አምላክ በወሰነው ጊዜ በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ እንደሚደርስበት ሁሉ ለአምላክ ለመገዛት አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች ሁሉ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ከባድ ኀዘን ይመጣባቸዋል። — መዝሙር 136:1, 11–15፤ ራእይ 11:17፤ 20:10, 14
10 የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡበት ዓላማ ፈጣሪያቸውን ለማገልገል ስለሆነ መገዛት ግዴታቸው ነው። ራእይ 4:11 “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” በማለት ይናገራል። እርሱ ታላቅ ሸክላ ሠሪ ነው። ዓላማውን ለማስፈጸም እንዲያገለግሉ ሰብዓዊ የሸክላ ዕቃዎችን ሠርቷል። — ኢሳይያስ 29:16፤ 64:8
11 ፈጣሪያችን ከማንም የበለጠ ጥበበኛ ስለሆነ ለእኛ ከሁሉ የተሻለውን የሚያውቅ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። (ሮሜ 11:33) ሕጎቹ የተሰጡት ‘ለራሳችን ጥቅም’ ነው። (ዘዳግም 10:12, 13) ከሁሉ በላይ ደግሞ “እግዚአብሔር ፍቅር” ስለሆነ ለእኛ የሚመኝልን ከሁሉ የተሻለውን ብቻ ነው። ፈጣሪያችን ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ለመገዛት የሚገፋፉ ምንኛ ብዙ ምክንያቶች አሉን! — 1 ዮሐንስ 4:8
በአምላካዊ ተገዥነት ፍጹም ምሳሌ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ተገዥነት ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የኢየሱስን የተገዥነት አቋም የሚያሳዩት የትኞቹ የኢየሱስ ቃላት ናቸው?
12 ያላንዳች ጥርጥር ለአምላካዊ ተገዥነት ፍጹም ምሳሌ የሚሆነን የይሖዋ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2:6–8 ላይ ይህን ቁምነገር በመጥቀስ እንዲህ ይላል:- “[ኢየሱስ] በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ [በተጨማሪም] በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት (በመከራ እንጨት ላይ ለመሞት አዓት) እንኳ የታዘዘ ሆነ።” ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከራሱ አመንጭቶ ምንም ነገር እንደማያደርግ በተደጋጋሚ ገልጿል። ምንጊዜም ለሰማያዊ አባቱ በመገዛት ቀጠለ እንጂ በራሱ ፈቃድ በመመራት የሠራው ነገር አልነበረም።
13 በዮሐንስ 5:19, 30 ላይ እንደሚከተለው እናነባለን:- “ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፣ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።” በተመሳሳይም ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት ምሽት “አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን” እያለ ደጋግሞ ይጸልይ ነበር። — ማቴዎስ 26:39, 42, 44፤ በተጨማሪም ዮሐንስ 7:28፤ 8:28, 42 ተመልከት።
ለአምላካዊ ተገዥነት በድሮ ዘመን የነበሩ ምሳሌዎች
14. ኖኅ አምላካዊ ተገዥነት ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
14 ለአምላካዊ ተገዥነት ምሳሌ ከሚሆኑን የቀድሞ ሰዎች መካከል አንዱ ኖኅ ነው። ኖኅ ተገዥነቱን በሦስት መንገዶች አሳይቷል። አንደኛ ከእውነተኛው አምላክ ጋር በመመላለስ በዘመኑ በነበሩት ሰዎች መካከል ጻድቅና እንከን የሌለው ሰው በመሆን። (ዘፍጥረት 6:9) ሁለተኛ መርከቡን በመሥራት። ኖኅ “እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:22) ሦስተኛ “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆን ስለ መጪው የውኃ መጥለቅለቅ ማስጠንቀቂያ በመስጠት። — 2 ጴጥሮስ 2:5
15, 16. (ሀ) በአምላካዊ ተገዥነት በኩል አብርሃም ምን ጥሩ ምሳሌ አሳይቷል? (ለ) ሣራ ተገዥነትን ያሳየችው እንዴት ነበር?
15 ሌላው አምላካዊ ተገዥነትን በማሳየት በኩል የላቀ ምሳሌ የተወልን አብርሃም ነው። “ከአገርህ . . . ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ” ብሎ ይሖዋ የሰጠውን ትዕዛዝ በመፈጸም ተገዥነቱን አሳይቷል። (ዘፍጥረት 12:1) ይህም በዑር የነበረውን ምቹ መኖሪያ ትቶ ለመቶ ዓመታት በባዕድ ምድር በዘላንነት እየተዘዋወረ መኖር ማለት ነበር። (የመሬት ቁፋሮ ጥናት እንደሚያሳየው ዑር ቀላል ግምት የሚሰጣት ከተማ አልነበረችም።) በተለይም አብርሃም ለአምላክ ተገዥነቱን ያሳየው ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛነቱን የሚጠይቅ ታላቅ ፈተና ሲቀርብለት እሺ ብሎ በመቀበሉ ነበር። — ዘፍጥረት 22:1–12
16 የአብርሃም ሚስት ሣራ አምላካዊ ተገዥነትን በማሳየት ሌላዋ መልካም ምሳሌያችን ናት። ወደ ማታውቀው አገር ሄዳ መንከራተቷ ብዙ የምቾት ማጣት እንዳስከተለባት ጥርጥር የሌለው ቢሆንም እንዳማረረች የሚገልጽ ነገር የትም ቦታ ላይ ተጽፎ አናገኝም። አብርሃም በአረማዊ ገዥዎች ፊት እህቱ እንደሆነች አድርጎ ሁለት ጊዜ ሲያቀርባት በሁለቱም ወቅቶች መልካም የሆነ የአምላካዊ ተገዥነት ምሳሌ አሳይታለች። ምንም እንኳን በመታዘዟ ከአረማውያን ገዥዎቹ ብዙ ሚስቶች ጋር ለመቆጠር ምንም ያህል ያልቀራት ቢሆንም አብርሃምን ተባብራዋለች። ለአምላካዊ ተገዥነቷ ምስክር የሚሆነው ባሏን በልቧ “ጌታዬ” ብላ መጥራቷ ነው። ይህም የልቧን ውስጣዊ ዝንባሌ ያሳያል። — ዘፍጥረት 12:11–20፤ 18:12፤ 20:2–18፤ 1 ጴጥሮስ 3:6
17. ይስሐቅ አምላካዊ ተገዥነትን አሳይቷል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
17 የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ የተወልን የአምላካዊ ተገዥነት ምሳሌም ችላ ተብሎ የማይታለፍ ነው። አብርሃም ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርበው ይሖዋ ባዘዘበት ጊዜ ይስሐቅ የ25 ዓመት ጎልማሳ እንደነበረ የአይሁድ አፈታሪክ ያመለክታል። ይስሐቅ ቢፈልግ ኖሮ በመቶ ዓመት የሚበልጠውን አባቱን አብርሃምን ከኃይል አንፃር ሊቋቋመው ይችል ነበር። ነገር ግን እንዲህ አላደረገም። ለመስዋዕት የሚሆን እንስሳ አለመኖሩ ቢያስገርመውም አባቱ በመሠዊያው ላይ ሲያጋድመውና ለማረድ ቢላዋውን ሲያሳርፍበት በደመ ነፍስ እንዳይፈራገጥ ለማገድ ወይም ለመቆጣጠር እጅና እግሩን ሲያስረው ለአባቱ በየዋህነት እሺ ብሏል። — ዘፍጥረት 22:7–9
18. ሙሴ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አምላካዊ ተገዥነት ያሳየው እንዴት ነበር?
18 ከብዙ ዓመታት በኋላም ሙሴ ለአምላካዊ ተገዥነት ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ነበረ” ተብሎ መገለጹ አምላካዊ ተገዥነቱን እንደሚያመለክት ጥርጥር የለውም። (ዘኁልቁ 12:3) ምንም እንኳን ሁለት ወይም ሦስት ሚልዮን የሚያህሉ አመፀኛ ሰዎችን በበላይነት ይመራ የነበረ ቢሆንም የይሖዋን ትዕዛዛት ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በታዛዥነት መፈጸሙ ለአምላካዊ ተገዥነቱ ተጨማሪ ምስክር ነው። በመሆኑም “ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ” የሚል ቃል እናነባለን። — ዘጸአት 40:16
19. ኢዮብ ምን ብሎ በመናገር ለይሖዋ ተገዥ መሆኑን አሳይቷል?
19 ለአምላካዊ ተገዥነት በጣም ጥሩ ምሳሌ የተወልን ሌላው ታዋቂ ሰው ኢዮብ ነው። ሰይጣን የኢዮብን ንብረት በሙሉ እንዲጠራርግበት፣ ልጆቹን እንዲገድልበትና “ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል እንዲመታው” ይሖዋ ከፈቀደ በኋላ የኢዮብ ሚስት “እስከ አሁን ድረስ ፍጹምነትህን [ፍጹም አቋም ጠባቂነትህን አዓት] ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። ሆኖም ኢዮብ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ሁሉ ተቀበልን፣ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?” ብሎ በመመለስ ለአምላክ ተገዥነቱን አሳይቷል። (ኢዮብ 2:7–10) “እነሆ፣ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግስት እጠባበቃለሁ” የሚሉት በኢዮብ 13:15 ላይ ያሉት ቃሎቹም ይህንኑ አቋሙን የሚገልጹ ናቸው። ምንም እንኳን ኢዮብን በጣም ያሳሰበው የራሱን ጻድቅነት የማረጋገጡ ጉዳይ ቢሆንም በመጨረሻው ይሖዋ ከሐሰተኛ አጽናኞቹ ለአንዱ “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል” እንዳለው መዘንጋት የለብንም። ያለጥርጥር ኢዮብ ለአምላካዊ ተገዥነት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። — ኢዮብ 42:7
20. ዳዊት አምላካዊ ተገዥነቱን ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
20 ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተጨማሪ አንድ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀስ ያህል ዳዊትም አለ። ንጉሥ ሳኦል እንደሚታደን እንስሳ ሲያሳድደው ዳዊት እርሱን በመግደል ከችግሩ ሊገላገል የሚችልባቸው ሁለት አጋጣሚዎች አግኝቶ ነበር። ሆኖም ዳዊት ለአምላክ የነበረው ተገዥነቱ ሳኦልን ከመግደል እንዲገታ አድርጎታል። በ1 ሳሙኤል 24:6 ላይ “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] የቀባው ነውና እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ [ይሖዋ አዓት] እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው” በማለት የተናገራቸውን ቃሎቹን እናነባለን። (በተጨማሪም 1 ሳሙኤል 26:9–11ን ተመልከት።) እንደዚሁም ስህተት ወይም ኃጢአት በፈጸመ ጊዜ ተግሳጽ ሲሰጠው አምላካዊ ተገዥነቱን አሳይቷል። — 2 ሳሙኤል 12:13፤ 24:17፤ 1 ዜና መዋዕል 15:13
የጳውሎስ የተገዥነት ምሳሌ
21-23. ሐዋርያው ጳውሎስ አምላካዊ ተገዥነትን ያሳየው በምን የተለያዩ ጊዜያት ነው?
21 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ለአምላካዊ ተገዥነት የላቀ ምሳሌ ያሳየውን ሐዋርያው ጳውሎስን እናገኛለን። በሌሎች የሐዋርያዊ አገልግሎቱ ገጽታዎች በሙሉ ጌታውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደመሰለ ሁሉ በአምላካዊ ተገዥነትም መስሎታል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ይሖዋ ከሌሎች ሐዋርያት ሁሉ በበለጠ ሁኔታ የተጠቀመበት ቢሆንም ጳውሎስ በራሱ ፈቃድ እየተመራ የሚሄድ ሰው አልነበረም። ወደ ክርስትና ለተለወጡ አሕዛብ ግዝረት ስለማስፈለጉ ጥያቄ በተነሳ ጊዜ “ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያትና ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ” በማለት ሉቃስ ይነግረናል። — ሥራ 15:2
22 የጳውሎስን የሚስዮናዊነት ሥራ በተመለከተ በገላትያ 2:9 ላይ “የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፣ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን” የሚል እናነባለን። ጳውሎስ በራሱ ሐሳብ ከመመራት ይልቅ አመራር ለማግኘት ይፈልግ ነበር።
23 በተመሳሳይም ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በነበረበት የመጨረሻ ጊዜ የሙሴን ሕግ የካደ አለመሆኑን ሰው ሁሉ እንዲያይ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ የሥዕለትን ሥርዓት እንዲፈጽም በሽማግሌዎች የተሰጠውን ምክር ተቀብሏል። እንዲህ ማድረጉ የሕዝብ ረብሻን ያስነሳበት መሆኑን ስናይ ለሽማግሌዎቹ ምክር ተገዥ መሆኑ ስህተት ነበርን? በሥራ 23:11 ላይ “በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ:- ጳውሎስ ሆይ፣ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮምም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ” የሚለውን ቃል በማንበብ በግልጽ እንደምንረዳው ለሽማግሌዎቹ ምክር መገዛቱ ፈጽሞ ስህተት አልነበረም።
24. በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ተገዥነትን በተመለከተ የሚብራሩት ምን ተጨማሪ ገጽታዎች ናቸው?
24 በእርግጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተገዥዎች እንድንሆን የሚያስችሉንን ኃይለኛ ምክንያቶችንና እንዲህ ዓይነቱን ተገዥነት ያሳዩ ሰዎችን አስደናቂ ምሳሌነት ያቀርቡልናል። በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ለይሖዋ አምላክ ልንገዛ የምንችልባቸውን የተለያዩ መስኮች፣ ለመገዛት የሚያግዙንን ነገሮችና ከመገዛት የሚገኙትን በረከቶች እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ሊያምረን የማይገባ ምን ዓይነት ነፃነት ነው?
◻ ለመገዛት እንቢተኛ መሆን ምንጩ ምንድን ነው?
◻ ለይሖዋ የመገዛት ግዴታ ያለብን በምን ምክንያቶች የተነሳ ነው?
◻ ስለ አምላካዊ ተገዥነት ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ጥሩ ምሳሌዎች ይሰጣሉ?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናምሩድ፣ ለአምላክ በመገዛት ላይ ለማመጽ የመጀመሪያ የሆነው ዓለማዊ ገዥ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኖኅ፣ ለአምላካዊ ተገዥነት እንከን የሌለው ምሳሌ ያሳየው ሰው።— ዘፍጥረት 6:14, 22