የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
አኗኗራቸውን ለወጡ
በመንገድ ዳር ለሌሎች ሲናገሩ፣ ከቤት ወደ ቤት እያንኳኩ ሰዎችን ሲጠይቁ ወይም በመንግሥት አዳራሾቻቸው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ እንዳየሃቸው ጥርጥር የለውም። ተገቢ የሆነ አለባበስና ጥሩ የጸጉር አበጣጠር ስላላቸው ወጣት የይሖዋ ምስክሮች መናገራችን ነው። ምስክሮች የሆኑት ወላጆቻቸው ምስክሮች እንዲሆኑ ስላስተማሯቸው ነው ብለህ ትደመድም ይሆናል። በአብዛኞቻቸው ረገድ ይህ እውነት ነው። በሌላ በኩል ግን ከእነዚህ ወጣቶች መካከል በጣም የተለየ አስተዳደግ የነበራቸውና ከዚህ በፊት አሁን ከሚኖሩት ሕይወት ጨርሶ የተለየ አኗኗር የነበራቸው አንዳንድ ወጣቶች አሉ። እንዲያውም በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚታዩት ወጣቶች ወንጀልና በአደንዛዥ መድኃኒት ያለአግባብ መጠቀም የየዕለት ተግባራቸው ከሆኑ ቡድኖች ጋር የሚተባበሩ ነበሩ። ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲለውጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? በኖርዌይ ያለች አንዲት ከተማን እንጎብኝና እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ ካደረጉት አንዳንድ ወጣቶች ጋር እንገናኝ።
ለለውጡ መሠረት የሆነው ነገር
ሁለት ምሥክሮች ከቤት ወደቤት ሲሄዱ አኔቴን ሲያገኟት የ19 ዓመት ወጣት ነበረች። ያለፈውን አስታውሳ ስትናገር “ከይሖዋ ምስክሮች ጋር እንዳልነጋገር ብዙ ጊዜ ተነግሮኝ ነበር፤ እኔ ግን የማወቅ ጉጉት አድሮብኝ ነበርና እንዲገቡ ጋበዝኳቸው” ትላለች። ከ11 ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ አደንዛዥ ዕፅ ትወስድ ነበር፤ በአያሌ ቤት ሰብሮ የመግባት ወንጀሎችና የመኪና ስርቆት ተካፋይ ሆና ነበር።
የመንግሥቱ ምስራች ማረካት። በተለይ ደግሞ በአምስት ዓመት ዕድሜዋ እናቷን በሞት ስላጣች የትንሳኤ ተስፋ አጽናናት። ስለዚህ ነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት የቀረበላትን ጥያቄ ተቀበለችና በስብሰባዎች ለመገኘት ወደ መንግሥት አዳራሹ መምጣት ጀመረች። ለወንድ ጓደኛዋና ለሌሎችም ያወቀችውን ነገረቻቸው። የእነርሱስ ምላሽ ምን ነበር? እነርሱ ይህን ነገር በፍጹም እንደማይፈልጉትና እርሷም አእምሮዋ እየታጠበ እንዳለ አምርረው ነገሯት። ሆኖም በዚያን ጊዜ በጣም ከተቃወሟት መካከል አንዳንዶቹ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።
ለምሳሌ ያህል የ20 ዓመት ጎረምሳ የሆነውን ኤስፔንን እንውሰድ። የመንግሥቱን ምሥራች ከአኔቲ የወንድ ጓደኛ ሰማና ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ፈለገ። ይሁን እንጂ አደንዛዥ ዕፅን በድብቅ በማስተላለፍ ወንጀልና እንደ አኔቲም በብዙ ቤት ሰብሮ በመግባት ወንጀሎች ተካፋይ ሆኖ ስለነበር የአራት ወር እሥራት ፍርዱን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ነበር። በተጨማሪም ትንባሆ፣ ማሪዋናና ሌሎችንም አደንዛዥ ዕፆች ይወስድ ነበር። ታዲያ በእንዲህ ዓይነት ነገሮች ተጠላልፎ የነበረውን ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲጀምር ሊያደርገው የቻለው ነገር ምን ነበር? ኤስፔን አኗኗሩ ባዶና ዓላማ ቢስ መሆኑን ተገነዘበ። እንዲህ ይላል:- “ለሕይወቴ ዓላማ የሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ የወደፊት ተስፋ ማረከኝ። ስለዚህ የተነገረኝ ነገር እውነት መሆኑን ለማወቅ ማጥናት ጀመርኩ።”
ሌሎች ሰዎችም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ፈለጉ
በዚሁ ጊዜ ላይ ከቡድናቸው ውስጥ እንደ እነርሱ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ ያለ አንድ ሰው የምሥራቹን ሰማና እርሱም ማጥናትና ወደ መንግሥት አዳራሹ መምጣት ጀመረ። ከዚህም በመቀጠል ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዱ ከሆነ ከሌላው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረና እርሱም በስብሰባዎች መገኘት ጀመረ። ጥቂት ቆይቶ አሁንም አንድ ሌላ ወጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ከጓደኞቹ ጋር መካፈልና መንፈሳዊ መሻሻል ማድረግ ጀመረ። ከዚያ በኋላም አሁንም ሌላው ጓደኞቹ በማድረግ ላይ ባሉት ለውጥ በመደነቅ ብዙም ሳይቆይ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ፈለገ።
አሁን ደግሞ በዚያው ቡድን ውስጥ ያለ ጊልበርት የሚባል አንድ ወጣት ሙዚቀኛ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ሁለቱም ወላጆቹ በካንሰር በሽታ ሞተውበታል፤ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ የትንሳኤ ተስፋ ተጽናና። (ዮሐንስ 5:28, 29) ማሪዋና የሚወስድና ብልሹ ሕይወት የሚመራ ነበር፤ በሮክ ሙዚቃ ኮከብ ለመሆንም ምኞት ነበረው። ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ጥሩ መንፈሳዊ መሻሻል አደረገና ወዲያው የይሖዋ ምስክር ለመሆን ወሰነ። በመጨረሻም የኤስፔን ታናሽ ወንድም መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርና ከምስክሮቹ ጋር መቀራረብ ጀመረ።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሕይወትን ይለውጣል
ደስ የማይል አለባበስና የተንጨባረረ ጠጉር የነበራቸው እንዲሁም በአደንዛዥ ዕጾች፣ በስርቆትና በሌሎችም ወንጀሎች ተካፋይ የነበሩ እነዚህ ወጣቶች በአኗኗራቸው ከፍተኛ ለውጥ አድርገዋል። አኔቲ ጥሩ የመንግሥት አስፋፊ ስትሆን ለአንድ ዓመት ያህል በአቅኚነት አገልግላለች። ኤስፔንና ጊልበርት ረዳት አቅኚዎች በመሆን የሚያገለግሉ ሲሆን ዲያቆናትም ጭምር ናቸው። ሁለቱም ከክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አግብተዋል። ከቀድሞው ቡድን ውስጥ የቀሩት አራቱ ደግሞ ቀናተኛ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው።
ኤስፔን ሊታሠር የነበረው የአራት ወር የእሥራት ፍርድስ ምን ሆነ? በሕይወቱ ውስጥ ባደረገው ለውጥ ምክንያት ፍርዱ ወደ 80 ሰዓት ሕዝባዊ ሥራ ተለወጠለት። በፖሊስና በሌሎችም ስምምነት እነዚህን ሰዓቶች በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ እየሠራ አሳለፋቸው። ፖሊሶች በዚህ ዝግጅት በጣም ደስ አላቸው።
አዎ፣ በዓለም ዙሪያ የወንጀለኝነት ታሪክ የነበራቸው ብዙ ሌሎች ወጣቶች አሉ። የአምላክ ቃል እውነት ግን ለትልልቆቹ ጥያቄዎቻቸው መልስና ለወደፊቱ ጊዜም የተረጋገጠ ተስፋ ሰጣቸው። ስለዚህ አሁን ወንጀለኞች ወይም አደንዛዥ ዕፅ ወሳጆች አይደሉም፤ ደስ የማይል ልብስ ለብሰውም አይሄዱም። አኗኗራቸውን በመለወጣቸው ከላይ እንደተጠቀሱት ዓይነት ሰዎች ሆነዋል። ጥሩ የጠጉር አያያዝ ያላቸውና ተግተው የሚሠሩ የይሖዋ ምስክር የሆኑ ወጣቶች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወጣቶችን ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች የመጽሐፍ ቅዱስን ዘላቂ መፍትሔ ለሌሎች ለማሳወቅ ይፈልጋሉ። — 1 ቆሮንቶስ 6:9–11ን ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤስፔን፣ አኔቲና ጊልበርት