የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • od ምዕ. 16 ገጽ 162-168
  • አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአስተሳሳብ ለውጥ
  • ዓለም አቀፋዊ አንድነታችንን መጠበቅ
  • አንዳችን ለሌላው አሳቢነት ማሳየት
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተለየ ሕዝብ
  • ሌሎችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • አሁን እየተገነባ ያለው የአዲሲቱ ዓለም መሠረት
    አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?
  • እውነተኛ ክርስቲያናዊ አንድነት—እንዴት?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
  • “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ”
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2013
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
od ምዕ. 16 ገጽ 162-168

ምዕራፍ 16

አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር

እስራኤላውያን ለ1,500 ዓመታት ያህል በይሖዋ ስም የሚጠሩ ሕዝቦች ሆነው ቆይተዋል። ከጊዜ በኋላ ግን ይሖዋ “ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ” ትኩረቱን ወደ አሕዛብ አዞረ። (ሥራ 15:14) ለይሖዋ ስም የሚሆኑት ሰዎች ስለ እሱ የሚመሠክሩ ከመሆኑም ሌላ በምድር ላይ የትም ይኑሩ የት በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት አንድ ናቸው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠው የሚከተለው ተልእኮ ለአምላክ ስም የሚሆኑ ሰዎች እንዲሰባሰቡ አስችሏል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19, 20

በብሔር፣ በጎሳ ወይም በኑሮ ደረጃ ባልተከፋፈለና አንድነት ባለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ታቅፈሃል

2 ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ስትጠመቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆነሃል። ይህም በብሔር፣ በጎሳ ወይም በኑሮ ደረጃ ባልተከፋፈለና አንድነት ባለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ እንድትታቀፍ አስችሎሃል። (መዝ. 133:1) በመሆኑም በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን የእምነት ባልንጀሮችህን ትወዳቸዋለህ እንዲሁም ታከብራቸዋለህ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከአንተ የተለየ ዘር፣ ብሔር ወይም የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፤ ምናልባትም ወደ እውነት ከመምጣትህ በፊት ከእነዚህ ሰዎች ጋር መቀራረብ አትፈልግ ይሆናል። ይሁንና ከእነዚህ ሰዎች ጋር በወንድማማች ፍቅር የተሳሰርክ ሲሆን ይህ ትስስር ከማኅበራዊ፣ ከሃይማኖታዊም ሆነ ከሥጋ ዝምድና ይበልጥ የጠበቀ ነው።—ማር. 10:29, 30፤ ቆላ. 3:14፤ 1 ጴጥ. 1:22

የአስተሳሳብ ለውጥ

3 አንዳንዶች በዘር፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሁኔታ አሊያም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ለሌሎች ያላቸውን ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ ማስወገድ ሊከብዳቸው ይችላል፤ እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ሃይማኖት ባሳደረባቸው ተጽዕኖ ምክንያት ከሌሎች ብሔራት ለመጡ ሕዝቦች የነበራቸውን ጥላቻ ማስወገድ ያስፈለጋቸውን የመጀመሪያዎቹን የአይሁድ ክርስቲያኖች ምሳሌ ማስታወሳቸው ሊጠቅማቸው ይችላል። ይሖዋ ጴጥሮስን ወደ ሮማዊው መቶ አለቃ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት እንዲሄድ ባዘዘው ጊዜ ለዚህ ተልእኮ በደግነት አዘጋጅቶታል።—ሥራ ምዕ. 10

4 ጴጥሮስ በአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንደ ርኩስ የሚታዩ አንዳንድ እንስሳትን አርዶ እንዲበላ በራእይ ተነገረው። ጴጥሮስ እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በተናገረ ጊዜ ከሰማይ የመጣ ድምፅ “አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው” አለው። (ሥራ 10:15) ጴጥሮስ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክልና ለሚቀበለው ተልእኮ አእምሮውን እንዲያዘጋጅ ለማድረግ አምላክ ጣልቃ መግባት አስፈልጎት ነበር። ጴጥሮስ ይሖዋ የሰጠውን ተልእኮ ከተቀበለ በኋላ ወደ ውስጥ ሲገባ በዚያ ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ዘር ጋር ይወዳጅ ወይም ይቀራረብ ዘንድ ሕጉ እንደማይፈቅድ በሚገባ ታውቃላችሁ፤ ሆኖም አምላክ ማንንም ሰው ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ማለት እንደማይገባኝ ገልጦልኛል። በመሆኑም በተጠራሁ ጊዜ ምንም ሳላንገራግር መጣሁ።” (ሥራ 10:28, 29) ከዚያም ጴጥሮስ፣ ቆርኔሌዎስንና ቤተሰቡን ይሖዋ እንደተቀበላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ተመልክቷል።

5 በሚገባ የተማረ ፈሪሳዊ የነበረው የጠርሴሱ ሳኦል ራሱን ዝቅ በማድረግ ቀደም ሲል ያገላቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር መቀራረብ አልፎ ተርፎም ከእነሱ መመሪያ መቀበል አስፈልጎት ነበር። (ሥራ 4:13፤ ገላ. 1:13-20፤ ፊልጵ. 3:4-11) እንደ ሰርግዮስ ጳውሎስ፣ ዲዮናስዮስ፣ ደማሪስ፣ ፊልሞናና አናሲሞስ ያሉ ሌሎች ግለሰቦችም ምሥራቹን ተቀብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ ምን ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ እንዳስፈለጋቸው መገመት እንችላለን።—ሥራ 13:6-12፤ 17:22, 33, 34፤ ፊልሞና 8-20

ዓለም አቀፋዊ አንድነታችንን መጠበቅ

6 በጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩህ ፍቅር ወደ ይሖዋና ወደ ድርጅቱ እንድትሳብ እንዳደረገህ አያጠራጥርም። የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መለያ ምልክት የሆነውን ፍቅር ተመልክተሃል፤ ኢየሱስ ራሱ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:34, 35) በጉባኤህ ውስጥ ያለው ፍቅር በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያለው ፍቅር ነጸብራቅ እንደሆነ ስትገነዘብ ደግሞ ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለህ አድናቆት ጨምሯል። በመጨረሻዎቹ ቀኖች ሰዎች ይሖዋን በሰላምና በአንድነት ለማምለክ እንደሚሰበሰቡ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እየተመለከትክ ነው።—ሚክ. 4:1-5

7 ሰዎችን የሚከፋፍሉ በርካታ ነገሮች ባሉበት በአሁኑ ጊዜ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች” የተውጣጣን ሕዝብ አንድ ማድረግ ይቻላል ብሎ ማን ሊያስብ ይችላል? (ራእይ 7:9) ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሚጠቀም ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ ሰዎችና ጥንታዊ በሆኑ ባሕሎችና ልማዶች በሚመሩ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት እስቲ ለማሰብ ሞክር። አንድ ዓይነት ዘርና ብሔር ባላቸው ሕዝቦች መካከል ያለውን ሃይማኖታዊ ቅራኔ ተመልከት። ብሔራዊ ስሜት እየጦፈ ስለሄደ ፖለቲካዊ ክፍፍል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተስፋፍቷል። እንዲሁም የኑሮ ልዩነትን ጨምሮ ሰዎችን ሊከፋፍሉ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታስብ ከተለያዩ ብሔራት፣ ቋንቋዎች፣ ቡድኖችና መደቦች የተውጣጡ ሰዎች ሊበጠስ በማይችል የፍቅርና የሰላም ማሰሪያ አንድ ሆነው ሊተሳሰሩ መቻላቸው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ብቻ ሊፈጽመው የሚችል ተአምር መሆኑን ትረዳለህ።—ዘካ. 4:6

8 እንዲህ ያለው አንድነት እውን ከመሆኑም ሌላ አንተም፣ ራስህን ለአምላክ የወሰንክና የተጠመቅክ የይሖዋ ምሥክር በሆንክበት ጊዜ በዚህ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ታቅፈሃል። በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ካለው አንድነት እየተጠቀምክ በመሆኑ ይህ አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ የበኩልህን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለብህ። ይህን ማድረግ የምትችለው በገላትያ 6:10 ላይ የሚገኘውን ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ሥራ ላይ በማዋል ነው፦ “አጋጣሚ እስካገኘን ድረስ ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም እናድርግ።” በተጨማሪም የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ፤ ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።” (ፊልጵ. 2:3, 4) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በሰብዓዊ ዓይን ከመመልከት ይልቅ ይሖዋ በሚያያቸው መንገድ ለማየት ጥረት ካደረግን በመካከላችን ሰላማዊና አስደሳች ግንኙነት ይኖራል።—ኤፌ. 4:23, 24

አንዳችን ለሌላው አሳቢነት ማሳየት

9 ሐዋርያው ጳውሎስ በምሳሌ እንደገለጸልን ጉባኤው የተከፋፈለ ሳይሆን እርስ በርስ የሚተሳሰቡ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ነው። (1 ቆሮ. 12:14-26) በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ካሉት አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር እጅግ ተራርቀን የምንገኝ ቢሆንም የእነሱ ደህንነት ያሳስበናል። በአንዳንድ ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰው ስደት ሁላችንንም ያስጨንቀናል። አንዳንዶች ቁሳዊ ነገሮችን አጥተው ከተቸገሩ አሊያም በተፈጥሮ አደጋ፣ በጦርነት ወይም በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ችግር ላይ ከወደቁ የቀሩት ወንድሞች በመንፈሳዊም ሆነ በቁሳዊ እነሱን ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ።—2 ቆሮ. 1:8-11

10 ሁላችንም በየቀኑ ስለ ወንድሞቻችን መጸለይ አለብን። አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ የሚደርስባቸውን ፈተና ተቋቁመው መኖር ይጠበቅባቸዋል። በአንዳንዶች ላይ የሚደርሰው መከራ በግልጽ የሚታወቅ ሊሆን ይችላል። ይሁንና በሌሎች ዘንድ እምብዛም የማይታወቅ ፈተና የሚደርስባቸው፣ ለምሳሌ ከሥራ ባልደረቦቻቸው አሊያም እምነታቸውን ከማይጋሩ የቤተሰባቸው አባላት ተቃውሞ የሚያጋጥማቸው ወንድሞቻችንም አሉ። (ማቴ. 10:35, 36፤ 1 ተሰ. 2:14) ዓለም አቀፋዊ በሆነ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የታቀፍን እንደመሆናችን መጠን የእነሱ ሁኔታ ሁላችንንም ያሳስበናል። (1 ጴጥ. 5:9) በመካከላችን በስብከቱ ሥራና በጉባኤ ግንባር ቀደም በመሆን ይሖዋን በትጋት የሚያገለግሉ ወንድሞች አሉ። በተጨማሪም ዓለም አቀፉን ሥራ በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸው ወንድሞች አሉ። እነሱን በቀጥታ ለመርዳት ማድረግ የምንችለው ነገር በማይኖርበት ጊዜም እንኳ ስለ እነሱ መጸለያችን እንደምንወዳቸውና ከልብ እንደምናስብላቸው ያሳያል።—ኤፌ. 1:16፤ 1 ተሰ. 1:2, 3፤ 5:25

11 በምድር ላይ የተለያየ ችግር እየደረሰ ባለበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች እርስ በርስ ለመረዳዳት ዝግጁ መሆን አለባቸው። እንደ መሬት መንቀጥቀጥና ጎርፍ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች መጠነ ሰፊ የመልሶ ማቋቋም ሥራና ከፍተኛ መጠን ያለው ቁሳዊ እርዳታ ማዘጋጀት የሚጠይቁበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል። በአንጾኪያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የሰጠውን ምክር በማስታወስ በይሁዳ ላሉ ወንድሞቻቸው ቁሳዊ እርዳታ ልከዋል። (ሥራ 11:27-30፤ 20:35) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ሥርዓት ባለው መንገድ የሚከናወነውን የእርዳታ ሥራ እንዲደግፉ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች አበረታቷቸዋል። (2 ቆሮ. 9:1-15) በዘመናችንም ወንድሞቻችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸውና ቁሳዊ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው ድርጅቱም ሆነ አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚያስፈልገውን ነገር ለመላክ አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳሉ።

የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተለየ ሕዝብ

12 ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን የተደራጀው የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ነው። በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ፈቃድ፣ ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር እንዲሰበክ ማድረግ ነው። (ማቴ. 24:14) ይሖዋ በዚህ ሥራ ስንካፈል፣ ከፍ ካሉት የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይፈልጋል። (1 ጴጥ. 1:14-16) አንዳችን ለሌላው ለመገዛትና ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ በትጋት ለመሳተፍ ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:21) ይህ ዘመን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የአምላክን መንግሥት በሕይወታችን ውስጥ የምናስቀድምበት እንጂ የግል ጥቅማችንን የምናሳድድበት አይደለም። (ማቴ. 6:33) ይህን በአእምሯችን በመያዝ ለምሥራቹ ስንል ተባብረን የምንሠራ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ደስታና እርካታ ወደፊት ደግሞ ዘላለማዊ በረከት እናገኛለን።

13 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ከተቀረው የሰው ዘር የተለየንና በአምላክ አገልግሎት በቅንዓት የምንካፈል ንጹሕ ሕዝብ ነን። (ቲቶ 2:14) ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ከሌሎች የተለየን ያደርገናል። በዓለም ዙሪያ ካሉ ወንድሞቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንሠራ ከመሆኑም ሌላ የእውነትን ቋንቋ እንናገራለን፤ እንዲሁም ከምንናገረው እውነት ጋር የሚስማማ ምግባር እናሳያለን። ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት በነቢዩ ሶፎንያስ አማካኝነት ስለዚህ ጉዳይ አስቀድሞ ተናግሯል፦ “ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩና እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።”—ሶፎ. 3:9

14 በመቀጠልም ይሖዋ፣ ሶፎንያስ በዛሬው ጊዜ እውን ሆኖ የምናየውን ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አስመልክቶ እንደሚከተለው በማለት እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል፦ “የእስራኤል ቀሪዎች ምንም ዓይነት ክፋት አይሠሩም፤ ውሸት አይናገሩም፤ በአፋቸውም ውስጥ አታላይ ምላስ አይገኝም፤ ይልቁንም ይመገባሉ፤ ይተኛሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።” (ሶፎ. 3:13) የይሖዋን የእውነት ቃል ስለተረዳን፣ አእምሯችንን ስላደስንና ይሖዋ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ጥረት ስለምናደርግ በአንድነት መሥራት ችለናል። ነገሮችን በሰብዓዊ ዓይን በሚመለከቱ ሰዎች ዘንድ ፈጽሞ የማይቻል የሚመስል ነገር ማከናወን ችለናል። በእርግጥም በመላው ምድር ላይ ለአምላክ ክብር የምናመጣ ለእሱ የተለየን ሕዝብ ነን።—ሚክ. 2:12

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ