እውነተኛ ክርስቲያናዊ አንድነት—እንዴት?
1 በ234 አገሮች የሚኖሩና ወደ 380 የሚጠጉ ቋንቋዎች የሚናገሩ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን አንድ ሊያደርግ የሚችለው ምንድን ነው? የይሖዋ አምልኮ ብቻ ነው። (ሚክ. 2:12፤ 4:1-3) የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛው የክርስትና አንድነት በዛሬው ጊዜ እውን እንደሆነ ከግል ተሞክሯቸው የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ‘በአንድ እረኛ’ የምንመራ ‘አንድ መንጋ’ እንደመሆናችን መጠን ከፋፋይ የሆነውን የዓለም መንፈስ ለመቋቋም ቆርጠናል።—ዮሐ. 10:16፤ ኤፌ. 2:2
2 አምላክ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ በእውነተኛው አምልኮ አንድ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ዓላማውን ከግብ ያደርሳል። (ራእይ 5:13) ኢየሱስ የዚህን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ስለነበረ ተከታዮቹ አንድነት እንዲኖራቸው ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርቧል። (ዮሐ. 17:20, 21) እያንዳንዳችን ለክርስቲያን ጉባኤ አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
3 አንድነቱ ሊደረስበት የሚችለው እንዴት ነው? ክርስቲያኖች ያለ አምላክ ቃልና ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ወደ አንድነት መድረስ አይችሉም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናነበውን ተግባራዊ ማድረጋችን የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ ያስችላል። ይህ ደግሞ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” ያስችለናል። (ኤፌ. 4:3) መንፈሱ እርስ በርስ በፍቅር ተቻችለን እንድንኖር ይገፋፋናል። (ቆላ. 3:13, 14፤ 1 ጴጥ. 4:8) አንተስ በየዕለቱ በአምላክ ቃል ላይ በማሰላሰል አንድነቱን ለማጠናከር የበኩልህን ታደርጋለህ?
4 እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠን ተልእኮም አንድ ያደርገናል። ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ‘ስለ ወንጌል እየተጋደልን’ አንድ ላይ ስናገለግል ‘ለእውነት አብረን የምንሠራ’ እንሆናለን። (ፊልጵ. 1:27፤ 3 ዮሐ. 8) እንዲህ ስናደርግ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር እርስ በርስ ያስተሳሰረን ፍቅር ይበልጥ ይጠናከራል። ታዲያ በዚህ ሳምንት አገልግሎት ስትወጣ በቅርቡ አብሮህ አገልግሎ የማያውቅን አንድ ክርስቲያን ለምን አትጋብዘውም?
5 በዛሬው ጊዜ የእውነተኛው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አካል በመሆናችን ምንኛ የታደልን ነን! (1 ጴጥ. 5:9) በቅርቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “ለአምላክ ክብር ስጡት” በተሰኙት ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ይህን ዓለም አቀፋዊ አንድነት በዓይናቸው ለመመልከት ችለዋል። እንግዲያው እያንዳንዳችን በየዕለቱ የአምላክን ቃል በማንበብ፣ አለመግባባቶችን በፍቅር በመፍታትና “በአንድ አሳብ” ምሥራቹን በመስበክ ለዚህ ውድ አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ የምናበረክት እንሁን።—ሮሜ 15:5, 6