የይሖዋ ቤተሰብ ውድ የሆነ አንድነት አለው
“ተመልከቱ! ወንድሞች ስምም ሆነው በኅብረት ሲቀመጡ ምንኛ መልካምና ምንኛ ያማረ ነው!”—መዝሙር 133:1 አዓት
1. በዛሬው ጊዜ ብዙ ቤተሰቦች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
በዛሬው ጊዜ ቤተሰብ ትልቅ ቀውስ ገጥሞታል። በብዙዎቹ ቤተሰቦች ውስጥ የጋብቻ ማሰሪያዎች የሚበጠሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የፍቺ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው፤ ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው ብዙ ልጆችም መሪር ሐዘን እየደረሰባቸው ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ደስታና አንድነት የላቸውም። ሆኖም እውነተኛ ደስታና አንድነት ያለው አንድ ቤተሰብ አለ። ይህ ቤተሰብ የይሖዋ አምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ነው። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በዓይን የማይታዩ መላእክት የተሰጧቸውን ሥራዎች ከመለኮታዊ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ያከናውናሉ። (መዝሙር 103:20, 21) ታዲያ በምድር ላይስ እንዲህ ዓይነት አንድነት ያለው ቤተሰብ አለ?
2, 3. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባላት እነማን ናቸው? በዛሬው ጊዜ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች በጠቅላላ ከምን ጋር ልናመሳስላቸው እንችላለን? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በእግዚአብሔር አብ ፊት በጉልበቴ ተንበርክኬ እጸልያለሁ። በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ ስሙን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው’ ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 3:14, 15 የ1980 ትርጉም) በምድር ላይ ያለውን የቤተሰብ የዘር ግንድ ሁሉ የፈጠረው አምላክ ስለሆነ ስሙን የሚያገኘው ከእርሱ ነው። ምንም እንኳ በሰማይ ሰብዓዊ ቤተሰቦች ባይኖሩም በምሳሌያዊ አነጋገር አምላክ ከሰማያዊ ድርጅቱ ጋር ተጋብቷል፤ ኢየሱስም በሰማይ ከእሱ ጋር አንድ የምትሆን መንፈሳዊ ሙሽራ አለችው። (ኢሳይያስ 54:5፤ ሉቃስ 20:34, 35፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50፤ 2 ቆሮንቶስ 11:2) በምድር ላይ ያሉት ታማኝ ቅቡዓን የአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አካል ናቸው፤ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የኢየሱስ “ሌሎች በጎች”ም የዚህ ቤተሰብ ዕጩ አባላት ናቸው። (ዮሐንስ 10:16፤ ሮሜ 8:14-17፤ ጥር 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31) ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን በጠቅላላ አንድነት ባለው አንድ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ መመሰል ይቻላል።
3 አንተ የአምላክ አገልጋዮችን ያቀፈው የዚህ ግሩም ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል ነህን? የዚህ ቤተሰብ አባል ከሆንክ ሰዎች ሊያገኟቸው ከሚችሏቸው ታላላቅ በረከቶች መካከል አንዱ የሆነውን ይህን በረከት አግኝተሃል ማለት ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ብጥብጥና መከፋፈል ባለበት ዓለም ውስጥ የሚገኘው የይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ ማለትም በዓይን የሚታየው ድርጅቱ ያለው ሰላምና አንድነት ልክ በበረሃ ውስጥ እንዳለ ገነት እንደሆነ ይናገራሉ። የይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ ያለው አንድነት እንዴት ሊገለጽ ይችላል? እንዲህ ዓይነቱ አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ነገሮችስ ምንድን ናቸው?
ምንኛ መልካምና ምንኛ ያማረ ነው!
4. መዝሙር 133 ስለ ወንድማማች አንድነት የሚናገረውን በራስህ አባባል እንዴት ትገልጸዋለህ?
4 መዝሙራዊው ዳዊት የወንድማማች አንድነትን በጣም ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። እንዲያውም በመንፈስ አነሣሽነት ተገፋፍቶ ስለዚህ ጉዳይ ዘምሯል! በገናውን ይዞ እንዲህ ብሎ ሲዘምር በዓይነ ሕሊናህ ተመልከተው፦ “ተመልከቱ! ወንድሞች ስምም ሆነው በኅብረት ሲቀመጡ ምንኛ መልካምና ምንኛ ያማረ ነው! (አዓት) ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፣ እስከ አሮን ጢም፣ በልብሱ መደረቢያም እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና።”—መዝሙር 133:1-3
5. በመዝሙር 133:1, 2 መሠረት እስራኤላውያንንና በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች እንዴት ማነጻጸር ይቻላል?
5 እነዚህ ቃላት የአምላክ የጥንት ሕዝቦች የነበሩት እስራኤላውያን የነበራቸውን የወንድማማች ኅብረት የሚያመለክቱ ናቸው። ሦስቱን ዓመታዊ በዓሎቻቸውን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በሚመጡበት ጊዜ ሁሉም ስምም ሆነው በአንድነት ይሰነብቱ ነበር። ከተለያዩ ነገዶች የተውጣጡ ቢሆኑም እንኳ አንድ ቤተሰብ ነበሩ። አንድ ላይ መሆናቸው ደስ የሚል ሽታ እንዳለው የሚያነቃቃ የቅባት ዘይት ጥሩ ስሜት ያሳድርባቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ዘይት በአሮን ራስ ላይ ሲፈስስ በጢሙ ላይ ወርዶ የልብሱ ኮሌታ ላይ ይንጠባጠብ ነበር። እስራኤላውያን አንድ ላይ መሰባሰባቸው በተሰባሰቡት ሰዎች ሁሉ ላይ ጥሩ ስሜት ያሳድር ነበር። በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶች ተፈትተው አንድነታቸው እንዲጠናከር ይደረግ ነበር። በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ መካከልም ተመሳሳይ አንድነት አለ። ዘወትር አንድ ላይ መሰብሰባቸው በአባላቱ ላይ ጥሩ መንፈሳዊ ስሜት ያሳድራል። የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር በሥራ ሲያውሉ በመካከላቸው የተፈጠሩ አለመግባባቶች ወይም ችግሮች ይወገዳሉ። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15-17) የይሖዋ ሕዝቦች በመካከላቸው ያለው የወንድማማች አንድነት የሚሰጣቸውን ማበረታቻ እጅግ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።
6, 7. የእስራኤላውያን አንድነት እንደ አርሞንዔም ተራራ ጠል የነበረው እንዴት ነው? ዛሬ የአምላክ በረከት የት ሊገኝ ይችላል?
6 እስራኤላውያን ስምም ሆነው አንድ ላይ መሰንበታቸው እንደ አርሞንዔም ጠል ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይህ ተራራ ከባሕር ወለል በላይ 2,800 ሜትር ከፍታ ያለው በመሆኑ ዓመቱን ሙሉ ማለት ይቻላል፣ በበረዶ የተሸፈነ ነው። በአርሞንዔም ተራራ ጫፍ ላይ ያለው በረዶ የሌሊቱን ተን እንዲቀዘቅዝና ከፍተኛ ጤዛ እንዲፈጠር በማድረግ ለረጅም ጊዜ በሚቆየው የበጋ ወቅት ተክሎች እንዳይደርቁ ይረዳል። ከአርሞንዔም ሸንተረር ላይ የሚነሳው እርጥበት አዘል አየር የሚተነውን ውኃ በደቡብ በኩል እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ሊወስደው ይችላል፤ በዚህ ሥፍራ ውኃው ወደ ጠልነት ይለወጣል። ስለዚህ መዝሙራዊው ‘በጽዮን ተራሮች ላይ ስለሚወርደው የአርሞንዔም ጠል’ የተናገረው ነገር ትክክል ነው። የይሖዋ አምላኪዎችን ቤተሰባዊ አንድነት የሚያጠናክረውን የሚያነቃቃ መንፈስ የሚያስታውስ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው!
7 የክርስቲያን ጉባኤ ከመቋቋሙ በፊት ጽዮን ወይም ኢየሩሳሌም የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል ነበረች። በመሆኑም አምላክ በረከቱ እንዲፈስ ያዘዘው በዚያ ነበር። የበረከቶች ሁሉ ምንጭ የሆነው አምላክ ይገኝ የነበረው እሱን ይወክለው በነበረውና ኢየሩሳሌም ውስጥ በነበረው ቤተ መቅደስ በመሆኑ በረከቶቹም ከዚያ መፍሰስ ነበረባቸው። በአሁኑ ጊዜ ግን እውነተኛ አምልኮ በአንድ ቦታ የተወሰነ ባለመሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ያላቸው በረከት፣ ፍቅርና አንድነት በመላው ምድር ላይ ይገኛል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ ያደረጉት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ለአንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች
8. ዮሐንስ 17:20, 21 ስለ አንድነት ምን ያስተምረናል?
8 የይሖዋ አምላኪዎች አንድነት የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች ጨምሮ ከአምላክ ቃል የተገኘውን ትክክለኛ እውቀት በመታዘዝ ላይ የተመሠረተ ነው። ይሖዋ ለእውነት እንዲመሠክርና መሥዋዕታዊ ሞት እንዲሞት ልጁን ወደ ዓለም በመላክ አንድነት ያለው የክርስቲያን ጉባኤ መቋቋም የሚችልበትን መንገድ ከፍቷል። (ዮሐንስ 3:16፤ 18:37) ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ መጸለዩ በዚህ ጉባኤ አባላት መካከል እውነተኛ አንድነት መኖር እንዳለበት ያሳያል፦ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፣ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ አንተ፣ አባት ሆይ፣ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።” (ዮሐንስ 17:20, 21) የኢየሱስ ተከታዮች በአምላክና በልጁ መካከል ያለውን ዓይነት አንድነት አግኝተዋል። ይህ የሆነው የአምላክን ቃልና የኢየሱስን ትምህርቶች በመታዘዛቸው ነው። በዛሬው ጊዜ በዓለም አቀፉ የይሖዋ ቤተሰብ መካከል ላለው አንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ይኸው ዝንባሌ ነው።
9. መንፈስ ቅዱስ በይሖዋ ሕዝቦች አንድነት ውስጥ ምን ሚና ይጫወታል?
9 የይሖዋን ሕዝቦች አንድ የሚያደርገን ሌላው ነገር ደግሞ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ያለን መሆኑ ነው። የተገለጠውን የይሖዋን ቃል እውነት እንድንረዳና አንድ ሆነን እንድናገለግለው ያደርገናል። (ዮሐንስ 16:12, 13) መንፈሱ እንደ ጠብ፣ ቅናት፣ ቁጣና ክርክር ያሉ የሚከፋፍሉ የሥጋ ሥራዎችን እንድናስወግድ ይረዳናል። የአምላክ መንፈስ ከዚህ ይልቅ አንድ የሚያደርጉትን እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት ያሉ ፍሬዎች እንድናፈራ ያስችለናል።—ገላትያ 5:19-23
10. (ሀ) አንድነት ያለው የአንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባላት ያላቸውን ፍቅር ለይሖዋ ያደሩ ሰዎች ካላቸው ፍቅር ጋር እንዴት ማመሳሰል ይቻላል? (ለ) አንድ የአስተዳደር አካል አባል ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ ጋር መሰብሰብን በተመለከተ የሚሰማውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው?
10 አንድነት ያለው የአንድ ቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው ከመዋደዳቸውም በላይ አንድ ላይ መሆን ያስደስታቸዋል። ልክ እንደዚሁም አንድነት ያለው የይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ አባላትም ይሖዋን፣ ልጁንና መሰል አማኞችን ያፈቅራሉ። (ማርቆስ 12:30፤ ዮሐንስ 21:15-17፤ 1 ዮሐንስ 4:21) እርስ በርሳቸው የሚዋደዱ የአንድ ሥጋዊ ቤተሰብ አባላት አንድ ላይ መመገብ እንደሚያስደስታቸው ሁሉ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችም በትንንሽም ሆነ በትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከሌሎች ጋር አብሮ መሰብሰብና ግሩም የሆነ መንፈሳዊ ምግብ መመገብ የሚሰጠውን ጥቅም ማግኘት ያስደስታቸዋል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ዕብራውያን 10:24, 25) አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ከወንድሞች ጋር መሰብሰብ ማለት ለእኔ፣ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ደስታና ማበረታቻ ከሚሰጡኝ ነገሮች አንዱ ነው። በተቻለ መጠን ወደ መንግሥት አዳራሽ ቀድመው ከሚደርሱትና መጨረሻ ከሚወጡት ሰዎች መካከል መሆን እፈልጋለሁ። ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ስነጋገር ውስጣዊ እርካታ ይሰማኛል። ከእነርሱ ጋር ስሆን ልክ ቤቴ ውስጥ ከቤተሰቤ ጋር እንዳለሁ ሆኖ ይሰማኛል።” አንተስ የሚሰማህ እንደዚያ ነውን?—መዝሙር 27:4
11. የይሖዋ ምሥክሮች በይበልጥ ደስታ የሚሰጣቸው ሥራ የትኛው ነው? መላው ሕይወታችን በአምላክ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር ማድረጋችን ምን ውጤት ያስገኝልናል?
11 አንድነት ያለው ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መሥራት ያስደስተዋል። በተመሳሳይም፣ በይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች የመንግሥቱን ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በአንድነት ማከናወን ያስደስታቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በዚህ ሥራ ዘወትር መሳተፋችን ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ ያደርገናል። በተጨማሪም መላው ሕይወታችን በአምላክ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር ማድረጋችንና የሕዝቡን የሥራ እንቅስቃሴዎች መደገፋችን በመካከላችን ያለውን የቤተሰቡን መንፈስ ያጠናክረዋል።
ቲኦክራሲያዊ ሥርዓት ወሳኝ ነው
12. አንድ ቤተሰብ ደስታና አንድነት ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የክርስቲያን ጉባኤዎች አንድነት ያጠናከረው ዝግጅት የትኛው ነው?
12 ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጥብቅ የሆነ አመራር የሚሰጥበትና ሥርዓታማ የሆነ ቤተሰብ አንድነትና ደስታ እንደሚኖረው የታወቀ ነው። (ኤፌሶን 5:22, 33፤ 6:1) ይሖዋ አምላክ ሁሉ ነገር በሥርዓት እንዲከናወን ይፈልጋል፤ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ደግሞ “ልዑል” አድርገው ይመለከቱታል። (ዳንኤል 7:18, 22, 25, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 14:33) በተጨማሪም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የሁሉም ነገር ወራሽ አድርጎ እንደሾመውና በሰማይና በምድር ያለውን ሥልጣን ሁሉ እንደሰጠው ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 28:18፤ ዕብራውያን 1:1, 2) በክርስቶስ ራስነት ሥር ያለው የክርስቲያን ጉባኤ ሥርዓታማና አንድነት ያለው ድርጅት ነው። (ኤፌሶን 5:23) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ጉባኤዎች ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠር ሐዋርያትንና ሌሎች በመንፈሳዊ የጎለመሱ “ሽማግሌዎች”ን ያቀፈ አንድ የአስተዳደር አካል ነበር። እያንዳንዱ ጉባኤ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ነበሩት። (ሥራ 15:6፤ ፊልጵስዩስ 1:1) በኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚያገለግሉትን ወንድሞች መታዘዛቸው አንድነት እንዲኖር አድርጓል።—ዕብራውያን 13:17
13. ይሖዋ ሰዎችን ወደ እሱ የሚስበው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል?
13 ይሁን እንጂ ይህ ሥርዓት መኖሩ የይሖዋ አምላኪዎች ያላቸው አንድነት ስሜት አልባ በሆነ ጥብቅ አመራር የተገኘ ነው ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! አምላክም ሆነ ድርጅቱ ማንኛውንም ነገር የሚያከናውኑት በፍቅር ነው። ይሖዋ ሰዎችን የሚስበው ፍቅር በማሳየት ነው፤ በመሆኑም በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን በሙሉ ልባቸው ለአምላክ መወሰናቸውን ለማሳየት በውኃ በመጠመቅ በፈቃደኝነትና በደስታ የይሖዋ ድርጅት አባል ይሆናሉ። መንፈሳቸው ለእስራኤላውያን መሰሎቹ የሚከተለውን ምክር ከሰጠው ከኢያሱ መንፈስ ጋር አንድ ነው፦ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”—ኢያሱ 24:15
14. የይሖዋ ድርጅት ቲኦክራሲያዊ ነው ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
14 የይሖዋ ቤተሰብ አባላት እንደመሆናችን መጠን ደስተኞች ከመሆናችንም በላይ ያለንበት ሁኔታ አስተማማኝ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ድርጅቱ ቲኦክራሲያዊ ስለሆነ ነው። የአምላክ መንግሥት ቲኦክራሲያዊ ነው (አምላክ የሚል ትርጉም ካለው ቴኦስ ከተባለው የግሪክኛ ቃልና አገዛዝ የሚል ትርጉም ካለው ክራቶስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው)። በአምላክ የሚመራና በእሱ የተቋቋመ አገዛዝ ነው። በመንፈስ የተቀባው የይሖዋ “ቅዱስ ሕዝብ” ለአምላክ አገዛዝ ተገዥ ስለሆነ እርሱም ቲኦክራሲያዊ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:9) ፈራጃችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ንጉሣችን የሆነው ታላቁ ቲኦክራት ይሖዋ ከጎናችን በመሆኑ አስተማማኝ ሁኔታ ሊሰማን ይገባል። (ኢሳይያስ 33:22) ሆኖም አንዳንድ አከራካሪ ጉዳዮች ተነስተው ደስታችንን፣ ያለንበትን አስተማማኝ ሁኔታና አንድነት አደጋ ላይ ቢጥሉትስ?
የአስተዳደር አካል እርምጃ ይወስዳል
15, 16. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምን ክርክር ተነስቶ ነበር? ለምንስ?
15 የአንድን ቤተሰብ አንድነት ለመጠበቅ አንዳንድ ጊዜ አንድን አከራካሪ ጉዳይ መፍታት ሊያስፈልግ ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩትን የአምላክ አምላኪዎች ቤተሰብ አንድነት ለመጠበቅ ሲባል አንድ መንፈሳዊ ችግር መወገድ ነበረበት እንበል። ምን ማድረግ ያስፈልግ ነበር? የአስተዳደር አካል በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንደሚያደርገው ሁሉ በዚያን ጊዜም እርምጃ ይወስድ ነበር። እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባ አለን።
16 በ49 እዘአ የአስተዳደር አካል አንድ ከባድ ችግር በመፍታት “የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች”ን አንድነት ለመጠበቅ በኢየሩሳሌም ተሰብስቦ ነበር። (ኤፌሶን 2:19) ከ13 ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስ ሰብኮለት የመጀመሪያዎቹ አሕዛብ ወይም የሌሎች ብሔራት ሰዎች የተጠመቁ አማኞች ሆነው ነበር። (ሥራ ምዕራፍ 10) በመጀመሪያው የጳውሎስ ጉዞ ወቅት ብዙ አሕዛብ ክርስትናን ተቀብለዋል። (ሥራ 13:1-14:28) እንዲያውም በሶርያ አንጾኪያ ውስጥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች ጉባኤ ተቋቁሞ ነበር። አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ወደ ክርስትና የተለወጡ አሕዛብ መገረዝና የሙሴን ሕግ መጠበቅ አለባቸው የሚል እምነት አድሮባቸው ነበር፤ ሆኖም በዚህ ሐሳብ ያልተስማሙም ነበሩ። (ሥራ 15:1-5) ይህ ክርክር መከፋፈልን ሊፈጥር ይችል ነበር፤ አልፎ ተርፎም ወገን የለዩ የአይሁድና የአሕዛብ ጉባኤዎች እንዲመሠረቱ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም የአስተዳደር አካሉ ክርስቲያናዊ አንድነትን ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ ወስዷል።
17. በሥራ ምዕራፍ 15 ላይ የተገለጸው ስምምነት በሰፈነበትና ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሥርዓት የተከናወነው ነገር ምንድን ነው?
17 ሥራ 15:6-22 በሚለው መሠረት “ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ።” ከአንጾኪያ ተወክለው የመጡ ሰዎችን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችም በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። በመጀመሪያ ጴጥሮስ ‘አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከአፉ ሰምተው እንዳመኑ’ ተናገረ። ከዚያም ‘ሕዝቡ ሁሉ’ በርናባስና ጳውሎስ “እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው” ሰሙ። ቀጥሎም ያዕቆብ ጥያቄው እንዴት ሊፈታ እንደሚችል ሐሳብ አቀረበ። የአስተዳደር አካሉ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ ጋር ከእነርሱ የተመረጡትን ሰዎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ይልኩ ዘንድ” እንደ ፈቀዱ ተገልጾልናል። ‘የተመረጡት ሰዎች’ ማለትም ይሁዳና ሲላስ ለመሰል አማኞች የሚያበረታታ ደብዳቤ ይዘው ሄዱ።
18. የሙሴን ሕግ በተመለከተ የአስተዳደር አካሉ ምን ውሳኔ አስተላለፈ? ይህስ በአይሁድና በአሕዛብ ክርስቲያኖች ላይ ምን ውጤት አስከተለ?
18 የአስተዳደር አካሉን ውሳኔ የሚገልጸው ደብዳቤ የመክፈቻ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞችም [“ወንድሞቻችሁ፣” የ1980 ትርጉም] በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ።” በዚህ ታሪካዊ ስብሰባ ላይ ሌሎች ወንድሞችም ተገኝተው የነበረ ቢሆንም የአስተዳደር አካሉ ያቀፈው “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች”ን እንደነበረ መረዳት ይቻላል። ደብዳቤው በሚለው መሠረት ውሳኔው የተላለፈው በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው፦ “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል።” (ሥራ 15:23-29፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ክርስቲያኖች እንዲገረዙና የሙሴን ሕግ እንዲከተሉ አይጠበቅባቸውም ነበር። ይህ ውሳኔ የአይሁድና የአሕዛብ ክርስቲያኖች የሚያደርጉትም ሆነ የሚናገሩት ነገር አንድ እንዲሆን ረድቷቸዋል። ጉባኤዎቹ ተደሰቱ፤ በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል መንፈሣዊ አመራር ሥር ባለው በምድር ዙሪያ በሚገኘው የአምላክ ቤተሰብ መካከል እንደሚታየው ሁሉ በዚያን ጊዜም በመካከላቸው የነበረው ውድ የሆነ አንድነት ተጠብቆ ቆየ።—ሥራ 15:30-35
በቲኦክራሲያዊ አንድነት አገልግሉ
19. በይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ ውስጥ ያለው አንድነት ሊጠናከር የቻለው ለምንድን ነው?
19 የአንድ ቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው ሲረዳዱ አንድነታቸው ይጠነክራል። በይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ ውስጥ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ ውስጥ የነበሩት ሽማግሌዎችና ሌሎች ከአስተዳደር አካሉ ጋር በመተባበርና ውሳኔዎቹን በመቀበል አምላክን ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ አገልግለዋል። በአስተዳደር አካሉ እርዳታ ሽማግሌዎቹ ‘ቃሉን ሰብከዋል፤’ የጉባኤዎቹ አባላትም በጥቅሉ ‘አንድ ንግግር ይናገሩ’ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:1, 2፤ 1 ቆሮንቶስ 1:10) በመሆኑም በኢየሩሳሌም፣ በአንጾኪያ፣ በሮም፣ በቆሮንቶስም ሆነ በሌላ በማንኛውም ቦታ በአገልግሎትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይቀርብ የነበረው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት አንድ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ቲኦክራሲያዊ አንድነት ዛሬም አለ።
20. ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ አለብን?
20 የይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል የሆንን ሁሉ አንድነታችንን ለመጠበቅ እንድንችል ቲኦክራሲያዊ ፍቅር ለማሳየት መጣር አለብን። (1 ዮሐንስ 4:16) ለአምላክ ፈቃድ መገዛት እንዲሁም ‘ለታማኝና ልባም ባሪያና’ ለአስተዳደር አካሉ የጠለቀ አክብሮት ማሳየት ይገባናል። ራሳችንን ለአምላክ የወሰንነው በደስታና በፈቃደኝነት እንደሆነ ሁሉ የምንታዘዘውም ልክ እንደዚሁ ነው። (1 ዮሐንስ 5:3) መዝሙራዊው ደስታንና ታዛዥነትን ግሩም በሆነ መንገድ አጣምሮ ገልጿቸዋል። “እናንት ሕዝቦች፣ ያህን አመስግኑ! ይሖዋን የሚፈራ፣ ትእዛዛቱንም እጅግ የሚወድድ ሰው ደስተኛ ነው” ሲል ዘምሯል።—መዝሙር 112:1 አዓት
21. ቲኦክራሲያዊ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
21 የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ቲኦክራሲያዊ ከመሆኑም በላይ ዘወትር የአባቱን ፈቃድ ያደርጋል። (ዮሐንስ 5:30) ስለዚህ እኛም አንድ ሆነን የይሖዋን ፈቃድ ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ በማከናወንና ከድርጅቱ ጋር ሙሉ በሙሉ በመተባበር ምሳሌያችንን እንከተል። እንዲህ ካደረግን “ተመልከቱ! ወንድሞች ስምም ሆነው በኅብረት ሲቀመጡ ምንኛ መልካምና ምንኛ ያማረ ነው!” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት ከልብ በመነጨ የደስታና የምስጋና ስሜት ማስተጋባት እንችላለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ክርስቲያናዊ አንድነታችን ከመዝሙር 133 ጋር ሊዛመድ የሚችለው እንዴት ነው?
◻ አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ ቲኦክራሲያዊ ሥርዓት ለአምላክ ሕዝቦች አንድነት ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአስተዳደር አካል አንድነትን ለመጠበቅ እርምጃ የወሰደው እንዴት ነው?
◻ በቲኦክራሲያዊ አንድነት ማገልገል ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአስተዳደር አካል አንድነትን ለመጠበቅ እርምጃ ወስዷል