የክፍል 9 ማስተዋወቂያ
በዚህ ክፍል ውስጥ በይሖዋ ላይ አስደናቂ እምነት ስላሳዩ ወጣቶች፣ ነቢያትና ነገሥታት እንማራለን። ሶርያ ውስጥ የምትኖር አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጅ የይሖዋ ነቢይ ንዕማንን እንደሚያድነው እምነት ነበራት። ነቢዩ ኤልሳዕ፣ ይሖዋ ከጠላት ሠራዊት እንደሚያድነው ሙሉ እምነት ነበረው። ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ሕፃኑን ኢዮዓስን ክፉ ከሆነችው ከአያቱ ከጎቶልያ እጅ ለማዳን ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሏል። ንጉሥ ሕዝቅያስ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከጠላት እንደሚታደጋት ስለተማመነ አሦራውያንን ፈርቶ እጅ አልሰጠም። ንጉሥ ኢዮስያስ ጣዖት አምልኮን አስወገደ፤ ቤተ መቅደሱን አደሰ፤ እንዲሁም ሕዝቡ ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲመለስ አደረገ።