ኩራት
ከልክ በላይ ራስን ከፍ አድርጎ መመልከት፣ አንድ ሰው ባለው ችሎታ፣ መልክ፣ ሀብት፣ ማዕረግ ወዘተ የተነሳ የሚሰማው የበላይነት ስሜት፣ ሌሎችን በንቀት መመልከት ወይም መያዝ፣ እብሪት ወይም ትዕቢት። አንዳንድ ጊዜ ኩራት አንድን ነገር በማድረግ ወይም በማግኘት መደሰትን ወይም መፈንደቅን ስለሚያመለክት ጥሩ ስሜትንም ሊገልጽ ይችላል። ለኩራት ከሚሰጡ አቻ ትርጉሞች መካከል ትምክህተኝነት፣ እብሪትና ትዕቢት ይገኙበታል።
ጋአህ የተባለው የዕብራይስጥ ግስ ቃል በቃል ሲተረጎም ‘ማደግ፤ ከፍ ማለት’ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ኩራትን ለመግለጽ ለሚያገለግሉ በርካታ የዕብራይስጥ ቃላት መነሻ ቃል ሆኗል። እነዚህ ቃላት “ትዕቢት” ተብለው የተተረጎሙ ሲሆን በመልካምም ሆነ በክፉ ‘ግርማዊነትን’ እና ‘ክብርን’ ለማመልከትም ተሠርቶባቸዋል።—ኢዮብ 8:11፤ ሕዝ 47:5 ባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም፤ ኢሳ 9:9፤ ምሳሌ 8:13፤ መዝ 68:34፤ አሞጽ 8:7
“መኩራራት፣ መደሰት” ተብሎ የተተረጎመው ካውካኦማይ የተባለው የግሪክኛ ቃልም በጥሩም ሆነ በመጥፎ የተሠራበት ሲሆን ትርጉሙ የሚወሰነው በቃሉ ዙሪያ ባለው ሐሳብ ነው።—1ቆሮ 1:29፤ ሮም 2:17፤ 5:2
ኩራት አታላይና አጥፊ ነው። ኩሩ የሆነ ሰው ኩራት እንዳለበት ላይታወቀው ይችላል፤ እንዲህ ያለው ሰው ኩራት እንዳለበት ላለመቀበል ሲል ለሚያደርጋቸው ነገሮች ሰበብ ሊያቀርብ ይችላል። እያንዳንዱ ሰው እንዲህ ያለ መጥፎ ባሕርይ እንዳለበትና እንደሌለበት ለማወቅ ራሱን ማለትም ዝንባሌውን በሚገባ መመርመር ይኖርበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ትክክለኛ ዝንባሌ መያዝና ራስን መመርመር አስፈላጊ መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ሲል ብሏል፦ “ሌሎችን ለመመገብ ያለኝን ሁሉ ብሰጥ እንዲሁም እኩራራ [ካውካኦማይ] ዘንድ ሰውነቴን አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም የማገኘው ጥቅም የለም።”—1ቆሮ 13:3
ስለዚህ ማንኛውም ሰው የኩራትን ባሕርይ ከውስጡ ነቅሎ ለማውጣት ጥረት ማድረግ አለበት፤ እንዲህ ማድረጉ ጥቅም ያስገኝለታል። በተለይ ደግሞ አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ሰው ይህን ማድረግ ይኖርበታል። እንዲያውም ኩራትን መጥላት ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የአምላክ ቃል “ይሖዋን መፍራት ማለት ክፉ ነገርን መጥላት ነው። ትዕቢትን፣ ኩራትን፣ ክፉ መንገድንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ” ይላል።—ምሳሌ 8:13
አንድ ሰው ያለበትን ኩራት ማስወገድ ካልቻለ ጉዳት ያገኘዋል። “ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል፤” (ምሳሌ 16:18) እንዲሁም “ይሖዋ የትዕቢተኞችን ቤት ያፈርሳል።” (ምሳሌ 15:25) ኩሩ የነበሩ ግለሰቦች፣ መንግሥታትና ብሔራት ውድቀት እንደደረሰባቸው የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎች አሉ።—ዘሌ 26:18, 19፤ 2ዜና 26:16፤ ኢሳ 13:19፤ ኤር 13:9፤ ሕዝ 30:6, 18፤ 32:12፤ ዳን 5:22, 23, 30
ኩራት አታላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ገላ 6:3) ኩሩ የሆነ ሰው በጣም የሚበጀውን ወይም የሚጠቅመውን አካሄድ እየተከተለ እንዳለ ሊሰማው ይችላል፤ ይሁን እንጂ በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ ምንም ቦታ የለውም። (ከኤር 49:16 እና ራእይ 3:17 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ “የትዕቢተኞችን ምርኮ ከመካፈል ይልቅ ከየዋሆች ጋር የትሕትና መንፈስ ማሳየት ይሻላል” ይላል።—ምሳሌ 16:19
መኩራራት። ካውካኦማይ (ኩራት) የተባለው የግሪክኛ ግስ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ኩራትን ለማመልከትም በተደጋጋሚ ተሠርቶበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ማንም ሰው በራሱ ወይም ባገኘው ስኬት መኩራራቱ ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራል። በቆሮንቶስ በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንዳንዶች በራሳቸው ወይም በሌሎች ሰዎች በመኩራራታቸው ምክንያት መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር። አስተሳሰባቸው ሥጋዊ ስለነበር ትኩረት ያደረጉት ከክርስቶስ ይልቅ በሰዎች ላይ ነበር። (1ቆሮ 1:10-13፤ 3:3, 4) እነዚህ ሰዎች ለጉባኤው መንፈሳዊ ደህንነት ግድ አልነበራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በውጫዊ መልክ ይኩራሩ ነበር፤ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው በአምላክ ዘንድ ጥሩ ልብ እንዲኖራቸው የመርዳት ፍላጎት አልነበራቸውም። (2ቆሮ 5:12) በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ አምላክና እሱ ባደረገላቸው ነገሮች ላይ እንጂ በሌላ በምንም ነገር መኩራራት እንደሌለባቸው በመግለጽ ለጉባኤው ጠንካራ ተግሣጽ ሰጥቷል። (1ቆሮ 1:28, 29፤ 4:6, 7) ልንከተለው የሚገባው ሕግ ይህ ነው፦ “የሚኩራራ በይሖዋ ይኩራራ።”—1ቆሮ 1:31፤ 2ቆሮ 10:17
የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ፣ ሊያደርጉ ባሰቧቸው ዓለማዊ እቅዶች የሚኩራሩ ሰዎችን ሲያወግዝ “እናንተ ከልክ በላይ ጉራ በመንዛት ትኩራራላችሁ። እንዲህ ያለው ጉራ ሁሉ ክፉ ነው” ብሏል።—ያዕ 4:13-16፤ ከምሳሌ 27:1 ጋር አወዳድር።
ተገቢ ኩራት። ጋአህ የተባለው የዕብራይስጥ ቃልም ሆነ ካውካኦማይ የተባለው የግሪክኛ ቃል እንዲሁም ከእነዚህ ቃላት የተገኙ ሌሎች ቃላት፣ አንድ ሰው ባከናወነው ወይም ባለው ነገር መኩራራቱ ተገቢ ሊሆን የሚችልባቸው ጊዜያት እንደሚኖሩ በሚያመለክት መንገድ ተሠርቶባቸዋል። መዝሙራዊው ስለ እስራኤል ሲናገር ‘ይሖዋ የሚወደው የያዕቆብ መመኪያ’ በማለት ገልጾታል። (መዝ 47:4) ኢሳይያስ ስለመታደስ ዘመን ትንቢት ሲናገር የምድሪቱ ፍሬ “የኩራት ምንጭ” እንደሚሆን ገልጿል። (ኢሳ 4:2) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በተሰሎንቄ ጉባኤ የሚገኙ ክርስቲያኖች እምነት፣ ፍቅርና ጽናት በማሳየታቸው “በአምላክ ጉባኤዎች መካከል እኛ ራሳችን ስለ እናንተ በኩራት እንናገራለን” ብሏቸዋል። (2ተሰ 1:3, 4) ክርስቲያኖች ይሖዋ አምላካቸው ስለሆነ፣ እሱን ማወቅ በመቻላቸውና እሱም ስላወቃቸው ይኮራሉ። ክርስቲያኖች የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ይከተላሉ፦ “የሚኩራራ በዚህ ነገር ይኩራራ፦ ስለ እኔ ጥልቅ ማስተዋልና እውቀት ያለው በመሆኑ እንዲሁም በምድር ላይ ታማኝ ፍቅር የማሳየው፣ ደግሞም ፍትሕና ጽድቅ የማሰፍነው እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በማወቁ ይኩራራ።”—ኤር 9:24፤ ከሉቃስ 10:20 ጋር አወዳድር።