ኩራት የሚያስከትለው መዘዝ—ምን ያህል የከፋ ነው?
ሆነ ብሎ አንተን ለማንኳሰስ የሚጥር ሰው አጋጥሞህ ያውቃል? ምናልባትም እንዲህ በጣም በንቀት የተመለከተህ ሰው ሥራ አስኪያጅህ፣ አለቃህ፣ ተቆጣጣሪህ ወይም የገዛ ዘመድህ ይሆን? ስለዚህ ሰው ምን ተሰማህ? ጠባዩ ማርኮህ ነበር? እንዳልማረከህ ምንም ጥርጥር የለውም! ለምን? ምክንያቱም ኩራት እንቅፋት ሆኖ ግንኙነታችሁን ስለሚያሻክረው ነው።
አንድ ሰው የኩራት መንፈስ ካለበት ማንንም ሰው ዝቅ አድርጎ እንዲመለከትና ምንጊዜም ከሌሎች የላቀ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። እንዲህ ዓይነት መንፈስ የተጠናወተው ግለሰብ ስለ ሌሎች በጎ ነገር መናገር አይቀናውም። ምን ጊዜም በንግግሩ ጣልቃ “አዎን፣ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም እገሌ እንዲህ ዓይነት ችግር አለበት ወይም ይህ ነገር ይጎድለዋል” እንደሚሉት ያሉ አፍራሽ አነጋገሮች አያጣም።
ቶውትስ ኦቭ ጎልድ ኢን ዎርድስ ኦቭ ሲልቨር የተባለ አንድ መጽሐፍ ኩራትን “ፈጽሞ አልበገር ያለ መጥፎ ጠባይ። የአንድን ሰው ክብር አሟጥጦ ለጉዳት የሚዳርግ” ባሕርይ በማለት ይገልጸዋል። ታዲያ ኩራት ከሚያጠቃው ሰው ጋር መሆን ማንንም ሰው የማያስደስት መሆኑ ምን ያስደንቃል? እንዲያውም ኩራት ብዙውን ጊዜ ጓደኞቻችን እንዲርቁን በማድረግ ይጎዳናል። “በአንፃሩ” ይላል ይኸው መጽሐፍ “ብዙ ሰዎች ትሑት ነኝ እያለ የሚኩራራን ሰው ሳይሆን በትክክል ከልቡ ትሑት የሆነን ሰው ይወድዳሉ።” መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ጋር በመስማማት “ሰውን ኩራቱ ውርደት ላይ ይጥለዋል፣ ራሱን የሚያዋርድ ግን ክብርን ይቀበላል” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 29:23 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል
ይሁን እንጂ ኩራት ወዳጆችን ከማራቅ ወይም በሰዎች ዘንድ ክብር ከማሳጣቱም ይበልጥ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና የሚነካበት እንዴት ነው? አምላክ ኩራተኛ፣ ትዕቢተኛና ትምክህተኛ የሆነን ሰው የሚመለከተው እንዴት ነው? ኩራተኛ ወይም ትሑት መሆንህ ለእርሱ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራልን?
ትሕትናን መማር
በመንፈስ ተነሳስቶ የምሳሌን መጽሐፍ የጻፈው ሰው “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል። ከዕቡያን ጋር ምርኮን ከመካፈል ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል” ብሏል። (ምሳሌ 16:18, 19) ኤልሳዕ የተባለው እስራኤላዊ ነቢይ በሕይወት በነበረበት ዘመን ይኖር በነበረው ሶርያዊ የጦር አዛዥ በንዕማን ላይ እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸው በሚገባ ታይቷል።
ንዕማን የሥጋ ደዌ በሽታ ነበረበት። እዚያ እንደደረሰ ኤልሳዕ በግል ቀርቦ እንደሚያነጋግረው በማሰብ ለበሽታው ፈውስ ፍለጋ ወደ ሰማርያ ተጓዘ። ነቢዩ ግን ወደ ንዕማን አገልጋዩን ላከና በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ እንዲታጠብ ነገረው። ንዕማን በተደረገለት አቀባበልና በተሰጠው ምክር በጣም ተበሳጨ። ነቢዩ አገልጋዩን ከመላክ ይልቅ ራሱ በግል ቀርቦ ያላነጋገረው ለምንድን ነው? ለወንዝ ለወንዝማ ከዮርዳኖስ ወንዝ የማይተናነሱ ወንዞች በሶርያም አሉ! ንዕማን ኩራት ነበረበት። ውጤቱ ምን ሆነ? የተነገረውን ጥበብ ያዘለ ምክር መቀበሉ ጥቅም አስገኘለት። “የእግዚአብሔርም ሰው እንደተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፣ ንጹሕም ሆነ።”—2 ነገሥት 5:14
አንዳንድ ጊዜ በመጠኑ ትሕትና በማሳየት ብቻ ብዙ በረከት ማግኘት ይቻላል።
ትዕቢት የሚያስከትለው ኪሣራ
ሆኖም ኩራት አንዳንድ ሊገኙ የሚችሉ ጥቅሞችን ወይም ትርፎችን በማሳጣት ብቻ የሚወሰን አይደለም። ዕብሪት የሚል ፍቺ ያለው በግሪክኛ ኢቭረስ የተባለ በደረጃው ላቅ ያለ ሌላ የኩራት ዓይነት አለ። ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ዊልያም ባርክሌይ እንደተናገሩት “ኢቭረስ የሚለው ቃል ኩራትንና ጭካኔን አጣምሮ የያዘ ሲሆን . . . [አንድ ሰው] ትዕቢት በተሞላበት ንቀት ተነስቶ እንደ እርሱ ያሉ ሰዎችን እንዲያዋርድ የሚያደርገው ነው።”
እንዲህ ዓይነቱን ከፍተኛ ኩራት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ይህም የአሞን ንጉሥ የነበረው የሃኑም ታሪክ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ናዖስ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቶት ስለነበር ዳዊት አባቱን በሞት ያጣውን ሐኖንን እንዲያጽናኑ መልእክተኞች ላከ። ይሁን እንጂ ዳዊት ይህን ያደረገው ሆን ብሎ በዘዴ ከተማዋን ለመሰለል ነው በማለት መኳንንቱ ስላሳመኑት ሐኖን የዳዊትን አገልጋዮች የጢማቸውን ገሚስ በመላጨትና ልብሳቸውን እስከ መቀመጫቸው ድረስ በመቅደድ አዋርዶ ወደ መጡበት ሰደዳቸው።”a ባርክሌይ ይህን ድርጊት በተመለከተ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “ድርጊቱ ኢቭረስ ነበር። ይህ ድርጊት ስድብን፣ የጭካኔ ተግባርንና በሰው ፊት ማዋረድን አጠቃሎ የያዘ ነበር” ብለዋል።—2 ሳሙኤል 10:1-5
አዎን፣ ኩሩ ሰው ስድ በመሆንና ሌሎችን በማዋረድ ዕብሪተኛ ሊሆን ይችላል። አንድን ሰው ርኅራኄና ስብዕና በጎደለው መንገድ መጉዳትና ከዚያም ሲሸማቀቅና ሃፍረት ሲሰማው ማየት ያስደስተዋል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለራሱ ያለው አክብሮት እንዲቀንስ ወይም ጨርሶ እንዲጠፋ ማድረግ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍ ነው። ይህም ጓደኛ እንዲያጣና ምናልባትም ጠላት ወደማፍራት ሊመራው ይችላል።
ማንኛውም እውነተኛ ክርስቲያን ቢሆን ጌታው ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ’ ብሎ አዞት ሳለ እንዴት እንዲህ ያለውን አደገኛ ኩራት ሊያንጸባርቅ ይችላል? (ማቴዎስ 7:12፤ 22:39) አምላክና ክርስቶስ ጨርሶ የማይደግፉት ነገር ነው። ባርክሌይ በጻፉት ዘገባ ውስጥ ይህን ሁኔታ እንዲህ በማለት ገልጸውታል:- “ዕብሪት አንድን ሰው አምላክን እስከ መናቅ የሚያደርሰው የኩራት ዓይነት ነው።” “አምላክ የለም” የሚያሰኘው ኩራት ነው። (መዝሙር 14:1) ወይም በመዝሙር 10:4 (የ1980 ትርጉም) ላይ እንደተገለጸው “ኃጢአተኛ ስለ እግዚአብሔር ግድ የለውም፤ በትዕቢቱም ‘እግዚአብሔር የለም’ ብሎ ያስባል።” እንዲህ ያለው ኩራት ወይም ትዕቢት አንድን ሰው ከወዳጆቹ ወይም ከዘመዶቹ ብቻ ሳይሆን ከአምላክም ጭምር ያርቀዋል። እንዴት ያለ ትልቅ ኪሣራ ነው!
ኩራት እንዲሸረሽርህ አትፍቀድለት
ኩራት በርካታ ገጽታዎች ሊኖሩት ይችላል፤ ከብሔራዊ ስሜት፣ ከዘረኝነት፣ ከመደብና ከኑሮ ደረጃ ልዩነት፣ ከትምህርት ደረጃ፣ ከሀብት፣ ዝናን ከማትረፍና ከሥልጣን ሊመነጭ ይችላል። መነሻው ምንም ይሁን ምን ኩራት ቀስ በቀስ ሊያድግና ባሕርይህን ሊሸረሽር ይችላል።
አንድ ሰው ከእሱ በላይ በሆኑ ወይም ሌላው ቀርቶ አቻ በሆኑት ሰዎች ፊት ትሑት ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ትሑት ተደርጎ ይታይ የነበረ ሰው ሥልጣን በሚይዝበት ጊዜስ? ወዲያው የበታቹ በሆኑት ላይ ሥልጣኑን አለአግባብ በመጠቀም ሕይወታቸውን የሚያስመርር ይሆናል! አንዳንዶች ሥልጣን ማግኘታቸውን የሚያሳይ የደንብ ልብስ ገና ከመልበሳቸው ወይም ገና ባጅ ከመለጠፋቸው እንዲህ ያለውን ድርጊት ይፈጽሙ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ሠራተኞች እንኳ የሕዝቡ አገልጋዮች መሆናቸውን ዘንግተው ሕዝቡ የእነርሱ አገልጋዮች እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ከሕዝቡ ጋር ባላቸው ግንኙነት ኩሩዎች ሆነው ሊታዩ ይችላሉ። ኩራት ክፉና ጨካኝ ሊያደርግህ ይችላል። ትሕትና ደግሞ ደግ እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል።
ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ሊኮራባቸውና ጨካኝ ሊሆንባቸው ይችል ነበር። ፍጹምና የአምላክ ልጅ ሆኖ ሳለ ይኖር የነበረው ግን ፍጽምና ከሌላቸው፣ ችኩልና አስቸጋሪ ከሆኑ ተከታዮቹ ጋር ነበር። ይሁን እንጂ ያዳምጡት ለነበሩት ሰዎች ምን ግብዣ አቅርቦ ነበር? “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28-30
እኛስ የኢየሱስን ምሳሌ ለመኮረጅ ሁልጊዜ ጥረት እናደርጋለን? ወይስ ጥብቅ፣ ግትር፣ በማን አለብኝነት የምንመላለስ፣ ምሕረት የለሾችና ኩሩዎች ነንን? ልክ እንደ ኢየሱስ ሰዎችን የምናሳርፍ ለመሆን መጣር አለብን እንጂ የምናስጨንቅ መሆን የለብንም። እንደ ዝገት ከሚበላው ከኩራት መንፈስ ራሳችንን እንጠብቅ።
ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር ወይስ ራስን ከልክ በላይ ከፍ ከፍ ማድረግ
በተጨማሪም ኩራት “ምክንያታዊ ወይም ተገቢ በሆነ ሁኔታ ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር ነው።” (ዌብስተር ናይንዝ ኒው ኮሊጂዬት ዲክሽነሪ) ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር ማለት ለራስህ አክብሮት ይኑርህ ማለት ነው። ይህም ሌሎች ስለ አንተ የሚሰጡት ግምት ያሳስብሃል ማለት ነው። ስለ አቋምህና ስለ ስምህ ታስባለህ። “ከእነማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ” የሚለው የስፓኒሽ አባባል እውነትነት አለው። ዝርክርክ፣ ሰነፍ፣ ስድና ባለጌ ከሆኑ ሰዎች ጋር የምትውል ከሆነ በኋላ አንተ ራስህ እንደ እነርሱ ትሆናለህ። ጠባያቸው ሊጋባብህና ልክ እንደነርሱ ለራስህ አክብሮት ልታጣ ትችላለህ።
በተቃራኒውም ኩራት ዕብሪተኛ ወይም ግብዝ ወደመሆንም ይመራል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በወጎቻቸውና በጽንፈኝነት አቋማቸው ይኩራሩ ነበር። ኢየሱስ ስለ እነሱ ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ብሏል:- “ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ [ሃይማኖተኛ መስለው ለመታየት ሲሉ] አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፣ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፣ በምኲራብም የከበሬታ ወንበር፣ በገበያም ሰላምታና:- መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።”—ማቴዎስ 23:5-7
ስለዚህ አስፈላጊው ነገር ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ውጫዊ መልክን ሳይሆን ልብን የሚያይ መሆኑን አስታውሱ። (1 ሳሙኤል 16:7፤ ኤርምያስ 17:10) ራስን ማመጻደቅ የአምላክ ጽድቅ አይደለም። ይሁን እንጂ አሁን የሚነሳው ጥያቄ እውነተኛ ትሕትና ልናዳብርና ኩራት ከሚያስከትለው መዘዝ ልንርቅ የምንችለው እንዴት ነው? የሚል ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንዕማን ትንሽ ትሕትና በማሳየቱ ብዙ ተጠቅሟል