የአምላክ መንፈስ ሕይወትህን እንዴት ሊነካው እንደሚችል
“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ባዶ ነበረች። አንዳችም አልነበረባትም። ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።” (ዘፍጥረት 1:1, 2) ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መግለጫ ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስ ያገኘውን ትልቅ ጥቅም አጉልቶ ይገልጻል። ይህ መንፈስ በፍጥረት ጊዜ ለሥራ ይንቀሳቀስ ነበር። ምድርም ለሰው ልጆች የተመቻቸ የመኖሪያ ስፍራ የሆነችው በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው።
ይሁን እንጂ ሰዎች ከመንፈስ ቅዱስ አሠራር የበለጠ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። በመንፈስ መሪነት የተጻፈ አንድ ምሳሌ “ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፣ እነሆ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ፣ ቃሌን አስተምራችኋለሁ” ይላል። (ምሳሌ 1:23) በዘመናችን የአምላክ ቃል ‘በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ’ ሰዎች በጻፉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቃልሎአል። (2 ጴጥሮስ 1:21፤ ማርቆስ 12:36፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ማንኛውም ቅን ልብ ያለው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ከመንፈስ ቅዱስ ይጠቀማል።
መንፈስ ቅዱስና የስብከቱ ሥራ
አንድ የይሖዋ ምስክር ወደ ቤትህ መጥቶ ስለ መንግሥቱ ምሥራች ሲያነጋግርህ መንፈስ ቅዱስ በአንድ ሌላ መንገድ ሕይወትህን ሊነካ ይችላል። ይህን እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥራቹን መስበክ በጀመረ ጊዜ “[የይሖዋ (አዓት)] መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ምሥራቹን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና . . . የተወደደችውን [የይሖዋን (አዓት)] ዓመት . . . እናገር ዘንድ” የሚለውን የነቢዩ ኢሳይያስን ቃል በራሱ ላይ እንደሚሰራ አድርጎ ተናግሯል። (ሉቃስ 4:18, 19፤ ኢሳይያስ 61:1, 2) አዎ፣ ኢየሱስ ምሥራቹን እንዲሰብክ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ነበር።
ከዚህም በላይ ኢየሱስ የምሥራቹ ስብከት ሥራ እርሱ ከሞተ በኋላ እንደሚቀጥል ተንብዮአል። “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተከታዮቹን “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዝዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ የመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን የታከለበትን የስብከትና የማስተማር ሥራ አካሂደዋል። የዛሬዎቹ የይሖዋ ምስክሮችም ምሥራቹን በዓለም በሙሉ በመስበክ የእነዚህን የጥንት ደቀ መዛሙርት አርዓያ ይከተላሉ።
ጥምቀትና መንፈስ ቅዱስ
አንድ ግለሰብ ምሥራቹን በጥሩ ልብ ሲቀበል “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንደሚጠመቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። በዚህ መንገድ የአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ ይነካል። “በ . . . ስም” የሚለው ሐረግ “በ . . . ሥልጣን” ወይም “የ . . . ን ቦታ በማወቅ” የሚል ትርጉም አለው።a ስለዚህ በአብ ሥም መጠመቅ ማለት በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን የበላይ ገዥነት አለምንም ጥያቄ መቀበል ማለት ነው። በወልድ ስም መጠመቅ ደግሞ ኢየሱስን እንደ አዳኝ፣ ምሳሌና ንጉሥ አድርጎ መቀበል ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅም በመንፈሱ ላይ ትምክህት መጣልንና ለመንፈሱ ኃይል ራስን ማስገዛትን ይጨምራል።
መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ ውስጥ
“ክርስቲያን” ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ የሚታየው አሳዛኝ የውሸትና የስርቆት ድርጊት፣ ብልግና፣ ብጥብጥና አጠቃላይ ዓመፅ እነዚህ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ለመንፈስ ቅዱስ እሺ ብለው እንደማይገዙለት ያጋልጥባቸዋል። ለመንፈስ ቅዱስ ግፊት እሺ ብለው የሚታዘዙት ግን ታላቅ በረከት ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በመንፈስ አነሳሽነትና መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነቡትን ሁሉ በቁም ነገር ይመለከቱታል፤ በሕይወታቸውም ላይ ይሠሩበታል። በዚህ መንገድ ጥበብ፣ ጥልቅ ማስተዋል፣ የማመዛዘን ችሎታ፣ ብልህነት፣ እውቀትና የማሰብ ችሎታ ሊኖራቸው ችሏል። (ምሳሌ 1:1-4 አዓት) እነዚህ ነገሮች በችግሮች በተናወጠው ዓለማችን ውስጥ ትልቅ ሀብት ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስ እንደነዚህ ያሉትን ግለሰቦች ከባድ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳቸዋል። በድሮ ጊዜ አምላክ ሕዝቦቹ አንድን በጣም አስቸጋሪ ሥራ እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ያሳያቸው ነበር። “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም” ሲል ይሖዋ ተናግሯል። (ዘካርያስ 4:6) ለአምላክና ለመንፈሱ እሺ ብለን ከተገዛን አስቸጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ልንፈጽምና በእኛ ሊወገዱ የማይችሉ መሰናክሎችን ለማለፍ እንችላለን።—ማቴዎስ 6:33፤ ፊልጵስዩስ 4:13
ከዚህም ሌላ የአምላክ መንፈስ አብዛኛው ዓለም የማያውቀውን ነፃነት አግኝተን እንድንደሰት ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ለአምላክ መንፈስ እሺ ብለው የሚገዙት ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖቶች፣ ከአጉል ባሕላዊ አስተሳሰብ፣ የወደፊቱን ጊዜ ከመፍራትና ባሪያ ከሚያደርጉ ከሌሎች ነገሮች ነፃ በመሆን በደስታ ይኖራሉ። የአምላክ መንፈስ ወደ ጥሩ የሚመራ ኃይል ነው! ሌላው ቀርቶ ሰዎችንም እንኳ ሊለውጣቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው።” (ገላትያ 5:22, 23) እያንዳንዱ ሰው ለአምላክ መንፈስ ራሱን አስገዝቶ በዚያ ቢመራ ኖሮ ይህች ዓለም እንዴት የተለየች በሆነች ነበር!
እውነተኛ ክርስቲያኖች በቡድን መልክ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስ ቅዱስን አንድነት” አግኝተው በደስታ ይኖራሉ። (ኤፌሶን 4:3) አንድነትና ሰላም በዛሬው ጊዜ እምብዛም የማይገኙ ነገሮች ናቸው። የአምላክ መንፈስ በሚሠራበት ቦታ ላይ ግን ይገኛሉ። አንድ የሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ ማሰሪያ በይሖዋ ምስክሮች ዘንድ ከሁሉም ዘሮች፣ ቋንቋዎችና ብሔራት የመጡ ሰዎችን ወደ እውነተኛ የ“ወንድማማች ማኅበር” አምጥቷቸዋል።—1 ጴጥሮስ 2:17
የአምላክ መንፈስና አንተ
ከአምላክ የተሰጠ ጥበብና እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የቱን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ይታይሃልን? ችግሮችን ለመፍታትና ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የውሃትንና ራስን መግዛትን ለመኮትኮት መለኮታዊ እርዳታ ማግኘት አስደናቂ አይደለምን? እንግዲያው ለአምላክ ኃይል ራስህን አስገዛ። ይሁንና አንድ ሰው እንደዚያ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አእምሮአችሁንና ልባችሁን እንዲለውጥ ፍቀዱለት። ሕይወታቸውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲለውጠው ከፈቀዱ ሰዎች ጋር ወዳጅ ሁኑ። መለኮታዊውን ፈቃድ ለመማርና ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ርምጃዎች አሁንኑ ውሰዱ። ይህን ካደረጋችሁ “የተስፋ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።”—ሮሜ 15:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በተጨማሪም ማቴዎስ 10:41ን ተመልከት። እዚያ ላይ ኢየሱስ “በነቢይ ስም” እና “በጻድቅ ስም” እያለ ተናግሯል።