ንጹሑ ልሳን እጅግ ብዙ ሕዝብ የሆኑ አምላኪዎችን አስተባብሮ አንድ ያደርጋል
ከአምላክ የተሰጠው ንጹሕ ልሳን ለክርስቲያን አንድነት የሚረዳ ኃይል ነው። የዚህ ማስረጃም ከ64 አገሮች የመጡ ምስክሮች በተገኙበት በምዕራብ በርሊን ሐምሌ 24 እስከ 27, 1990 ከማክሰኞ እስከ ዐርብ በተደረገው የይሖዋ ምስክሮች ስብሰባ ለተካፈሉት ሁሉ ግልጽ ሆኖ ታይቷል።
“ለአምላክ ያደሩ መሆን” በሚል ርዕስ በ1989 በፖላንድ የወረዳ ስብሰባ በተደረገ ጊዜ ከሩሲያና ከቼኮዝሎቫኪያ በሺህ የሚቆጠሩ ተወካዮች መጥተው ነበር። ይሁን እንጂ ከምሥራቅ ጀርመን የመጡት በጥቂት መቶ የሚቆጠሩ ብቻ ነበሩ። ከዚያ ወዲህ የዓለም ሁኔታ በፖለቲካ ረገድ ምን ያህል ተለወጠ! በዚህኛው ስብሰባ ላይ በምዕራብ በርሊኑ ኦሊምፒያ እስቴዲየም ከተሰበሰቡት ምስክሮች ጋር በግምት 30,000 የሚሆኑ ከምሥራቅ ጀርመን የመጡ ተወካዮች ተሰብስበዋል። ይህ ስብሰባ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ከሐሙስ እስከ እሁድ ከተደረጉት በመቶ ከሚቆጠሩት ሌሎች ትላልቅ ስብሰባዎች ጋር አንድ ዐይነት ነበር።
ማክሰኞ ዕለት በመክፈቻ ንግግሩ ላይ የስብሰባው ሊቀ መንበር የይሖዋ ምስክሮች ንጹሑን ልሳን እንዲናገሩ ለመርዳት ከ1919 ጀምሮ ታላላቅ ስብሰባዎች ያበረከቱትን ድርሻ ዘረዘረ። ይህ ስብሰባም እንደዚሁ የተሰበሰቡት ሁሉ ንጹሑን ልሳን ለመናገርና በሱ ለመኖር ያላቸውን ችሎታ እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል። የይሖዋ ሕዝቦች በፀጉር አበጣጠራቸውና በፀባያቸው ንጹሑን ልሳን በመናገር ያደረጉትን መሻሻል እንደሚያሳዩ ሊቀ መንበሩ ተሰብሳቢዎቹን አሳስቧቸዋል።
“ንጹሕ ልሳን ለሁሉም ሕዝቦች”
ከዚህም ጋር በመስማማት የስብሰባውን መንፈስ አጠቃልሎ የሚገልጸውን ንግግር ከላይ የተጠቀሰውን አጠቃላይ መልዕክት አጉልቷል። ንግግሩም አምላክ እንደሚከተለው ሲል ቃል በገባለት በሶፎንያስ 3:9 ላይ የተመሠረተ ነበር፦ “በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሑን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።” ንጹሑ ልሳን ስለ አምላክና ስለ ዓላማው የሚገልጸውን እውነት በሚገባ መረዳትና ማድነቅ ማለት ነው። በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይህን መስጠት የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ከስነ ምግባር ርኩሰት ሁሉ ነፃ የሆነውን ንጹሕ ልሳን ለመማር ግፊቱ የሚመነጨው ለእውነት ካለ ፍቅር መሆን አለበት።
በተጨማሪም ንጹሑን ልሳን መናገር አንዳንድ ቃላትን የመጠቀም ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አኗኗራችን ከአንደበታችን ከሚወጣው ጋር መስማማት አለበት። እንዲያውም የድምፃችን ቃና፣ ፊታችንና ስንናገር የሰውነት እንቅስቃሴያችን ትልቅ ቦታ አላቸው ምክንያቱም ከውስጣችን ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን ያንፀባርቃሉ። እያደገ ከሚሄደው ንጹሕ ልሳን ጋር እኩል ለመራመድ እንድንችል የማያቋርጥ የጥናት ፕሮግራም ሊኖረንና በጉባኤ ስብሰባዎችም አዘውትረን መገኘት አለብን።
ንጹሑን ልሳን መማር
የማክሰኞ ከሰዓት በኋላው ንግግር አጥብቆ እንደገለጸው ንጹሑን ልሳን መማር ማለት “ከመሠረቶች ወደ ጉልምስና (ብስለት) መሸጋገር” ማለት ነው። በመንፈሳዊ እያዳበርን መሄዳችንን ለመቀጠል ከፈለግን እድገት ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ያም ማለት ለመንፈሳዊ እድገት በተደረጉልን ዝግጅቶች ሁሉ መጠቀምና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል ማለት ነው።
በንጹሕ ልሳን በቂ ችሎታ ያለን እንድንሆን “ከይሖዋ የተማርን” መሆን አለብን። ሐሙስ ጠዋት በተከታታይ ተናጋሪዎች የተብራራው ንግግር ርዕስ እርሱ ነበር። የመጀመሪያው ተናጋሪ ከይሖዋ የተማሩ በመሆን ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት አርዓያችን እንደሆነ አመለከተ። ኢየሱስ ከይሖዋ የተማረ ለመሆኑ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ በግልጽ የሚታይ ነበር። ስለዚህ በማስተማር ዘዴው ልንመስለው እንፈልጋለን። እንዲሁም ኢየሱስ ሁልጊዜ ለአባቱ ፈቃድ ራሱን ያስገዛ እንደነበረ እኛም እንዲሁ ማድረግ አለብን።
ተከታዮቹ ሦስት ተናጋሪዎች ይሖዋ በጉባኤዎችና በትልልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት እንዴት እንደሚያስተምር አመለከቱ። ከአምስቱም የጉባኤ ስብሰባዎች ጥቅም ስለምናገኝ አንዳቸውንም ችላ ልንላቸው አይገባንም። እያንዳንዱ ስብሰባ ለመንፈሳዊ እድገታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህም ሌላ ይሖዋ በክልልና በወረዳ ስብሰባዎች እንዲሁም በልዩ የስብሰባ ቀን ፕሮግራሞች አማካኝነት ያስተምረናል። ከእነዚህ ሁሉ ለመጠቀም እንድንችል ልብ ብለን ማዳመጥና የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ አለብን።
ይህን ሲምፖዚየም የተከተለው “ለግል ጥናት መሥዋእት መክፈል” የሚለው ንግግር ነው። ለዚህ ጥናት ጊዜ ለማግኘት አነስተኛ ጠቃሚነት ካላቸው ነገሮች ጊዜ እንድንዋጅ የሚነግረንን የኤፌሶን 5:15, 16 ምክር መስማት ይኖርብናል።
ንጹሑን ልሳን ስንማር ግባችን ሊሆን የሚገባው አንዱ ነገር ሕይወትን መወሰንና ጥምቀት ነው። ይህ ሐቅ “ንጹሑን ልሳን የሚማሩት ሰዎች የሚያደርጉት ጥምቀት” በሚለው ንግግር ጎልቶ ተገልጿል። ይህ ልሳን ብዙዎችን ሕይወታቸውን ወደ መወሰንና ወደ ጥምቀት መርቷቸዋል። ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ አንድ ሰው የምሥራቹን በቅንዓት በመስበክ፣ አዲሱን ባሕርይ በመልበስና ከዓለም ተለይቶ በመኖር የኢየሱስን አርዓያ መከተሉን መቀጠል አለበት።
ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ
ተሰብሳቢዎቹ በትንቢታዊ ድራማዎች ፍጻሜ ላይ የተመሠረቱ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግቦች ሲያገኙ ተደስተው ነበር። ሐሙስ ዕለት ከሰዓት በኋላ ከሕዝቅኤል ትንቢት በተወሰዱ ዋና ሐሳቦች ላይ የተመሠረቱ ሁለት ንግግሮች ተሰጥተዋል። የመጀመሪያው “የይሖዋ ሰማያዊ መንኮራኩር ተነሣ” የተሰኘው ንግግር በጣም ትልቅ የሆነ ክብራማና ድንቅ የሆነ ሰማያዊ መጓጓዣ በመብረቅ ፍጥነት እንደሚንቀሳቀስ ገለጸ። መንኮራኩሩም ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም የሚጠቀምበትንና በሚጓዝበት ሁሉ በፍቅር የሚመራውን የይሖዋን ሰማያዊ ድርጅት ያመለክታል። ነቢዩ ሕዝቅኤል በተለይ ከ1919 ጀምሮ ያሉትን ቅቡዓን ቀሪዎች ያመለክታል። እነርሱም በተለይ ከ1935 ወዲህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ተባብረዋቸዋል።—ራእይ 7:9
የተከታዩ ንግግር ርዕስ “ከሚታየው ድርጅት ጋር እኩል ተራመዱ” የሚል ነበር። የሚታየው የአምላክ ድርጅት ከመንኮራኩር መሰሉ ሰማያዊ ድርጅቱ ጋር እኩል እየተራመደ ስለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ሕዝቅኤል እንዳደረገው ዛሬም የይሖዋ አገልጋዮች ግዴለሽነት፣ ፌዝ ወይም ተቃውሞ ሳይቀር ቢያጋጥማቸውም ትንቢታዊ ተልዕኳቸውን በታዛዥነት መፈጸም አለባቸው። እኩል መራመድ ባሁኑ ጊዜ ወደ ብዙ በረከት ያደርሳል፤ በፍጥነት እየቀረበ ባለው አዲስ ዓለም ደግሞ የዘላለም ሕይወት።
ዐርብ ዕለት ጠዋት በኢሳይያስ ምዕራፍ 28 ላይ በተመሠረቱ ሦስት ንግግሮች አማካኝነት ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ቀርቦ ነበር። ከእነሱም የመጀመሪያው በኃይለኛ አነጋገር የጥንቷ እስራኤል መንፈሳዊ ሰካራሞች የሕዝበ ክርስትናን መንፈሳዊ ሰካራሞች እንደሚያመለክቱ አሳየ። እነዚያን የጥንቷ እስራኤል መንፈሳዊ ሰካራሞች የይሖዋ የቁጣ ፍርድ እንዳጋጠማቸው ሁሉ የሕዝበ ክርስትናዎቹም እንዲሁ ይመጣባቸዋል።
ርዕሱ “መሸሸጊያቸው ሐሰት ነው” የተሰኘው ተከታዩ ንግግር ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ይዞ ነበር። ይኸውም ልክ የጥንቷ ይሁዳ በግብፅ መታመኗ ከንቱ ሆኖ እንደቀረ ሕዝበ ክርስትናም ከዛሬዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መተባበሯ እንዲሁ ከንቱ ነው። “ስለ ይሖዋ እንግዳ ሥራ ማስጠንቀቃችሁን ቀጥሉ” የተሰኘው የኢሳይያስ ምዕራፍ 28 ሦስተኛ ንግግር የቀረበው ለይሖዋ ሕዝቦች ነበር። ይሖዋ በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚያደርገው ሥራ ፈጽሞ ሳታስበው ስለሚመጣ እንግዳ ሥራ መባሉ ተገቢ ነው። ባሁኑ ጊዜ ይሖዋ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች አነስተኛ ቡድንና ከአራት ሚልዮን ለሚበልጡት “ሌሎች በጎች” የክብር አክሊላቸው ነው። (ዮሐንስ 10:16) ተናጋሪው “ቅንዓታችን፣ ቁርጥ ውሳኔያችንና ታማኝነታችን ለአምላካችን ለይሖዋ ዘላለማዊ ምስጋና ድርሻ ያበርክት!” በሚሉት የሚያነቃቁ ቃላት ንግግሩን ደመደመ።
ንጹሑን ልሳን መናገር ማለት የወንድማማችነት ፍቅር ማሳየት ማለት ነው
ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ተሰብሳቢዎቹ ንጹሑን ልሳን መናገር ማለት “ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን በመከራቸው መጠየቅ” ማለትም እንደሆነ ተገነዘቡ። አባት የሌላቸው ልጆች የግል ማሠልጠኛ እንዲያገኙ ሊረዱ ይችላሉ። የሚያበረታቱ የደግነት ቃላት በመናገር እንዲሁም በክርስቲያናዊ ሥራዎቻችንና በማኅበራዊ ስብሰባዎቻችን እነሱን በመጨመር፣ እንዲሁም የሚገባቸው ከሆነና በእውነት የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ቁሳዊ እርዳታ በማድረግ ባል ለሞተባቸው አሳቢነታችንን ልናሳይ እንችላለን። እነዚህ የአሳቢነት መግለጫዎች እንዴት እየተደረጉ እንዳሉ ቃለ ምልልሶች አሳይተዋል።
ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ሌላ ልብን የሚያሞቅ “ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚረዳዱ” አሳየ። የይሖዋ ምስክሮች በተለይ እንደ አውሎ ነፋስና የመሬት መናወጥ የመሳሰሉት አደጋዎች ሲደርሱ፣ ለባለ ሥልጣኖች ደብዳቤ መጻፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ወይም በአንድ አካባቢ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ እርስ በርሳቸው በመረዳዳት መልካም መዝገበ ታሪክ አላቸው። ይሁን እንጂ በሰብአዊ አለፍጽምና ምክንያት ችግር ሲነሣ በማቴዎስ 5:23, 24 እና ማቴ 18:15-17 ባለው የኢየሱስ ምክር ውስጥ የሚገኙትን ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል አለብን። በተለይ ወንድሞች በሥራ ጉዳይ የሚገናኙ ከሆነ አሠሪውም ሆነ ሠራተኛው መንፈሳዊ ዝምድናቸውን በራስ ወዳድነት እንዳይጠቀሙበት እርስ በርስ መከባበርና ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ንጹሑን ልሳን መናገር ማለት ስለ አኗኗራችን ጥንቃቄ ማድረግ ነው
ስለ አኗኗራችን የመጠንቀቅ አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ተሰጥቶበታል። ስለዚህ የማክሰኞው የከሰዓት በኋላ መጀመሪያ ተናጋሪ “የአምላክን ቃል መስማትና መጠበቅ” በሚለው አጠቃላይ መልዕክት ላይ ንግግር አደረገ። ወደ ትልልቅ ስብሰባዎች የምንመጣባቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች መኖራቸውን ገለጸ። እነሱም ትክክለኛ እውቀት ለመውሰድና በዚያ ትክክለኛ እውቀት መሠረት ለመኖር ማነቃቂያ ማግኘት ናቸው።
የረቡዕ ጠዋት የመጀመሪያ ንግግር “ክርስቶስ ዓመፃን ጠልቷል፤ እናንተስ?” የሚል ልብ የሚመረምር ጥያቄ አቀረበ። ጽድቅን መውደድ ብቻ በቂ አይደለም። መልካም ሕሊና ለመያዝ፣ ከይሖዋ ጋር ያለንን መልካም ዝምድና ለመጠበቅ፣ በስሙ ላይ ነቀፌታን ከማምጣት ለመራቅና የዓመፃ ፍሬዎች የሆኑትን ውድቅ ግብረገብነትንና ሞትን ከማጨድ ለመራቅ ዓመፃንም መጥላት አለብን።
ከዚያ አጠቃላይ መልዕክት ጋር አብሮ የሚሄድ “ዓለማዊ ቅዠትን አስወግዱ፣ የመንግሥቱን እውነተኛ ነገሮች ተከታተሉ” የሚል ርዕስ ያለው ተከታዩ ንግግር ነበር። ሰይጣን፣ ሔዋንና ኃጢአተኞቹ መላእክት ሁሉም ለውድቀት ያበቃቸውን ቅዠት ተከትለዋል። ስለ ቁሳዊ ነገሮች ማለምን ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ የፆታዊ ግንኙነት ሐሳቦችን የሚጨምሩት ዓለማዊ ቅዠቶች ያሰቡት ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ወደሚመጣው መጥፎ የስሜት ጉዳትና ምናልባትም ወደ ከፍተኛ መጥፎ ተግባር ሊያደርሱ ይችላሉ። እነዚህን ቅዠቶች ለመከላከል በጥናት፣ በጸሎት፣ ስብሰባ በመካፈልና በሕዝባዊ አገልግሎት አማካኝነት የመንግሥቱን እውነተኛ ነገሮች መከታተል አለብን።
ቀና የሆነ ክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር ረቡዕ ዕለት ከሰዓት በኋላ የተሰጠውን “ክርስቲያኖች እንደ አቅማችሁ ኑሩ” የሚለውንም ምክር በሥራ ማዋል አለብን። ይህን አለማድረግ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ጎጂ ውጤቶች አሉት። የጥበቡ መንገድ ሳያስፈልግ ወደ ዕዳ ባለመግባትና ሚዛናዊ ባጀትን አቅዶ ከእሱ ጋር በመጣበቅ የስስት ምኞትን መግታት ነው። በማንኛውም ጊዜ ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ዝንባሌ መኮትኮት አለብን። በቃኝ ከማለት ጋር ተጨምሮ ይህ ታላቅ ማትረፊያ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8
ስለ ባልንጀራዎቻችን የመጠንቀቅን አስፈላጊነት “ወዳጆቻችሁ የይሖዋ ወዳጆች ናቸውን?” በተሰኘው የማክሰኞ ዕለቱ ንግግር ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ወዳጆቻችን ክርስቶስ መሰሉን ባሕርይ የለበሱና በስብከቱ ሥራ ቀናተኞች የሆኑ ክርስቲያኖች መሆን ይኖርባቸዋል። ዓለማዊ ጓደኞች የአምላክ ወዳጆች አይደሉም። በመሆኑም እነሱን ከተጠጋን በራሳችን ላይ ጉዳት ሳናስከትል አንቀርም። ወዳጅነታችን በእውነት የሚያንጽ እንዲሆን ከተፈለገ በጉባኤ ውስጥም እንኳ ሳይቀር መራጮች መሆን አለብን።
ጠባይን በሚመለከት ከዚህ በላይ የተሰጠው ምክር በዘመናዊ ድራማ ጉልህ በሆነ መንገድ ተገልጿል። ርዕሱ “የዲያብሎስን የሽንገላ ድርጊቶች መቋቋም” የተሰኘ ነበር።
የንጹሕ ልሳን ምክር ለቤተሰቦች
ረቡዕ ዕለት የተሰጠው “ወላጆች ግዴታዎቻችሁን ፈጽሙ” የሚለው ንግግር በጣም አስፈላጊ ነበር። ወላጆች ራሳቸው የአምላክን ፈቃድ የሚያውቁ ሊሆኑና የተቻላቸውን ያህል ሊፈጽሙት ይገባቸዋል። በተጨማሪም የአምላክን ቃል በልጆቻቸው ልብ ውስጥ መቅረጽ ይገባቸዋል። ከዚህም በላይ ልጆችን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ወደ መስክ አገልግሎት መውሰድ ብቻ በቂ አይደለም። ይሖዋን እንዲያፈቅሩትና አምላካዊ ነገሮችን የማድረግን ተግባራዊ ጥበብ እንዲያዩ ሊማሩ ይገባቸዋል።
ቀጥሎም “ቤተሰብ በዘመናችን” የሚል ርዕስ በተከታታይ ተናጋሪዎች ተሸፈነ። የመጀመሪያው ተናጋሪ ቤተሰብ የተመሠረተው በአምላክ መሆኑን ገለጸ። አባቶች መንፈሳዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለልጆቻቸው በሚገባ ሊያስተላልፉ ይገባቸዋል። እናቶች ጥሩ ቤት ያዦች መሆን አለባቸው። ልጆችም ከወላጆቻቸው ጋር በመተባበር ለይሖዋ አክብሮት ማሳየት አለባቸው።
ተከታዩ ተናጋሪ ቤተሰብ “በጠላቶች በመጠቃት ላይ” መሆኑን አመለከተ። ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጉዳት በማድረስ ላይ ናቸው። የሥራ ቦታ መጥፎ ለመሥራት በሚፈታተኑ ነገሮች የተሞላ ነው። የዜና ማሰራጫዎችም በዓመፅ፣ የተከለከሉ የጾታ ግንኙነቶችና ለፍቅረ ንዋይ ስሜት በሚቀሰቅሱ ነገሮች ተበላሽተዋል። ትምህርት መስጠቱ ልጆች ገና ትንሽ እያሉ መጀመር አለበት። ዓለማዊ ተጽእኖዎችን ለማሸነፍ ታላቅ ትጋት ያስፈልጋል። በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አማካኝነት በሚቀርቡት አምላካዊ መሣሪያዎች ጥሩ አጠቃቀም መደረግ አለበት።
‘ቤተሰብ ወደ አዲሱ ሥርዓት በሕይወት እንዲያልፍ’ በሚል ርዕስ የቀረበው ተከታዩ ንግግር ወላጆች ያለባቸውን ከባድ ኃላፊነት አስምሮበታል። የልጆች ማሠልጠኛ በታላቅ ቁርጠኝነት ሊደረግ ይገባል። የልጆችን ልብ ለመንካት ሲባል የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትንና ምን ሊጠና እንደሚችል በማስመልከት መልካም ምክር ተሰጥቷል። እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው ወላጆችና ልጆች እንደ ቤተሰብ ሆነው ወደ አዲሱ ዓለም ለመግባት ተስፋ ሊያደርጉ የሚችሉት።
ብዙ ምስክሮች ስለሚኖሩበት የቤተሰብ ሁኔታ ጠቃሚ ምክር ያቀረበው ንግግር “በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ መጽናት” የሚል ነበር። በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ የማያምነው ወገን አንድ ቀን አማኝ ሊሆን ስለሚችል ፈጽሞ ተስፋ እንዳይቆርጡ ተመክረዋል። ከማያምነው ጋር የምታሳልፉት ጊዜ ይኑራችሁ። ከአንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ የሚፈለገውን ሁሉ እንደምታሟሉም እርግጠኞች ሁኑ። ከሽማግሌዎች ወይም ምናልባትም በተከፋፈለ ቤተሰብ ከሚኖሩ ከሌሎች እርዳታ ማግኘት ትችሉ ይሆናል።
ንጹሑን ልሳን ለሌሎች መናገር
ንጹሑን ልሳን ለሌሎች ለማስተማር የምናገኛቸውን አጋጣሚዎችን ሁሉ ስለ መጠቀማችን ብዙ ትኩረት መስጠቱ በጣም ተገቢ ነበር። ስለሆነም ረቡዕ ዕለት ጠዋት ተሰብሳቢዎቹ “እጅግ ውድ የሆነውን ጊዜያችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት” የሚለውን ንግግር አዳምጠዋል። ያን ለማድረግም “አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን መፈለጋችሁን ቀጥሉ” ከሚለው ማቴዎስ 6:33 ጋር በመስማማት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ነገሮች ማወቅ ያስፈልገናል። ያም ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ መመደብን፣ በሁሉም ስብሰባዎች መካፈልን፣ በመስክ አገልግሎቱ አዘውታሪዎች መሆንን ያጠቃልላል። ይህም ምንም እንኳ የሚያስደስቱ ቢሆኑም አነስተኛ ጥቅም ካላቸው ሥራዎች ጊዜ መዋጀትን ይጠይቃል። አንዳንዶች ይህን እንዴት ያከናውኑት እንደነበረ አያሌ ቃለ ምልልሶች አስረድተዋል።
የይሖዋ ምስክሮች መሆናችንን ፈጽሞ መርሳት የለብንም። ሐሙስ ዕለት ከሰዓት በኋላ “ንጹሑን ልሳን በማንኛውም ጊዜ መናገራችሁን ቀጥሉ” በሚል አጠቃላይ መልዕክት ስር የተሰጡ በርካታ ትዕይንቶች ይህንኑ ነጥብ አስገንዝበዋል። ይህም ከመንገድ ወደ መንገድ በሚደረገው ምስክርነት፣ በአጋጣሚ ምስክርነትና ቴሌፎንን በመጠቀም እንዴት ሊደረግ እንደሚችል እነዚሁ ትዕይንቶች አሳይተዋል። ለይሖዋ አምላክና ለጎረቤታችን ያለን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ንጹሑን ልሳን በማንኛውም አጋጣሚ እንድንናገር ያንቀሳቅሰናል።
ከዚህ አጠቃላይ መልዕክት ጋር የተያያዘው ቀጥሎ የቀረበው “እያመካኙ ወደ ኋላ የማያፈገፍጉት የሚያገኙት በረከት” የሚለው ንግግር ነበር። ከሕዝበ ክርስትና በጣም በተለየ ሁኔታ በጣም ደምቆ የሚታየው የይሖዋ ምስክሮች አስተማሪ ድርጅት ነው። በግለሰብ ደረጃ ግልጽ ተቃውሞ፣ እየተስፋፋ ያለው ግዴለሽነትና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመሳሰሉትን ግፊቶች መቋቋም አለብን። ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ የተመሠረቱ ትዕይንቶች እነዚህን ግፊቶች እንዴት መቋቋም እንደሚቻል አሳይተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በቅንዓት መስበክን የሚያበረታታው የአምላክን ፈቃድ በቅንዓት ማድረግ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ነበረ። ድራማው የሁ (ኢዩ) ለይሖዋ ስም የቱን ያህል ቀናተኛ እንደነበረና እኛም ለአምላክ ሥራ ተመሳሳይ ድፍረትና ቅንዓት ማሳየታችን ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን አሳይቷል።
በስብሰባው የወጡ አዳዲስ ጽሑፎች
በስብሰባው ወቅት በእንግሊዝኛና በጀርመንኛ ቋንቋዎች የወጡ ግሩም የሆኑ አዳዲስ ጽሑፎች ነበሩ። ከእነዚህ የመጀመሪያው ጽሑፍ “ሕይወትህን በደም አማካኝነት የምታድነው እንዴት ነው?” ከሚለው ንግግር ጋር በማያያዝ ወጥቷል። ተናጋሪው በመጀመሪያ የሌላውን ደም ከመውሰድ ጋር የሚመጡ አደጋዎችን ገለጸ። የፈሰሰውን ደም መልሶ ለመተካት ከደም ሌላ ብዙ አማራጮች መኖራቸውን አመለከተ። የይሖዋ ምስክሮች ከደም የሚርቁት የጤና ጠንቅ በመሆኑ ሳይሆን ደም መቀበሉ መርከስ ማለት በመሆኑ ነው። ከደም የሚርቁት ደሙ የተበከለ ሊሆን ስለሚችል ሳይሆን ለአምላክ ውድ በመሆኑ ነው። እውነተኛ ሕይወት አድን የሆነው ደም ቤዛ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ተናጋሪው ንግግሩን ሲደመድም ደም ሕይወትህን የሚያድነው እንዴት ነው? የሚለውን ባለ 32 ገጽ ብሮሹር በማሳየት አድማጮቹን ሁሉ አስደሰታቸው።
በስብሰባው ላይ ሁለተኛው ጠቃሚ ጽሑፍ የወጣው “እናንተ ሕዝቦች ሆይ ይሖዋን ፈልጉ” ከሚለው ንግግር ጋር በማያያዝ ነበር። በጠቅላላው ሲታይ ሕዝቦች አምላክን እየፈለጉት አይደለም። ብዙ የተለያዩ ሃይማኖቶች መኖራቸው ሰው የአምላክን ቃል ችላ ስላለ አምላክን መፈለጉ ምን ያህል አቅጣጫውን የሳተ መሆኑን ያመለክታል። በያመቱ የሚከበረው መታሰቢያ በዓል ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አቋማቸውን ለይሖዋ እንዲወስዱ መረዳት ያስፈልጋቸዋል። ኢሳይያስ 55:6, 7 ይሖዋ በእውነት አፍቃሪና መሐሪ አምላክ እንደሆነና “በሰፊው ለመማር (ምሕረት ለማድረግ)” ዝግጁ መሆኑን ያመለክታል። ምስክሮቹ እንደመሆናችን መጠን ከእኛ ጋር አንድ ሆነው ይሖዋን ለማገልገል ይተባበሩን ዘንድ ሌሎችን እንረዳ ዘንድ ንጹሕ ልሳን ተሰጥቶናል።
በአሁኑ ጊዜ ሕዝቦች በከፍተኛ ደረጃ ከቦታ ወደ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱና በውጤቱም በክልላችን የሚኖሩ ሰዎች ሁሉም ዓይነት ሃይማኖቶችን የያዙ ሊሆኑ ስለሚችሉ የይሖዋ ሕዝቦች ልዩ ጥረት የሚጠይቅ ሁኔታ እያጋጠማቸው ነው። ሒንዱዎችን፣ ቡድሂስቶችን፣ ሺንቶዎችንና የሌላ ብዙ ሃይማኖቶችን ተከታዮች ለመርዳት እንችል ዘንድ ድርጅት ባለ 384 ገጽ የሆነውን የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የሚል መጽሐፍ አቅርባልናለች። መጽሐፉ ከሕዝበ ክርስትና ውጭ ያሉ ዋና ዋና ሃይማኖቶችን መሠረታዊ ትምህርቶች በታማኝነት አቅርቧል። ይሁን እንጂ በሕዝበ ክርስትና ውስጥም የሐሰት ሃይማኖትን ታሪክም ከስሩ ገልጾታል። ይህ መጽሐፍ ብዙ የተለያዩ ሃይማኖቶች ካላቸው ሰዎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር መንገድ ሊከፍት ይችላል።
የሕዝብ ንግግርና የመደምደሚያ ሐሳቦች
የዐርብ ዕለቱ የሕዝብ ንግግር ርዕስ “በንጹሕ ልሳን አማካኝነት የተባበራችሁ ሁኑ” የሚል ነበር። ተናጋሪው ምንም እንኳ ዛሬ ያሉት ሦስት ሺህ ቋንቋዎች ለአንድነት መሰናክል ሊሆኑ ቢችሉም ንጹሑ ልሳን ኃይለኛ አስተባባሪ ኃይል መሆኑን አመለከተ። ንጹሑ ልሳን የይሖዋን ሕዝቦች ከባቢሎናዊ ስሕተቶች ጠብቋቸዋል፤ ለሕይወትና ለደም አክብሮትን አስተምሯቸዋል፤ በመንፈሳዊና በአካል በሚጠቅሟቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች እንዲኖሩም ረድቷቸዋል። ሁሉም ንጹሑን ቋንቋ ስለ መማርና ስለ መናገር ሊያስቡበት ያስፈልጋቸዋል ምክንያቱም ከአርማጌዶን የሚተርፉት እንዲህ የሚያደርጉ ብቻ ናቸውና። በሶፎንያስ 2:1-3 ያለውን ምክር በተግባር ለማዋል የምንዘገይበት ጊዜ የለም።
“በጸሎት ንቁ መሆን” ስለማስፈለጉ መልካም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ከተሰጠ በኋላ “ከንጹሕ ልሳን ጋር ተስማምቶ መኖር” በሚል አጠቃላይ መልዕክት ላይ የመደምደሚያ ሐሳቦች ተሰጥተዋል። ባሁኑ ጊዜ ከንጹሑ ልሳን ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በእውነት እየጨመረ ነው። እነዚህን ስብሰባዎች የተካፈሉት ሰዎችም በንጽሕናቸው፣ በሥርዓታማነታቸውና በድርጅታዊ ስምምነታቸው ለንጹሑ ልሳን ያላቸውን አክብሮት አሳይተዋል። አዲስ ታትመው የወጡት ጽሑፎችም ሁሉንም የይሖዋ ሕዝቦች ንጹሑን ልሳን በበለጠ ውጤታማነት እንዲያሰራጩ ይረዷቸዋል።
የመጨረሻው የስብሰባው ተናጋሪ የመጽናትን አስፈላጊነት ለሁሉም አሳሰበ። በዚህ ስብሰባ አማካኝነት ሁሉም ወደፊት ለመግፋት ያላቸው ቁርጠኝነት እንደሚጠናከር አመለከተ። “አፍቃሪ ሰማያዊ አባታችንን ይሖዋ አምላክን አሁንና ለዘላለም እናከብረው ዘንድ አምላክ ከሰጠን ንጹሕ ልሳን ጋር ተስማምተን መኖራችንን እንቀጥል!” በሚሉት ቃላት ንግግሩን ደመደመ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በምዕራብ በርሊን በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 44,532 የነበረ ሲሆን 1,018 ተጠምቀዋል። የጥምቀት እጩዎቹ ከኦሊምፒያ ስታዲየም በሰልፍ ለመውጣት 19 ደቂቃ ወስዶባቸዋል። በዚህ ጊዜ የማያቋርጥ ጭብጨባ ነበረ። እንግሊዝኛ ተናጋሪ ለሆኑት ተሰብሳቢዎች ልዩ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ነበር። 6,000 የሚያክሉት መላውን ፕሮግራም በራሳቸው ቋንቋ መከታተል ችለዋል። በዚህ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከፖላንድ 4,500 መጥተው ነበር። የአስተዳደር ክፍል አባላት እነርሱን ለመጥቀም የሁለት ሰዓት ንግግር ሰጥተዋል።
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
1. ምዕራብ በርሊን የሚገኘው የኦሊምፒያ ስታዲየም
2. የስብሰባው ፕሮግራም በጽሑፍ
3. ሁለት መቶ አውቶቡሶች ከምሥራቅ ጀርመን የስብሰባውን ተካፋዮች አመጡ
4. ከፖላንድ የመጡ ተሰብሳቢዎች አዲስ የወጡትን ጽሑፎች በማግኘታቸው ተደሰቱ
5. መድረኩን ለማስዋብ የተጠቀሙበት የአበባ ጌጥ
6. ከአስተዳደር አካል አባል አንዱ የሆነው ኤ. ዲ. ሽሩደር በምዕራብ በርሊን ውስጥ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ