እምነትና ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ
ከአንደኛ ጢሞቴዎስ የተገኙ ዋና ዋና ነጥቦች
ሐዋርያው ጳውሎስ በ56 እዘአ ገደማ ላይ ከመካከላቸው “ጨካኝ ተኩላዎች” እንደሚነሱና “ደቀ መዛሙርትንም ወደኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን” እንደሚናገሩ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች አስጠንቅቆ ነበር። (ሥራ 20:29, 30) ገና ብዙ ዓመት ሳይቆይ የክህደት ትምህርት በጣም በመስፋፋቱ ጢሞቴዎስ የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅና የእምነት ባልደረቦቹ በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ ለመርዳት መንፈሣዊ ውጊያ እንዲያካሂድ ጳውሎስ መክሮት ነበር። በ61-64 እዘአ ላይ በመቄዶንያ ሆኖ ጳውሎስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ለጢሞቴዎስ የጻፈበት ዋነኛ ምክንያት ይኸው ነበር።
ለጢሞቴዎስ ስለ ሽማግሌ የሥራ ግዴታዎች፣ ለሴቶች ከአምላክ ስለተሰጠው ቦታ፣ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሊኖራቸው ስለሚገባው ብቃትና ስለሌሎች ጉዳዮች መመሪያ ተሰጥቶታል። ይህ ዓይነቱ መመሪያ ዛሬም በጣም ጠቃሚ ነው።
ስለ እምነት የተሰጠ ምክር
ጳውሎስ ደብዳቤውን የከፈተው እምነትና ጥሩ ሕሊና ስለመያዝ ምክር በመስጠት ነበር። (1ጢሞ 1:1-20) በኤፌሶን እንዲቆይና አንዳንዶች የተለየ ትምህርት እንዳያስተምሩ እንዲያዝ ጢሞቴዎስን አሳሰበው። ጳውሎስ የኢየሱስን ተከታዮች ያሳደደው በድንቁርናና እምነት በማጣት ምክንያት መሆኑን አምኖ ስለተሰጠው አገልግሎት አመስጋኝ መሆኑን ገልጾአል። ጢሞቴዎስ የእምነት መርከባቸው እንደሰጠመባቸው አንዳንድ ሰዎች ሳይሆን እምነትና በጎ ሕሊና ይዞ መንፈሣዊ ውጊያ እንዲያደርግ ሐዋርያው አዝዞታል።
ስለ አምልኮ የተሰጠ ምክር
ከዚህ ቀጥሎ ጳውሎስ “በእምነትና በእውነትም የአሕዛብ አስተማሪ” እንደመሆኑ መጠን ስለዚሁ ጉዳይ ምክር ሰጠ። (2:1-15) ክርስቲያኖች በሰላም መኖር እንዲችሉ ስለ ባለሥልጣኖች መጸለይ ያስፈልግ ነበር። ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ የአምላክ ፈቃድ ነው። ክርስቶስ ራሱን ለሰው ሁሉ ቤዛ አድርጎ መስጠቱም ዋነኛ መሠረተ ትምህርት ነበር። ሴት ራስዋን በልከኝነት ማስጌጥ እንደሚገባትና በወንድ ላይም መሰልጠን እንደማይኖርባት ገለጸ።
ጉባዔው በሚገባ መደራጀት ነበረበት። (3:1-16) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ የበላይ ተመልካቾችና ዲያቆናት ማሟላት የሚኖርባቸውን ብቃት ዘረዘረ። ጢሞቴዎስ ሐዋርያው ከጻፈለት መመሪያ “የእውነት አምድ” በሆነው ጉባኤ ውስጥ እንዴት እንደሚኖር ለማወቅ ይችል ነበር።
ጢሞቴዎስ ከሐሰት ትምህርት እንዲጠበቅ የሚረዳው ምክር ጳውሎስ ሰጥቶታል። (4:1-16) በኋለኛው ዘመን አንዳንዶች ከእምነት ይወድቃሉ። እርሱ ግን ለራሱና ለትምህርቱ ዘወትር በመጠንቀቅ ራሱንም ሆነ የሚሰሙትን ለማዳን ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ ጢሞቴዎስ ሽማግሌዎችንም ሆነ ወጣቶችን እንዴት እንደሚይዝ ምክር ተሰጥቶታል። (5:1-25) ለምሳሌ ጥሩ ክርስቲያናዊ ዝና ላተረፉ መበለቶች መርጃ ተስማሚ ዝግጅት መደረግ ነበረበት። ወጣት መበለቶችም ሐሜተኞች ከመሆን ይልቅ አግብተው ልጅ መውለድ ነበረባቸው። በጥሩ ሁኔታ የሚመሩ ሽማግሌዎች እጥፍ ድርብ ክብር ሊሰጣቸው ይገባ ነበር።
ኑሮዬ ይበቃኛል እያሉ ለአምላክ ማደር
ጳውሎስ ደብዳቤውን የደመደመው ለአምላክ ስለማደር ምክር በመስጠት ነው። (6:1-21) “ኑሮዬ ይበቃኛል እያሉ ለአምላክ ማደር” (አዓት) ትልቅ ማትረፊያ ነው። ባለጠጋ ለመሆን መፈለግ ግን ወደ ጥፋትና ወደ ብዙ ጉዳት ያደርሳል። ጢሞቴዎስ መልካሙን የእምነት ገድል እንዲጋደልና የዘላለምን ሕይወት አጥብቆ እንዲይዝ ጳውሎስ መከረው። ባለጠጎች ይህን እውነተኛ ሕይወት ለማግኘት “በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ” ምክር ተሰጣቸው።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በመውለድ ትድናለች፦ ጳውሎስ “በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች” ሲል የጻፈው አምላካዊ የሆነች ሴት ሊኖራት የሚገባውን የሥራ ድርሻ ለማመልከት ነው እንጂ የዘላለም ሕይወት መዳንን ስለማግኘት ለመግለጽ ፈልጎ አልነበረም። (1 ጢሞቴዎስ 2:11-15) አንዲት ሴት ልጆች ወልዳ በማሳደግና ቤትዋን በማስተዳደር ሥራ ስትጠመድ ሥራ ፈት ሐሜተኛና በሰው ነገር ገቢ ከመሆን “ትድናለች።” (1 ጢሞቴዎስ 5:11-15) በቤት ውስጥ የምታከናውነው ሥራ ለይሖዋ ለምታቀርበው አገልግሎት ማሟያ ይሆንላታል። እርግጥ፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ጠባያቸውን መጠበቅና በጊዜያቸው በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 5:15, 16