ሃይማኖትን በቁም ነገር መያዝ የሚገባን ለምንድን ነው?
“ሰው በእንጀራ ብቻ መኖር አይችልም።” (ማቴዎስ 4:4 የእንግሊዝኛው አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ) ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ይህ ቃል በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ስለዘነጉት ለሰው ልጆች አስፈላጊ ስለሆነ ነገር ይናገራል። ሊረካ የሚፈልግ መንፈሳዊ ክፍለ ፍጥረት እንዳለን ያመለክታል። ይህን ቃል የተናገረው ኢየሱስ ክርስቶስ “አምላክ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያውቁ የተባረኩ ናቸው” ያለው በዚህ ምክንያት ነው።”—ማቴዎስ 5:3 አዲሱ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ
አምላክ ያስፈልገናል፤ ይህ ፍላጎት ሊሟላልን የሚችለው ግን በሃይማኖት ብቻ ነው። ስለ ሕይወት አመጣጥ፣ ዓላማና፣ ትርጉም የሚነሳብንን መሠረታዊ ጥያቄ ሊመልስልን የሚችለው ሃይማኖት ብቻ ነው። ለሕይወታችን እውነተኛ ትርጉምና ቁምነገር የሚሰጠው ሃይማኖት ብቻ ነው። ይህን ሁሉ ሊያደርግ የሚችለው ግን ማንኛውም ሃይማኖት አይደለም። ኢየሱስ ለአንዲት ሣምራዊት ሴት “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት ያመልኩታል” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 4:23) ‘በእውነት ማምለክ’ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ልማዶችንና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ከማክበር የበለጠ ትርጉም አለው። እነዚህ ልማዶችና ሥርዓቶች ለተከታዮቻቸው ጊዜያዊ የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ከማድረግ አልፎ መንፈሳዊ ረሐባቸውን አያረካላቸውም።
ለምሳሌ ያህል በጃፓን የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የነበሩት ኤድዊን ኦ ራይሻወር “ለአብዛኞቹ ሰዎች ሺንቶና ቡድሂዝም ትርጉም ያለው እምነት ሳይሆን ተራ ልማድና ባሕል ነው” ብለዋል። ብዙ ጃፓናውያን በዚህ ረክተው እንደሚኖሩ አይካድም። ይሁን እንጂ በጃፓን አገር “አዳዲስ ሃይማኖቶች” ማቆጥቆጣቸው ብዙ ሰዎች በወግ ላይ በተመሰረተው ሃይማኖት አለመርካታቸውን ያሳያል።
“አዲሶቹ ሃይማኖቶች” የሚያተኩሩት ሰውን በስሜታዊ ንግግር የመሳብ ችሎታ ባላቸው መሪዎቻቸው ላይ ነው እንጂ በአምላክ ላይ አይደለም። ከእነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ብዙዎቹ የአምላክ መንፈስ አስነስቶናል ይላሉ። ይሁን እንጂ መሠረተ ትምህርታቸው የቡድሂስት፣ የሺንቶ፣ የሌሎች ሃይማኖቶችና የሃይማኖቱ መስራች ፍልስፍና ቅልቅል ከመሆን አላለፈም። ተከታዮች የሚስቡት የተሻለ ህይወት ታገኛላችሁ ወይም ሚሥጥራዊ ወይም የመፈወስ ኃይል አለን በማለት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሃይማኖቶች ተከታዮቻቸው “በመንፈስና በእውነት” እንዲያመልኩ እንደሚያስተምሯቸው የሚያሳይ ማስረጃ አለን? በፍጹም የለም። ምክንያቱም እነዚህ ሃይማኖቶች ዛሬ ብቅ ብለው ነገ ይጠፋሉ። የወረትነት ባሕርይ ስላላቸው በቁም ነገር እንዲወሰዱ የሚያበቃ ምክንያት የለም።
በቁም ነገር ሊወሰድ የሚገባው ሃይማኖት
ይሁን እንጂ ከማንኛውም ዓይነት አምልኮ የበለጠ ጥንታዊነት ያለው ሃይማኖት አለ። እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ሃይማኖት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ የጀመረው ከ35 መቶ ዓመታት በፊት ነው። በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች ተመዝግበው የሚገኙት ታሪኮች ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሺህ ዓመት ቀደም ብሎ የተፈጸሙ ናቸው።a ስለ ሃይማኖት አመጣጥ ጥንታዊ መዝገብ የምናገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ይህ ብቻውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሃይማኖት በጥሞና እንድንመረምር የሚገፋፋን በቂ ምክንያት ነው።
ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፣ “ብርሃኑ በዓለም ሁሉ ተዳርሶአል።” የዓለም መሰልጠን ተስፋ ይበልጥ እውን እየሆነ በሄደበት በዚህ ዘመን ተጠንቶ የማያልቀው ትምህርቱ ትልቅ ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ቅርስ ሆኖ ይታያል።” ይሁን እንጂ አንድ መጽሐፍ ለእውነተኛው ሃይማኖት አስተማማኝ መመሪያ ከሆነ በብዛት መሰራጨትና ለእውነት ፈላጊዎች ሁሉ መዳረስ እንደሚገባው አትጠብቅምን?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ መጽሐፍ ነው። በከፊል ወይም በሙሉ በ1,928 ቋንቋዎች ተተርጉሞአል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዛት የተሠራጨ መጽሐፍ የለም። ከዚህም በላይ በታሪካዊነቱም ሆነ በሳይንሳዊነቱ አስተማማኝነቱ ተረጋግጦአል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው በታሪክም ሆነ በመሬት ቁፋሮ ጥናት ተመስክሮአል። ከማንኛውም ዓይነት የመናፍስትነት ሥራ፣ ከምዋርትና ከምስጢራዊ ተግባራት የነጻ ነው። ይህ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነትና መሪነት ስለመጻፉ ከሚናገረው ጋር የሚስማማ ነው።b—2 ጢሞቴዎስ 3:16
የእውነተኛ ሃይማኖት ፍሬዎች
ይሁን እንጂ ብዙ ሃይማኖቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ተከታዮች ነን ይሉ የለምን? ክርስቲያኖች ነን በሚሉ ሰዎች መካከል ውዝግብ፣ ጠላትነትና ግብዝነት የተስፋፋ አይደለምን? አዎ፣ እውነት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን መጽሐፍ ቅዱስን ችላ ለማለት በቂ ምክንያት አይሆንም። ክርስቲያን ነን ከሚሉ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደማያገኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አመልክቶአል። (ማቴዎስ 7:13, 14, 21-23ን ተመልከት።) ታዲያ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነተኛ ሃይማኖት የሚከተሉትን ሰዎች እንዴት ለይቶ ማወቅ ይችላል? ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ሰጥቶአል፦ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። ስለዚህ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።—ማቴዎስ 7:16, 17, 20
አዎ፣ እውነተኛ ሃይማኖት በአምላኪዎች ላይ ጠቃሚ ውጤት የሚያመጣ፣ በጎ ግፊት የሚያሳድር ኃይል መሆን ይኖርበታል። ራሱ “ሥጋ የለበስኩ የፉክክር መንፈስ ነበርኩ” ያለውን ጃፓናዊ ምሳሌ እንውሰድ። እውቅ ከሆነ ዩኒቨርስቲ የመመረቅና ዝነኛ በሆነ ድርጅት ውስጥ የመቀጠር ግቡን አሟሏ። ሃይማኖት ለሕይወት አስፈላጊ መሆኑ አልታየውም ነበር። ‘ሃይማኖት የሚያስፈልገው ለኑሮአቸው ምርኩዝ ለሚያስፈልጋቸው ደካሞች ብቻ ነው’ ብሎ ያስብ ነበር።
በውጥረትና በድካም ምክንያት ከባድ በሽታ ይዞት እስኪወድቅ ድረስ ሁሉም ነገር የተሳካለት ይመስል ነበር። አንገቱ ተጣመመ፤ አገጩ በግራ ትከሻው ላይ ደረቀ። በአኪኖሪ ኩባንያ ይሰሩ ከነበሩት “ወዳጆቹ” ብዙዎቹ በመከራው ጊዜ አላጽናኑትም። (ከምሳሌ 17:17 ጋር አወዳድር) በዚህም ምክንያት በጠጪነት አዘቅት ውስጥ ወደቀ። እንዲያውም ሕይወቱን ለማጥፋት ማሰብ ጀመረ።
ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የአኪኖሪ ሚስት ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። አንድ ቀን እየተጨዋወቱ ሳለ በገላትያ 6:7 ላይ “ሰው ሁሉ የዘራውን ያጭዳል” የሚለውን ጥቅስ ጠቀሰችለት። አኪኖሪ በእነዚህ ቃላት ልቡ ተነካና ከሚስቱ ጋር አብሮ ማጥናት ጀመረ። በጥናቱ ላይ የተማረው ነገር ስለ ሕይወት ትርጉም ያለውን አስተሳሰብ ለወጠው። የአኪኖሪ አመለካከት ብሩሕ እየሆነ በሄደ መጠን በጭንቀት ምክንያት የመጣበት ሥቃይ እየተወው መጣ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንደሚለው “ሰላም ያለው አእምሮ ለሰውነት ጤንነትን ያስገኛል።” (ምሳሌ 14:30) አዎ! እውነተኛ ሃይማኖት ጥሩ ፍሬ ያፈራል።
እውነተኛ ሃይማኖት ወደ ጥሩ የሚገፋፋ ኃይል ሊሆን እንደሚችል የተገነዘበው ሌላ ሰው ጃፓናዊው ቶሺሮ ነው። ሃይማኖተኛ መሆን ጥቅም እንዳለው ቢያምንም ራሱ ሃይማኖተኛ ለመሆን ያደረገው ጥረት አልነበረም። ምኞቱና ፍላጎቱ በሙሉ የራሱ የሆነ ቤት በማግኘት ላይ ያተኮረ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ምኞቱን ማግኘቱ የጠበቀውን ደስታ አላስገኘለትም። ከዚህም በላይ በመሥሪያ ቤቱ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ሲመለከት የሸፍጥ ድርጊት የተስፋፋ እንደሆነና በዚህም ምክንያት የእርስ በእርስ ግጭት በጣም የበዛ መሆኑን ተገነዘበ። ቶሺሮ በሚያያቸው ነገሮች በሙሉ በጣም ያዝንና ይተክዝ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን ሚስቱ የአካባቢው የይሖዋ ምስክሮች ጉባዔ ሽማግሌ ቶሺሮን እንዲጠይቀው ጋበዘች። ሽማግሌው ከሥራ ባልደረቦቹ የተለየ ሰው መሆኑን ለማስተዋል ለቶሺሮ ብዙ ጊዜ አላስፈለገውም። ምክንያቱም ሽማግሌው የመጽሐፍ ቅዱስን ሥርዐቶች በሥራ ላይ ለማዋል የሚጣጣር ሰው ነበር። ቶሺሮም ልቡ በዚህ ተነካና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። የመጽሐፍ ቅዱስን ሃይማኖት የሕይወቱ መመሪያ ማድረግ ጀመረ።
አንተም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትተዋወቅ እንጋብዝሃለን። “ፍሬያቸው” “በእውነትና በመንፈስ” የሚያመልኩ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ማንኛውንም ችግር ተቋቁመው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሕይወታቸው ውስጥ እንዲሠራ ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። በነፍስ ወከፍ ደረጃ ፍጹም ናቸው ሊባሉ የማይችሉ ቢሆኑም በቡድን ደረጃ ግን እውነተኛው ሃይማኖት እንዴት ያለ መልካም ውጤት የሚያስገኝ መንፈሳዊ ኃይል መሆኑን አስመስክረዋል።
በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አንድ ጊዜ በአኗኗራቸው የማይደሰቱ ነበሩ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥርዓት በሕይወታቸው ውስጥ በሥራ በማዋል በቀላሉ የማይገመት ለውጥ ለማድረግ ችለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈስ ፍሬ የሚላቸውን የፍቅር፣ የደስታ፣ የሰላም፣ የትዕግሥት፣ የደግነት፣ የበጎነት፣ የእምነት፣ የየዋህነትና ራስን የመግዛት ባሕርያት በመኮትኮት ደስታ የሚገኝበትን ምስጢር አውቀዋል።—ገላትያ 5:22, 23
እውነተኛውን ሃይማኖት በመከተል የሚገኙ ዘላለማዊ ጥቅሞች
ይሁን እንጂ እውነተኛው ሃይማኖት ባሕርይ ከመለወጥ ወይም የግል ችግር ከማስወገድ የበለጠ ነገር መፈጸም ይኖርበታል። እንደ አካባቢ መበከል፣ የኒውክልዬር ጦርነት ስጋትና የአካባቢያችን መመናመን የመሰሉት ዓለም አቀፍ ችግሮች ውብ የሆነችውን ምድራችንን ሊያጠፉ ተቃርበዋል። የኢኮኖሚ ችግር በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ደስታ አሳጥቶአቸዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ ችግሮች የሚፈቱበትን ተስፋ የማይሰጥ ሃይማኖት በቁም ነገር ሊከታተሉት የሚገባው አይደለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖት እንዲህ ያለ ተስፋ ይሰጣል። አምላክ በሰማያዊ መንግሥት የሚተዳደር ጻድቅ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቶአል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራዕይ 21:3, 4) ለሰው ልጆች ሥቃይ በሙሉ ፈውስ የሚሆነው ይህ መንግሥት ብቻ ነው። ስለዚህ ዓለም አቀፍ በረከት ዘላቂነት መጽሐፍ ቅዱስ ሲያረጋግጥ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) ይሁን እንጂ ከሚመጣው መንግሥት ጥቅም የሚያገኙት በእውነተኛው ሃይማኖት መመላለስን እንደ ትልቅ ቁም ነገር አድርገው የሚይዙት ሰዎች ብቻ ናቸው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናት እንድትጀምር እንመክርሃለን።c (ዮሐንስ 17:3) የአምላክ ቃል ብርሃን በሕይወትህ ውስጥ እንዲበራ ማድረግ ስትጀምር ‘ለአምላክ ያለህ ፍላጎት’ ደረጃ በደረጃ ስለሚሟላ ትልቅ ደስታ ታገኛለህ። ሃይማኖትን እውነተኛውን ሃይማኖት በቁም ነገር ስለተከተልህ የዘላለም በረከት ታገኛለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 2:4፤ 5:1፤ 6:9 ተመልከት።
b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን በዚህ መጽሔት አዘጋጂዎች የታተመውን መጽሐፍ ተመልከት።
c በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ደስተኞች ናቸው። የዚህን መጽሔት አታሚዎች ወይም በአካባቢህ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ብታነጋግር ነጻ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊዘጋጅልህ ይችላል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ከ1,900 በሚበልጡ ቋንቋዎች መተርጎሙ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነትና መሪነት የተጻፈ ከመሆኑ ጋር ይስማማል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖት በዓለም በሙሉ በሰማያዊ መንግሥት ሥር ሰላም እንደሚሰፍን ተስፋ ይሰጣል