ይሖዋን ማክበር—ለምንና እንዴት?
“ያከበሩኝን አከብራለሁ፣ የናቁኝም ይናቃሉ።”—1 ሳሙኤል 2:30
1. በዓለም ከፍተኛ ዝና ያለውን የኖቤል ሽልማት የሚሸለሙት እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው? ብዙ ሰዎች ይህን ሽልማት እንዴት ይመለከቱታል?
በየዓመቱ አራት የእስካንዲኔቪያ ተቋሞች ‘በቀደመው ዓመት ለሰው ልጆች በጣም የላቀ ውለታ ለፈጸሙ ሰዎች’ የኖቤል ሽልማት ይሰጣሉ። ሽልማቶቹ የሚሰጡት በስድስት መስኮች ከፍተኛ ሥራ ለፈጸሙ ሰዎች ነው። የኖቤል ሽልማት ለሰው ሊሰጥ ከሚችለው ክብር ሁሉ የላቀ እንደሆነ ተደርጎ በብዙዎች ይታሰባል።
2. የኖቤል ሸላሚዎች ማንን ዘንግተዋል? እርሱስ ከሁሉ ይበልጥ ክብር ሊሰጠው የሚገባው ለምንድነው?
2 ለሚገባቸው ሰዎች ክብር መስጠት ስህተት ባይሆንም እነዚህን ሽልማቶች የሚሰጡ ሰዎች ከሁሉ የበለጠ የሰው ልጆች ባለውለታ የሆነውን ስለማክበር አስበው ያውቃሉን? ይህ የሰው ልጆች ባለውለታ ከ6, 000 ዓመታት በፊት የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ቁጥር ሥፍር ለሌለው በጎ አድራጎት ለሰው ልጆች ፈጽሞአል። ይህ ፈጣሪ በተደጋጋሚ የሚገባውን ክብር አለማግኘቱ በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው የኢዮብ ጓደኛ ኤሊሁ የተናገረውን ያስታውሰናል። “በሌሊት መዝሙርን የሚሰጥ . . . ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው? የሚል የለም።” (ኢዮብ 35:10) ታላቁ ባለውለታችን ‘መልካም ማድረጉን፣ ዝናብና ፍሬ የሚሰጡትን ወራት መስጠቱን፣ ልባችንንም በምግብና በደስታ መሙላቱን’ አላቋረጠም። (ሥራ 14:16, 17፤ ማቴዎስ 5:45) በእውነትም “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ” ከይሖዋ የሚመጡ ናቸው።—ያዕቆብ 1:17
ክብር መስጠት ምን ማለት ነው?
3. “ክብር” ተብለው የተተረጎሙት ዋነኞቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት የትኞቹ ናቸው? ትርጉማቸውስ ምንድነው?
3 ክብር ተብሎ የተተረጎመው ዋነኛ የዕብራይስጥ ቃል ካቮድ ሲሆን ቃል በቃል ትርጉም “መክበድ” ማለት ነው። ስለዚህ ክብር የሚሰጠው ሰው ከባድ፣ ባለግርማና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው ማለት ነው። ይህ ካቮድ የተባለው የግሪክኛ ቃል ብዙ ጊዜ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ግርማ” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። ይህም የተከበረው ሰው ምን ያህል አስፈላጊና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ያመለክታል። ሌላው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ክብር” ተብሎ የሚተረጎመው ዬቃር የተባለው የዕብራይስጥ ቃል ደግሞ “ውድ”፣ “ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር” ተብሎ ተተርጉሞአል። ስለዚህ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ክብር የሚለው ቃል ከግርማና ከውድነት ጋር የተዛመደ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ክብር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪከኛ ቃል ቲሜ ሲሆን እርሱም ከፍተኛ፣ ውድና ባለብዙ ዋጋ መሆንን የሚገልጽ ቃል ነው።
4, 5. (ሀ) ለአንድ ግለሰብ ክብር መስጠት ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) በአስቴር 6:1-9 ላይ የተገለጸው ታሪክ ለአንድ ሰው ክብር መስጠት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽልን እንዴት ነው?
4 ስለዚህ አንድ ሰው ሌላውን የሚያከብረው ለተከበረው ሰው ከፍተኛ ግምትና ከበሬታ በመስጠት ነው። ለምሳሌ ያህል ታማኝ አይሁዳዊ ስለነበረው ስለ መርዶክዮስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ሁኔታ ተመልከት። መርዶክዮስ አንድ ጊዜ የጥንታዊቷ ፋርስ ንጉሥ በነበረው በአርጤክስስ ሕይወት ላይ የተደረገ ሤራ አጋልጦ ነበር። በኋላም ንጉሡ እንቅልፍ አልወስድ ባለው አንድ ሌሊት መርዶክዮስ ስላደረገው ድርጊት አወቀ። በዚህም ምክንያት አገልጋዮቹን ጠራና “ስለዚህ ነገር መርዶክዮስ ምን ክብርና በጎነት ተደረገለት?” ብሎ ጠየቀ። እነሱም “ምንም አልተደረገለትም” አሉት። በጣም አሳሳቢ ነገር ነበር። መርዶክዮስ የንጉሡን ሕይወት አድኖ ንጉሡ አድናቆቱን ለማሳየት ምንም ሳያደርግ ቀርቶአል።—አስቴር 6:1-3
5 ስለዚህም ጥሩ አጋጣሚ ጊዜ መርጦ ሐማ የተባለውን ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ንጉሡ የተደሰተበትን ሰው እንዴት እንደሚያከብረው ጠየቀው። ሐማም ወዲያው በልቡ “ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ያከብር ዘንድ ይወድዳል?” ብሎ አሰበ። ስለዚህም “ንጉሡ የለበሰው የክብር ልብስ” እንዲያለብሱት “ንጉሡ የተቀመጠበት ፈረስ” መጥቶለት እንዲቀመጥ ነገረው። በመጨረሻም “በፈረሱም ላይ አስቀምጠውት በከተማይቱ አደባባይ ያሳልፉት፤ በፊቱም ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ አዋጅ ይነገር” አለው። (አስቴር 6:4-9) በዚህ መንገድ ክብር የተሰጠው ሰው በሰዎች ሁሉ ዘንድ ከፍ ተደርጎ የሚታይ ይሆናል።
ለይሖዋ ክብር ሊሰጥ የሚገባው ለምንድን ነው?
6. (ሀ) ከሁሉ በላይ ክብር ሊቀበል የሚገባው ማነው? (ለ) “ታላቅ” የሚለው ቃል ይሖዋን በትክክል የሚገልጸው እንዴት ነው?
6 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለሰዎች እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ለማይገባቸው ሰዎች ክብር ሲሰጥ ቆይቷል። (ሥራ 13: 21-23) ይሁን እንጂ ከሁሉ የበለጠ ክብር ሊሰጠው የሚገባ ማን ነው? ከይሖዋ አምላክ በቀር ማን ሊሆን ይችላል? እርሱ በጣም ትልቅ ስለሆነ ክብር ሊከበር ይገባዋል። ብዙ ጊዜ “ትልቅ” ወይም “ታላቅ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። እርሱ ታላቅ፣ ትልቅ ሠሪ፣ ታላቅ አስተማሪ፣ ታላቅ ንጉሥ፣ ታላቅ ጌታ ነው። (መዝሙር 48:2፤ መክብብ 12፡1፤ ኢሳይያስ 30:20፤ 42:5፤ 54:5፤ ሆሴዕ 12፡4) ትልቅ የሆነ ሁሉ ባለግርማ፣ ባለክብር፣ ከፍ ያለ፣ ከፍተኛ ማዕረግ ያለውና የሚያስፈራ ነው። ይሖዋ የሚተካከለው፣ የሚፎካከረው ወይም የሚመሳሰለው የለም። እርሱ ራሱ ይህንን ሲያረጋግጥ “በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?” ብሎአል።—ኢሳይያስ 46:5
7. ቢያንስ በስንት መንገዶች ይሖዋ የተለየ ነው ለማለት እንችላለን? በሥልጣን ረገድ እኩያ ወይም ተወዳዳሪ የለውም ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ ቢያንስ በሰባት የተለያዩ መንገዶች የሚተካከለው የለም። እነዚህም ይሖዋን እንድናከብር የሚገፋፉን ምክንያቶች ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ አምላክ በሥልጣኑ ተወዳዳሪ የለውም። ጌታ ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ልዑልና የሁሉ የበላይ ነው። እርሱ ፈራጃችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ንጉሣችን ነው። በሰማይም ሆነ በምድር ያሉት ፍጥረታት ሁሉ በይሖዋ ተጠያቂዎች ሲሆኑ እርሱ ግን በማንም አይጠየቅም። “ታላቅ አምላክ፣ ኃያልም የሚያስፈራም” መባሉ ተገቢ ነው።—ዘዳግም 10:17፤ ኢሳይያስ 33:22፤ ዳንኤል 4:35
8. ይሖዋ (ሀ) በደረጃው (ለ) በዘላለማዊ ሕልውናው ረገድ እኩያ የለውም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
8 ሁለተኛ፣ ይሖዋ አምላክ በደረጃው አቻ የሌለው በመሆኑ ከሁሉ የበለጠ ክብር ሊቀበል ይገባዋል። እርሱ “ከፍ ያለና ልዑል” ከሁሉ የሚበልጥ ነው። (ኢሳይያስ 40:15፤ 57:15፤ መዝሙር 83:18) ሶስተኛ፣ ይሖዋ አምላክ በዘላለማዊ ሕልውናው እኩያ የለውም። መጀመሪያ የሌለውና ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር እርሱ ብቻ ነው።—መዝሙር 90:2፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17
9. ይሖዋ (ሀ) በደማቅ ክብሩ (ለ) በመሠረታዊ ባሕርያቱ ረገድ እኩያ የሌለው በምን መንገድ ነው?
9 አራተኛ፣ ይሖዋ አምላክ ታላቅ ባለግርማ በመሆኑ ትልቅ ክብር ሊሰጠው ይገባል። እርሱ “የሰማይ ብርሃናት ሁሉ አባት ነው።” ሁለንተናው በጣም ደማቅ በመሆኑ እርሱን አይቶ በሕይወት ሊኖር የሚችል የለም። በእውነትም እርሱ ባለ ታላቅ ግርማና የሚያስፈራ ነው። (ያዕቆብ 1:17፤ ዘፀዓት 33:22፤ መዝሙር 24:10) በአምስተኛ ደረጃ ይሖዋ አምላክ ባሉት ባሕርያት ምክንያት በጣም ታላቅ ክብር ሊሰጠው ይገባል። ሁሉን የሚችልና ለኃይሉ ዳርቻ የሌለው አምላክ ነው። ሁሉን ያውቃል፣ ለዕውቀቱም ወሰን የለውም። በፍርድ ረገድ ፍጹም የሆነ የፍትሕ አምላክ ሲሆን ሁለመናው ፍቅር ነው።—ኢዮብ 37:23፤ ምሳሌ 3:19፤ ዳንኤል 4:37፤ 1 ዮሐንስ 4:8
10. ይሖዋ (ሀ) በፍጥረት ሥራዎቹና በባለንብረትነቱ (ለ) በስሙና በዝናው ረገድ እኩያ የማይገኝለት በምን መንገድ ነው?
10 ስድስተኛ፣ ይሖዋ በታላላቅ የፍጥረት ሥራዎቹ ምክንያት ከፍተኛው የአክብሮት መጠን ሊሰጠው ይገባል። በሰማይና በምድር ያሉትን ሁሉ የፈጠረ እንደመሆኑ መጠን የሁሉም ነገሮች ባለቤት እርሱ ነው። በመዝሙር 89:11 ላይ “ሰማያት የአንተ ናቸው፣ ምድርም የአንተ ናት” የሚል ቃል እናነባለን። በሰባተኛ ደረጃ አምላካችን ይሖዋ ከሌሎች ሁሉ የበለጠ ክብር ሊቀበል የሚገባው በስሙና በዝናው ረገድ ተወዳዳሪና እኩያ የሌለው በመሆኑ ነው። “የመሆን ምክንያት” የሚል ትርጉም ያለውን ይሖዋ የተባለ ስም የተሸከመው እርሱ ብቻ ነው። የዘፍጥረት 2:4ን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ይሖዋን የምናከብረው እንዴት ነው?
11. (ሀ) ይሖዋን የምናከብርባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ለ) በይሖዋ በመታመን በእርግጥ እርሱን እንደምናከብር የምናሳየው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ እነዚህን የመሰሉ ታላላቅ ባሕርያት ያሉት አምላክ ከሆነ እርሱን ልናከብር የምንችለው እንዴት ነው? ቀጥለን እንደምንመለከተው እርሱን በመፍራትና ለእርሱ ቅድስና በማሳየት፣ እርሱን በመታዘዝ፣ በመንገዳችን ሁሉ እርሱን በማወቅ፣ ሥጦታ በመስጠትና ወደ እርሱ በመጸለይ ልናከብረው እንችላለን። “በፍጹም ልብህ በ[ይሖዋ (አዓት)] ታመን” ተብለን ተመክረናል። ስለዚህ ይሖዋ የገባልንን ቃል በማመን እናከብረዋለን። ለምሳሌ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፣ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፣ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ” ብሎአል። (ምሳሌ 3:5፤ ኢሳይያስ 41:10) ሙሉ በሙሉ በእርሱ አለመታመን እርሱን አለማክበር ይሆናል።
12. ይሖዋን በማክበር ረገድ ታዛዥነትና ፍርሐት ምን ቦታ አላቸው?
12 ከዚህ ጋር በቅርብ የሚዛመደው ይሖዋ አምላክን የምናከብርበት ሌላው መንገድ ደግሞ እርሱን መታዘዝ ነው። ታዛዥ ለመሆን ደግሞ ፈሪሐ አምላክ፣ አዎ አምላክን እንዳናስቀይም መፍራት በጣም አስፈላጊ ነው። አብርሃም ልጁን ይሥሐቅን በታዛዥነት ለመሰዋት ከተዘጋጀ በኋላ አምላክ የተናገረው ቃል በመፍራትና በመታዘዝ መካከል ያለውን ዝምድና ያሳያል። ይሖዋ “እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንክ አሁን አውቄአለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 22:12) ሐዋርያው ጳውሎስም ልጆች ለወላጆቻቸው ስላለባቸው ግዴታ ሲጽፍ ታዛዥነትና አክብሮት አብረው የሚሄዱ ነገሮች መሆናቸውን አመልክቶአል። (ኤፌ 6:1-3) ስለዚህ ከባድ ያልሆኑትን የአምላክ ትዕዛዛት በመፈጸም ይሖዋን እናከብራለን። ይሖዋ አምላክን አለመታዘዝ እርሱን አለማክበር እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ዮሐንስ 5:3
13. ይሖዋን ማክበራችን ስለምንሰራቸው ልዩ ልዩ ነገሮችና ስለወደፊት እቅዳችን ምን አስተሳሰብ እንዲኖረን ያደርገናል?
13 ከዚህም በላይ በምሳሌ 3:6 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል የሚገባውን ክብር እንሰጠዋለን። “በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ እርሱም ጎዳናህን ያቃናልሃል።” ደቀመዝሙሩ ያዕቆብ በዚህ ረገድ ጥሩ ምክር ይሰጠናል። በየዕለቱ በራሳችን በመተማመንና በግል ችሎታችን ከመመካት ይልቅ [ይሖዋ (አዓት)] ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” ማለት ይገባናል። (ያዕቆብ 4:15) ከዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ነገር ሲናገሩ በዚያ ቃል ላይ D.V. የሚለውን የአህጽሮት ቃል ይጨምሩ ነበር። ይህም ዲዮ ቮሎንቴ ማለት ሲሆን ትርጉሙም “አምላክ ፈቃዱ ቢሆን” ማለት ነው።
14. (ሀ) አምላክን ለማክበር ከፈለግን ስለጥረታችን ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል? (ለ) የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን በማዘጋጀት ረገድ ምን ዝንባሌ ታይቶአል?
14 በተጨማሪም የትሕትና መንፈስ በማሳየት ላገኘነው መልካም ውጤት ሁሉ ይሖዋ እንዲመሰገን ስናደርግ ይሖዋ አምላክን እናከብረዋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ትክክለኛ ዝንባሌ እንዳለው ሲያሳይ እንዲህ ብሎአል። “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ። ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር። እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7) በእውነትም ጳውሎስ አጥብቆ ያስብ የነበረው ራሱን ወይም ማንኛውንም ሌላ ግለሰብ ለማስከበር ሳይሆን መከበር የሚገባውን አምላክ ለማስከበር ነበር። ዛሬም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች የፀሐፊዎቻቸውን ማንነት አይገልጹም። ፀሐፊዎቹም ቢሆኑ ስለጻፉት ነገር ለሌሎች አያሳውቁም። በዚህ መንገድ አንባቢዎች ሁሉ ይሖዋን እንዲያስከብር ታስቦ በተዘጋጀው ትምህርት ላይ እንጂ በማንኛውም ግለሰብ ላይ እንዳያተኩሩ ይደረጋል።
15. ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን የትህትና መንፈስ መረዳት እንደሚያስቸግራቸው የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?
15 ይህ በይሖዋ ላይ ብቻ የማተኮርና ይሖዋ ብቻ እንዲከበር የማድረግ አሠራር አንዳንዶችን በጣም ያስደንቃቸዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የይሖዋ ምሥክሮች በኒው ዮርክ ከተማ ማዕከላዊ መናፈሻ ለሚደረግ የሕዝብ ንግግር የጽምጽ ማጉያ መሣሪያ በሚተክሉበት ጊዜ መሞከሪያ እንዲሆናቸው የመንግሥት ዜማዎች የተባለውን ክር ያጫውቱ ነበር። ጥሩ ልብስ የለበሱ ባልና ሚስት መጡና አንዱን የይሖዋ ምሥክር ሙዚቃው ምን እንደሆነ ጠየቁት። የተጠየቀውም ወንድም የይሖዋ ምሥክሮች መሰሉትና “የመንግሥት ዜማ ቁጥር 4 ነው” አላቸው። “ግን ይህን ሙዚቃ የደረሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። የይሖዋ ምሥክሩም “ደራሲው አይታወቅም” አላቸው። ባልና ሚስቱም መልሰው “እንደዚህ ያለ ሙዚቃ የሚደርሱ ሰዎች ስማቸውን አይደብቁም” አሉት። ወንድም “የይሖዋ ምሥክሮች ግን እንዲህ ያደርጋሉ” አላቸው። አዎ፣ ይህን የሚያደርጉት ክብር ለይሖዋ እንዲሰጥ ሲሉ ነው።
16. እንዴት ባሉ የተለያዩ መንገዶች በድምጻችን በመጠቀም ይሖዋን ልናከብር እንችላለን?
16 ይሖዋን የምናከብርበት ሌላው መንገድ ስለ እርሱ በከንፈራችን በመመስከር ነው። ይሖዋን ስለማስከበር አጥብቀን የምናስብ ከሆነ የመንግሥቱን ምሥራች ለማዳረስ እንተጋለን። ይህንንም የምናደርገው ከቤት ወደ ቤት በመሄድና ባገኘነው ዘዴ ሁሉ በአጋጣሚ ምሥክርነት ጭምር በመጠቀም ነው። (ዮሐንስ 4:6-26፤ ሥራ 5:42፤ 20:20) ከዚህም በተጨማሪ በጉባዔ ስብሰባዎቻችን ሐሳብ በመስጠትና የመንግሥት መዝሙሮቻችንን ከልባችን በመዘመር አምላካችንን በድምጻችን የማክበር አጋጣሚ እናገኛለን። (ዕብራውያን 2:12፤ 10:24, 25) በተጨማሪም በዕለታዊ ንግግራችን በከንፈራችን ይሖዋን ልናከብር እንችላለን። መጠነኛ ጥረት ካደረግን ማንኛውንም ጭውውት አቅጣጫውን ለውጠን በመንፈሳዊ የሚያንጽ ልናደርገው እንችላለን። ይህም ለይሖዋ ክብር ያመጣለታል።—መዝሙር 145:2
17. (ሀ) ጥሩ ምግባር ይሖዋን ማክበርን በተመለከተ ምን ቦታ አለው? (ለ) መጥፎ ምግባር ምን ውጤት አለው?
17 ይሖዋን በከንፈራችን ማክበር ጥሩ የመሆኑን ያህል በጠባያችንም እርሱን ማክበር አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ በከንፈራቸው አምላክን እያከበሩ ልባቸው ግን ከእርሱ የራቀውን ሰዎች አውግዞአል። (ማርቆስ 7:6) መጥፎ ጠባይ ይሖዋን ማዋረዱ የማይቀር ነው። ለምሳሌ በሮሜ 2:23, 24 ላይ እንዲህ እናነባለን፣ “በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደተጻፈ።” በቅርብ ዓመታት ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከይሖዋ ሕዝቦች ጉባዔ ተወግደዋል። ከእነዚህ የሚበልጡ ብዙ ሰዎችም ወራዳ ድርጊት ቢፈጽሙም ንሥሐ ስለገቡ ሳይወገዱ ቀርተዋል። እነዚህ እነዚህ ሁሉ በከንፈራቸው ይሖዋን ሲያከብሩ ቢቆዩም በጠባያቸው ሳያከብሩት ቀርተዋል።
18. (ሀ) ልዩ መብት የተሰጣቸው አንዳንድ ሰዎች ለይሖዋ የሚገባውን ክብር ለመስጠት ከፈለጉ ስለምን ነገር አጥብቀው ማሰብ ይኖርባቸዋል። (ለ) ስለዚህ ነገር ማሰብ አስፈላጊ መሆኑን በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ካህናት ያደረጉት ነገር የሚያስገነዝበን እንዴት ነው?
18 በተለያዩት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ሁሉ፣ በቤቴልም ሆነ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ወይም በሚሲዮናዊ አገልግሎት ወይም በአቅኚነት የሚያገለግሉ ሁሉ ይሖዋን ለማክበር ልዩ አጋጣሚ ስለተሰጣቸው የተባረኩ ናቸው። በማንኛውም ሥራ ቢመደቡ ’በትልቁም ሆነ በትንሹ ታማኝ ሆነው ለመገኘት’ የተቻላቸውን ሁሉ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። (ሉቃስ 16:10) በአንዳንድ መንገዶች የተሰጣቸው የተከበረ ቦታ በጥንትዋ እሥራኤል ለነበሩት ሌዋውያንና ካህናት የተሰጠው ጥላው ነበር ባይባልም ሁኔታቸውን ለማስረዳት ሊያገለግል ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ካህናት በሚልክያስ ዘመን ግድየለሾች ስለሆኑ ይሖዋ “እኔስ አባት ከሆንኩ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ?” ብሎአቸው ነበር። (ሚልክያስ 1:6) እነዚህ ካህናት እውር፣ አንካሳና በሽተኛ እንስሳት በመሰዋት የይሖዋን ስም ያቃልሉ ነበር። በዛሬውም ዘመን ልዩ የአገልግሎት መብት የተሰጣቸው ሰዎች የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ካልተጣጣሩ እነዚህ ካህናት የተሰጣቸው ዓይነት ተግሣጽ ሊሰጣቸው ይችላል። አምላክን በማክበር ረገድ ጎደሎዎች ይሆናሉ።
19. (ሀ) በምሳሌ 3፡9 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋን የምናከብርበት ሌላው ተጨማሪ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን የምናከብርበት ሌላው ትልቅ መንገድ ምንድን ነው?
19 ይሖዋን የምናከብርበት ሌላው መንገድ ይሖዋ ላዘዘው ዓለም ዓቀፍ የስብከቱ ሥራ የሚያግዝ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ ነው፤ “[ይሖዋን (አዓት)] ከሀብትህ አክብር፣ ከፍሬህም ሁሉ በኩራት” ተብለን ተመክረናል። (ምሳሌ 3:9) እንዲህ ያለ መዋጮ የማድረግ መብት ማንም ሰው ችላ ሊለው የማይገባ ይሖዋን የምናከብርበት አጋጣሚ ነው። በተጨማሪም በጸሎታችን ይሖዋን በማወደስና በማመስገን ልናከብረው እንችላለን። (1 ዜና 29:10-13) እንዲያውም በትሕትናና በታላቅ አክብሮት ወደ እርሱ ስለምንቀርብ በጸሎት ወደ አምላክ መቅረባችን ብቻውን ለእርሱ ክብር መስጠት ማለት ነው።
20. (ሀ) በዓለም ሰዎች ዘንድ አብዛኛውን ጊዜ የሚከበሩት እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው? እንዴትስ? (ለ) ይሖዋን ከዚህ በተጨማሪ የምናከብረው የትኛውን ትእዛዛት በመፈጸም ነው?
20 በዛሬው ዘመን በተለይ ወጣቶች የሚያደንቁአቸውን ሰዎች በመምሰል፣ እንደነርሱ በመናገርና እነርሱ የሚያደርጉትን በማድረግ ያከብሩአቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ የሚያደንቁአቸው ሰዎች የስፖርት ጀግኖች ወይም የመዝናኛው ዓለም ኮኮቦች ናቸው። እኛ ግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋን ለመምሰል በመጣር እርሱን ለማክበር መፈለግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ እንድናደርግ ሲያስገነዝበን “እንደተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን [የምትመስሉ(አዓት)] ሁኑ . . . በፍቅር ተመላለሱ” በማለት ጽፎአል። (ኤፌሶን 5:1, 2) አዎ፣ ይሖዋን ለመምሰል ጥረት በማድረግ እናከብረዋለን።
21. (ሀ) ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ እንድንሰጥ የሚያስችለን ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ እርሱን ለሚያከብሩ ሁሉ የሚሰጠው ሽልማት ምንድን ነው?
21 በእውነትም ይሖዋን ልናከብር የምንችልባቸውና የምንገደድባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አዘውትረን ቃሉን በመመገብና ከእርሱ ጋር በይበልጥ በመተዋወቅ ይሖዋን በበለጠ ሁኔታ ልናከብረው እንደምንችል መዘንጋት የለብንም። ይህንን በማድረጋችን ምን ሽልማት እናገኛለን? ይሖዋ “የሚያከብሩኝን አከብራለሁ” ይላል። (1 ሳሙኤል 2:30) ይሖዋ በተወሰነው ጊዜ አምላኪዎቹ በሙሉ በሰማይ ከልጁ ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች እንዲሆኑ በማድረግ ወይም በገነቲቱ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በማድረግ ያከብራቸዋል።
ታስታውሳለህን?
◻ ሰዎች በአብዛኛው የሚያከብሩት እነማንን ነው? የማያከብሩትስ ማንን ነው?
◻ አንድን ሰው ማክበር ማለት ምን ማለት ነው? ክብርስ የሚሰጠው በምን መንገዶች ነው?
◻ ይሖዋ ክብር ሊሰጠው የሚገባ የሆነው በምን መሠረታዊ ምክንያቶች የተነሣ ነው?
◻ ይሖዋን ከምናከብርባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
◻ ይሖዋ ለሚያከብሩት ዋጋቸውን የሚሰጣቸው በምን መንገዶች ነው?