ሌሎችን አክብሩ
“እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ።”—ሮሜ 12:10 የ1980 ትርጉም
1, 2. (ሀ) ትሕትናን ለማሳየት ምን ማድረግ ይገባናል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ “ማክበር” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት እንዴት ነው? ለሌሎች አክብሮት ማሳየት የማይከብዳቸው ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?
የፊተኛው ርዕስ “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” የሚለውን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ጎላ አድርጎ ገልጾ ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:5) ትሕትናን እንደ ልብስ መታጠቅ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ለሌሎች አክብሮት በማሳየት ነው።
2 “ማክበር” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ለሌሎች የምናሳየውን አክብሮት፣ ለሌሎች ያለንን ከፍ ያለ ግምትና አሳቢነት ለማመልከት ነው። ሌሎችን በደግነት በመያዝ፣ ክብራቸውን በመጠበቅ፣ የሚሰጡትን አስተያየት በማዳመጥ፣ እንድናደርግላቸው የሚጠይቁንን ነገሮች ለመፈጸም ዝግጁ በመሆን ለሌሎች አክብሮት እናሳያለን። ትሑት የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ አይከብዳቸውም። ሆኖም ትዕቢተኛ ልብ ያላቸው ሰዎች ሌሎችን ከአንጀት ማክበር ሊከብዳቸው ይችላል። ከዚያ ይልቅ በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆንና አንድ ዓይነት ጥቅም ለማግኘት የሽንገላ ቃላት መናገር ይቀናቸዋል።
ይሖዋ ሰዎችን ያከብራል
3, 4. ይሖዋ ለአብርሃም አክብሮት ያሳየው እንዴት ነው? ለምንስ?
3 አክብሮት በማሳየት ረገድ ይሖዋ ራሱ ምሳሌ ትቶልናል። ሰዎችን ነፃ ምርጫ ሰጥቶ ስለፈጠራቸው እንደ ሮቦት አድርጎ አይመለከታቸውም። (1 ጴጥሮስ 2:16) ለምሳሌ ያህል በከተማዋ ተስፋፍቶ በነበረው ክፋት ምክንያት ሰዶምን እንደሚያጠፋት ለአብርሃም በነገረው ጊዜ አብርሃም “በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን?” በማለት ጥያቄ አቀረበ። ይሖዋም ለ50 ጻድቃን ስል ከተማዋን አላጠፋም በማለት መለሰለት። አብርሃምም በከተማዋ ውስጥ 45፣ 40፣ 30፣ 20፣ 10 ቢገኙሳ? እያለ በትሕትና መማጸኑን ቀጠለ። ይሖዋም በከተማዋ ውስጥ አሥር ጻድቃን እንኳ ቢገኙ ሰዶምን ፈጽሞ እንደማያጠፋ ለአብርሃም አረጋገጠለት።—ዘፍጥረት 18:20-33
4 ይሖዋ በሰዶም አሥር ጻድቃን ሰዎች እንደሌሉ ያውቅ ነበር፤ ሆኖም የአብርሃምን አስተያየት በማዳመጥና ከእርሱ ጋር በመነጋገር አብርሃምን አክብሮታል። ለምን? ምክንያቱም አብርሃም ‘እግዚአብሔርን ስላመነና ጻድቅ ሆኖ ስለተቆጠረ ነው።’ አብርሃም “የእግዚአብሔር ወዳጅ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፍጥረት 15:6፤ ያዕቆብ 2:23) ከዚህም በላይ አብርሃም ሌሎችን የሚያከብር ሰው እንደሆነ ይሖዋ ተመልክቷል። በእርሱና በወንድሙ ልጅ በሎጥ እረኞች መካከል ወሰንን በተመለከተ ጭቅጭቅ በተነሳ ጊዜ ሎጥ የሚፈልገውን ቦታ ቀድሞ እንዲመርጥ በማድረግ አብርሃም ሎጥን አክብሮታል። ሎጥ የተሻለ ነው ብሎ ያሰበውን መሬት ሲመርጥ አብርሃም ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ ሄዷል።—ዘፍጥረት 13:5-11
5. ይሖዋ ሎጥን ያከበረው እንዴት ነበር?
5 በተመሳሳይም ይሖዋ ጻድቁን ሎጥ አክብሮታል። ሰዶም ከመጥፋቷ በፊት ሎጥ ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ ነገረው። ሆኖም ሎጥ ወደዚያ አካባቢ መሄድ እንደማይፈልግ ተናገረ፤ ከዚህ ይልቅ ከተማዋ ጥፋት በተበየነበት አካባቢ የምትገኝ ብትሆንም ሎጥ በአቅራቢያው ወደምትገኘው ወደ ዞዓር መሸሽን መረጠ። ይሖዋም ለሎጥ “የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ” አለው። ይሖዋ፣ ሎጥ የፈለገውን ነገር በማሟላት ለታማኙ ሎጥ አክብሮት እንዳለው አሳይቷል።—ዘፍጥረት 19:15-22፤ 2 ጴጥሮስ 2:6-9
6. ይሖዋ ሙሴን ያከበረው እንዴት ነበር?
6 ሙሴ ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዲያወጣና የአምላክን ሕዝቦች እንዲለቅ ለፈርዖን እንዲናገር ይሖዋ ወደ ግብፅ በላከው ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ እኔ . . . አፈ ትብ ሰው አይደለሁም” በማለት መልሷል። ይሖዋም ‘እኔ ከአፍህ . . . ጋር እሆናለሁ፣ የምታደርገውንም አስተምርሃለሁ’ በማለት ማረጋገጫ ሰጠው። ሆኖም ሙሴ አሁንም ማቅማማቱን ቀጠለ። በዚህ ወቅት ይሖዋ እንደገና ማረጋገጫ ሰጠውና ቃል አቀባዩ ሆኖ ከእርሱ ጋር እንዲሄድ አሮንን ላከለት።—ዘጸአት 4:10-16
7. ይሖዋ ሌሎችን ለማክበር ፈቃደኛ የሆነው ለምን ነበር?
7 በእነዚህ ሁሉ ወቅቶች ይሖዋ ሌሎችን በተለይ ደግሞ አገልጋዮቹን ለማክበር ፈቃደኛ መሆኑን አሳይቷል። የሚያቀርቡት ጥያቄ ይሖዋ አስቀድሞ ካሰበው ነገር ጋር የሚጋጭ ቢሆንም እንኳ ጥያቄያቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዓላማው ጋር እስካልተጋጨ ድረስ የጠየቁትን አድርጎላቸዋል።
ኢየሱስ ሌሎችን አክብሯል
8. ኢየሱስ በከፍተኛ ሕመም ትሠቃይ ለነበረች አንዲት ሴት አክብሮት ያሳየው እንዴት ነበር?
8 ኢየሱስ ለሌሎች አክብሮት በማሳየት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ ተከትሏል። በአንድ ወቅት ለ12 ዓመታት ደም ይፈሳት የነበረች አንዲት ሴት በተጨናነቀ ሕዝብ መካከል ነበረች። ሐኪሞች ሊያድኗት አልቻሉም። በሙሴ ሕግ መሠረት እንደ ርኩስ የምትታይ ሲሆን በሕዝቡ መካከልም መገኘት አልነበረባትም። ከኢየሱስ ኋላ ሄደችና ልብሱን ነክታ ተፈወሰች። ኢየሱስ ሕጉ የሚጠይቀውን ደንብ መጠበቅ ነበረብሽ በማለት አላወገዛትም። ከዚያ ይልቅ ያለችበትን ሁኔታ አውቆ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ” በማለት አክብሮት አሳይቷታል።—ማርቆስ 5:25-34፤ ዘሌዋውያን 15:25-27
9. ኢየሱስ ለአንዲት አሕዛብ አክብሮት ያሳየው እንዴት ነበር?
9 በሌላ ጊዜ አንዲት ከነናዊት ሴት ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች።” ኢየሱስ ለአሕዛብ ሳይሆን ለእስራኤል ሕዝብ የተላከ መሆኑን ተረድቶ “[የእስራኤልን] የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች [ለአሕዛብ] መጣል አይገባም” አላት። እርሷም መልሳ “ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች።” ከዚያም ኢየሱስ “አንቺ ሴት፣ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ወደድሽ ይሁንልሽ አላት።” ልጅዋ ዳነች። ኢየሱስ ይህች ሴት ባሳየችው እምነት አክብሯታል። የመንደር ውሾችን ከመጥቀስ ይልቅ “ቡችሎች” የሚለውን ቃል መጠቀሙ ጉዳዩን ቀለል ከማድረጉም በላይ ርኅራኄውን የሚያሳይ ነበር።—ማቴዎስ 15:21-28
10. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ምን ከፍተኛ መልእክት ያዘለ ትምህርት አስተማራቸው? ይህስ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?
10 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እኔ ልቅደም ከሚለው መንፈስ ገና ያልተላቀቁ በመሆናቸው ትሑት የመሆንንና ለሌሎች አክብሮት የማሳየትን አስፈላጊነት ደጋግሞ አስተምሯቸዋል። በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ ኢየሱስ “የተከራከራችሁበት ነገር ምን ነበር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱ ግን “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው” በማለት ተከራክረው ስለነበር ዝም አሉ። (ማርቆስ 9:33, 34 የ1980 ትርጉም) ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት እንኳ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” የሚል ክርክር ተነስቶ ነበር። (ሉቃስ 22:24 የ1980 ትርጉም) ስለዚህም ኢየሱስ የፋሲካ በዓል እየተከበረ ሳለ “በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፣ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብ” ተነሳ። ይህ እንዴት ያለ ከፍተኛ መልእክት ያዘለ ትምህርት ነው! ኢየሱስ በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ከይሖዋ ቀጥሎ ሥልጣን ያለው የአምላክ ልጅ ነበር። ሆኖም እግራቸውን በማጠብ ለደቀ መዛሙርቱ የማይረሳ ትምህርት አስተማራቸው። “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” አላቸው።—ዮሐንስ 13:5-15
ጳውሎስ ለሌሎች አክብሮት አሳይቷል
11, 12. ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ምን ትምህርት ቀሰመ? ከፊልሞና ጋር በተያያዘ መንገድ ይህን ትምህርት በሥራ ላይ ያዋለው እንዴት ነበር?
11 ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች አክብሮት አሳይቷል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) “ክብርን ከሰው አልፈለግንም። ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን” በማለት ተናግሯል። (1 ተሰሎንቄ 2:6, 7) አንዲት ሞግዚት ለትንንሽ ልጆቿ እንክብካቤ ታደርጋለች። ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ትሕትና ማሳየትንና መሰል ክርስቲያኖችን በጥንቃቄ በመያዝ ማክበርን ተምሯል። በሮም እስረኛ በነበረበት ወቅት የተፈጸመ አንድ ሁኔታ እንደሚያሳየው ያላቸውንም ነፃ ምርጫ ያከብርላቸው ነበር።
12 ከጌታው የኮበለለ አናሲሞስ የተባለ አንድ ባሪያ የጳውሎስን ስብከት አዳመጠ። ከዚያም ክርስትናን ከመቀበሉም በላይ የጳውሎስ ወዳጅ ሆነ። የባሪያው ጌታ በትንሿ እስያ የሚኖረው ፊልሞና የተባለ ክርስቲያን ነበር። ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ ላይ አናሲሞስ እርሱን ምን ያህል ይጠቅመው እንደነበረ በመናገር “ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር” ብሏል። ሆኖም ጳውሎስ “በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም” ብሎ በመጻፍ ወደ ፊልሞና ልኮታል። ጳውሎስ ሐዋርያነቱን መከታ በማድረግ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ አልሞከረም። አናሲሞስ በሮም ከእርሱ ዘንድ እንዲቀር ከመጠየቅ በመቆጠብ ለፊልሞና ያለውን አክብሮት አሳይቷል። ከዚህም በላይ ጳውሎስ “ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም” አድርጎ በመመልከት ለአናሲሞስ አክብሮት እንዲያሳየው ፊልሞናን አጥብቆ መክሮታል።—ፊልሞና 13-16
በጊዜያችን አክብሮት ማሳየት
13. ሮሜ 12:10 ምን እንድናደርግ ይነግረናል?
13 የአምላክ ቃል “እርስ በርሳችሁ ለመከባበር ተሽቀዳደሙ” በማለት ምክር ይሰጣል። (ሮሜ 12:10) ይህም ሌሎች ለእኛ አክብሮት እስኪያሳዩን ድረስ አንጠብቅም ማለት ነው። ከዚያ ይልቅ እኛ ራሳችን ቀዳሚ ሆነን እንገኛለን። “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።” (1 ቆሮንቶስ 10:24፤ 1 ጴጥሮስ 3:8, 9) በዚህም የተነሳ የይሖዋ አገልጋዮች በቤተሰብ ክልል ውስጥ፣ በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ መሰል ክርስቲያኖችና ሌላው ቀርቶ ከጉባኤ ውጪ ለሚገኙ ሰዎች እንኳ አክብሮት ለማሳየት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይፈልጋሉ።
14. ባልና ሚስቶች እርስ በርሳቸው አክብሮት ሊሰጣጡ የሚችሉት እንዴት ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ” እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ክርስቶስ ጉባኤውን በያዘበት መንገድ ባልየው ሚስቱን እንዲይዝ ይሖዋ ይጠብቅበታል። በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ ባል ሚስቱን ‘እንደ ተሰባሪ ዕቃ በጥንቃቄ በመያዝ እንዲያከብራት’ ታዝዟል። ይህንንም ሚስቱ ስትናገር ለማዳመጥ ፈቃደኛ በመሆንና የምትሰጠውን አስተያየት ግምት ውስጥ በማስገባት ሊያሳይ ይችላል። (ዘፍጥረት 21:12) ምንም ዓይነት መሠረታዊ ሥርዓት የማያስጥስ እስከ ሆነ ድረስ የእርሷን ምርጫ ሊያስቀድም ይችላል፤ በተጨማሪም ይደግፋታል በደግነትም ይይዛታል። እንዲሁም ‘ሚስት ለባልዋ የጠለቀ አክብሮት ማሳየት ይኖርባታል።’ (ኤፌሶን 5:33 NW) ታዳምጠዋለች፣ ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ካልሆነ አትልም፤ አታቃልለውም ወይም አትነዘንዘውም። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የላቀ ችሎታ ያላት ቢሆን እንኳ በባሏ ላይ ከመሠልጠን በመራቅ ትሕትና ታሳያለች።
15. አረጋውያንን እንዴት መመልከት ይገባል? እነርሱስ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል?
15 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አረጋውያንን የመሳሰሉ አክብሮት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሰዎችም አሉ። “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም [ወይም አሮጊቷንም] አክብር።” (ዘሌዋውያን 19:32) በተለይ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ ለቆዩት እንዲህ ያለው አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል። ምክንያቱም “የሸበተ ጠጉር የክብር ዘውድ ነው፣ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል።” (ምሳሌ 16:31) የበላይ ተመልካቾች በዕድሜ ለሚበልጧቸው ክርስቲያን ባልደረቦቻቸው ተገቢውን አክብሮት በማሳየት ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል። እርግጥ ነው፣ አረጋውያንም ቢሆኑ ወጣቶች ለሆኑት በተለይ ደግሞ መንጋውን የመጠበቅ ኃላፊነት ለተሰጣቸው አክብሮት ማሳየት ይኖርባቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:2, 3
16. ወላጆችና ልጆች እርስ በርሳቸው ሊከባበሩ የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ልጆች ወላጆቻቸውን ማክበር ይገባቸዋል። “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።” በተመሳሳይም ወላጆች “በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው” ተብሎ ስለተነገራቸው ልጆቻቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 6:1-4፤ ዘጸአት 20:12
17. “እጥፍ ክብር” ሊሰጣቸው የሚገባቸው እነማን ናቸው?
17 በተጨማሪም ጉባኤውን በማገልገል ለሚደክሙት አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል። “በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፣ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 5:17) እንዲህ ያለውን አክብሮት ልናሳያቸው የምንችልበት አንደኛው መንገድ “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ” የሚለውን በዕብራውያን 13:17 ላይ የሰፈረውን መመሪያ በመከተል ነው።
18. ከጉባኤ ውጭ ለሚገኙ ሰዎች ምን እንድናደርግ ይጠበቅብናል?
18 ከጉባኤ ውጭ ለሚገኙ ሰዎችስ አክብሮት ማሳየት ይገባናል? አዎን። ለምሳሌ ያህል “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ” ተብለን ታዝዘናል። (ሮሜ 13:1) እነዚህ የይሖዋ መንግሥት እስኪተካቸው ድረስ በሥልጣን ላይ እንዲቀመጡ የተፈቀደላቸው ዓለማዊ ገዥዎች ናቸው። (ዳንኤል 2:44) “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ።” (ሮሜ 13:7) “ሁሉን [ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን] አክብሩ።”—1 ጴጥሮስ 2:17
19. ለሰዎች ‘መልካም ልናደርግና’ አክብሮት ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ከጉባኤ ውጭ ለሚገኙ ሰዎች አክብሮት ማሳየታችን የሚገባ ቢሆንም እንኳ የአምላክ ቃል ምን ነገርን ጎላ አድርጎ እንደሚገልጽ ልብ በል:- “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።” (ገላትያ 6:10) እርግጥ ነው፣ ለሌሎች ‘መልካም ማድረግ’ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን በመቀስቀስና በማርካት ነው። (ማቴዎስ 5:3) ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ማሳሰቢያ በመከተል ይህን ማድረግ እንችላለን። “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።” በምሥክርነቱ ‘አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም’ የተገኘውን አጋጣሚ በዘዴ ስንጠቀም ለሁሉም መልካም እያደረግንላቸው ከመሆኑም በላይ አክብሮትም እያሳየናቸው ነው።—2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ 4:5
ይሖዋን ማክበር
20. በፈርዖንና በሠራዊቱ ላይ ምን ደረሰባቸው? ለምንስ?
20 ይሖዋ ለፍጥረታቱ አክብሮት ያሳያል። ስለዚህ እኛም በአጸፋው ለእርሱ አክብሮት ማሳየታችን የተገባ ነው። (ምሳሌ 3:9፤ ራእይ 4:11) ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ቃል “ያከበሩኝን አከብራለሁና፣ የናቁኝም ይናቃሉና” በማለት ይናገራል። (1 ሳሙኤል 2:30) የግብፁ ፈርዖን የአምላክን ሕዝቦች እንዲለቅ በተነገረው ጊዜ “ቃሉን እሰማ ዘንድ . . . እግዚአብሔር ማን ነው?” በማለት በእብሪት መለሰ። (ዘጸአት 5:2) ፈርዖን እስራኤላውያንን ለመደምሰስ ሠራዊቱን በላከ ጊዜ ይሖዋ ቀይ ባሕርን ለሁለት በመክፈል እስራኤላውያንን አሻገራቸው። ሆኖም ግብፃውያን ተከትለዋቸው በገቡ ጊዜ ይሖዋ ውኃውን ወደ ቀድሞ ቦታው እንዲመለስ አደረገ። “[ይሖዋ] የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው።” (ዘጸአት 14:26-28፤ 15:4) ስለዚህ ፈርዖን ይሖዋን ለማክበር በኩራት አሻፈረኝ ማለቱ ለጥፋት ዳረገው።—መዝሙር 136:15
21. ይሖዋ ብልጣሶርን የተቃወመው ለምን ነበር? በመጨረሻስ ምን ደረሰበት?
21 የባቢሎን ንጉሥ ብልጣሶር ይሖዋን ለማክበር እምቢተኛ ሆኖ ነበር። የመጠጥ ግብዣ ባደረገ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በተወሰዱና ከወርቅና ከብር በተሠሩ ቅዱስ ዕቃዎች የወይን ጠጅ በመጠጣት በይሖዋ ላይ ተሳለቀ። አረማዊ አማልክቱንም አመሰገነ። የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ዳንኤል “በሰማይ ጌታ ላይ ኮራህ እንጂ ልብህን አላዋረድህም” በማለት ተናገረው። በዚያች ሌሊት ብልጣሶር ተገደለ፤ መንግሥቱንም ተነጠቀ።—ዳንኤል 5:22-31
22. (ሀ) ይሖዋ በእስራኤል መሪዎችና በሕዝቦቻቸው ላይ የተቆጣው ለምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ለእነማን ሞገሱን አሳየ? በዚህስ ምክንያት ምን አገኙ?
22 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ንጉሥ ሄሮድስ ንግግር ባቀረበ ጊዜ ሕዝቡ “የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም” በማለት በጩኸት ተናገሩ። ኩራተኛው ንጉሥ ሕዝቡን ከመቃወም ይልቅ ክብር ማግኘትን ፈለገ። በዚያን ወቅት “የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ።” (ሥራ 12:21-23) ሄሮድስ ከይሖዋ ይልቅ ራሱን ማክበሩ ሞት አስከተለበት። በዚያን ወቅት የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የአምላክን ልጅ ኢየሱስን ለመግደል በማሴር አምላክን አዋረዱ። አንዳንድ መሪዎች ኢየሱስ ያስተማረው እውነት እንደሆነ ቢያውቁም “ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር” በመውደዳቸው ምክንያት አልተከተሉትም። (ዮሐንስ 11:47-53፤ 12:42, 43) በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቡ ለይሖዋም ሆነ የእርሱ ወኪል ሆኖ ለተሾመው ለኢየሱስ አክብሮት ሳያሳዩ ቀሩ። ይሖዋም በምላሹ እነርሱን ማክበሩን በማቆም እነርሱም ሆኑ ቤተ መቅደሳቸው እንዲደመሰስ ፈቀደ። ሆኖም ለእርሱና ለልጁ አክብሮት የነበራቸውን ከጥፋቱ እንዲተርፉ አድርጓል።—ማቴዎስ 23:38፤ ሉቃስ 21:20-22
23. በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ ይገባናል? (መዝሙር 37:9-11፤ ማቴዎስ 5:5)
23 ይህ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ አምላክንና ልጁን ክርስቶስ ኢየሱስን ማክበርና ለሁለቱም መታዘዝ አለባቸው። (ዮሐንስ 5:22, 23፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11) እንዲህ ያለውን አክብሮት የማያሳዩ ሁሉ “ከምድር ይጠፋሉ።” በሌላ በኩል ግን ለአምላክና ለክርስቶስ አክብሮት ያላቸው ቅን ሰዎች “በምድር ላይ ይቀመጣሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22
ለክለሳ ያህል
◻ ሌሎችን ማክበር ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋስ ይህን ያደረገው እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስና ጳውሎስ ሌሎችን ያከበሩት እንዴት ነበር?
◻ በጊዜያችን አክብሮት የሚገባቸው እነማን ናቸው?
◻ ይሖዋንና ኢየሱስን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የአብርሃምን ልመና በመስማት አክብሮታል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተሳካ ትዳር ውስጥ ባልና ሚስት እርስ በርስ ይከባበራሉ