ወደ ሀብታም አገር ከመዛወራችሁ በፊት ወጪውን አስቡት
በታዳጊ አገሮች ውስጥ በሚገኙ የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ላይ ሁልጊዜ የሚታይ ነገር ነው። በእንግዳ መቀበያው ክፍል ውስጥ ታጭቀው በተረበሸ መንፈስ ባለሥልጣን ፊት ቀርበው የሚቀርብላቸውን ጥያቄ የሚጠባበቁ ሰዎች ሁልጊዜ ይታያሉ። በዚያ አጭር ነገር ግን በጣም አስፈላጊ በሆነ ውይይት መሠረት በኢንዱስትሪ ወደበለጸጉ የምዕራብ አገሮች ለመሄድ ቪዛ ማግኘት አለማግኘታቸው ይወሰናል። ብዙዎቹ ይህ ወደ ብልጽግና የሚያደርሳቸው ቲኬት እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። “ለአራት ዓመታት ያህል ጠንክሬ ብሠራም ራዲዮ እንኳ መግዛት አልቻልኩም” በማለት አንድ ምዕራብ አፍሪካዊ ወጣት ብስጭቱን ገለጸ። ቀጥሎም “በእንግሊዝ አገር ወይም በዩናይትድ ስቴትስ ብኖር ኖሮ ግን እስከ አሁን መኪናና የምኖርበት ቤት ይኖረኝ ነበር” አለ።
በድሃና ባዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ለምን እንደዚህ እንደሚሰማቸው መረዳቱ አስቸጋሪ አይሆንም። ለእነርሱ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ክፍያውም ቢሆን አነስተኛ ነው። የኑሮ ውድነት የተገኘውን ገንዘብ ይጨርሰዋል። ቤት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ በአንድ ቤት ውስጥ ተጣበው ይኖራሉ። ሰዎች የሚለብሱት ልብስ በሃብታም አገሮች ውስጥ የሚጣለውን ውራጅ ነው። ብዙዎች በኢኮኖሚ ወጥመድ እንደተያዙ ሆኖ ይሰማቸዋል።
የበለጸገው ምዕራቡ ዓለም እንዴት ማራኪ መስሎ ይታያቸዋል! አንድ በሴራ ሊዮን የሚኖር ወጣት እንዲህ አለ፦ “ወደ ውጭ አገር ሄደው የተመለሱ አንዳንድ ሰዎች በኢንዱስትሪ የበለጸገውን ዓለም እኛ ራሳችን ሄደን እንድናየው የሚያደፋፍሩ ታሪኮች ይነግሩናል። ብዙ መሥራት ያስፈልግሃል፤ ቢሆንም ደህና ገንዘብ ስለምታገኝ ራስህን መርዳት እንዲያውም እንደ መኪና ያሉ አንዳንድ የምቾት ዕቃዎችን መግዛት ትችላለህ እያሉ ይነግሩናል። ሁለት ሺ ዶላር ይዘህ ወደዚህ ብትመጣ አንድ ዓይነት ንግድ ታቋቁማለህ፤ ትዳርም ትይዛለህ ይሉናል።”
አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮችም እንዲሁ ቢሰማቸው ምንም አያስደንቅም። አንዲት አፍሪካዊት እህት እንዲህ አለች፦ “እኛ በአምላክ ድርጅት ውስጥ የምንገኝ ወጣቶች ወደ ውጭ አገር የሄዱት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆኑ ሲነገር እንሰማለን። ስለዚህ ራሴን አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፦ ‘እኔስ? እዚህ የምሰቃየው ምን በወጣኝ ነው? ልሂድ ወይስ እዚህ ልቅር?’”
በድሃ አገር ውስጥ የምትኖር ከሆነ አንተም ወደ ሌላ አገር መሄዱ ኑሮህን ሊያሻሽል ይችል እንደሆነ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ወደ ሌላ አገር መሄድ በጣም ከፍተኛ የሆነ ውሳኔ፣ ብዙ ወጪን የሚጠይቅና ከባድ እርምጃ ነው። አዲስ ቋንቋ መማርን፣ አዲስ የሥራ ችሎታ ማዳበርን፣ ከአዲስ ባሕል ጋር ራስን ማስማማትን፣ በዚያ የሚኖሩ ብዙዎች ለሌላ አገር ሰዎች የሚያሳዩትን ጥላቻ ችሎ መኖርንና ፍጹም አዲስ የሆነ ሕይወት መቀበልን ሊጨምር ይችላል። ብዙ ክርስቲያኖች ይህን ሁሉ በተሳካ ሁኔታ ተቋቁመው በአዲሱ አገራቸው ውስጥ በሚገኙ ጉባኤዎች ምሳሌ የሚሆኑ አስፋፊዎች፣ አቅኚዎች፣ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሆነው በማገልገል ለጉባኤዎች ጥሩ ሐብት ሆነዋል።
ሆኖም የተሳካላቸው ሁሉም አይደሉም። ወደ ሌላ አገር የመሄዱ አሳብና ጭንቀት በአንዳንዶች ላይ መንፈሳዊ መፍረስ አስከትሎባቸዋል። ስለዚህ እንዲህ ያለው ጉዞ ከመደረጉ በፊት በከባድ ጸሎት ሊታሰብበት እንደሚገባ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 3:5, 6 ላይ እንዲህ በማለት ይመክራል፦ “በፍጹም ልብህ [በይሖዋ (አዓት)] ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህም ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” አዎን፣ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እርምጃ ስለ መውሰድህ እርግጠኛ መሆን ትፈልጋለህ። (ያዕቆብ 4:13-15) ኢየሱስም አድማጮቹ ‘ኪሣራውን እንዲያሰሉ’ ባሳሰበ ጊዜ ለአንተም ሊጠቅም የሚችል ተግባራዊ ምክር ሰጥቷል። (ሉቃስ 14:28) ይህም የገንዘቡን ሁኔታ ብቻ ከማስላት የበለጠ ነገርን የሚጨምር ነው። አገርን ትቶ መሄድ ሊያስከትል የሚችለውን መንፈሳዊ ኪሣራ ጭምር ማስላት ማለትም ነው።
በውጭ አገር የመኖር እውነተኛ ሁኔታዎች
ወደ የትም ቦታ ከመሄድህ በፊት ወደዚያ ቦታ ስትደርስ ሊያጋጥምህ ስለሚችለው ነገር ጥሩና እውነተኛ የሆነ አስተሳሰብ ሊኖርህ ይገባል። የሚቻል ከሆነ ቅድመ ጉብኝት አድርገህ ሁኔታዎቹ ምን እንደሚመስሉ ራስህ ተመልከት። ያለበለዚያ ከሌላ ሰው በምታገኘው መረጃ ብቻ ልትመራ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፦ “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 14:15
አንዳንድ ሰዎች ስለ ምዕራብ ዓለም አኗኗር ሐሳብ የሚያገኙት ከሲኒማና ከቴሌቪዥን ትርዒቶች ነው። በዚህም ምክንያት በዚያ የሚኖረው ሁሉ ሃብታም እንደሆነ፣ አዲስ መኪና እንደሚነዳና በተሟላ ቤት ውስጥ በምቾት እንደሚኖር አድርገው ያምናሉ። እውነተኛው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ብዙ የበለጸጉ አገሮች በድህነት፣ በቤት እጥረትና በሥራ አጥነት የሚሰቃዩት ኗሪዎቻቸው ቁጥር የሚያስፈራ ነው። በጣም ድሆች የሆኑት አብዛኞቹ ነዋሪዎች አዲስ መጤዎች ናቸው። በአንድ ድሃ አገር ውስጥ የሚገኝ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ቆንስላ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፦ “በአሜሪካ ውስጥ ኑሮን መመሥረት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሰዎች አይረዱም። አንዳንዶች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይኸውም ሁለት መኪናና ቤት እንደገዙ ወደ አገራቸው ደብዳቤ ይጽፋሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በትግል ላይ ናቸው።
በሌሎች ስፍራዎችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሚስተር ሳህር ሶሪ በለንደን የኖሩና የተማሩ ምዕራብ አፍሪካዊ አስተማሪ ናቸው። እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጡ፦ “ከአፍሪካ ወጥቶ በእንግሊዝ ውስጥ ተደላድሎ መኖር ቀላል አይደለም። በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው የውጭ አገር መጤዎች በጣም ዝቅተኛ የሆነ ኑሮ ይኖራሉ። በፊታቸው ላይ የጭንቀት ኑሮ መሥመሮችን ትመለከታላችሁ። አንዳንዶች ስልክ የሚደውሉበትን 20 ሳንቲም ማግኘት ይቸግራቸዋል። አብዛኛውን ጊዜም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ትንሽ ቤት ውስጥ ተጨናንቀው ይኖራሉ። ከቅዝቃዜው ሙቀት የሚሰጣቸው ትንሽ ማሞቂያ ብቻ ይኖራቸዋል። ሊያገኙ የሚችሉት ዝቅተኛ ሥራ ብቻ ነው፤ ይህም ሆኖ ዕዳቸውን ለመክፈል አይበቃቸውም። ከድህነት ለማምለጥ አፍሪካን ትተው የሚሄዱ ሰዎች ብዙ ጊዜ በአውሮፓ የድሆች መኖሪያ አካባቢ ለመኖር ስለሚገደዱ ሁኔታውን የባሰ ሆኖ ያገኙታል።”
በአዲስ አገር ውስጥ ኑሮን ለመመሥረት ሲባል አብረው የሚመጡት የገንዘብ ተጽዕኖዎች የአንድን ሰው መንፈሳዊነት በቀላሉ ሊያንቁት ይችላሉ። (ማቴዎስ 13:22) እርግጥ ነው፣ ጠንክሮ መሥራትን መጽሐፍ ቅዱስ ይደግፋል። (ምሳሌ 10:4፤ 13:4) ነገር ግን ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ብዙ ሰዎች ገንዘብ የማጠራቀም ግባቸው ላይ ለመድረስ ወይም የዕለት ጉርስ ለማግኘት ሁለት ወይም ሦስት ዓይነት ሥራዎችን ለመያዝ ይገደዳሉ። የአምላክን አምልኮ ለመከታተል ምንም ጊዜ አይኖራቸውም። ክርስቲያን ስብሰባዎችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትንና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማካፈልን ይተዋሉ። “ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” የሚለው የኢየሱስ ቃል በአሳዛኝ ሁኔታ ይፈጸምባቸዋል።—ማቴዎስ 6:24
የስነ ምግባር ተጽዕኖዎች
አዲስ መኖሪያህ እንዲሆን ስላሰብከው አገር የስነ ምግባር ሁኔታም ልታስብ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ሎጥ በዮርዳኖስ አካባቢ መኖር እንደመረጠ ይነግረናል። በሥጋዊ አንጻር ሲታይ ውሳኔው ጥበብ ያለበት ይመስላል፤ ምክንያቱም አካባቢው “ውሃ የሞላበት . . . እንደ [ይሖዋ (አዓት)] ገነት . . . አምሳል ነበር።” (ዘፍጥረት 13:10) ይሁን እንጂ አዲሶቹ የሎጥ ጎረቤቶች “ክፉዎችና [በይሖዋ (አዓት)] ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ።” ከተፈጥሮ ውጭ የጾታ ድርጊት የሚፈጽሙ ነበሩ። (ዘፍጥረት 13:13) በዚህም ምክንያት “ጻድቅ ሎጥ በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበር።”—2 ጴጥሮስ 2:8
ዛሬም በተመሳሳይ ወደ ምዕራቡ የሚደረገው ጉዞ አንተንም ሆነ ቤተሰብህን በአገርህ ከሚገኙት በጣም ለሚብሱ የስነ ምግባር ግፊቶችና ተጽዕኖዎች የሚያጋልጣችሁ ይሆናል። በተጨማሪም አረጋውያን በአገራቸው ይሰጣቸው የነበረውን ዓይነት ክብር አያገኙም። የአካባቢው ሁኔታ ወላጆችን ማክበርን የሚያበረታታ ላይሆን ይችላል። ጎረቤቶች እርስ በርሳቸው ምንም ግድ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉት ተጽዕኖዎች አንተንና ቤተሰብህን እንዴት ሊነኩ ይችሉ ይሆን? ይህም በጸሎት ሊታሰብበት የሚገባው ነገር ነው።
ልጆቻቸውን ጥለው የሚሄዱ ወላጆች
አንዳንድ ወላጆች ቤተሰቦቻቸውን ትተው ብቻቸውን ወደ ውጭ አገር ለመሄድ መርጠዋል። ዕቅዳቸው አንዴ እዚያ ከተደራጁ በኋላ ለቤተሰባቸው ገንዘብ ለመላክ ወይም ምናልባት ወደ አገራቸው ብዙ ገንዘብ ይዘው ለመመለስ ነው። እንዲህ ያለው ዝግጅት ጥበብ ያለበት ነውን?
ቅዱሳን ጽሑፎች ወላጆች ለቤተሰባቸው ሥጋዊ ፍላጎት የሚያስፈልገውን ለማቅረብ መሥራት እንዳለባቸው ያስገድዳሉ፤ በአንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎችም ምክንያት አንድ ወላጅ እንዲህ ያለውን ዝግጅት ለማድረግ ከአገሩ ውጭ ከመሥራት ሌላ አማራጭ ላይኖረው ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) አሁንም ቢሆን ወላጆች የቤተሰባቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት የማሟላት ግዴታ አለባቸው። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን [በይሖዋ (አዓት)] ምክርና በተግሣጽ አሳድጓቸው እንጂ አታስቆጡአቸው።”—ኤፌሶን 6:4
አንድ አባት ለወራት አንዳንድ ጊዜም ለዓመታት ከቤተሰቡ ርቆ የሚሄድ ከሆነ ይህንን በተሟላ ሁኔታ ማከናወን ይችላልን? መቻሉ በጣም አጠራጣሪ ነው። ስለዚህ ከልጆችህ ተለይተህ መኖርህ የሚያስከትላቸውን ነገሮች ስትመለከት የምታገኛቸው ሥጋዊ ጥቅሞች ያን ያህል እርምጃ ልትወስድላቸው የሚገባ ስለመሆኑ ማሰብ ይኖርብሃል። ከዚህም ሌላ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ሰዎች ያሰቡትን ‘የዕድሜ ልክ ገንዘብ’ ማግኘቱ ብዙውን ጊዜ ቀላል ሆኖ አያገኙትም። ወደ ውጭ የሄደው ግለሰብ ቤተሰቡን ወደ እርሱ ለማምጣት ገንዘብ መክፈል ካልቻለ ተለያይቶ መኖሩ ለብዙ ዓመታት ሊጓተት ይችላል። ይህም እንደገና ከባድ የስነ ምግባር አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል። (ከ1 ቆሮንቶስ 7:1-5 ጋር አወዳድር) እንደነዚህ ባሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ የወደቁ አንዳንዶች በጾታ ብልግና መሸነፋቸው ያሳዝናል።
አምላክ በሚሰጠን ነገሮች መተማመን
የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ እየተበላሸ ሲሄድ የአምላክ አገልጋዮች አምላክ ይተወናል ብለው መፍራት እንደሌለባቸው ማስታወሱ ጥሩ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:31-33
ዛሬ የይሖዋ ምስክሮች በቅንዓት ምሥራቹን በመስበክ የአምላክን መንግሥት ጉዳዮች ለማራመድ ያገለግላሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በብዙ ድሃ አገሮች ውስጥ የመንግሥቱ ሰባኪዎች በከፍተኛ ደረጃ ያስፈልጋሉ። በተለይ የጎለመሱ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት እጥረት አለ። ብዙ እርዳታ ወደማያስፈልግበት በኢኮኖሚ ወደ በለጸገ አገር ከመሄድ ይልቅ ብዙዎች በትውልድ አገራቸው ለመቆየት መርጠዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ኑሮአቸው እንዴት ሆኖ አግኝተውታል?
ለ30 ዓመታት በትውልድ አገርዋ ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስትሠራ የቆየችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አሊሲያ እንዲህ ትላለች፦ “ወደ ውጭ የመሄድ አጋጣሚ ነበረኝ። ያልሄድኩበት ምክንያት ከራሴ ሕዝቦችና ዘመዶች ጋር ለመኖር ስለፈለግሁ ነው። አብረን ይሖዋን ለማገልገል እንድንችል እውነትን እንዲያውቁ ልረዳቸው ፈለግሁ። እዚህ በመቆየቴ ምንም የጎደለብኝ ነገር የለም፤ የምጸጸትበትም ምንም ነገር የለም።”
ዊኒፍሬድም እንደዚሁ በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ የምትኖር ሴት ነች። በዚያ አገር ውስጥ ያለው የኑሮ ደረጃ በዓለም ላይ ዝቅተኛ ከሚባሉት እንደ አንዱ የሚቆጠር ነው። ይሁን እንጂ ለ42 ዓመታት የሙሉ ጊዜ አቅኚ በመሆን ካገለገለች በኋላ እንዲህ ትላለች፦ “በኢኮኖሚ በኩል ነገሮችን ሁል ጊዜ ማሳካቱ ቀላል አይደለም። ሰይጣን ነገሮችን ለማክበድ ይሞክራል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ነገር አሟልቶልኛል፤ ተንከባክቦኛል።”
በጥንት ዘመን አብርሃም ‘[አምላክ] የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ ያምን ነበር።’ (ሮሜ 4:21) አንተስ እንደ አብርሃም ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽምና በሕይወትህ ውስጥ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ካስቀደምህ እንደሚንከባከብህ ታምናለህን? እንደሚከተለው ሲል ከጻፈው መዝሙራዊ ጋር ትስማማለህን? “ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ (የአምላክ) ሕግ ይሻለኛል።” (መዝሙር 119:72) ወይስ የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ በሥራ ላይ ማዋል ያስፈልግህ ይሆን? በ1 ጢሞቴዎስ 6:8 ላይ “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” ሲል ጽፎአል። ማድረግ የሚገባህ አዲስ አካባቢን መፈለግ ሳይሆን አሁን ያለህን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም ይሆንን?
በብዙ አገሮች ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ለክርስቲያኖች ከባድ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ አንድ ቤተሰብ ከላይ ያሉትን ነገሮች በሙሉ በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ከወሰነ ሌሎች የሚተቹበት ምንም ምክንያት የለም። (ገላትያ 6:5) በአገራቸው የቀሩት ግን አምላክ በሚሰጣቸው መንፈሳዊ በረከቶች እየተደሰቱ ይህ ሥርዓት ያመጣባቸውን ችግሮች ለመሸከም የሚያስችላቸውን እርዳታ እንዲሰጣቸው ሳያቋርጡ ይሖዋን ሊጠይቁ ይችላሉ። በዚህ ዓለም ላይ ያሉት የፍትሕ መጓደልና የኑሮ አለመመጣጠን ሁሉ በአምላክ መንግሥት ሥር የሚስተካከሉ መሆናቸውን አስታውሱ። በዚያን ጊዜ መዝሙራዊው እንደጻፈው ይሆናል፦ “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።”—መዝሙር 145:16