የአንባቢያን ጥያቄዎች
◼ ዮሐንስ 18:15 በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ስለ ታወቀ አንድ ደቀ መዝሙር ይናገራል። ይህ ደቀ መዝሙር በማርቆስ 14:51, 52 ላይ ቀደም ሲል “ዕርቃኑን” እንደሮጠ የተገለጸው ደቀመዝሙር ነውን?
አይደለም፤ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሐዋርያው ዮሐንስ ይመስላል፤ ‘ራቁቱን’ የሸሸው ግን ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ ነበር።
እነዚህን ታሪኮች በጊዜ ቅደም ተከተል ስናስቀምጣቸው ከጌተሰማኒ የአትክልት ሥፍራ እንጀምራለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ተይዞ ሲታሰር ሐዋርያት በፍርሃት ተሸንፈው “ሁሉም ትተውት ሸሹ።” በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የሚገኘው የሚቀጥለው ቁጥር አንድ የዚያ ተቃራኒ የሆነ ሁኔታ ያቀርባል፦ “ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፤ ጎበዛዝቱም ያዙት እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።”—ማርቆስ 14:50-52
ስለዚህ 11ዱ ሐዋርያት ያሳዩት የመጀመሪያ የፍርሃት ሁኔታ ይህ ስሙ ያልተጠቀሰ ደቀ መዝሙር ከወሰደው እርምጃ ጋር ተነፃፅሯል። ስለዚህ እርሱ ከሐዋርያት አንዱ አይደለም ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይሆናል። ይህ ታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው የበርናባስ የእህት ልጅና ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው ዮሐንስ ማርቆስ በጻፈው ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት ተይዞ የሚሄደውን ኢየሱስን መከተል የጀመረው ነገር ግን ጭፍራው እርሱንም ለመያዝ በሚሞክሩበት ጊዜ የሸሸው “አንድ ጎበዝ” ማርቆስ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስችል ምክንያት አለ።—ሥራ 4:36፤ 12:12, 25፤ ቆላስይስ 4:10
በዚያ ሌሊት በአንድ ወቅት ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስም ጭምር ከአደጋ ራሱን ለመጠበቅ ሩቅ ሆኖ ኢየሱስን ይከተለው ነበር። በዚህ በኩል ተመሳሳይነት አለ፤ ወጣቱ ደቀመዝሙር (ማርቆስ) ኢየሱስን መከተል ጀመረ፤ በኋላ ግን አቆመ። ከዚያም በኋላ ሸሽተው የነበሩት ሁለት ሐዋርያት ተይዞ የታሰረውን ጌታቸውን መከተላቸውን ቀጠሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፈው ወንጌል ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀመዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀመዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበር።”—ዮሐንስ 18:15
ሐዋርያው ዮሐንስ አጥማቂውን ዮሐንስን ለማመልከት “ዮሐንስ” በሚለው ስም ይጠቀማል፤ ራሱን ለማመልከት ግን በፍጹም ይህን ስም አልጠቀሰም። ለምሳሌ ያህል “ስለ እነዚህም የመሰከረ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀመዝሙር ነው” ብሎ ጽፎአል። በተመሳሳይም፦ “ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል” ብሏል። (ዮሐንስ 19:35፤ 21:24) በዮሐንስ 13:23 ላይ ያለውንም ልብ በል፦ “ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀመዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ።” ይህ የሆነው ኢየሱስ ከመታሰሩ ከጥቂት ጊዜ በፊት ነበር። በዚያን ቀን ቆየት ብሎ ተሰቅሎ የነበረው ኢየሱስ ዮሐንስ በተመሳሳይ አነጋገር የጠቀሰውን አንዱን ደቀመዝሙር ለብቻው ጠርቶ፦ “ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን፦ አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ አላት” ይላል።—ዮሐንስ 19:26, 27፤ ከዮሐንስ 21:7, 20 ጋር አወዳድር
ይህ ራሱን በስም ያለመጥቀስ ጠባይ በዮሐንስ 18:15ም ላይ በግልጽ ይታያል። ከዚህም በላይ በዮሐንስ 20:2-8 ላይ በሚገኘው ከትንሣኤ በኋላ የተፈጸመውን በሚገልጸው ታሪክ ውስጥ ዮሐንስና ጴጥሮስ ተያይዘው ተጠቅሰዋል። እነዚህ ማስረጃዎች “በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ” ደቀ መዝሙር የተባለው ሐዋርያው ዮሐንስ እንደነበር ያመለክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ገሊላዊ ሐዋርያ (ዮሐንስ) ሊቀ ካህናቱን እንዴት እንዳወቀና በሊቀ ካህናቱም እንዴት እንደታወቀ የሚገልጽ ምንም የኋላ ታሪክ አይሰጠንም። ሆኖም በሊቀ ካህናቱ ቤተሰብ የታወቀ መሆኑ ዘበኛውን አልፎ ወደ ግቢ ውስጥ እንዲገባና ጴጥሮስንም ጭምር የመግቢያ ፈቃድ እንዲያገኝ አስችሎታል።