የሙት ባሕር ጥቅሎች—ከፍተኛ ዋጋ ያለው ግኝት
ከኢየሩሳሌም ደቡባዊ ምሥራቅ ወደ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዋዲ ኤን ናር የሚባል ወደ ምሥራቅ ሙት ባሕር የሚደርስ ባዶና ደረቅ የሆነ የውሃ መውረጃ መንገድ ይገኛል። በወንዙ ዳርቻ ላይ አለፍ አለፍ እያለ ገደሎች አሉ። በዚህ ሜዳ ላይ ሞቃት በሆኑት ቀኖችና ቀዝቃዛ በሆኑት የበልግ ሌሊቶች የታሚሬህ ዘላኖች የበግና የፍየል መንጎቻቸውን ያሠማራሉ።
በ1947 አንድ ዘላን የሆነ ወጣት እረኛ መንጎቹን እየጠበቀ ሳለ በአንድ በፈራረሰ የገደሉ ትንሽ ቀዳዳ በኩል ወደ ውስጥ ድንጋይ ወረወረ። የተወረወረው ድንጋይ በሰጠው ድምጽም ተገረመ፤ ድምጹ የተሰማው አንድ የሸክላ ማሰሮ ሲሰበር ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ፈርቶ ሸሸ። ሆኖም ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሶ መጣና ተለቅ ባለውና ከፍ ባለው ክፍት ቦታ ወደ ውስጥ ለመግባት ወደ 300 ጫማ ያህል ወደ ላይ ወጣ። ዓይኖቹ ከጨለማው ጋር ሲለማመዱም አሥር ረጃጅም ማሰሮዎች በዋሻው ግድግዳ ላይ ተደርድረው ተመለከተ። በመሬቱ ላይ ወድቀው ከሚታዩትም ድንጋዮች መካከል ብዛት ያለው የተሰባበረ ሸክላ ተበታትኖ ይታያል።
አብዛኞቹ ማሠሮዎች ባዶ ቢሆኑም አንዱ ሦስት የመጻሕፍት ጥቅልሎችን ይዟል፣ ከእነዚህም ሁለቱ በጨርቅ የተሸፈኑ ነበሩ። እርሱም ጥንታዊ በኩረ ጽሑፎቹን ወደ ዘላኖች ካምፕ ወሰዳቸውና በቦርሳ አድርጎ በድንኳኑ ምሰሶ ላይ ሰቅሎ ለአንድ ወር ያህል እዚያው ተዋቸው። በመጨረሻም አንዳንድ ዘላኖች ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ለማወቅ የመጻሕፍት ጥቅልሎቹን ወደ ቤተልሔም ወሰዷቸው። ዘላኖቹ ወደ አንድ ገዳም ሲሄዱ የመጻሕፍት ጥቅልሎቹ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው ተነግሯቸው አፍረው ተመለሱ። ሌላው አሻሻጭም በኩረ ጽሑፎቹ አርኪዎሎጂካዊ ዋጋ እንደሌላቸው ተናገረ፤ እንዲያውም ከአይሁዶች ምኩራብ የተሠረቁ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ተጠራጠረ። ነገር ግን በጣም ተሳስቶ ነበር! በመጨረሻም በአንድ ሶሪያዊ ጫማ ሠሪ ደላላነት ዋጋቸው በትክክል ታወቀ። ወዲያውኑ ሌሎቹም የብራና ጽሑፎች ዋጋ ወጣላቸው።
ከእነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች ውስጥ አንዳንዶቹ ኢየሱስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን አካባቢ የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ያደርጉት ስለነበረው እንቅስቃሴ ፈጽሞ አዲስ የሆነ እውቀት የሚሰጡ ነበሩ። ሆኖም ይበልጥ ዓለምን ያስደነቀው የኢሳይያስን ትንቢት የያዘው የብራና መጽሐፍ ነበር። ለምን?
ትልቅ ሽልማት
አዲስ የተገኘው የኢሳይያስ የመጻሕፍት ጥቅልል በመጀመሪያ ወደ 25 ጫማ ርዝመት ነበረው። እርሱም እንደ ከእንስሳት ቆዳ በጥንቃቄ ከተዘጋጁ 17 ስስ የቆዳ መጻፊያዎች የተሠራ ነበር። ጽሑፉ 54 አምዶች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ ዐምድ በአማካይ ሠላሳ መሥመሮች ነበሩት። መሥመሮቹ በጥንቃቄ የተሰመሩ ነበሩ። በእነዚህም መሥመሮች ላይ ጥሩ ችሎታ ያለው ጸሐፊ የጥቅሱን ፊደሎች አስቀምጧል። ሐሳቦቹ በአንቀጽ በአንቀጽ የተከፋፈሉ ናቸው።—ፎቶግራፉን ተመልከት።
የመጽሐፍ ጥቅልሉ በእንጨት ላይ የተጠቀለለ አልነበረም፤ መሃሉ ላይ ለማንበብ ሲባል ብዙ ጊዜ በእጅ ስለተያዘ በጣም ደብዝዟል። በጣም የሠራ መሆኑ በጥሩ ችሎታ በመጠገኑና በተደረገለት ማጠናከሪያ ሊታይ ይችላል። በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ ሊቆይ የቻለውም በማሰሮ ውስጥ በጥንቃቄ ታሽጎ በመቀመጡ ነው። ይህ ጽሑፍ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎችና ለሁላችንም ምን ያህል ዋጋ ያለው ነው?
ይህ የነቢዩ ኢሳይያስ ጥንታዊ ጽሑፍ በወቅቱ ከነበሩት ከሌሎች የኢሳይያስ መጽሐፍ ቅጂዎች በዕድሜው በአንድ ሺህ ዓመት የሚበልጥ ቢሆንም በውስጡ የሚገኘው ሐሳብ እምብዛም ልዩነት የለውም። በ1950 መጽሐፉን ያሳተሙት ፕሮፌሰር ሚላር ባሮውስ እንዲህ ብለው ነበር፦ “በዚህ የብራና ጽሑፍ ውስጥ የሚገኘው በፊደልና በሰዋሰው እንዲሁም በዛ ያሉ ወይም መጠነኛ ክብደት ባላቸው የተለያዩ አነባበቦች ጉልህ ልዩነት ያለው የኢሳይያስ ጥቅስ ከጊዜ በኋላ [ማሶሬቲክ ሂብሩ ቴክስት] በሚባለው ትርጉም ውስጥ በአስተማማኝ ሁኔታ ቀርቧል።”a በተጨማሪም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በዕብራይስጥ ይሖዋ የተባለውን የአምላክን ቅዱስ ስም በሚገልጹት ቴትራግራማቶን יהוה ያለማቋረጥ መጠቀሙ ነው።
ሌሎች ጠቃሚ የብራና ጽሑፎች
መለኮታዊው ስም በዚሁ ዋሻ (አሁን ዋሻ ቁጥር 1 ተብሎ በሚጠራው) ውስጥ በተገኘ በሌላ ጥንታዊ ጽሑፍም ላይ ይገኛል። ስለ ዕንባቆም መጽሐፍ በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ቴትራግራማቶን በሰፊው ከሚታወቁት የአራት ማዕዘን ቅርጽ ካላቸው የዕብራይስጥ ፊደላት በሚለዩት በአሮጌው የዕብራይስጥ ፊደላት ስታይል አራት ጊዜ ያህል ተጽፎ ይገኛል።—በባለ ማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱስ የዕንባቆም 1:9ን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
በዋሻው ውስጥ ሌሎች የኢሳይያስ የመጻሕፍት ጥቅልል ክፍሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው የዳንኤል መጽሐፍ የቆዳ ቁርጥራጮች ጋር ተገኝተዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ በተገኙት ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ እንደታየው በዳንኤል 2:4 ላይ ከዕብራይስጥ ወደ አረማይክ የተደረገውን ለውጥ ጠብቆ አቆይቶታል።
በደንብ ተጠብቀው የተቀመጡት የመጻሕፍት ጥቅልሉ ትንንሽ ክፍሎች በአሁኑ ጊዜ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የመጽሐፍ ቤተ መቅደስ ተብሎ በሚጠራው ሙዚየም ውስጥ ለሕዝብ ይታያሉ። ይህ ሙዚየም ከመሬት በታች የሚገኝ ሲሆን በዚያ ቦታ ጉብኝት ስታደርግ ዋሻ ውስጥ እንደገባህ ሆኖ ይሰማሃል። የላይኛው የሙዚየሙ ክፍል የኢሳይያስ የሙት ባሕር ጥቅልል በተገኘበት ማሰሮ ክዳን ቅርጽ የተሠራ ነው። ሆኖም በዚያ የምታየው የኢሳይያስን የብራና ጽሑፍ ግልባጭ ብቻ ነው። ውድ ዋጋ ያለው በኩረ ጽሑፍ በአቅራቢያው በሚገኝ መጋዘን ውስጥ በአስተማማኝ ቦታ ተቀምጧል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዋና ዋና የሆኑት አንዳንዶቹ ንባቦች ማጣቀሻ ባለው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ በኢሳይያስ 11:1፤ 12:2፤ 14:4፤ 15:2፤ 18:2፤ 30:19፤ 37:20, 28፤ 40:6፤ 48:19፤ 51:19፤ 56:5፤ 60:21 ላይ ተጠቅሰዋል። የመጽሐፍ ጥቅልሉ በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ 1QIsa በሚል ተለይቶ ይታወቃል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
Courtesy of The British Museum
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Israel Antiquities Authority፤ The Shrine of the Book, Israel Museum፤ D. Samuel and Jeanne H. Gottesman Center for Biblical Manuscripts