የሙት ባሕር የመጻሕፍት ጥቅልል—ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሐብት
በሙት ባሕር ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘው በዋዲ ኩምራን ግርጌ ጥንታዊ ፍርስራሽ ይገኛል። ለረጅም ጊዜ የሮማውያን ጊዜያዊ ካምፕ እንደነበረ ተደርጎ ይታሰብ ስለነበር የቁፋሮ ታሪክ ተመራማሪዎችም ብዙ ትኩረት አልሰጡትም ነበር። ሆኖም በ1947 የሙት ባሕር የኢሳይያስ ጥቅልል መገኘቱ ቦታውን እንደገና ለማጥናት የሚያነሣሣ ሆኗል።
ብዙም ሳይቆይ ተመራማሪዎች በቦታው ያሉት ሕንፃዎች የአይሁድ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ንብረት እንደነበሩ አወቁ። ወዲያውኑም ወደ አእምሮአቸው የመጣው ግምት እነዚህ ሰዎች በአቅራቢያው በሚገኙ ገደላ ገደሎች ውስጥ የመጻሕፍት ጥቅልሎችን ደብቀዋል የሚል ነበር። ሆኖም በኋላ የተገኙት ማስረጃዎች በዚህ አባባል ላይ ጥርጣሬን ፈጠሩ።
ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግኝት
ዘላኖቹ አስቀድመው ስላገኙአቸው ጥንታዊ ጽሑፎች ዋጋማነት ንቁ ሆኑ። ስለዚህም በ1952 አንድ ሽማግሌ ወጣት በነበሩበት ጊዜ አንዲት የቆሰለች ወፍ ሲያባርሩ በድንጋይ ሥር ወደሚገኝ ጉድጓድ ውስጥ ገብታ እንደተሰወረችና በዚያም ቦታ አንዳንድ የሸክላ ዕቃዎችንና ጥንታዊ የዘይት ኩራዝ ማግኘታቸውን ስለ ገለጹ እንደገና አዲስ ፍለጋ ቀጠለ።
ሽማግሌው አሁንም ቢሆን ጥልቅ በሆኑት ገደሎች ውስጥ የዋሻውን አፍ ለይተው ለማወቅ ይችሉ ነበር። ይህም ሰው ሰራሽ ዋሻ ሆኖ ተገኘ። በዛሬው ጊዜ ዋሻ ቁጥር 4 በመባል ይታወቃል። በዚያም ዘላኖቹ በጊዜው ከነበረው የመሬት ወለል ጥቂት ጫማ ወረድ ብሎ ቁርጥራጭ ጥንታዊ ጽሑፎችን አገኙ። ከእነዚህ ቁርጥራጮች ውስጥ አንዳቸውም በማሰሮዎች ውስጥ የተቀመጡ አልነበሩም፤ በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ በጣም የበሰበሱ፣ የጠቆሩና በጣም የተቀዳደዱ ነበሩ። ውሎ አድሮ ወደ 400 የሚጠጉ የጥንታዊ ጽሑፎች ክፍል የሆኑ 40,000 ቁርጥራጮች ተገኙ። በ100ዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ጽሑፎች ውስጥ ከአስቴር መጽሐፍ በስተቀር ሁሉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍት ተገኙ። በዋሻ ቁጥር 4 የተገኘው አብዛኛው ጽሑፍ እስከ አሁን ድረስ ገና በጽሑፍ አልወጣም።
ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው የብራና መጻሕፍት አንዱ በአንድ ነጠላ ጥቅልል የተገለበጠው የሳሙኤል መጽሐፍ ነው። ምናልባት 57 ከሚሆኑት ውስጥ በ47 አምዶች ተጠብቆ የሚገኘው የሳሙኤል መጽሐፍ የዕብራይስጥ ጽሑፍ የግሪክ ሰፕቱጀንት ትርጉም ተርጓሚዎች ከተጠቀሙበት ጽሑፍ ጋር ተመሳሳይ ነው። በተጨማሪም በአንደኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበሩ የዘሌዋውያንና የዘኁልቁ የሴፕቱጀንት የግሪክ ቁርጥራጭ ጽሑፎችም አሉ። የዘሌዋውያን ጥንታዊ ጽሑፍ በዕብራይስጥ יהוה ለሚለው መለኮታዊው ስም በግሪክኛው ኪሪዮስ “ጌታ” በማለት ፋንታ IAO በማለት ይጠቀማል።a
የዕብራይስጥ ክፍል የሆነው ከዘዳግም መጽሐፍ የተገኘው ስባሪ ሸክላ በሴፕቱጀንት ትርጉም ላይ የተገኘውንና በዕብራውያን 1:6 ላይ የተጠቀሰውን፦ “የአምላክ መላዕክት ሁሉ ለእርሱ ይስገዱ” የሚለውን “ከዘዳ ምዕራፍ 32 ቁጥር 43 ጀምሮ ያለውን ክፍል ይጨምራል። ይህ በየትኛውም የጥንት የዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ ሲገኝ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር፣ የግሪክኛውን ትርጉም በግልጽ የሚደግፍ ጥቅስ ነው። ስለዚህም ተመራማሪዎች ብዙ ጊዜ በክርስቲያን ግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለሚጠቀሰው የሴፕቱጀንት ጥቅስ አዲስ ማስተዋል አግኝተዋል።
በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተጻፈ አንድ የዘፀዓት መጽሐፍ ጥቅልል፣ በዚያው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የተጻፈ የሳሙኤል መጽሐፍ ጥቅልል እና በ225 እና በ175 ከዘአበ መካከል የተጻፈ የኤርምያስ መጽሐፍ ጥቅልል ተገኝቷል። ከሦስተኛው መቶ ዘመን እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ ድረስ በዕብራይስጥና በአረማይክ ሆሄያት ውስጥ በአጻጻፍ ዘይቤዎችና በነጠላ ፊደላት ያሉትን ልዩነቶች ለማወቅ የሚያስችል በቂ ጽሑፍ ተገኝቷል። ይህም ጥንታዊ ጽሑፎቹ መቼ እንደተጻፉ ለማወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
ዋሻ ቁጥር 11 ያልታሰበ ነገር ተገኘበት
በመጨረሻ በአካባቢው ባሉት ዘላኖችና በቁፋሮ ታሪክ አጥኚዎች በኩምራን ዙሪያ የሚገኘው አካባቢ በሙሉ በደንብ ተፈተሸ። በ1956 አንዳንድ ዘላኖች በዋሻ ቁጥር 1 በስተ ሰሜን ካሉት ገደሎች ከሚገኙ ክፍት ቦታዎች ውስጥ የሌሊት ወፎች ሲወጡ ተመለከቱ። በዚያም አቅጣጫ ወደ ላይ ሲወጡ መግቢያው የተዘጋ ሌላ ዋሻ አገኙ። ዋሻውን ለመክፈት ሁለት ቶን የሚያክል ድንጋይ ማንሣት የሚጠይቅ ነበር። በዋሻው ውስጥ የተገኙት ነገሮች በጣም አስደናቂ ነበሩ። ሁለት የተሟሉ ጥንታዊ ጽሑፎችና አምስት ትልልቅ የሌሎች መጻሕፍት ክፍሎች ተገኙ።
ከሁሉም በላይ በጣም ጠቃሚ የሆነው ግኝት ውብ የሆነው የመዝሙር መጻሕፍት ጥቅልል ነው። የተጻፈበት ቆዳ ወፍራም መሆኑ ከፍየል ቆዳ የተሠራ ሳይሆን ምናልባት ከጥጃ ቆዳ የተሠራ እንደሆነ ያመለክታል። በአጠቃላይ አምስት ነጠላ የቆዳ መጻፊያዎች አራት ሊለያዩ የሚችሉ ቅጠሎች እና አራት የሸክላ ስባሪዎች ከ13 ጫማ በላይ ርዝመት እንዲኖረው ያደርጉታል። የዚህ የመጻሕፍት ጥቅልል የላይኛው ጠርዝ በደንብ የተጠበቀ ቢሆንም የታችኛው ጠርዝ ግን በስብሶአል። የተጻፈበት ጊዜ በአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ የመጀመሪያ አጋማሽ አካባቢ ሲሆን የ41 መዝሙሮችን ክፍል የያዘ ነው። ቴትራግራማቶን የሚባሉት የአምላክን ስም የሚወክሉት ፊደላት (יהוה) በጥንታዊው አናባቢ የሌለው የዕብራይስጥ አጻጻፍ 105 ጊዜ ተጽፈው ይገኛሉ። የአራት ማዕዘን ቅርጽ ካላቸው የዕብራይስጥ ጽሑፎች መካከል ተለይተው እንዲታዩም ጎላ ተደርገዋል።
ሌላው የዘሌዋውያን መጽሐፍ ጥንታዊ ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ በዕብራይስጥ ጽሕፈት የተጻፈ ነው፤ ለምን እንደዚህ ሆኖ እንደተጻፈ ግን አጥጋቢ ማብራሪያ ገና አልተገኘም። በእንደዚህ ዓይነት አጻጻፍ ተጽፈው ከሚገኙት ሁሉ ረጅም የሆነው ይህ ነው። ይህም በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ላይ አይሁዶች ወደ ባቢሎን ተማርከው በሄዱበት ጊዜ በሰፊው ይሠራበት የነበረ ነው።
የኢዮብ መጽሐፍ የአረማይክ ትርጉም የሆነው የታርገም ቅጂም ተገኝቷል። ይህም በጽሑፍ ከቀረቡት ጥንታዊ አረማይክ ትርጉሞች ውስጥ አንዱ ነው። በተለያዩ ዋሻዎች ውስጥ በዛ ያሉ ስለ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተሰጡ ማብራሪያዎችም ተገኝተዋል። እነዚህ ሁሉ የመጻሕፍት ጥቅልሎች በእነዚህ ዋሾች በጥሩ ሁኔታ ተደብቀው ሊቀመጡ የቻሉት እንዴት ነበር?
ቀደም ሲል እንደተገለጸው አንዳንዶቹ በኩምራን ማኅበረሰብ የተደበቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከማስረጃዎች ለመገመት እንደሚቻለው ብዙዎቹን ጽሑፎች እዚያ ያስቀመጧቸው ከሁለት ዓመት በኋላ በኢየሩሳሌም ላይ የመጨረሻው ጥፋት ከመምጣቱ በፊት በ68 እዘአ ሮም በይሁዳ ላይ ከሚያደርገው ከበባ የሸሹት አይሁዶች ሳይሆኑ አይቀሩም። የይሁዳ ምድረ በዳ ውድ ለሆኑት ጥንታዊ ጽሑፎች የተፈጥሮ መሸሸጊያ የሆነው በኩምራን አጠገብ በሚገኙት ዋሻዎቹ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰሜን ብዙ ኪሎሜትሮች ርቆ በሚገኘው አካባቢ፣ በኢያሪኮ ዙሪያና ወደ ደቡብ ደግሞ በማሳዳ አጠገብ የሚገኘው ቦታ ነው። እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች ተጠብቀው በመቆየታቸው በጣም አመስጋኞች መሆን ይገባናል! በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የይሖዋ አምላክ ቃል የማይለወጥ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጡናል። በእርግጥም፦ “የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—ኢሳይያስ 40:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ባለ ማጣቀሻ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን አፔንዲክስ (ተጨማሪ ማብራሪያ) 1C (5) እና የዘሌዋውያን 3:12ን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት። በዚህ ላይ ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ 4Q LXX Levb በሚል ተለይቶ ይታወቃል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወደፊት የበለጠ ዕውቀት ይገኝ ይሆን?
ምንም እንኳ የተገኙት ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት ቢሆንም ብዛት ያላቸው የሙት ባሕር የመጻሕፍት ጥቅልል ቁርጥራጮች ገና አልታተሙም። ታህሣሥ 2, 1990 የወጣው የኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት እንዲህ በማለት ያወግዛል፦ “የፎቶግራፍ ምስሎቻቸውም እንኳን ሳይቀሩ ከጓደኞቻቸው በሚሸሹትና በእጃቸው ከሚገኘው ጽሑፍ ውስጥ አብዛኛውን ለማተም እምቢ ባሉት አንድ ዓላማ ባላቸው ሴረኛ የምሁራን ቡድን ምርኮኛ ሆነው ተይዘዋል።” ሆኖም መጽሔቱ እንደገለጸው በቅርቡ በዚህ የሕትመት ቡድን የአስተዳደር ለውጥ ስለተደረገ ምናልባት ይህ “በመጻሕፍት ጥቅልሎቹ ዙሪያ ያለው ሴራ” ሊቆረጥና “ዓለም በታሪክ ውስጥ ልዩ ስለነበረው ዘመን ተጨማሪ ዕውቀት ሊያገኝ ይችላል።”
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.