የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን አስቡ
“አምላክ . . . ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏል።”—ሮሜ 9:22
1. (ሀ) በመንፈስ የተጻፈው የአምላክ ቃል ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ረገድ እዚህ ላይ የትዕግሥትን ጠባይ የምንመለከተው ለምንድን ነው?
ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። መጽሐፉ ‘ለእግራችን መብራት ለመንገዳችንም ብርሃን’ በመሆን ያገለግለናል። (መዝሙር 119:105) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ‘ለበጎ ሥራ ሙሉ በሙሉ የተዘጋጀን እንድንሆን’ ይረዳናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ለዚህ ዝግጁ እንድንሆን እኛን ከሚረዳባቸው መንገዶች አንዱ የትዕግሥት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ስለሚጠቅስልን ነው። ይህ ጠባይ ከአምላክ የመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ሲሆን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘትና ከሌሎች ሰዎች ጋር በስምምነት ለመኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።—ገላትያ 5:22, 23
2. “ትዕግሥት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ይህንንስ ጠባይ በማሳየት ቀዳሚ የሆነው ማን ነው?
2 “ትዕግሥት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የመንፈስ ርዝማኔ” ማለት ነው። ትዕግሥት ለሚለው ቃል “የሚረብሽ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ በችኮላ አጸፋ የማይመልስ፣ ወይም ወዲያውኑ የማይቀጣ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶአል። (በቫይን የተዘጋጀው የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቃላት ገላጭ መዝገበ ቃላት ጥራዝ 3 ገጽ 12) መታገሥ ሲባል ራስን መግዛትና ለቁጣ የዘገዩ መሆን ማለት ነው። ታዲያ ለቁጣ የዘገየ በመሆንና ትዕግሥትን በማሳየት በኩል ዋነኛው ማን ነው? ከይሖዋ አምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ስለዚህም በዘፀዓት 34:6 ላይ ይሖዋ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም (ለቁጣ የዘገየ)፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” እንደሆነ እናነባለን። እንዲያውም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በስምንት ተጨማሪ ቦታዎች ላይ ይሖዋ “ለቁጣ የዘገየ” እንደሆነ ተገልጿል።—ዘኁልቁ 14:18፤ ነህምያ 9:17፤ መዝሙር 86:15፤ 103:8፤ 145:8፤ ኢዩኤል 2:13፤ ዮናስ 4:2፤ ናሆም 1:3
3. ይሖዋ ትዕግሥተኛ እንዲሆን አስተዋጽዎ ያደረጉት የትኞቹ ጠባዮች ናቸው?
3 ታጋሽ፣ ወይም ለቁጣ የዘገዩ መሆን ከይሖዋ አምላክ ልንጠብቀው የሚገባ ጠባይ ነው፤ ምክንያቱም እርሱ ለኃይሉና ለጥበቡ ወሰን የሌለው፣ በፍትሑ ፍጹም የሆነ፣ እንዲሁም ሁለንተናው ፍቅር የሆነ አምላክ ነው። (ዘዳግም 32:4፤ ኢዮብ 12:13፤ ኢሳይያስ 40:26፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ባሕርዮቹ ከቁጥጥሩ ውጭ አይሄዱም፤ ምን ጊዜም በፍጹም ሚዛን ጠብቆ ሊያሳያቸው ይችላል። አምላክ ፍጽምና ለሌላቸው ሰዎች ትዕግሥቱን ለምንና እንዴት እንዳሳየ ቃሉ ምን ይገልጻል?
ለስሙ ሲል ያሳየው ትዕግሥት
4. አምላክ ለኃጢአተኞች ትዕግሥትን ያሳየው በምን ጥሩ ምክንያቶች የተነሳ ነው?
4 ይሖዋ ታጋሽ የሆነው ለምንድን ነው? ኃጢአተኞችን ወዲያውኑ የማይቀጣው ለምንድን ነው? ግድ የለሽ ስለሆነ ወይም ለጽድቅ ቅንዓት ስለሌለው አይደለም። ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ የሆነውና ወዲያውኑ ሰዎችን የማይቀጣው በጥሩ ምክንያት የተነሳ ነው። አንዱ ምክንያት ስሙ እንዲታወቅ ሲል ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ በኤደን በተነሣው አመጽ ስለ አምላክ ሉዓላዊነትና ስለ ሰው የአቋም ጽኑነት ለተነሡት አከራካሪ ጉዳዮች መልስ ለመስጠት ጊዜ በማስፈለጉ ነው። አሁንም አምላክ ትዕግሥት ያሳየበት ሌላው ምክንያት ኃጢአተኛ ሰዎች መንገዳቸውን እንዲያስተካክሉ ዕድል ለመስጠት ነው።
5, 6. ከሰው አመጽ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ትዕግሥትን ያሳየው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓውያን ባልና ሚስት በትዕግስት ይዟቸዋል። መልካሙንና ክፉውን ከምታስታውቀው ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ባፈረሱ ጊዜ ይሖዋ እነርሱንና ሔዋንን ያሳታትን መልአክ ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። የይሖዋ የጽድቅና የፍትሕ ስሜት እንደተጎዳና በሦስቱ አመጸኞች ላይ ቁጣው እንደተነሳሳ ምንም አያጠያይቅም። ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ፍጹም መብት ነበረው። አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” ብሎ አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አዳም ኃጢአት በሠራበት በዚያው ቀን አምላክ ጥፋተኞቹን ስለ አድራጎታቸው ጠይቆ ሞት ፈረደባቸው። ከፍርድ አንፃር አዳምና ሔዋን በዚያኑ ዕለት ሞተዋል። ሆኖም ታጋሹ ፈጣሪያችን አዳም ለ930 ዓመት እንዲኖር ፈቅዶለታል።—ዘፍጥረት 5:5
6 አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ታጋሽ ወይም ለቁጣ የዘገየ የሚሆንበት ጥሩ ምክንያቶች ነበሩት። እነዚህን አመጸኞች ወዲያውኑ ቢያጠፋቸው ኖሮ ይሖዋ አምላክ መመለክ አይገባውም እንዲሁም ለእርሱ ባላቸው የደጋፊነት አቋም የሚጸኑ ሰብዓዊ አገልጋዮች ሊያገኝ አይችልም በማለት ዲያብሎስ በተዛዋሪ ለተናገረው ስድብ መልስ አይሆንም። ከዚህም በላይ እንደሚከተሉት ያሉት ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ ይቀሩ ነበር፦ አዳምና ሔዋን ኃጢአት መሥራታቸው ጥፋቱ የማን ነው? ይሖዋ ከመጀመሪያው ፈተና ለመቋቋም የማይችሉ ደካማ ፍጥረታት አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ ወደ ክፉ የሚገፋፋውን ፈተና ሳትቋቋሙ ቀርታችኋል ብሎ ቀጣቸውን? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ በኢዮብ መጽሐፍ በምዕራፍ 1 እና 2 ላይ በሚገኘው ታሪክ ውስጥ በግልጽ ይታያል። የሰብዓዊው ዘር ቁጥር እንዲጨምር በመፍቀድ ይሖዋ ሰይጣን ያነሣቸው ክሶች ሐሰት መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ለሰዎች ዕድል ሰጣቸው።
7. ይሖዋ ፈርዖንን ወዲያውኑ ያልገደለው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ ሕዝቡን እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ ባወጣበት ጊዜ ታጋሽ መሆኑን እንደገና አረጋግጧል። ይሖዋ ፈርዖንንና የጦር ኃይሉን ወዲያውኑ መደምሰስ ይችል ነበር። ሆኖም ይህን ከማድረግ ይልቅ አምላክ ለጊዜው ታገሣቸው። የታገሣቸው በምን ጥሩ ምክንያቶች የተነሳ ነው? ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን ፈርዖን እስራኤላውያንን ነፃ የይሖዋ ሕዝብ አድርጎ ለመልቀቅ በእምቢተኝነት አቋሙ ይበልጥ ደነደነ። በዚህም መንገድ ይሖዋን በመዳፈሩ ጥፋት የሚገባው ‘የቁጣ ዕቃ’ መሆኑን አሳየ። (ሮሜ 9:14-24) ሆኖም አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ታጋሽ የሆነበት ሌላም ትልቅ ምክንያት ነበረ። በሙሴ በኩል ለፈርዖን እንዲህ አለው፦ “አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፣ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ።”—ዘፀዓት 9:15, 16
8. አምላክ አመጸኞቹን እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ያላጠፋቸው በምን ጥሩ ምክንያት ነው?
8 የይሖዋ ትዕግሥት እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜም ለጥሩ ምክንያቶች ሲባል ታይቷል። የወርቅ ጥጃ ባመለኩበትና አሥሩ ሰላዮች መጥፎ ዜና ይዘው በተመለሱበት ጊዜ የይሖዋን ትዕግሥት ምንኛ ተፈታትነውት ነበር! ነገሩ ስሙን የሚነካ በመሆኑ አምላክ ሕዝቡን እንዳሉ አልደመሰሳቸውም። አዎን፣ ይሖዋ ስለ ስሙ ሲል ትዕግሥት አሳይቷል።—ዘፀዓት 32:10-14፤ ዘኁልቁ 14:11-20
ስለ ሰዎች ሲል ያሳየው ትዕግሥት
9. ይሖዋ በኖኅ ዘመን ትዕግሥት ያሳየው ለምንድን ነው?
9 አዳም የወደፊት ዘሮቹን ሁሉ ቢበድላቸውና ኃጢአት በመሥራት ትልቅ የፍትህ መጓደል ቢፈጽምባቸውም ይሖዋ ለሰው ዘሮች ጥቅም ሲል ትዕግሥቱን አሳይቷል። የአምላክ ትዕግሥት ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ከእርሱ ጋር እንዲታረቁ ለማድረግ ጊዜ በመፍቀዱ የተፈጸመው በደል እንዲስተካከል አስችሎአል። (ሮሜ 5:8-10) በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ በኖኅ ዘመን ለሰዎች ትዕግሥት አሳይቷል። በዚያን ጊዜ ይሖዋ “የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደበዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ።” (ዘፍጥረት 6:5) አምላክ ይህንን ሁኔታ ሲመለከት ወዲያውኑ ሰብዓዊውን ዘር ጠራርጎ ለማጥፋት የሚችል ቢሆንም ይህንን ሁኔታ በ120 ዓመታት ውስጥ ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው አስታወቀ። (ዘፍጥረት 6:3) ይህ የትዕግሥት መግለጫ ኖኅ ሦስት ልጆችን እንዲወልድ፣ ልጆቹም አድገው እንዲያገቡና ነፍሳቸውን ለማዳንና የእንስሳትን ፍጥረት ለማትረፍ ለዚህ ቤተሰብ መርከብ እንዲሠሩ ጊዜ እንዲኖር ፈቀደ። በዚህ መንገድ አምላክ ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ተግባራዊ ለመሆን ዕድል ለማግኘት ቻለ።
10, 11. ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ ያን ያህል የታገሠው ለምንድን ነው?
10 ሌላው የትዕግሥት ትርጉም በተለይ አምላክ ከሕዝቡ ጋር ላለው ግንኙነት ይሠራል። ይህም ሁለተኛ ትርጉም “በደል ወይም የሚያስቆጣ ነገር ሲፈጸም በትዕግሥት መቻል፣ የሻከረው ግንኙነት ሊሻሻል አይችልም ብሎ ተስፋ አለመቁረጥ” ማለት ነው። (ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 262፤ በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትንንሽ ጽሑፎች ማኅበር የታተመ) ይኸኛው የቃሉ ፍቺ አምላክ ለእስራኤላውያን ታጋሽ የሆነበት ተጨማሪ ምክንያት ምን እንደነበረ ይጠቁምልናል። እነርሱ በተደጋጋሚ ከይሖዋ ዘወር በማለታቸው በአሕዛብ ብሔራት ባርነት ሥር ወድቀዋል። ቢሆንም እርሱ እስራኤላውያንን በማዳንና ንስሐ እንዲገቡ ዕድል በመስጠት ትዕግሥቱን አሳይቷል።—መሳፍንት 2:16-20
11 አብዛኞቹ የእስራኤል ነገሥታት ተገዥዎቻቸውን ወደ ሐሰት አምልኮት መርተዋል። ታዲያ አምላክ ሕዝቡን በአንድ ጊዜ አስወገዳቸውን? እንደዚያ አላደረገም፤ የሻከረው ዝምድናቸው የመሻሻል ተስፋ እንደሌለው አድርጎ በፍጥነት አልተዋቸውም። በዚህ ፋንታ ይሖዋ ለመቆጣት ታገሠ። ትዕግሥቱን በማሳየት አምላክ ንስሐ እንዲገቡ በተደጋጋሚ ዕድል ሰጣቸው። በ2 ዜና 36:15, 16 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “የአባቶቻቸውም አምላክ [ይሖዋ (አዓት)] ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልዕክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን [የይሖዋ (አዓት)] ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ [በእውነተኛው አምላክ (አዓት)] መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።”
12. የክርስትያን ግሪክኛ ጽሑፎች ይሖዋ ታጋሽ ስለሆነበት ምክንያት ምን ምስክርነት ይሰጣሉ?
12 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችም ይሖዋ ስሕተት ላይ የወደቁ ሕዝቦቹን ለመርዳት ስላሳየው ትዕግሥት ማስረጃ ይሰጣሉ። ለምሳሌም ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ኃጢአት የሠሩ ክርስቲያኖችን “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለ ጠግነት ትንቃለህን?” በማለት ጠይቋል። (ሮሜ 2:4) ቀጥሎ ያሉት የጴጥሮስ ቃላትም ተመሳሳይ ሐሳብ አላቸው፦ “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው [ይሖዋ (አዓት)] ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9) ስለዚህ “የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቁጠሩ” ተብሎ የተነገረን ነገር በጣም ተገቢ ነው! (2 ጴጥሮስ 3:15) ስለዚህ ይሖዋ ታጋሽ የሆነው በስሜታዊነት ወይም በግድየለሽነት ምክንያት ሳይሆን ስሙንና ዓላማዎቹን የሚነካ በመሆኑና መሐሪና አፍቃሪ ስለሆነ መሆኑን እንመለከታለን።
ኢየሱስ ያሳየው የትዕግሥት ምሳሌ
13. ኢየሱስ ክርስቶስ ታጋሽ እንደነበረ የሚገልጽ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?
13 አምላክ ካሳየው ዓይነት ትዕግሥት ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ምሳሌ የሚሆነው መሲሑ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ የሚያስቆጣ ሁኔታ ቢደርስበትም በችኮላ አጸፋዊ እርምጃ ባለመውሰዱ እጅግ በጣም ጥሩ ምሳሌ ነው።a መሲሑ ታጋሽ እንደሚሆን በሚከተሉት የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት ውስጥ ተተንብዮ ነበር፦ “ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።” (ኢሳይያስ 53:7) ጴጥሮስ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራን ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” ሲል የተናገረው ቃልም ለዚሁ እውነት ተጨማሪ ምሥክርነት ይሰጣል። (1 ጴጥሮስ 2:23) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመካከላቸው ታላቅ ስለሚሆነው ሰው በተደጋጋሚ በመከራከር እንዴት ፈትነውት ይሆን! ሆኖም እርሱ እንዴት ያለ ታጋሽነትና ቻይነት አሳይቷቸዋል!—ማርቆስ 9:34፤ ሉቃስ 9:46፤ 22:24
14. ኢየሱስ ያሳየው የትዕግሥት ምሳሌ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
14 ኢየሱስ ታጋሽ በመሆን የተወልንን ምሳሌ መከተል ይገባናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል (በመከራ እንጨት) ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።”—ዕብራውያን 12:1-3
15. ኢየሱስ ታጋሽ እንደነበረና የደረሰበትን መከራ ሁሉ በፈቃደኝነት እንደቻለ እንዴት እናውቃለን?
15 ኢየሱስ ታጋሽ እንደነበረና የደረሰበትን መከራ በፈቃደኝነት ችሎ ለመጽናቱ ተይዞ በታሠረበት ጊዜ ባሳየው ዝንባሌ ሊታይ ይችላል። ጴጥሮስ ጌታውን ለመከላከል ሰይፍ በማንሣቱ ከገሰፀው በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?”—ማቴዎስ 26:51-54፤ ዮሐንስ 18:10, 11
ሌሎች የትዕግሥት ምሳሌዎች
16. ቅዱሳን ጽሑፎች የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ትዕግሥተኛ እንደነበረ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
16 ፍጽምና የጐደላቸው ኃጢአተኛ ሰዎችም ቢሆኑ ትዕግሥትን ማሳየት ይችላሉ። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች የደረሰባቸውን በደል በመቻል ትዕግሥት ያሳዩ ሰዎችን ምሳሌ ይዘዋል። ለምሳሌም ያህል ከጥንት አባቶች አንዱ የሆነው የዕብራዊው የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ አለ። ወንድሞቹና የጶጢፋር ሚስት ያደረሱበትን ግፍ እንዴት በትዕግሥት ቻለ! (ዘፍጥረት 37:18-28፤ 39:1-20) ዮሴፍ እነዚህ መከራዎች እንዲያስመርሩት አልፈቀደም። ይህም ለወንድሞቹ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረበት ጊዜ በግልጽ ታይቷል፦ “አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፣ አትቆርቆሩም፤ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን አስቀድሞ ሰድዶኛልና።” (ዘፍጥረት 45:4, 5) ዮሴፍ ለትዕግሥት እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው!
17, 18. ዳዊትን በተመለከተ ምን የትዕግሥት ማስረጃ እናገኛለን?
17 ዳዊት የሚደርስበትን በደል ችሎ በመጽናት ትዕግሥትን ያሳየ ሌላው ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ነው። ቀናተኛው ንጉሥ ሳኦል እንደ ውሻ ቢያሳድደውም ዳዊት ባገኛቸው ሁለት አጋጣሚዎች እርሱን በመግደል ሊበቀለው ይችል ነበር። (1 ሳሙኤል 24:1-22፤ 26:1-25) ይሁን እንጂ ዳዊት ለአቢሳ ከተናገረው ቃል ለማየት እንደሚቻለው አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ጠበቀ፦ “[ይሖዋ (አዓት)] (ሳኦልን) ይመታዋል፣ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፣ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል፤ እኔ ግን [ይሖዋ (አዓት)] በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ [ይሖዋ (አዓት)] ከእኔ ያርቀው።” (1 ሳሙኤል 26:10, 11) አዎን፤ ዳዊት ሳኦል የሚያደርስበትን ስደት ለማቆም የሚያስችል ኃይል በእጁ ነበረ። በዚህ ፋንታ ዳዊት ለመታገሥ መረጠ።
18 ዳዊት ከተንኮለኛው ልጁ ከአቤሴሎም ሲሸሽ የደረሰውንም ጭምር አስቡት። ከሳኦል ቤት የሆነው ብንያማዊው ሳሚ በዳዊት ላይ ድንጋይ እየወረወረ ይረግመውና “ሂድ አንተ የደም ሰው፣ ምናምንቴ ሂድ” እያለ ይጮህበት ነበር። አቢሳ ሳሚን ለመግደል ፈለገ፤ ዳዊት ግን አጸፋ ለመመለስ እምቢ አለ። ከዚህ ይልቅ እንደገና የትዕግሥትን ባሕርይ አሳየ።—2 ሳሙኤል 16:5-13
የጳውሎስን ምሳሌ አስቡ
19, 20. ሐዋርያው ጳውሎስ ትዕግሥት ያለው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
19 በክርስትያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ፍጹም ካልሆኑት ሰዎች መካከል ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሌላውን ሰው ሐዋርያው ጳውሎስን እናገኛለን። እርሱ ለሃይማኖታዊ ጠላቶቹም ይሁን ክርስቲያን ነን ለሚሉት ግለሰቦች የመቻልን ባሕርይ፤ ትዕግሥትን አሳይቷል። አዎን፤ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩ አንዳንዶች “መልዕክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፣ ሰውነቱ ሲታይ ግን ደካማ ነው” ቢሉትም ትዕግሥትን አሳይቷል።—2 ቆሮንቶስ 10:10፤ 11:5, 6, 22-33
20 እንግዲያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንደሚከተለው ብሎ መናገሩ በጥሩ ምክንያት ነበር፦ “ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጦም፣ በንጽሕና፣ በእውቀት፣ በትዕግሥት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ ግብዝነት በሌለው ፍቅር።” (2 ቆሮንቶስ 6:4-6) ሐዋርያው በተመሳሳይ መንገድ ለሥራ ባልደረባው ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎ ሊጽፍለት ችሏል፦ “አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ . . . ጌታም ከሁሉ አዳነኝ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:10, 11) ሐዋርያው ጳውሎስ ትዕግሥት በማሳየት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!
21. የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንዴት ሊረዳን ይችላል?
21 በግልጽ እንደሚታየው ቅዱሳን ጽሑፎች በትዕግሥት በኩል በጥሩ ምሳሌዎች የተሞሉ ናቸው። ይሖዋና የተወደደው ልጁ ዋነኞቹ ምሳሌዎች ናቸው። ይሁን እንጂ እንደ ዮሴፍ፣ ዳዊትና ሐዋርያው ጳውሎስ የመሳሰሉ ፍጽምና የጐደላቸው ሰዎች ይህን ባሕርይ እንዳሳዩ ማወቁ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንደነዚህ ያሉትን መልካም ምሳሌዎች እንድንከተል እኛን ለመርዳት ታቅዶ የተዘጋጀ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ትዕግሥት ተብሎ የተተረጐመው የእንግሊዝኛ ቃል “ሎንግ ሳፈሪንግ” ሲሆን ቃሉ ለረጅም ጊዜ መሰቃየት ማለት አይደለም። ለረጅም ጊዜ መከራ የደረሰበት ሰው ለመበቀል ባለመቻሉ ምክንያት ቢበሳጭ ወይም ቢማረር ትዕግሥት ማሳየቱ አይደለም።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ትዕግሥት ሲባል ምን ማለት ነው?
◻ ይሖዋ ትዕግሥተኛ የሆነው በተለይ በምን ምክንያቶች የተነሳ ነው?
◻ ኢየሱስ ትዕግሥተኛ መሆኑን ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
◻ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ትዕግሥትን ሊያሳዩ እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዮሴፍ፣ ኢየሱስ፣ ዳዊት፣ ጳውሎስና ኢዮብ የትዕግሥት ምሳሌ ናቸው
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ትዕግሥት አሳይቷቸዋል