የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 5/15 ገጽ 16-20
  • ሁሉንም ሰው ታገሡ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሁሉንም ሰው ታገሡ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወንድሞቻችንን መቻል
  • በቤተሰብ ክልል ውስጥ
  • በውጭ ላሉት ሰዎች
  • እምነትና ተስፋ ትዕግሥት ለማሳየት ይረዳሉ
  • ጸሎት፣ ትሕትናና ፍቅር ይረዳሉ
  • በደስታ ታገሡ?
  • “ትዕግሥትን ልበሱ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን አስቡ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ይሖዋ ታጋሽ አምላክ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ትዕግሥት
    ለይሖዋ ዘምሩ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 5/15 ገጽ 16-20

ሁሉንም ሰው ታገሡ

“ወንድሞች ሆይ፣ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።”​—1 ተሰሎንቄ 5:14

1. የይሖዋ ምስክሮች ትዕግሥትን ያሳዩት መቼና በምን ሁኔታዎች ሥር ነው?

ትዕግሥት በማሳየት በኩል በዘመናችን የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች እንዴት ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ! እነርሱም በቀድሞዎቹ የናዚና የፋሺስት አገሮች ውስጥ እንዲሁም እስከ ዘመናችን ድረስ እንደ ማላዊ ባሉ አንዳንድ አገሮች ብዙ መከራንና ስደትን ተቋቁመዋል። በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩትም ቢሆኑ በትዕግሥት ጸንተው ይኖራሉ።

2. የይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊ ገነት እንዲያገኙ ምክንያት የሆኑ ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 ለይሖዋ የተወሰኑት ሕዝቦች ስደትና መከራዎች ቢደርሱባቸውም በመንፈሳዊው ገነት በረከቶች ተደስተው ይኖራሉ። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ1919 ጀምሮ ይህንን ማግኘት እንደጀመሩ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። ይህ መንፈሳዊ ገነት ሊገኝ የቻለው በምን ምክንያት ነው? ከሁሉ በፊት እነዚህ ገነታዊ ሁኔታዎች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሊኖሩ የቻሉት አምላክ ቅቡዓን አገልጋዮቹን ወደ “ምድራቸው” ወይም ወደ ንጹሑ አምልኮት በመመለሱ ነው። (ኢሳይያስ 66:7, 8) መንፈሳዊው ገነት እየበለጸገ ሊሄድ የቻለበት ሌላው ምክንያት በውስጡ የሚኖረው ሁሉም ሰው የአምላክን የመንፈስ ፍሬዎች ስለሚያሳይ ነው። ከእነዚህም አንዱ ትዕግሥት ነው። (ገላትያ 5:22, 23) ይህ ጠባይ ለመንፈሳዊ ገነታችን በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ ዊልያም ባርክሌይ በሰጡት በሚከተለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ ለማየት ይቻላል፦ “ያለ ማክሮቱሚያ [ትዕግሥት] ክርስቲያናዊ ወዳጅነት የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም። . . . ለዚህም ምክንያቱ የሚከተለው ነው፤ ይኸውም ማክሮቱሚያ ታላቁ የአምላክ ባሕርይ ነው። (ሮሜ 2:4፤ 9:22)” (የአዲስ ኪዳን የቃላት መጽሐፍ ገጽ 84) አዎን፤ ትዕግሥት ይህን ያህል አስፈላጊ ነገር ነው!

ወንድሞቻችንን መቻል

3. ኢየሱስ ትዕግሥተኛ ስለ መሆን ለጴጥሮስ ምን ትምህርት ሰጠው?

3 ሐዋርያው ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ላይ ትዕግሥትን ማሳየት የከበደው ይመስላል፤ ምክንያቱም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን?” ብሎ ጠይቆታል። ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም” ብሎ መከረው። (ማቴዎስ 18:21, 22) በሌላ አባባል እርስ በርስ ለመቻቻል ወይም ለበደለን ሰው ይቅርታ ለማድረግ የተወሰነ ቁጥር የለም ማለት ነው። አንድ ሰው እስከ 77 ጊዜ ይቆጥራል ብለን ልንገምት አንችልም። ሆኖም ያንን ያህል ጊዜ ይቅር ለማለት ትዕግሥተኛነት ወይም ቻይነት ያስፈልጋል።

4. በተለይ ሽማግሌዎች ትዕግሥተኞች መሆን የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

4 ለመንፈሳዊ ወንድሞች ትዕግሥት ማሳየትን በተመለከተ የጉባኤ ሽማግሌዎች ምሳሌ መሆን እንደሚገባቸው ምንም አያጠያይቅም። አንዳንድ የእምነት ጓደኞቻቸው ግድ የለሾች ወይም ቸልተኞች በመሆናቸው ምክንያት ትዕግሥታቸው ሊፈተን ይችላል። ሌሎችም መጥፎ ልማዶችን ለማረም ዳተኞች ሆነው ይሆናል። ሽማግሌዎች በክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ድክመቶች ምክንያት በቀላሉ እንዳይበሳጩ ወይም እንዳይጎዱ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ይልቅ እነዚህ መንፈሳዊ እረኞች “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል” የሚለውን ምክር ማስታወስ ያስፈልጋቸዋል።​—ሮሜ 15:1

5. ትዕግሥተኞች ከሆንን ምንን ችለን እናልፋለን?

5 ከዚህም በተጨማሪ በሰብዓዊ ድካሞችና ጉድለቶች ምክንያት የባሕርይ ግጭቶች ሊነሡ ይችላሉ። በድካሞቻችንና ባሉን ተፈጥሮአዊ ልዩነቶች ምክንያት ወንድሞቻችንን በተሳሳተ መንገድ ልንጎዳቸው እንችላለን፤ እነርሱም እኛን ሊጎዱን ይችላሉ። ስለዚህ “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥት አድርጉ፤ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ [በነፃ (አዓት)] ይቅር ተባባሉ፤ [ይሖዋ በነፃ (አዓት)] ይቅር እንዳላችሁ እንዲሁ አድርጉ” የሚለው ምክር እዚህ ላይ እንዴት ተስማሚ ነው! (ቆላስይስ 3:13) ‘እርስ በርስ ትዕግሥት ማድረግ’ ሲባል ለቅሬታ በቂ መሠረት ቢኖረንም መቻል አለብን ማለት ነው። ወንድማችንን መበቀል ወይም መቅጣት እንዲያውም በእርሱ ላይ ቂም እንኳን መያዝ አይገባንም።​—ያዕቆብ 5:9

6. ትዕግሥተኛ መሆን የጥበብ መንገድ የሆነው ለምንድን ነው?

6 በሮሜ 12:19 ላይ የሚገኘው ምክርም ከላይ ካለው ጋር ተመሳሳይ ውጤት ያለው ነው፦ “ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቁጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል [ይሖዋ (አዓት)] ተብሎ ተጽፎአልና።” ‘ለቁጣ ፈንታ ስጡ’ ሲባል ለቁጣ የዘገዩ መሆን ወይም መቻል ማለት ነው። ይህንን ጠባይ ማሳየት የጥበብ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም እኛንም ሌሎችንም ይጠቅማል። አንድ ችግር ተነሥቶ ከሆነ እኛ ትዕግሥት በማሳየታችን ነገሩ እንዲባባስ ስላላደረግን ጥሩ ስሜት ይሰማናል። ትዕግሥታችንን የምናሳየውም ሰው ቢሆን ስላልቀጣነው ወይም በአንድ መንገድ ብድሩን ስላልመለስንበት ጥሩ ይሰማዋል። ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስትያን ጓደኞቹን “ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” ብሎ ማስጠንቀቁ አያስደንቅም።​—1 ተሰሎንቄ 5:14

በቤተሰብ ክልል ውስጥ

7. የተጋቡ ሰዎች ትዕግሥተኞች መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

7 ደስታ የሰፈነበት ትዳር የሁለት ጥሩ ይቅር ባዮች ኅብረት ነው መባሉ ትክክል ነው። ይህ ምን ማለት ነው? እነዚህ በደስታ ተጋብተው የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርስ ትዕግሥት ያሳያሉ ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ ግለሰቦች ባሏቸው ተቃራኒ ጠባዮች ምክንያት እርስ በርስ ይሳሳባሉ። እነዚህ ልዩነቶች ስሜትን የሚስቡ ቢሆኑም ተጋብተው የሚኖሩት ክርስትያኖች ቀደም ሲል “በሥጋቸው ላይ መከራ” በሆኑባቸው ጭንቀቶችና መከራዎች ላይ ተጨማሪ ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ለምሳሌ ያህል አንድ ባል ለዝርዝር ጉዳዮች ምንም የማይጨነቅ ሊሆን ወይም በአጠቃላይ ግድ የሌለው፤ ስለ ልብሱም የማያስብ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በደግነት አነጋገር የሰጠችው ሐሳብ ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ከተገነዘበች ያለው አማራጭ በትዕግሥት ችሎ መኖር ብቻ ሊሆን ይችላል።

8. ባሎች በምን ምክንያት ትዕግሥተኞች መሆን ሊያስፈልጋቸው ይችላል?

8 በሌላም በኩል አንዲት ሚስት ጥቃቅን ነገሮችን የምትከታተልና ባልዋን የምትነዘንዝ ልትሆን ትችላለች። ይህም “ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በቤት ጣሪያ ላይ መኖር ይሻላል” የሚለውን ጥቅስ ሊያስታውሰን ይችላል። (ምሳሌ 25:24 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ይህን የመሰለ ሁኔታ ሲያጋጥም “ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው” ከሚለው የጳውሎስ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ትዕግሥት ማድረግ ያስፈልጋል። (ቆላስይስ 3:19) በተጨማሪም ባሎች የሚከተለውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር መከተሉ ትዕግሥት ይጠይቅባቸዋል፦ “እናንተ ባሎች ሆይ፣ [ለደካማ ዕቃ እንደምትጠነቀቁት አድርጋችሁ (አዓት)] ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል፣ አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:7) የሚስቱ ድካሞች አንዳንድ ጊዜ ባልን ይፈትኑት ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ትዕግሥት እነዚህን ችሎ ለመኖር ይረዳዋል።

9. ወላጆች ትዕግሥት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

9 ወላጆች ልጆቻቸውን በተሳካ ሁኔታ ለማሳደግ ከፈለጉ ትዕግሥት ያስፈልጋቸዋል። ልጆች ያንኑን ስሕተት አሁንም አሁንም እየደጋገሙ ሊሠሩት ይችላሉ። የነገሯቸውን ፈጽሞ የማይሰሙ ወይም ለመማር ዝግተኞች እንደሆኑ ሊመስሉ ይችላሉ። በዚህም የወላጆቻቸውን ትዕግሥት ያለ ማቋረጥ ሊፈትኑ ይችላሉ። እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ክርስትያን ወላጆች ለቁጣ የዘገዩ መሆን፣ መንፈሳቸውን ማረጋጋት፣ ሚዛናቸውን መጠበቅ እንጂ በቁጣ መገንፈል አይገባቸውም። ሆኖም ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥብቅ መሆን ይኖርባቸዋል። አባቶች በአንድ ወቅት እነርሱም ልጅ እንደነበሩና ስህተቶችን ይሠሩ እንደነበረ ማስታወስ አለባቸው። “አባቶች ሆይ፣ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” በማለት ጳውሎስ የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋቸዋል።​—ቆላስይስ 3:21

በውጭ ላሉት ሰዎች

10. በተቀጠርንበት የሥራ ቦታ እንዴት መመላለስ ይገባናል? ለዚህስ ምን ተሞክሮ ተጠቅሷል?

10 በሰብዓዊ አለፍጽምናና በራስ ወዳድነት ምክንያት አንድ ክርስትያን በሚሠራበት ቦታ ደስ የማይሉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በአነጋገር ሌላውን ላለማስቀየም ዘዴኛ መሆንና ስለ ሰላም ሲባል በደሎችን መቻል የጥበብ መንገድ ነው። ይህን ማድረጉ ምን ያህል ጥበብ እንደሆነ በአንድ ክርስቲያን ላይ የደረሰው ሁኔታ ዓይነተኛ ማስረጃ ነው። በእርሱ የቀና የሥራ ባልደረባው ብዙ ችግር ፈጠረበት። ወንድም በጉዳዩ ከመጨቃጨቅ ይልቅ ትዕግሥተኛ በመሆኑ ውሎ አድሮ ከዚህ ችግር ፈጣሪ ሠራተኛ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ችሏል።

11. ትዕግሥተኞች መሆን የሚያስፈልገን በተለይ መቼ ነው? ለምንስ?

11 የይሖዋ ሕዝቦች በተለይ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉት ሰዎች በሚመሰክሩበት ጊዜ ትዕግሥተኞች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ክርስትያኖች በየጊዜው አክብሮት የጐደለው ወይም ሻካራ መልስ ያጋጥማቸዋል። ታዲያ በተመሳሳይ መንገድ አጸፋ መመለሱ ተገቢና ጥሩ ይሆናልን? አይሆንም፤ ምክንያቱም ይህ ትዕግሥትን የሚያሳይ አይደለም። የጥበብ መንገድ የሚሆነው “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሻካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች” የሚለውን ምሳሌ ማስታወሱና መከተሉ ነው።​—ምሳሌ 15:1

እምነትና ተስፋ ትዕግሥት ለማሳየት ይረዳሉ

12, 13. የትኞቹ ጠባዮች ትዕግሥተኞች ለመሆን ይረዱናል?

12 ትዕግሥትን ለማሳየት፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቻል ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው? አንዱ ነገር በአምላክ ተስፋዎች ላይ እምነት ማድረግ ነው። አምላክን የተናገረውን ቃል ያለ ምንም መጠራጠር መቀበል ይገባናል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ፦ “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 10:13) በሌላ አባባል አንድ ለብዙ ዓመት በእውነት ውስጥ የቆየ ወንድም “አምላክ ከፈቀደው እችለዋለሁ ማለት ነው” ሲል እንደገለጸው ነው። አዎን፤ በትዕግሥት ፈተናውን ለመቋቋም እንችላለን።

13 ከእምነት ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው በአምላክ መንግሥት ላይ ተስፋ ማድረግ ነው። ይህ መንግሥት በምድር ላይ መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ ጭንቀት የሚፈጥሩብን መጥፎ ሁኔታዎች ሁሉ ይወገዳሉ። ይህን በተመለከተ መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና። ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ [ይሖዋን (አዓት)] ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።” (መዝሙር 37:8, 9) በቅርቡ አምላክ እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚያስወግድ ያለን እርግጠኛ ተስፋ ትዕግሥተኞች እንድንሆን ይረዳናል።

14. ለማያምን የትዳር ጓደኛ ትዕግሥት ማሳየት እንደሚገባን የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?

14 አንድ የማያምን የትዳር ጓደኛ ጭንቀት የሚፈጥርብን ቢሆን ምን ማድረግ አለብን? እርዳታ ለማግኘት ወደ አምላክ መመልከታችሁን ቀጥሉ፤ ተቃዋሚው አንድ ቀን ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ይሆናል ብላችሁ ተስፋ አድርጉ። አንድ ክርስቲያን ሚስቱ አንዳንድ ጊዜ ምግቡን ለማዘጋጀትና ልብሶቹን ለማጠብ እምቢ ትለው ነበር። ቀፋፊ ቃል ትናገረው ነበር፤ ለብዙ ቀኖችም አታነጋግረውም፣ በጥንቆላ ልታስደግምበትም ሞከረች። እርሱ እንዲህ ይላል፦ “ነገር ግን ሁል ጊዜ ወደ ይሖዋ በጸሎት እቀርብ ነበር፤ የክርስትያን ሚዛኔንም እንዳላጣ ጥሩውን የትዕግሥት ጠባይ ለማሳደግ እንዲረዳኝ በእርሱ እተማመን ነበር። በተጨማሪም አንድ ቀን የልቧ ዝንባሌ እንደሚለወጥ ተስፋ አደርግ ነበር።” ለ20 ዓመታት በዚህ ሁኔታ ከያዛት በኋላ ሚስቱ መለወጥ ጀመረች፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ትዕግሥትን እንድኮተኩት ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ፤ ምክንያቱም አሁን ውጤቱን ለማየት ችያለሁ። ሚስቴ በሕይወት መንገድ መጓዝ ጀምራለች!”

ጸሎት፣ ትሕትናና ፍቅር ይረዳሉ

15. ጸሎት ትዕግሥተኞች ለመሆን ሊረዳን የሚችለው ለምንድን ነው?

15 ትዕግሥትን ለማሳየት የሚረዳን ሌላው ትልቅ ነገር ጸሎት ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አሳስቦናል፦ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) በተጨማሪም “[ሸክምህን በይሖዋ (አዓት)] ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” የሚለውን ምክር አስታውስ።​—መዝሙር 55:22

16. ትዕግሥተኞች ለመሆን ትሕትና ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

16 የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ትዕግሥትን ለመኮትኮት የሚረዳን ሌላው ትልቅ እርዳታ ትሕትና ነው። የሚኰራ ሰው ትዕግሥት የለውም። በቀላሉ ይጎዳል፣ በቶሎ ይቆጣል፣ ምንም ዓይነት ችግር እንዲደርስበት አይፈልግም። ይህ ሁሉ የትዕግሥተኛነት ወይም የመቻል ተቃራኒ ነው። ትዕግሥተኛ ሰው ግን ስለ ክብሩ አይጨነቅም። ዳዊት በንጉሥ ሳኦል ሲሳደድና በቢንያማዊው ሳሚ ሲሰደብ እንዳደረገው ይህም ትሑት የሆነ ሰው ይሖዋን ይጠብቃል። (1 ሳሙኤል 24:4-6፤ 2 ሳሙኤል 16:5-13) ስለዚህ “በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ” ከሚለው ምክር ጋር ተስማምተን ለመሄድ መፈለግ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 4:2) ከዚህም በላይ ራሳችንን ‘በይሖዋ ፊት ማዋረድ’ ይገባናል።​—ያዕቆብ 4:10

17. ፍቅር ትዕግሥተኞች ለመሆን የሚረዳን ለምንድን ነው?

17 በተለይ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ትዕግሥተኞች እንድንሆን ይረዳናል። ፍቅር ለሌሎች ከልባችን ጥሩውን ነገር እንድንመኝላቸው ስለሚገፋፋን በእርግጥም “ፍቅር ይታገሣል።” (1 ቆሮንቶስ 13:4) ፍቅር ራሳችንን በሌሎች ቦታ አስቀምጠን ነገሮችን እንድንመለከት ይረዳናል። ከዚህም በላይ ፍቅር ትዕግሥተኞች እንድንሆን ይረዳናል፤ ምክንያቱም ፍቅር “ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር አይወድቅም።” (1 ቆሮንቶስ 13:7, 8) አዎን ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የመንግሥት መዝሙር ቁጥር 200 እንዳስቀመጠው፦

“ፍቅር መልካሙን የሚያዩ ዓይኖች አሉት፣

ፍቅር ወንድማማችነትን ይገነባል።

ፍቅር ለሚሳሳቱት ደግ ነው፣

ጥሩውን ጎናቸውን ለማግኘት ይፈልጋል”

በደስታ ታገሡ?

18. በደስታ ለመታገሥ የሚቻለው እንዴት ነው?

18 ጳውሎስ በቆላስይስ የነበሩትን የእምነት ጓደኞቹ ለይሖዋ እንደሚገባ ሆነው እንዲመላለሱ፣ እንዲያስደስቱትና በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እንዲያፈሩ በትክክለኛ የአምላክ ፈቃድ እውቀት እንዲሞሉ ጸልዮአል። በዚህም መንገድ “ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ” የበረቱ ይሆናሉ። (ቆላስይስ 1:9-11) አሁንም ቢሆን አንድ ሰው ‘በደስታ ሊታገሥ’ የሚችለው እንዴት ነው? ይህ እርስ በርሱ የሚቃረን ሐሳብ አይደለም፤ ምክንያቱም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሰው ደስታ እንዲሁ ላይ ላዩን መፍለቅለቅ ማለት አይደለም። የመንፈስ ፍሬ የሆነው ደስታ በአምላክ ፊት ትክክለኛውን ነገር ከማድረግ የሚመጣውን ጥልቅ የእርካታ ስሜትን ይጨምራል። በተጨማሪም አንድ ሰው ትዕግሥት በማሳየቱ ከአምላክ ሽልማት አገኛለሁ ለሚለው ተስፋው መግለጫ ነው። ኢየሱስ እንደሚከተለው ያለው ለዚህ ነው፦ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን [ደስተኞች] ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሐሴትንም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።”​—ማቴዎስ 5:11, 12

19. ትዕግሥተኛም ደስተኛም መሆን እንደሚቻል የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ?

19 ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱ ደስታ ነበረው። ‘እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱ ስላለው ደስታ በመስቀል [በመከራ እንጨት (አዓት)] ታግሦአል።’ (ዕብራውያን 12:2) ይህ ደስታ ኢየሱስ ታጋሽ እንዲሆን አስችሎታል። በተመሣሣይም ሐዋርያት ተገርፈው ‘በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ’ በታዘዙበት ጊዜ ምን እንደሆነ አስታውሱ። “እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር።” (ሥራ 5:40-42) ይህ የክርስቶስ ተከታዮች በደስታ መታገሥ እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ ነው!

20. ትዕግሥት የምናሳይ ከሆነ ይህ ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና የሚነካው እንዴት ነው?

20 በእርግጥም የአምላክ ቃል እንዳንበቀል፣ ሁኔታው ይሻሻላል ብለን ተስፋ በማድረግ ለቁጣ የዘገየን እንድንሆን፤ አዎን ትዕግስተኞች እንድንሆን የሚሰጠን ምክር በእርግጥ ጥሩ ነው። በጉባኤው ውስጥ ካሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በቤተሰብ ክልል ውስጥ ካሉት፣ በሥራ ቦታችን ካሉት ሰዎች፣ እንዲሁም በክርስትያን አገልግሎታችን ከምናገኛቸው ግለሰቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ዘወትር መጸለይና ይህን የአምላክ መንፈስ ፍሬ ማሳየት ያስፈልገናል። ትዕግሥት ለማሳየት ሊረዱን የሚችሉትስ ነገሮች ምንድን ናቸው? እምነት፣ ተስፋ፣ ትህትና፣ ደስታና ፍቅር ናቸው። በእርግጥም እነዚህ ጠባዮች ካሉን ሰውን ሁሉ መታገሥ እንችላለን።

ታስታውሳለህን?

◻ ከመንፈሳዊ ገነት ተካፋዮች እንድንሆን ትዕግሥት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

◻ በተለይ ሽማግሌዎች ትዕግሥተኞች መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

◻ ባሎችና ሚስቶች ትዕግሥትን መኮትኮት የሚገባቸው ለምንድን ነው?

◻ የትኞቹ ሌሎች ጠባዮች ትዕግሥተኞች ለመሆን ይረዱናል?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ ትዕግሥተኛ እንዲሆን የረዳው ከኢየሱስ ያገኘው ምን ምክር ነበር?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ