መጽሐፍ ቅዱስ—ከአምላክ የመጣ ነውን?
ገደብ የሌለው ኃይልና ሥልጣን ባለቤት የሆነው አምላክ ይሖዋ ከሰብዓዊው ፍጥረቱ ጋር እርሱ በፈለገው መንገድ ለመገናኘት የማያጠያይቅ መብት አለው። በጽሑፍ በሠፈረ ቃል ግንኙነት ለማድረግ ከመረጠ መልዕክቱን በዘመናት ሁሉ ጠብቆ ማቆየት ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ነገሩ እንደዚህ ሆኖአልን?
ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ1,500 ዓመታት ገደማ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ በጀመረበት ጊዜ ሌሎች ብዙ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ነበሩ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ከአገልግሎት ውጭ እየሆኑ ሄደው በመጨረሻው ጠፉ። አንዳንዶቹም በአርኪዮሎጂስቶች በመሬት ቁፋሮ ከወጡ በኋላ በቤተ መዘክሮች ውስጥ የሚታዩ የሰው የእጅ ሥራ ናሙና ሆነዋል። በሌላው በኩል ግን ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በፍጹም አልተረሱም። ቅጂዎቻቸውም እስከ ዘመናችን ድረስ ቆይተዋል። በተለይ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የደረሰውን ጥላቻ ስናስብ ይህ የሚያስደንቅ ነው። ይህንን ያህል ከፍተኛ ተቃውሞና ጥላቻ ያጋጠመው ሌላ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ወይም ለሌላ ማስተላለፍ በገንዘብ፣ በእስራት፣ በማሰቃየትና ብዙውን ጊዜም በሞት የሚያስቀጣ ነበር።
አንድ ተራ መጽሐፍ እንደዚህ ካሉት ሁኔታዎች ሁሉ አምልጦ እንዴት እስከ ዛሬ ድረስ ለመኖር ቻለ? ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ “[የይሖዋ (አዓት)] ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት መልሱን ይነግረናል። (1 ጴጥሮስ 1:25) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ መጽናቱና ለመጥፋት አለመቻሉ ቅዱሱ የአምላክ ቃል እርሱ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል።
በተጨማሪም አምላክ ለሰው ዘር በሙሉ እንዲተላለፍ ያዘጋጀው መልዕክት በዓለም በሙሉ ይዳረሳል ብለን መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታ እንደዚያ ነውን? በእርግጥ ነው! በዚህ በኩል በታሪክ ውስጥ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠጋ ምንም መጽሐፍ የለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ወደ 3,000,000,000 ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተገምቷል። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ ሌላ መጽሐፍ የለም። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉው ወይም በከፊል ከ1,900 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች ሊነበብ ይችላል። የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ 98 ከመቶ ለሚሆነው የዓለም ሕዝብ ሊደርስ እንደቻለ ይገልጻል። አዲሱ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ መጽሐፍ ቅዱስን “በሰው ታሪክ ሰውን በመሳብ ተወዳዳሪ የሌለው የመጻሕፍት ስብስብ ሳይሆን አይቀርም” ብሎታል። በዚህ ምክንያት በምድር ላይ ካሉት መጻሕፍት ሁሉ ታላቁ መጽሐፍ ተብሎ ቢገለጽ አግባብነት የሌለው አይደለም።
ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን የሚያሳይ ኃይለኛ ማስረጃ ነው። በተለያየ ጊዜ የኖሩ 40 ግለሰቦች 1,600 ዓመታት በፈጀ ጊዜ የጻፏቸው ጽሑፎች እርስ በርስ የሚስማሙና መሠረታዊ የሆነ አንድ አጠቃላይ መልዕክት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ይሆናልን? ይህ ለአጋጣሚ ወይም ለተራ ሰው አመራር ብቻ የተተወ ቢሆን ኖሮ የማይቻል ነገር ይሆን ነበር። ሆኖም አንድ ላይ ተሰባስበው መጽሐፍ ቅዱስ የሆኑትን 66 መጻሕፍት በተመለከተ ይህ ነገር እውነት ሆኗል። እንደዚህ ያለውን አስደናቂ ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው ለረጅም ጊዜ የኖረ አእምሮ ያለው ከሰው በላይ የሆነ አንድ አካል ብቻ ነው።
ታሪክ ብቻ አይደለም
መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው ታሪኮች አስደናቂ ናቸው። ሆኖም ከአምላክ የመጣልን መልዕክት የታሪክ መዝገብ ብቻ ቢሆን ኖሮ ለእኛ የሚኖረው ጠቀሜታ የተወሰነ ይሆን ነበር። መመሪያና ተግባራዊ ጥበብ ያስፈልገናል። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊገኝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የዋሃትንና ራስን መግዛትን’ እንድንኮተኩት ያበረታታናል። ስለነዚህ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ ብዙ ነገር ተጽፎአል። (ገላትያ 5:22, 23፤ ቆላስይስ 3:12-14) መጽሐፍ ቅዱስ ታታሪነትን፣ ንጽህናን፣ ሐቀኝነትን፣ ለጋብቻ ታማኝ መሆንን፣ ለሌሎች ሰዎች አክብሮትንና ፍቅርን ማሳየትን ያበረታታል። በቤተሰብ ውስጥና በኅብረተሰቡ መሃል ሊኖር ስለሚገባው ጠባይም ሰፊ የሆነ የምክር ሃብት ይዟል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ በእውነት ጠቃሚ በመሆኑ ሊወዳደረው የሚችል ምንም ነገር የለም። ከድንቁርናና ከአጉል እምነት ነፃ ያደርገናል። (ዮሐንስ 8:32) የያዘው ተግባራዊ መሆን የሚችለው ጥበብም ተወዳዳሪ የለውም። በእርግጥም መለኮታዊ ጥበብ የያዘ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።
“የአምላክ ቃል ሕያው የሆነና የሚገፋፋ ኃይል ያለው ነው” የሚለው አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን በእርግጥ የሚለውጥ ከመሆኑ ሐቅ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። (ዕብራውያን 4:12 አዓት) ባሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ከልብ በመቀበላቸው ጎጂ ጠባዮችን አሸንፈዋል፤ አፍራሽ የነበረውንም የቀድሞ አኗኗራቸውን በመልካም አኗኗር ለውጠዋል።—ኤፌሶን 4:22
የመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ችላ ሲባሉ ውጤቱ ምን ይሆናል? ውጤቱ ኀዘንና ሥቃይ፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችና የፈራረሱ ቤተሰቦች ናቸው። ሊጠበቁ የሚችሉት እንደነዚህ ያሉት ነገሮች ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን መናቅ ማለት ሰውን የፈጠረውንና ፍላጎቱን የሚያውቅለትን የአምላክን አመራር አለመቀበል ማለት ነው።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጪው ጊዜም ይተነብያል። ይህ ደግሞ ሰዎች ሊያደርጉት የማይችሉት ነገር ነው። ከባቢሎን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ በነበሩት ብዙ መቶ ዘመናት ውስጥ የተነሡት የዓለም ኃይላት መፈራረቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት ተነግሮ ነበር። (ዳንኤል ምዕራፍ 2, 7, 8) በተጨማሪም ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የሚኖሩት ሁኔታዎች ትክክለኛ ዝርዝር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጨምሯል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24, 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ራእይ 6:1-8) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸው በገጾቹ ላይ ተመዝግበው ያሉት ስለ አስደሳች የወደፊት ጊዜ የሚገልጹት ተስፋዎችም እውነተኞች እንደሆኑ ያረጋግጥልናል።
የእኛ ኃላፊነት
ይህ ሁሉ አምላክ በእርግጥ ለሰዎች መልዕክት ማስተላለፉን የሚያሳይ የማያወላውል ማስረጃ ነው። እውነት ነው፤ አምላክ መልዕክቱን ያስተላለፈው ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች እጅ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን አምላክ በአፉ እየተናገረ ቢያስጽፈው ወይም በመላእክት እጅ የተሰጠ ወይም በሰማይ በተአምራዊ መንገድ ተጽፎ በምድር ላይ ላሉ ሰዎች በእጅ ቢሰጥ ኖሮ የበለጠ እውነተኛ ይሆን ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያት አይሆንም።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱስና መለኰታዊ ምንጭ አለው ብለን መቀበላችን ኃላፊነት ይጥልብናል። ይሖዋ ቃሉን አዘውትረን እንድናነበው ይጠብቅብናል። ደግሞም ትክክል ነው። (መዝሙር 1:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስን ፍሬያማ በሆነ መንገድ ለማንበብ ትክክለኛ ዝንባሌ መያዝ ያስፈልጋል። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንደማንኛውም ስነ ጽሑፍ ተቆጥሮ ሊነበብ እንደማይገባ በአእምሮው መያዝ አለበት። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ሲቀርብ “እንደ ሰው ቃል ሳይሆን በእውነት እንዳለ እንደ እግዚአብሔር ቃል” አድርጎ መመልከት ይኖርበታል።—1 ተሰሎንቄ 2:13
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነገሮች ለመረዳት አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አዘውትሮ በማንበብ አንድ ሰው የመረዳት ችሎታው እያደገ ይሄዳል፤ የአምላክ ፈቃድና ዓላማ በይበልጥ ይገባዋል። (ዕብራውያን 5:14) ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ገና አላመንክም ይሆናል። ታዲያ እውነት ለመናገር በጥንቃቄ ሳታጠናው አምኛለሁ ወይም አላመንኩም ማለት እንዴት ትችላለህ?
መለኰታዊ አመጣጥ ያለው ስለመሆኑ የዘመኑ ጥርጣሬ ቢኖርም አስተዋይ የሆኑ ብዙ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ መመርመር በሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት “ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን”በማለት እንዲያስተጋቡ አድርጓቸዋል።—ሮሜ 3:4
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ግራፍ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ባሁኑ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ 98 በመቶ የሚሆነው መጽሐፍ ቅዱስን አግኝቶ ማንበብ ይችላል
መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ድረስ 3,000,000,000 ቅጂ እንደታተመ ይገመታል። በታሪክ ውስጥ ወደዚህ ቁጥር የሚጠጋ ሌላ መጽሐፍ የለም። አዲሱ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ “በታሪክ ውስጥ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ ሰውን የሳበ የመጻሕፍት ስብስብ” ብሎ ይጠራዋል
[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች እንደ ቅርስ ተቆጥረው በየሙዚየሙ ሲጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ ቦታውን ሳይለቅ ቆይቷል
ላይኛው፦ ስለ ውኃ ጥፋት የሚናገር የአሦራውያን ጽሑፍ ነው
በስተቀኝ በኩል ያለው፦ ራ ለተባለው የግብጻውያን አምላክ የቀረበ ጸሎት ነው
[ምንጭ]
Both: Courtesy of the Trustees of The British Museum
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
1,600 ዓመታት በሚያህል ጊዜ በ40 የተለያዩ ግለሰቦች የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ አንድ አጠቃላይ መልዕክት ብቻ ይከተላል። እንደዚህ ያለ አስደናቂ ጽሑፍ ማውጣት የሚችለው ከሰው በላይ የሆነና ለረጅም ዘመን የኖረ አምላክ ብቻ ነው
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባቢሎን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ባለፉት መቶ ዘመናት የትኞቹ የዓለም ኃይላት እንደሚነሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት ተገልጾ ነበር (ዳንኤል ምዕራፍ 2፣ 7፣ 8)
በስተቀኝ በኩል ያለው፦ አውጎስቶስ ቄሣር ነው
[ምንጭ]
ሙዜዮ ዴላ ቺቪታ ሮማና፤ ሮማ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ የሚኖረውን ሁኔታ አስቀድሞ ተንብዮ ነበር። (ማቴዎስ 24፣ 25፤ ማርቆስ 13፤ ሉቃስ 21፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ራእይ 6:1-8) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምንም ሳይሳሳት መፈጸሙ ምድር ገነት ትሆናለች ሲል አምላክ የሰጠው ተስፋ በእርግጥ እንደሚፈጸም ያረጋግጥልናል
[ምንጭ]
Reuters/Bettmann Newsphotos