ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
“ኢየሱስ አምላክ የጠየቀውን ሁሉ ጨረሰ” የሚለው በተከታዮቹ ገጾች ላይ የሠፈረው ርዕሰ ትምህርት “ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ” በሚል አርዕስት ለረጅም ጊዜ በተከታታይ ሲወጡ ለነበሩት የመጨረሻው ይሆናል። ይህ ተከታታይ አርዕስት ከሚያዝያ 1, 1985 ዕትም አንስቶ በ149 ተከታታይ ዕትሞች ላይ በመጠበቂያ ግንብ ለስድስት ዓመታት ሲወጣ ቆይቷል።
ይህ የመጠበቂያ ግንብ ተከታታይ ትምህርት ሐዋርያው ጳውሎስ “ኢየሱስን አተኩረን እንድንመለከት” የሰጠውን ምክር እንድትከተሉና “እርሱን ስሙት” ሲል ያዘዘውን የአምላክን ትዕዛዝ ልብ እንድትሉ እንደረዳችሁ ተስፋ አለን። (ዕብራውያን 12:2, 3፤ ማቴዎስ 17:5) ባለፉት ዓመታት በዚህ ረገድ እርዳታ አግኝተናል በማለት ብዙዎች ጽፈውልናል። አንድ አንባቢ “ልክ እርሱን እያዳመጥኩ እንዳለሁና የሚሠራውን ሁሉ እየተመለከትኩ እንዳለሁ ያህል ነው” በማለት ጽፎአል። “በእነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች የተነሣ በይበልጥ ላፈቅረው ችያለሁ።”
ሌላ አንባቢ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “እያንዳንዱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ያለፍኩትን (ያላስተዋልኩትን) አንድ ነጥብ የሚይዝ ይመስላል። እያንዳንዱን ርዕሰ ትምህርት በማንበብ በኢየሱስ ሕይወት የተፈጸሙ የተለያዩ ድርጊቶችን በቅደም ተከተል አፈጻጸማቸው በተሻለ ልረዳ በመቻሌ ተደስቻለሁ።” ብዙዎች ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት መቼና የት ምን እንዳስተማረና እንዳደረገ በመማራቸው ተመሳሳይ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በስፔይን የምትኖር አንዲት ሴት እንዲህ አለች፦ “ርዕሰ ትምህርቶቹን በሙሉ ከመጀመሪያው ጀምሬ አስቀምጫቸዋለሁ። ለአዋቂዎችም ሆነ ለልጆች በጣም ትምህርት አዘል ናቸው። ዕድሜዬ 44 ዓመት ነው። እነዚህን ታሪኮች ሳነብ በደስታ እዋጣለሁ። በእያንዳንዱ ታሪካዊ ድርጊት ወቅት እንደነበርኩ ያህል ነው።”
ከዩናይትድ ስቴትስ አንዲት እናት ስትጽፍ “በርዕሰ ትምህርቶቹ አጭርነትና ቀላል አገላለጽ ምክንያት ባሌም በቤተሰብ ጥናታችን አብሮ መካፈል ጀመረ። የስምንት ዓመት ልጄ አባቱ አሁን መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያጠና ምስጋናዬን እንድገልጽላችሁ ጠየቀኝ። እነዚህን ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶች ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ ማካፈል እንዲችል በመጨረሻው ላይ በመጽሐፍ እንዲታተም ጠይቆኛል” ብላለች።
ምናልባት በቅርቡ እንደሚከተለው በማለት ኀዘኑን እንደገለጸው ሰው ያለ ስሜት ይኖራችሁ ይሆናል፦ “አሁን እየቀረቡ ያሉት የኢየሱስ ሕይወት የመጨረሻዎቹ ቀኖች ስለሆኑ ይህ ተከታታይ ትምህርት በቅርቡ ማብቃቱ ነው ብዬ አዝኛለሁ። በመጠበቂያ ግንብ ውስጥ በቦታቸው ሳጣቸው በእውነት አዝናለሁ። ወደፊት መጠበቂያ ግንብ ላይ ሳጣቸው በጣም ይሰማኛል።” በዚህ “ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ” በሚል ርዕስ በተከታታይ ሲወጡ ለቆዩት ትምህርቶች የመጨረሻ የሆነውን ቀጥሎ ያለውን ርዕሰ ትምህርት በማንበብ እንደምትደሰቱ ተስፋ እናደርጋለን።