በቅርቡ በሽታ ወይም ሞት አይኖርም!
በመታመሙ የሚደሰት ማንም ሰው የለም፤ ወይም ሰዎች ለመሞት አይፈልጉም። አንድ የሕክምና ሶሺዮሎጂ ፕሮፌሰር እንዲህ በማለት አረጋግጠዋል፦ “ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚደረገው ምርመራ ዓለም አቀፋዊ ባሕርይ ያለውና በአብዛኞቹ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚገኝ ነው። መሠረታዊ ከሆነው ራስን የመጠበቅ ግፊት ጋር ዝምድና ያለው ነው። . . . ፖንስ ዴሊዮን ረጅም ዕድሜን በመፈለግ ሕይወታቸውን ካሳለፉ ከብዙ ሰዎች ውስጥ አንዱ በጣም ዝነኛ ሰው ነው። አብዛኛው የሕክምና ሳይንስ በሽታንና ሞትን በመዋጋት ረጅም ዕድሜን ለመስጠት ባለው ዓላማ የተወሰነ ነው።”
ሞት ወዳጆችንና የቤተሰብ አባሎችን ሲወስድ የውስጣዊ ተፈጥሮአችን ስሜት በጣም ስለሚጐዳብን በተፈጥሮ የሚያስከትለውን ውጤት ለመደበቅና ራሳችንን ለማጽናናት እንሞክራለን። በመላው ዓለም ያሉ የቀብር ሥርዓቶች የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በጣም ኋላ ቀር የሚባሉትም ይሁኑ በሥልጣኔ የመጠቁ ናቸው የሚባሉት የሞቱትን አባሎቹ በሥርዓት የማይቀብር ማኅበረሰብ በፍጹም አይገኝም። . . . እንደዚያ ማድረጉ ጥልቅ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ ግፊቶችን ያረካል። ይህንን መፈጸሙ እንደ ‘ትክክል’ ተደርጎ ይታያል፤ ይህንን አለመፈጸሙ ደግሞ በተለይ በቤተሰብ፣ በስሜት፣ በኑሮ፣ በጋራ ተሞክሮ ወይም በሌሎች ዝምድናዎች በቅርብ ለተሳሰሩት ‘ስህተት’ የሆነ፣ ከተፈጥሮ ውጭ በመሆኑ የተተወ፣ ይቅርታ ሊጠየቅበት ወይም ሊታፈርበት እንደሚገባ ነገር ተደርጎ ይታያል። . . . [ሰው] ሙታኑን በአንድ ዓይነት ሥርዓት የሚቀብር ፍጡር ነው።”
የበሽታና የሞት አመጣጥ
ስለዚህ በሽታና ሞት አንድ ቀን ይወገዳሉ የሚለው ሐሳብ በኃይል ይማርካል፤ ይሁን እንጂ እንደዚህ ብሎ ለማመን መሠረት አለን? በእርግጥም አለ፤ ይህ መሠረት ምክንያታዊ፣ ትምክህት የሚጣልበትና የማይዋሽ ነው። ይህም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የፈጣሪያችን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ይህ መጽሐፍ በሰው ላይ መከራ እንዴት እንደመጣ በግልጽ ይናገራል። የመጀመሪያው ሰው አዳም በአምላክ እንደተፈጠረና በመካከለኛው ምሥራቅ በአንድ ቦታ ላይ ትገኝ በነበረች ገነታዊ መኖሪያ ውስጥ እንደተቀመጠ ይነግረናል። አዳም ፍጹም ሆኖ ተፈጠረ፤ በሽታንና ሞትን አያውቃቸውም ነበር። ብዙም ሳይቆይ እንደ እርሱ ፍጹም የሆነች ሚስት የኑሮ ተባባሪው ሆነች፤ እነርሱም በአንድ ላይ ሆነው በምድር ላይ በተሰጣቸው የዘላለም ሕይወት ዝግጅት ይደሰቱ ነበር።—ዘፍጥረት 2:15-17, 21-24
ይህ ተስማሚ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ አልቆየም። ለምን? ምክንያቱም አዳም ራስ ወዳድ በመሆን ከአምላክ ውጭ ራሱ የሚወስነው የሕይወት መንገድ ስለመረጠ ነው። ውጤቱም ለፍቶ ማደር፣ ሥቃይ፣ በሽታ፣ በመጨረሻም ሞት ሆነ። (ዘፍጥረት 3:17-19) ዘሮቹም አዳም የመረጠውን አሳዛኝ አኗኗር ወረሱ። ሮሜ 5:12 “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ይገልጻል። ሮሜ 8:22ም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” የሚል ሐሳብ ይጨምራል።
በምድር ላይ ወይስ በሰማይ?
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ ታዛዥ የሆነውን የሰው ዘር አዳምና ሔዋን ወዳጡት አስደሳች ሁኔታ እንደሚመልስ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ራእይ 21:3, 4 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት ሁሉ አልፎአልና።” አንድ ጥንታዊ ነቢይም በተመሳሳይ “በዚያ የሚቀመጥ ታምሜያለሁ” የማይልበት ዘመን እንደሚመጣ አስቀድሞ አይቶ ነበር።—ኢሳይያስ 33:24
ሆስፒታሎች፣ የሬሣ ማቆያ ቦታዎችና መቃብሮች የሌሉበትን ዓለም በዓይነ ኅሊናህ ለመመልከት ትችላለህን? ከሥቃይና ከሞት ሥጋትም ጭምር ተገላግለህ ለሁልጊዜ መኖር እንደሚቻል ልታስብ ትችላለህን? አዎን አምላክ የገባልን ቃል በሁላችንም ውስጥ ያሉትን ጥልቅ ስሜቶች የሚነካ ነው። ይሁንና ይህ አስደናቂ ተስፋ በሰማይ ሳይሆን በፕላኔትዋ ምድራችን ላይ የሚፈጸም ስለ መሆኑ እንዴት እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን? ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ፊትና ኋላ ያሉትን ሐሳቦች ተመልከት። የራእይ ምዕራፍ 21 የመጀመሪያ ቁጥር ስለ ‘አዲስ ሰማይና ስለ አዲስ ምድር’ ይናገራል። አምላክ ከሰዎች ጋር እንደሚሆንና እነርሱም ሕዝቡ እንደሚሆኑ ግልጽ ሐሳብ ቀርቧል። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኘው ተስፋ ቀጥሎ ‘ኃጢአታቸው ይቅር ስለሚባልላቸው’ ‘በምድሪቱ ስለሚቀመጡ’ ሰዎች ተገልጿል።
ስለዚህ እነዚህ የሚያበረታቱ ተስፋዎች በምድር ላይ የሚኖረውን ሕይወት ያመለክታሉ! “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ኢየሱስ ለአባቱ ካቀረበው ጸሎት ጋርም ይስማማሉ።—ማቴዎስ 6:10
በቅርቡ የምንለው ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምስክሮች እነዚህ ተስፋዎች በቅርቡ የሚፈጸሙ መሆናቸውን እንዲያውቁ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ረድተዋል። ሆኖም ስለዚህ ነገር እርግጠኞች ለመሆን የቻሉት በምን መሠረት ነው? አሁን በምድር ላይ ባለው የነገሮች ሥርዓት ወይም ዝግጅት “የመጨረሻ ቀኖች” ውስጥ መኖራችንን በሚያሳውቀው ከፍተኛ ማስረጃ መሠረት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የኢየሱስ ደቀመዛሙርት የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ መቼ መሆኑን የሚያሳውቅ ምልክት እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር። ኢየሱስ መልስ ሲሰጥ አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ከፈነዳ ወዲህ የደረሱትን እየተባባሱ የሄዱ የዓለም ሁኔታዎች በዝርዝር ተናገረ።a ከዚያም ጨምሮ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።” ስለዚህ በ1914 ከነበረው ትውልድ መካከል የአሁኑ የዓለም ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት ቆይተው የሚያዩ ይኖራሉ።—ማቴዎስ 24:33, 34
በዚያን ጊዜ ይሖዋ አምላክ ልጁን ክርስቶስ ኢየሱስን ሄዶ ከዚህች ውብ ፕላኔት ምድር ገጽ ላይ የመከራንና የሥቃይን ሁሉ ምንጭ እንዲያጠፋ ያዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የክፋትን መወገድ በአርማጌዶን የሚሆን “ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” በማለት ይናገርለታል።—ራእይ 16:14, 16
ብዙ ቁጥር ያላቸው አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ከዚህ አስፈሪ ሁኔታ ድነው ሰላማዊው የክርስቶስ ኢየሱስ ግዛት ሲጀምር ይመለከታሉ። (ራእይ 7:9, 14፤ 20:4) እርሱ የሚገዛው ከሰማይ ቢሆንም ጠቃሚ የሆኑትን የአገዛዙ ውጤቶች በምድር ላይ የሚኖሩት በሙሉ ይኸውም የአርማጌዶን ጦርነት ተራፊዎችና በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ በኋላ ከሞት የሚነሱ ሰዎች ያገኙአቸዋል። በዚያን ጊዜ የሚከተለው ተስፋ እውን ይሆናል፦ “[ክርስቶስ] ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:25, 26
ስለዚህ በትምክህት “በቅርቡ በሽታና ሞት አይኖሩም!” ብለን በደስታ ለመናገር እንችላለን። ይህ ሕልም ወይም ምኞት የወለደው አሳብ አይደለም። “ሊዋሽ የማይችለው” ይሖዋ አምላክ የሰጠው የተረጋገጠ ተስፋ ነው። በዚህ ተስፋ ላይ እምነት ለማድረግ ፈቃደኛ ትሆናለህን? ለዘላለም ሊጠቅምህ ይችላል!—ቲቶ 1:2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሰው ልጅ በመጨረሻዎቹ ቀኖች እንደሚኖር ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር የተጻፈውን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 18 ተመልከቱ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ በሽታና ሞት በፍጹም ጤንነትና በዘላለም ሕይወት ይተካሉ