ዋጋ ሊተመንለት የማይቻለውን የአምላክን ዕንቁ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር!
በ1867 ሻልክ ቫን ናይከርክ የተባለ አንድ የደቡብ አፍሪካ ገበሬ ልጆች በድንጋይ ሲጫወቱ ተመለከተ። በተለይ አንድ የተለየና ደማቅ የሆነ የሚያምር ድንጋይ ትኩረቱን ሳበው። የልጆቹም እናት “ከፈለግኸው ልትወስደው ትችላለህ” አለችው። ቫን ናይከርክም ድንጋዩን የማዕድን አዋቂዎች እንዲመረምሩት ላከው። ልጆቹ 500 የእንግሊዝ ፓውንድ የሚያወጣ ዋጋ ባለው አንድ ትልቅ አልማዝ እየተጫወቱ እንደነበሩ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም!
አንተስ ሳታውቀው ዋጋ ሊተመንለት የማይቻል ዕንቁ ይኖርህ ይሆን? ለምሳሌ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው፤ ምክንያቱም በሙሉ ወይም በከፊል ከ1,900 ቋንቋዎች በላይ ይገኛል። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አላነበቡትም፤ ስለሆነም ምን ሐሳብ እንደያዘ አያውቁም።
መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት’ እንደተጻፈና የአምላክ ቃል እንደሆነ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ ከ1 ተሰሎንቄ 2:13 ጋር አወዳድር) የሰው ዘር ካለው ሐብት ሁሉ የበለጠ ውድ ሐብት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በእርሱም አማካኝነት የአሁኑን ሕይወታችን እንዴት ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት እንደምንችል፤ ከዚህም በላይ እንዴት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንደምንችል እንማራለን። (ዮሐንስ 17:3, 17) ከዚህ የበለጠ ውድ ዋጋ ያለው ነገር ሊኖር ይችላልን?
ሆኖም ይህንን የከበረ ድንጋይና ገጽታዎቹን በሙሉ ተረድቶ ለማድነቅ በመጀመሪያ ምንነቱን ማወቅ ያስፈልጋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ገለጥ አድርጎ ማየቱ በጣም አስቸጋሪ ሊያስመስለው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የ66 የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ነው። እነዚህ መጻሕፍት ምን ይዘዋል? በአሁኑ ጊዜ ያላቸው ቅደም ተከተል እንዲይዙ የተደረገበት ምክንያት ይኖራልን? ከሆነስ አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝን አንድን የተለየ ምንባብ እንዴት ማውጣት ይችላል?
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቁ ትግልን የሚጠይቅ ነው። ይሁን እንጂ ልክ እንደ እውነተኛው ዕንቁ መጽሐፍ ቅዱስም ቅርጽና ሥርዓት አለው። ይዘቱን ባጭሩ ብንመረምር ይህንን ለመመልከት እንችላለን።
ወደ ክርስቶስ የሚያመለክቱ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች
ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ብሉይ ኪዳን” እና “አዲስ ኪዳን” በመባል ይከፈላል። ሆኖም እነዚህ አባባሎች “አሮጌው ኪዳን” ጊዜ እንዳለፈበትና ዋጋ እንደሌለው ስለሚያስመስሉ የተሳሳቱ መጠሪያ ናቸው። ይኸኛው ክፍል በመጀመሪያ በአብዛኛው በዕብራይስጥ ቋንቋ ስለተጻፈ ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው ስም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚለው ነው። “አዲስ ኪዳን” የተጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን በግሪክኛ ቋንቋ ነው። ስለዚህ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ተብሎ ቢጠራ ተገቢ ይሆናል።
የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ዘፍጥረት አምላክ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረባቸው ከእልፍ አእላፋት ዓመታት ይጀምርና ምድርን ለሰው መኖሪያነት እንዳዘጋጀ ይገልጻል። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ባልና ሚስት ፍጹም ሆነው ተፈጥረው ነበር። ይሁን እንጂ የኃጢአትን መንገድ መረጡ፤ ይህም በዘሮቻቸው ላይ አሳዛኝ ውጤቶችን አስከተለ። ሆኖም በጨለማ ውስጥ እንደሚያበራ ዕንቁ መጽሐፍ ቅዱስ በኃጢአት ውስጥ ለወደቀው የሰው ዘር የተስፋ ብርሃን ይፈነጥቃል። ይህም ተስፋ ኃጢአትና ሞት የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች በመጨረሻ ስለሚያጠፋ “ዘር” ይናገራል። (ዘፍጥረት 3:15) ይህ ዘር ማን ይሆን? የዘፍጥረት መጽሐፍ እንደ አብርሃም እንደ ይስሐቅና ያዕቆብ ባሉት የዘሩ ታማኝ የቀድሞ አባቶች ላይ በማተኮር ሊመጣ ያለውን የዚህን ዘር መሥመር ማመልከት ይጀምራል።
የዘፀዓት መጽሐፍም ቀጥሎ ስለ ሙሴ መወለድ ይገልጻል። የሙሴ ሕይወት በብዙ መንገዶች ለሚመጣው ዘር ጥላ የሚሆን ነበር። አሥር መቅሰፍቶች ከደረሱ በኋላ እስራኤላውያን ከግብጽ በመነሳት ከፍተኛ ጉዞ ካደረጉ በኋላ በሲና ተራራ የአምላክ የተመረጠ ሕዝብ ሆነው ተቋቋሙ። ዘሌዋውያን ስሙ እንደሚያመለክተው በእስራኤል ውስጥ አምላክ ስለ ሌዋዊው ክህነት ያወጣቸውን ሕጎች ይገልጻል። ዘኁልቁም እስራኤላውያን (በሕዝብ ቆጠራ) ስለተቆጠሩበት ጊዜና እስራኤላውያን በምድረ በዳ በቆዩበት ጊዜ ስለተፈጸሙት ሁኔታዎች ይነግረናል። አሁን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ሲቃረቡ ሙሴ ለእስራኤላውያን የመጨረሻውን ምክር ሰጣቸው። የዘዳግም መጽሐፍ የያዘው ይህንን ጉዳይ ነው። ሙሴ ሊመጣ ወዳለው ዘር በማመልከት ሕዝቡ ‘አምላክ የሚያስነሳውን ነቢይ’ እንዲሰሙ አሳሰባቸው።—ዘዳግም 18:15
ከዚህ በኋላ ታሪክ የያዙት መጻሕፍት ይቀጥላሉ። እነዚህም በአብዛኛው ታሪኩ የተፈጸመበትን የዘመናት ቅደም ተከተል የያዙ ናቸው። የኢያሱ መጽሐፍ የተስፋይቱ ምድር በድል ስለመያዟና ለነገዶች ስለ መከፋፈልዋ ይገልጻል። መሳፍንትም ከዚያ በኋላ ባሉት ቀጣይ ዓመታት እስራኤል በተከታታይ በመሳፍንት ስትገዛ የተከናወኑትን አስደናቂ ታሪኮች ይገልጻል። የሩት መጽሐፍም በመሳፍንት ዘመን ትኖር ስለነበረችና የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆን መብት ስላገኘች አምላክን የምትፈራ ሴት ይነግረናል።
ሆኖም መሳፍንት የገዙበት ዘመን ከጊዜ በኋላ አበቃ። አንደኛ ሳሙኤል የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ የሆነው ሳኦል በነቢዩ ሳሙኤል ዓይን ሲታይ ስለገዛበት አስከፊ አገዛዝ ይናገራል። ሁለተኛ ሳሙኤል ደግሞ በሳኦል ምትክ ስለነገሠው ስለ ዳዊት የተሳካ የግዛት ዘመን ያብራራል። አንደኛ እና ሁለተኛ ነገሥትም ከክብራማው የሰለሞን የግዛት ዘመን ጀምሮ የእስራኤል ሕዝብ በ607 ከዘአበ በአሳዛኝ ሁኔታ ወደ ባቢሎን ተማርከው እስከሄዱበት ጊዜ ያደርሰናል። አንደኛ እና ሁለተኛ ዜና መዋዕልም ይህን ታሪክ ከምርኮ ከተመለሰው ሕዝብ አንፃር በማየት ያንኑን ታሪክ በድጋሚ ይገልጹታል። በመጨረሻም ዕዝራ፣ ነህምያ እና አስቴር እስራኤላውያን እንዴት ወደ ገዛ ምድራቸው እንደተመለሱና ከዚያ በኋላ ስላለው አንዳንድ ታሪካቸው ይገልጻሉ።
ቀጥሎ ያሉት ከመቼውም ይበልጥ ውብ የሆኑ ቅኔዎችን የያዙ በግጥም መልክ የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው። የኢዮብ መጽሐፍ በመከራ ሥር በአቋም መጽናት ስለሚያስገኘው ሽልማት አስደናቂ የሆነ ሥዕል ይሰጠናል። የመዝሙር መጽሐፍም ለይሖዋ የቀረቡ የውዳሴ መዝሙሮችንና ይቅርታና እርዳታ ለማግኘት የተደረጉ ጸሎቶችን ይዟል። እነዚህ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የአምላክ አገልጋዮች አበረታተዋል። በተጨማሪም የመዝሙር መጽሐፍ ሊመጣ ስላለው መሲሕ ያለንን እውቀት የሚጨምሩ በዛ ያሉ ትንቢቶችን ይዟል። ምሳሌ እና መክብብም ቁም ነገር በያዙት አባባሎች የመለኮታዊውን ጥበብ ገጽታዎች ያመለክታሉ። የሰለሞን መዝሙር ወይም መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን ደግሞ ጥልቅ ትንቢታዊ ትርጉም ያለውን አስደናቂ የፍቅር ግጥም የያዘ ነው።
ከኢሳይያስ እስከ ሚልክያስ ያሉት የሚቀጥሉት 17 መጻሕፍት በአብዛኛው ትንቢታዊ ናቸው። ከሰቆቃወ ኤርምያስ በስተቀር ሁሉም የጸሐፊውን ስም የያዙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ትንቢቶች ቀደም ሲል አስደናቂ ተፈጻሚነታቸውን አግኝተዋል። በተጨማሪም በዘመናችንና በቅርቡ ወደሚፈጸሙ የመጨረሻ ሁኔታዎች የሚያመለክቱ ናቸው።
ስለዚህ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በቅርጽና በአጻጻፍ ስልት አስደናቂ ልዩነቶችን ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም የጋራ የሆነ አንድ አጠቃላይ መልዕክት አላቸው። ትንቢቶቻቸው፣ የትውልድ ሐረግ ዝርዝሮቻቸውና የያዙት አስደናቂ ታሪክ ተግባራዊ ጥበብንና ትንቢታዊ ትርጉምን ያንጸባርቃል።
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች—ዘሩ ተገለጠ
ሰው ወደ ኃጢአት ከወደቀ አራት ሺህ ዓመታት አልፈው ነበር። በድንገት በምድር ገጽ ላይ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲጠበቅ የነበረው ዘር መሲሑ ኢየሱስ ተገለጠ! የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በሰው ታሪክ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ያለውን የዚህን ሰው ታሪክ ወንጌሎች ተብለው በሚጠሩ በአራት የተለያዩ ነገር ግን ተደጋጋፊ በሆኑ መጻሕፍት መዝግበው ይዘዋል። እነዚህም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ ናቸው።
እነዚህ አራት ወንጌሎች ለክርስቲያኖች እንዴት ያሉ ውድ ሐብት ናቸው! አስገራሚ ስለሆኑት የኢየሱስ ተዓምራት፣ ትርጉም ስላላቸው ምሳሌዎቹ፣ ስለ ተራራ ስብከቱ፣ ትሑት በመሆን ስላሳየው ምሳሌ፣ ስለ ርህራሄውና ለአባቱ ስላሳየው የማያወላውል ታዛዥነት፣ “ለበጎቹ” ስላለው ፍቅር፣ በመጨረሻም መስዋዕታዊ ሞት ስለ መሞቱና በክብር ስለ መነሣቱ ይናገራሉ። ወንጌሎችን ማጥናታችን በውስጣችን ለአምላክ ልጅ ጥልቅ ፍቅርን ይገነባል። ከሁሉ በላይ ግን ክርስቶስን ወደላከው ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ የሚያቀርቡን ናቸው። እነዚህ ታሪኮች ተደጋግመው ሊነበቡ የሚገባቸው ናቸው።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ወንጌሎች ካቆሙበት ይቀጥላል። በክርስቲያን ጉባኤ የልጅነት ዓመታት ይኸውም ከጴንጤቆስጤ ቀን ጀምሮ ጳውሎስ በ61 እዘአ በሮም እስከታሠረበት ጊዜ ባሉት ዓመታት የተፈጸሙትን በዝርዝር ይገልጻል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ መጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት ስለ እስጢፋኖስ፣ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለሆነው ስለ ሳውል ወደ ክርስትና መለወጥ፣ በመጀመሪያ አሕዛብ ወደ ክርስትና ስለመለወጣቸውና ጳውሎስ ስላደረጋቸው አስደናቂ የወንጌላዊነት ጉዞዎች እናነባለን። እነዚህ ታሪኮች አስደሳችና እምነትን የሚገነቡ ናቸው።
ከዚህ በኋላ ሃያ አንድ ደብዳቤዎች ወይም መልዕክቶች ይቀጥላሉ። የመጀመሪያዎቹ 14 ደብዳቤዎች ጳውሎስ የጻፋቸው ሲሆን ደብዳቤዎቹ በተጻፈላቸው ክርስቲያኖች ወይም ጉባኤዎች ስም የሚጠሩ ናቸው። የቀሩት ደግሞ በጸሐፊዎቹ ማለትም በያዕቆብ፣ በጴጥሮስ፣ በዮሐንስና በይሁዳ ስም የተሰየሙ ናቸው። እነዚህ ደብዳቤዎች እንዴት ያለ የምክርና የማበረታቻ ሐብት ይዘዋል! መሠረተ ትምህርቶችንና የትንቢት ፍጻሜዎችን ይዘዋል። ክርስቲያኖች ከሚኖሩበት ክፉ አካባቢ ተለይተው እንዲኖሩ የሚረዱ ደብዳቤዎች ናቸው። የወንድማዊ ፍቅርንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርዮችን የመኮትኮቱን አስፈላጊነት አጉልተው ይገልጻሉ። በመንፈሳዊ ሽማግሌ በሆኑ ሰዎች አመራር ጉባኤዎች እንዴት መደራጀት እንዳለባቸው ምሳሌ ይሰጣሉ።
የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በትንቢት እንደሚያበቁት ሁሉ የግሪክኛ ጽሑፎችም በዚሁ መንገድ ይደመደማሉ። በ96 እዘአ በሐዋርያው ዮሐንስ የተጻፈው የራእይ መጽሐፍ የተለያዩ ትንቢቶችንና በመሲሐዊው መንግሥቱ አማካኝነት የይሖዋ ስም መቀደሱን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልዕክት ያጠቃልላል። ተከታታይ የሆኑ ራእዮች በሥዕላዊ መግለጫ የተበላሸውን የሰይጣን ሥርዓት የሃይማኖት፣ የወታደራዊና የፖለቲካ ኃይሎች ጥፋት ያሳያሉ። እነዚህ ሁሉ ትኩረቷን ወደ ምድር ጉዳዮች በምታዞረው በክርስቶስ መንግሥታዊ ከተማ ይተካሉ። በዚህ መንግሥታዊ አገዛዝ ሥር አምላክ ‘እንባን ሁሉ ከዓይን ለማበስና ሞትን ከእንግዲህ ወዲህ ለማስቀረት’ ቃል ገብቶአል።—ራእይ 21:4
ይህ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊውን ብርሃን የሚያንጸባርቅ እንከን የለሽ ዕንቁ መሆኑ ያጠራጥራልን? ሙሉ በሙሉ ያላነበብከው ከሆነ ለምን ከአሁን ጀምረህ አታነበውም? በአቀራረቡ ትማረካለህ፣ በእውቀት ብርሃን ሰጪነቱ እውቀትህን ታሰፋለህ፣ በውበቱ ትመሰጣለህ፣ በመልዕክቱም ትደሰታለህ። በእርግጥም “ከሰማያዊ ብርሃናት አምላክ የተገኘ ፍጹም ስጦታ ነው።”—ያዕቆብ 1:17
[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሰንጠረዥ
ጸሐፊው፣ የተጻፈበት ቦታ፣ ተጽፎ ያለቀበት ጊዜ፣ መጽሐፉ የሚያጠቃልለው ጊዜና ሁኔታ ተጠቅሰዋል።
የአንዳንዱ መጽሐፍት ጸሐፊዎች ስምና የተጻፉበት ቦታዎች የተረጋገጠ አይደለም። ብዙዎቹ ቀኖች መቶ በመቶ ትክክል ባይሆኑም ወደዚያ የተጠጉ ናቸው። “አ” አካባቢ ማለት ነው።
የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች (ከዘአበ)
መጽሐፍ ጸሐፊ(ዎች) የተጻፈበት ቦታ ተጽፎ
ያለቀበት የሚሸፍነው ጊዜ ርዝመት
ዘፍጥረት ሙሴ በምድረበዳ 1513 “በመጀመሪያ”
እስከ 1657
ዘጸአት ሙሴ በምድረበዳ 1512 1657-1512
ዘሌዋውያን ሙሴ በምድረበዳ 1512 1 ወር (1512)
ዘኁልቁ ሙሴ በምድረበዳ/
በሞዓብ
ሜዳ 1473 1512-1473
ዘዳግም ሙሴ በሞዓብ
ሜዳ 1473 2 ወር (1473)
ኢያሱ ኢያሱ ከነዓን 1450አ 1473-1450አ
መሣፍንት ሳሙኤል እስራኤል 1100አ 1450አ-1120አ
ሩት ሳሙኤል እስራኤል 1090አ በመሣፍንት የ11
ዓመት ግዛት
1 ሳሙኤል ሳሙኤል፣
ጋድ፣ ናታን፣ እስራኤል 1078አ 1180አ-1078
2 ሳሙኤል ጋድ፣ ናታን፣ እስራኤል 1040አ 1077አ-1040
1 ነገሥት ኤርምያስ ኢየሩሳሌም/
ይሁዳ 580 1040አ-911
2 ነገሥት ኤርምያስ ኢየሩሳሌም/
ግብጽ 580 920አ-580
1 ዜና መዋዕል እዝራ ኢየሩሳሌም (? ) 460አ ከ ከ1 ዜና 9:44 በኋላ፣
1077-1037
2 ዜና መዋዕል እዝራ ኢየሩሳሌም (?) 460አ 1037-537
እዝራ እዝራ ኢየሩሳሌም 460አ 537-አ467
ነህምያ ነህምያ ኢየሩሳሌም 443 በኋላ 456-443በ
አስቴር መርዶክዮስ ረቢዎችና፣
ኤላም 475አ 493-475አ
ኢዮብ ሙሴ በምድረበዳ 1473አ በ1657እና 1473
መካከል 140 ዓመት
በላይ
መዝሙር ዳዊትና
ሌሎች 460አ
ምሳሌ ሰለሞን፣
አጉር፣
ልሙኤል ኢየሩሳሌም 717አ
መክብብ
ሰለሞን ኢየሩሳሌም ከ1000 በፊት
መኀልይ ሰለሞን ኢየሩሳሌም 1020አ
ኢሳይያስ ኢሳይያስ ኢየሩሳሌም ከ732 በኋላ 778አ-732 በኋላ
ኤርምያስ ኤርምያስ ይሁዳ/
ግብጽ 580 647-580
ሰቆቃወ ኤርምያስ በኢየሩሳሌም
አካባቢ 607
ሕዝቅኤል ሕዝቅኤል ባቢሎን 591አ 613-591አ
ዳንኤል ዳንኤል ባቢሎን 536አ 618አ-536
ሆሴዕ ሆሴዕ ሰማሪያ
(አውራጃ) ከ745 በኋላ ከ804 በፊት-745 በኋላ
ኢዩኤል ኢዩኤል ይሁዳ 820አ (?)
አሞጽ አሞጽ ይሁዳ 804አ
አብድዩ አብድዩ 607አ
ዮናስ ዮናስ 844አ
ሚክያስ ሚክያስ ይሁዳ ከ717 በፊት 777አ-717
ናሆም ናሆም ይሁዳ ከ632 በፊት
ዕንባቆም ዕንባቆም ይሁዳ 628አ (?)
ሶፎንያስ ሶፎንያስ ይሁዳ ከ648 በፊት
ሐጌ ሐጌ ኢየሩሳሌም 520 112 ቀናት (520)
ዘካርያስ ዘካርያስ ኢየሩሳሌም 518 520-518
ሚልክያስ ሚልክያስ ኢየሩሳሌም ከ443 በኋላ
የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች (እዘአ)
መጽሐፍ ጸሐፊ የተጻፈበት ቦታ ተጽፎ ያለቀበት የሚሸፍነው ጊዜ ርዝመት
ማቴዎስ ማቴዎስ ፍልስጥኤም 41አ 2 ከዘአበ–
33 እዘአ
ማርቆስ ማርቆስ ሮም 60-65 አ 29-33 እዘአ
ሉቃስ ሉቃስ ቂሣርያ 56-58 አ 3 ከዘአበ–
33 እዘአ
ዮሐንስ ሐዋርያው ዮሐንስ ኤፌሶን ወይም
ባቅራቢያው 98 አ ከመቅድሙ በኋላ
29-33 እዘአ
የሐዋርያት ሥራ ሉቃስ ሮም 61 አ 33-
61 እዘአ አካ.
ሮሜ ጳውሎስ ቆሮንቶስ 56 አ
1 ቆሮንቶስ ጳውሎስ ኤፌሶን 55 አ
2 ቆሮንቶስ ጳውሎስ መቄዶንያ 55 አ
ገላትያ ጳውሎስ ቆሮንቶስ
ወይም የሶሪያ
አንጾኪያ 50-52 አ
ኤፌሶን ጳውሎስ ሮም 60-61 አ
ፊልጵስዩስ ጳውሎስ ሮም 60-61 አ
ቆላስይስ ጳውሎስ ሮም 60-61 አ
1 ተሰሎንቄ
ጳውሎስ ቆሮንቶስ 50 አ
2 ተሰሎንቄ
ጳውሎስ ቆሮንቶስ 51 አ
1 ጢሞቴዎስ ጳውሎስ መቄዶንያ 61-64 አ
2 ጢሞቴዎስ ጳውሎስ ሮም 65 አ
ቲቶ ጳውሎስ መቄዶንያ (?) 61-64 አ
ፊልሞና ጳውሎስ ሮም 60-61 አ
ዕብራውያን ጳውሎስ ሮም 61 አ
ያዕቆብ የኢየሱስ ወንድም
ያዕቆብ ኢየሩሳሌም 62 አ
1 ጴጥሮስ ጴጥሮስ ባቢሎን 62-64 አ
2 ጴጥሮስ ጴጥሮስ ባቢሎን (?) 64 አ
1 ዮሐንስ ሐዋርያው
ዮሐንስ ኤፌሶን ወይም
ባቅራቢያው 98 አ
2 ዮሐንስ ሐዋርያው ዮሐንስ ኤፌሶን ወይም
ባቅራቢያው 98 አ
3 ዮሐንስ ሐዋርያው ዮሐንስ ኤፌሶን ወይም
ባቅራቢያው 98 አ
ይሁዳ የኢየሱስ ወንድም
ይሁዳ ፍልስጥኤም (?) 65 አ
ራእይ ሐዋርያው
ዮሐንስ ፍጥሞ 96 አ