ከእናት መሬት አምልኰ ወደ መራባት የሴት አማልክት
በዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ የተሳለችውን ሴት አምላክ ማን እንደሆነች ታውቃለህን? አይሲስ የተባለችው የጥንቷ ግብጽ ሴት አምላክ ናት። ቤተመዘክርን ጐብኝተህ ወይም የጥንት ታሪክ መጻሕፍትን አገላብጠህ የምታውቅ ከሆነ ይህን ሐውልት ወይም እሱን የሚመስል ሌላ ሐውልት ሳታይ አትቀርም። ይሁን እንጂ እስቲ ይህን አስብ፦ አይሲስ ለተባለችው ሴት አምላክ ትሰግድላትና ታመልካት ነበርን?
ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የአንዱ አባል ከሆንህ ጥያቄው እንግዳ ሊሆንብህ ይችላል። እኔ “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ” የምንለውን ፈጣሪ ብቻ ነው የማመልከው ብለህ አጠንክረህ ትናገር ይሆናል። (ማቴዎስ 6:9) እንደ እናት ለሚቆጠሩ ሴት አማልክት ተንበርክኮ የመስገድ ሐሳብ እንግዳ እንዲያውም አስጸያፊ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አምልኰ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የተስፋፋ ነበር። በዛሬው ጊዜም ታላቋን እናት ሴት አምላክ እነማን እያመለኩ እንዳሉ መሆናቸውን ስታውቅ ትደነግጥ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ ከመወያየታችን በፊት በጥንት ዘመን የእናት ሴት አማልክት አምልኰ ምን ያህል ተስፋፍቶ እንደነበረ ከግምት በማስገባት እንነሣ። ይህ ዓይነቱ አምልኰ የሐሰት አምልኰ ከጀመረበት አካባቢ አንስቶ የነበረ ይመስላል። በአውሮፓ በሙሉና ከሜዲቴራንያን አገሮች እስከ ሕንድ ድረስ በሚገኙ ጥንታውያን ቦታዎች ራቁታቸውን የሆኑ የእናት ሴት አማልክት ሐውልቶችና ምስሎች በመሬት ቆፋሪዎች ተገኝተዋል።
እናት ምድር የሁሉም ዓይነት ሕይወት ምንጭ እንደሆነችና ሕይወትን ሰጥታ በሞት ጊዜ ደግሞ መልሳ እንደምትወስድ ተደርጋ ትታይ ነበር። እንደዚህ ተደርጋ በመታየት ትመለክና ትፈራ ነበር። መጀመሪያ አባለ ዘሯ ለጾታ ግንኙነት እንደማያገለግል ተደርጎ ይታመን ነበር። ከዚያም አፈታሪኩ እንደሚገልጸው ተባዕታይ ጾታ ያለውን የሰማይ አባት ወለደችና ሚስቱ ሆነች። እነዚህ ባልና ሚስት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ተባዕትና እንስት አማልክትን ወለዱ።
ባቢሎናዊው አመጣጥ
በባቢሎናውያን አማልክት መካከል ኢሽታር ዋነኛዋ ሴት አምላክ ስትሆን እናና ከተባለችው የሴሜራውያን የመራባት ሴት አምላክ ጋር አንድ ዓይነት ናት። የሚገርመው በአንድ በኩል የጦርነት በሌላው በኩል የፍቅርና የጾታዊ ፍትወት ሴት አምላክ ነች የሚል እርስ በርሱ የማይጣጣም አስተሳሰብ ነበር። “የባቢሎንና የአሦር ሃይማኖቶች”በተባለው መጽሐፋቸው ተመራማሪው ኢዶርድ ዶርሜ ስለ ኢሽታር እንዲህ ብለዋል፦ “ሴት አምላክ፣ እመቤት፣ ጸሎትን የምትሰማ፣ ርህሩህ እናትና በተቆጡ አማልክት ፊት ቀርባ የምታማልድና የምታበርዳቸው ነበረች። . . . ከሁሉም በላይ ከፍ ያለች ነበረች። የእንስት አማልክት ሁሉ አምላክ፣ የአማልክት ሁሉ ንግሥት፣ የሰማይና የምድር አማልክት ሁሉ የበላይ ሆነች።”
የኢሽታር አምላኪዎች “ድንግሏ” “ቅድስት ድንግል” እና “ድንግል እናት” እያሉ ይጠሯት ነበር። የጥንቱ የሱሜራውያንና የአካዳውያን “ለኢሽታር የሚቀርብ የለቅሶ ጸሎት” እንዲህ ይላል፦ “የእመቤቶች እመቤት፣ የሴት አማልክት ሁሉ አምላክ፣ የሁሉም ሕዝብ ንግሥት ሆይ፤ ወዳንቺ እጸልያለሁ። . . . የግዛትን አክሊል የምትለብሺ፣ የመለኰታዊ ኃይል ሁሉ ባለቤት . . . የጸሎት ቤቶችሽ፣ ልዩ ልዩ ቅዱስ ሥፍራዎች ሁሉ አንቺን ይሰማሉ። . . . ምስልሽ ያልተቀረጸባቸው ቦታዎች የት አሉ? እመቤቴ ሆይ ተመልከቺኝ፣ ጸሎቶቼን ተቀበይ።”a
የእናት ሴት አማልክት አምልኮ ተሰራጨ
የሩቅ ምሥራቅን ታሪክ የሚያጠኑት ኤዶርድ ዶርሜ ስለ “ኢሽታር አምልኰ መስፋፋት” ይናገራሉ። አምልኰቱ በሜሶፖታሚያ በሙሉ ተሰራጭቶ ነበር። ኢሽታር ራስዋ ወይም በተለያዩ ስሞች ሆኖ የእርሷን ጠባይ የያዙ ተመሳሳይ ሴት አማልክት በግብጽ፣ በፊንቄ፣ በከነዓን፣ በአናቶሊያ (ትንሹ እስያ)፣ በግሪክና በኢጣሊያ ይመለኩ ነበር።
በግብጽ ትመለክ የነበረችው ዋነኛዋ እናት ሴት አምላክ አይሲስ ነበረች። ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ እንዲህ ጽፈዋል፦ “አይሲስ ሕይወታቸውን ለሷ የተሳሉ ብዙ ታማኝ አምላኪዎችን ስባለች። እንደ ሰማይ ንግሥት ከፍ ተደርጋ በመታየት ሕፃኑን ሆሬስን አቅፋ የሚያሳየው ምስሏ በቤተመቅደሱ ቆሟል። በፊቷ ሻማዎች ነደው ቀልጠው ፈሰዋል። በዙሪያዋም ነደው ያበቁ ጧፎች ተሰቅለዋል።” (የታሪክ ቢጋር) የአይሲስ አምልኮ በግብጽ ከመጠን በላይ በሕዝብ ተወዳጅ ነበር። በሜድቴራኒያን አካባቢ ሁሉ በተለይ ደግሞ ወደ ግሪክና ሮም እስከ ምዕራብና ሰሜናዊው አውሮፓ ድረስ ተሰራጭቶ ነበር።
በፊንቄና በከነዓን የእናት ሴት አምላክ አምልኰ ያተኰረው የበዓል ሚስት ናት ትባል በነበረችው በአሽቶሬት ወይም አስታርቴ ላይ ነበር። እንደ ባቢሎናዊቷ አምሳያዋ እንደ ኢሽታር እርሷም የመዋለድና የጦርነት አምላክ ነበረች። በግብጽ አስታርቴ የሰማይ እመቤት፣ የሰማይ ንግሥት ተብላ የተጠራችበት የተቀረጸ ጥንታዊ ጽሑፍ ተገኝቷል። እሥራኤላውያን ይህን የመራባት ሴት አማልክት አምልኰ ግፊት ያለማቋረጥ መዋጋት ነበረባቸው።
በአናቶሊያ በስተሰሜን ምዕራብ ከኢሽታር ጋር የምትተካከል ታላቋ የአማልክት እናት ተብላ የምትታወቅ ሲቤሌ ነበረች። እሷም የሁሉም ወላጅ፣ የሁሉም መጋቢና የተባረኩ ሰዎች እናት ተብላ ትጠራ ነበር። ይህ የሲቤሌ አምልኰ ከአናቶሊያ ተነስቶ መጀመሪያ ወደ ግሪክና እስከ ዘመናችን አቆጣጠር ድረስ ተንሰራፍቶ ወደቆየበት ሮም ድረስ ተሰራጭቶ ነበር። የዚህች የመዋለድ ሴት አምላክ አምልኰ ኃይለኛ ስሜት የታከለበት ጭፈራና፣ ቀሳውስቱ የገዛ ሰውነታቸውን ክፉኛ በመቧጠጥ ማቁሰልን፣ ለክህነት ዕጩ የሆኑት ደግሞ የገዛ አባለዘርአቸውን ማኰላሸትንና የሴት አምላኳን ቅርጽ በከፍተኛ ድምቀት ተሸክመው የሚሄዱበት ጉዞንም ያጠቃልል ነበር።b
የጥንት ግሪኮች ጊያ ተብላ ትጠራ የነበረችውን የእናት ምድርን ሴት አምላክ ያመልኩ ነበር። ይሁን እንጂ የአማልክቶቻቸው ቡድን የመዋለድና የፍቅር ሴት አምላክ ብለው ያምኑባት የነበረችውን የኢሽታር ዓይነቷ አፍሮዲጥን፣ የጦርነት ሴት አምላክ የነበረችውን አቴናን፣ የእርሻ ሴት አምላክ የነበረችውን ዲሜጥሮን ያጠቃልል ነበር።
የሮም የፍቅር ሴት አምላክ የነበረችው ቬነስ ነበረች። እንዲህ በመሆኗም ከግሪኳ አፍሮዲጥና ከባቢሎኗ ኢሽታር ጋር ትመሳሰል ነበር። ይሁን እንጂ ሮማውያን በአንዱም ይሁን በሌላ መንገድ የባቢሎኗ ኢሽታር ቅጂዎች የሆኑትን ሴት አማልክት ማለትም አይሲስን፣ ሲቤሌንና ሚኔርቫን (የግሪኳን አቴና) ያመልኩ ነበር።
በግልጽ እንደሚታየው ለሺህ ዓመታት የእናት ሴት አማልክት አምልኰ ለታላቁ ፈጣሪ ለይሖዋ ንጹሕ አምልኰ ታላቅ ተቀናቃኝ ሆኖ ነበር። የታላቋ እናት ሴት አምላክ አምልኰ ጠፍቷልን? ወይስ እስከ ዘመናችን ድረስ ዘልቋል? ቀጥሎ ያለውን አንብቡ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጥንታውያን የቅርቡ ምሥራቅ ጽሑፎች—በጄምስ ቢ ፕሪቻርድ ታርሞ የተዘጋጀ። ፕሪንስተን፣ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት፣ ገጽ 383-4
b በትንሹ እስያ ትመለክ የነበረችው ሌላዋ ሴት አምላክ አርጤሚስ ነበረች። ስለ እርሷ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እናብራራለን።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የባቢሎኗ ኢሽታር ኮከብ ሆና ስትለወጥ
[ምንጭ]
Courtesy of The British Museum
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የግብጿ አይሲስ ሕፃኑን ሖረስን አቅፋ
[ምንጭ]
Musée du Louvre, Paris