እናት የሴት አምላክን ማምለክ አሁንም ሕያው ነውን?
እናት ሴት አምላክን ማምለክ በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ዘመንም ነበረ። ሐዋርያው ጳውሎስንም በትንሹ በኤፌሶን አጋጥሞት ነበር። ሌላ ሴት አምላክን አምላኪ በሆነችው ከተማ በአቴና እንዳደረገው ሁሉ እዚያም “ዓለምን ስለፈጠረው አምላክ” “በሰው ብልሃትና አሳብ እንደተቀረጸው ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ” ስላልሆነው ሕያው ፈጣሪ ምሥክርነት ሰጥቶ ነበር። አብዛኞቹ አርጤምስ የተባለች እናት ሴት አምላክ ያመልኩ ለነበሩት የኤፌሶን ሰዎች ይህን መቀበል የማይታሰብ ነገር ነበር። ብር እያነጠሩ የሴት አምላክ ምስልን በመሥራት ይተዳደሩ የነበሩት ሰዎች ረብሻ አነሳሱ። ሕዝቡ ለሁለት ሰዓት ያህል “የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት” እያሉ ጮኹ።—ሥራ 17:24, 29፤ 19:26, 34
የኤፌሶን አርጤምስ
ግሪኰችም አርጤምስን ያመልኩ ነበር። ይሁን እንጂ በኤፌሶን ትመለክ የነበረችው አርጤምስ ከግሪኳ አርጤምስ ጋር የነበራት ተመሳሳይነት በጣም ጥቂት ነበር። የግሪኳ አርጤምስ የአደንና የልጅ መውለድ ድንግል ሴት አምላክ ነበረች። የኤፌሶን አርጤምስ የመራባት ሴት አምላክ ነበረች። በኤፌሶን የነበረው ግዙፉ ቤተ መቅደሷ ከሰባቱ የዓለም አስደናቂ ነገሮች እንደ አንዱ ተቆጥሯል። ደረቱ ላይ የዕንቁላል ቅርጽ ያላቸው ጡቶች የተደረደሩበትና ከሰማይ የወረደ ነው ተብሎ ይታመን የነበረ ምስሏ ሁለንተናዋ የመራባት ሴት አምላክ እንደሆነች አድርጎ ያቀርባታል። የእነዚህ ጡቶቿ ልዩ ቅርጽ የተለያየ ማብራሪያ ለመስጠት ምክንያት ሆኖአል። ለምሳሌ የተደረደሩ ዕንቁላሎች ናቸው ወይም የበሬ ብልት ፍሬዎች ናቸው ተብለዋል። የትኛውም ማብራሪያ ትክክል ይሁን የመራባት ምሳሌነቱ ግልጽ ነው።
አዲሱ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው ከሆነ የዚች ሴት አምላክ የመጀመሪያ ምስል “ከወርቅ፣ ከጥቁር እንጨት፣ ከብርና ከጥቁር ድንጋይ የተሠራ ነበር።” ከሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ወዲህ የቆየው የኤፌሶኗ አርጤምስ ሐውልት ጥቁር ፊት፣ ጥቁር እጆችና እግሮች እንዳሏት አድርጎ ያሳያል።
የአርጤምስ ምስል በጐዳናዎች ላይ ሰዎች በሰልፍ ተሸክመው ያዞሩት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ የሆኑት አር ቢ ራክሃም እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በአርጤምስ ቤተመቅደስ ውስጥ በታላላቅ በዓሎች ቀን ወደ ከተማይቱ ተሸክመዋቸው የሚወጡና በዕፁብ ድንቅ የሰልፈኛ ጉዞ የሚመልሱአቸው ከወርቅና ከብር የተሠሩ ምስሎች፣ የቤተመቅደሱ ምስሎችና፣ ንዋየ ቅድሳት ይቀመጡ ነበር።” እነዚህ ክብረ በዓሎች ከትንሹ እስያ በሙሉ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ተሳላሚዎችን ይስቡ ነበር። የሴት አምላኳን የቤተ መቅደስ ምስል ገዝተው ይሄዱና “ጸሎቶችን የምትሰማና የምትቀበል” ታላቅ እመቤታቸው፣ ንግሥት፣ እንዲሁም ድንግል እያሉ ያወድሷት ነበር። ሁኔታው እንዲህ በሆነበት አካባቢ ጳውሎስና የቀድሞ ክርስቲያኖች “ከወርቅና ከብር ወይም ከድንጋይ” ከተሠሩ አማልክትና ጣዖታት ይልቅ “ዓለሙን የሠራውን አምላክ” ማወደስ ታላቅ ድፍረት ጠይቆባቸው ነበር።
ከእናት አምላክ ወደ “አምላክ እናት” መሸጋገር
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደፊት ክህደት እንደሚነሣ የተናገረው ለኤፌሶን የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌዎች ነበር። ከሃዲዎች እንደሚነሱና “ጠማማ ነገሮችን” እንደሚናገሩ አስጠነቀቀ። (ሥራ 20:17, 28-30) በኤፌሶን ምን ጊዜም ያደቡባቸው ከነበሩት አደጋዎች አንዱ ወደ እናት አምላክ አምልኰ እንደገና መመለስ ነበር። ይህስ በእርግጥ ደረሰን?
በአዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ወደ ቅዱስ ስፍራ ለሚደረግ ጉዞ መናኸሪያ በመሆኗ ኤፌሶን (ሐዋርያው)ዮሐንስ የተቀበረበት ስፍራ እንደሆነች ይታሰብ ነበር። . . . የኤፌሶኑ የአቡኖች ጉባኤ (431 እዘአ) ማስረጃ የሆነለት ሌላ ሃይማኖታዊ ወግ ‘የተባረከችውን ድንግል ማርያምን’ አስተሳሰብ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ያያይዙታል። ጉባኤው የተደረገበት የችሎት አዳራሽ የማርያም ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተጠራ።” ሌላ የካቶሊክ ጽሑፍ (ቲኦ—አዲስ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ) ማርያም ቀሪ ሕይወቷን ወዳሳለፈችበት ወደ ኤፌሶን ዮሐንስን ተከትላ ሄደች ስለሚል “እውነት የሚመስል ወግ” ይናገራል። ይህ በኤፌሶንና በማርያም መካከል አለ የተባለው ግንኙነት ለእኛ ዛሬ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አዲሱ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ይመልስልን፦ “የአምላክን እናት ማክበር ኃይል ያገኘው ቤተ ክርስቲያን በቆስጠንጢኖስ ጊዜ የንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ቤተ ክርስቲያን በሆነች ጊዜና አረማዊ ሕዝቦች ወደ ቤተክርስቲያኗ መጉረፍ ሲጀምሩ ነበር። . . . ሃይማኖተኛነታቸውና ሃይማኖታዊ ግንዛቤያቸው የተገነባው በዘመናት ሂደት ወደኋላ ሲቆጠር ወደ ጥንቶቹ ዝነኛ የባቢሎንና የአሦር ሃይማኖቶች በሚደርስ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሥር በሰደደ “የታላቋ እናት” ሴት አምላክና “መለኰታዊት ድንግል” አምልኰ ላይ ነው። ታዲያ የእናት ሴት አምላክ አምልኰን “ክርስቲያን ለማድረግ” ከኤፌሶን የተሻለ ምን ቦታ ሊገኝ ይችላል?
እንግዲያውስ በ431 እዘአ ሦስተኛው የክርስቲያን አንድነት ጉባኤ በተባለው ስብሰባ ላይ ማርያም ትርጉሙ “የአምላክ ወላጅ” ወይም “የአምላክ እናት” በሆነ የግሪክኛው ቃል “ቲኦቶኮስ” ተብላ የተጠራችው በኤፌሶን ነበር። አዲሱ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “ቤተክርስቲያኗ ይህን ስም መጠቀሟ በኋለኞቹ መቶ ዓመታት ለተደረጉ የማርያም መሠረተ ትምህርትና አምልኰ መስፋፋት ወሳኝ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም” ይላል።
ይህ ጉባኤ የተደረገበት “የድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን” ፍርስራሽ በጥንቷ ኤፌሶን ስፍራ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ይታያል። በወግ መሠረት ማርያም የኖረችበትና የሞተችበት ቤት ነው የተባለው የጸሎት ቤትም ይታያል። ፓፓ ጳውሎስ ስድስተኛ እነዚህን በኤፌሶን የሚገኙ የማርያም ቅዱስ ሥፍራዎች በ1967 ጐብኝተዋል።
አዎን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስን ያጋጠመው ዓይነት የአረማዊት እናት ሴት አምላክ አምልኰ ማርያምን እንደ “የአምላክ እናት” አድርጎ ከፍ ያለ አምልኰ ወደ መስጠት የተለወጠበት ቦታ ኤፌሶን ናት። እንግዲህ የእናት ሴት አምላክ አምልኰ በሕዝበ ክርስትና ምድር እስከ ዛሬ ሊኖር የቻለበት ዋነኛ መንገድ ለማርያም ፍቅራዊ አምልኮ በመስጠት ነው።
የእናት ሴት አምላክ አምልኰ ዛሬም ሕያው ነው
የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ኢንሳይክሎፒዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ የሆኑትን ደብልዩ ኤም ራምሴይን ጠቅሶ እንደሚናገረው “በአምስተኛው መቶ ዘመን ለማርያም በኤፌሶን የተሰጠው ክብር የጥንቱ የአረማዊት ድንግል እናት የአናቶሊያ አምልኮ በአዲስ መልክ የመጣ ነው።” የአዲስ ኪዳን መንፈሣዊ ትምህርት አዲስ ኢንተርናሽናል መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፦ “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ‘የአምላክ እናት’እና‘የሰማይ ንግሥት’ አስተሳሰብ ከአዲስ ኪዳን በኋላ ቆይቶ የተገኘ ቢሆንም የመነጨው ከቀድሞው የምሥራቅ ሃይማኖትና ታሪክ ነው። . . . ቆይቶ በመጣው የማርያም አምልኰት ውስጥም ብዙ የመለኰታዊት እናት አረማዊ አምልኰት ርዝራዦች አሉበት።”
እነዚህ ርዝራዦች በቁጥር በጣም በርካታና ጥቃቅን ከመሆናቸው የተነሣ እንደ አጋጣሚ የመጣ ነገር ሊሆን አይችልም። ድንግል ማርያም ልጅዋን ታቅፋ በሚያሳየው ምስልና እንደ አይሲስ በመሳሰሉት አረማዊ የሴት አምላክ ምስሎች መካከል ያለው የእናትና ልጅ ምስሎች ተመሳሳይነት ማንም ሳያስተውለው ሊያልፈው አይችልም። በዓለም ዙሪያ በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ የጥቁሯ እመቤት ሐውልቶችና ምስሎች የአርጤምስን ሐውልት ሳያስታውሱን ሊያልፉ አይችሉም። ቲኢ—አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ስለ እነዚህ ጥቁር ድንግሎች እንዲህ ይላል፦ “ለዲያና (አርጤምስ). . . ወይም ሲቤሌ ይሰጥ የነበረውን ዝነኛ አምልኰተ ፍቅር የቀረውን ነገር ወደ ማሪያም ማዛወሪያ መንገዶች እንደሆኑ በግልጽ ይታያሉ።” በካቶሊኮች ዘንድ በፍልሰታ ጊዜ ለድንግል ማርያም የሚደረገው ታላቅ በዓል ለሲቤሌና ለአርጤምስ ይደረግ ከነበረው ታላቅ የአከባበር ሥርዓት የመጣ ነው።
ለማርያም የተሰጧት የማዕረግ ወይም መጠሪያ ስሞችም የአረማዊ እናት ሴት አማልክትን ያስታውሱናል። ኢሽታር “ቅድስት ድንግል” “እመቤት” እና “ጸሎትን የምትሰማ ርኅሩኅ እናት” እየተባለች ትወደስ ነበር። አይሲስና አስታሬት “የሰማይ ንግሥት” በመባል ይጠሩ ነበር። ሲቤሌ “የተባረኩ ሰዎች ሁሉ እናት” በመባል ተጠርታለች። በትንሹ ብቻ እየተለወጡ እነዚህ ሁሉ አጠራሮች ለማርያም ተሰጥተዋል።
የቫቲካን ሁለተኛ ጉባኤ “የቅድስት ድንግልን” አምልኰ አበረታቷል። ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ለማርያም የጋለ አምልኰታዊ ፍቅር ያላቸው በመሆናቸው በጣም የታወቁ ሆነዋል። በበርካታ ጉዞዎቻቸው ወቅት በማርያም የተጠሩ ቅዱስ ስፍራዎችን ሁሉ ሳይጐበኙ ፈጽሞ አያልፉም። በፖላንድ የምትገኘውን የቼስቶኮዋ ጥቁር እመቤት ሳይቀር ጐብኝተዋል። መላውን ዓለም ለማርያም አደራ ሰጥተዋል። እንግዲያውስ አዲሱ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ “እናት ሴት አምላክ”በሚለው ርዕስ ሥር የሚከተለውን ቢጽፍ አያስደንቅም፦ “እናት አምላክ የሚለው መጠሪያ የድንጋይ ዘመን በተባለው ጊዜ ለነበሩት የተለያዩ ምስሎችና ለድንግል ማርያም አገልግሎአል።”
የእናት አምላክ አምልኰ እስከ ዘመናችን የዘለቀበት ብቸኛ መንገድ የሮማ ካቶሊክ የማርያም አምልኰታዊ አክብሮት ብቻ አይደለም። ለየት ባለ መንገድ የሴቶች ንቅናቄ ደጋፊዎች በእናት አምላክ አምልኰ ላይ ብዙ ሥነ ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል። በዚህ ወንድ በእብሪት በሚገዛው ዓለም ውስጥ ሴቶች በጣም እንደተጨቆኑና በሴት ላይ ያተኰረ አምልኰ እብሪት ለሌለበት ዓለም የሰው ልጅ ያለውን ናፍቆት ያንጸባርቃል ብለው ያምናሉ። እንዲሁም ይበልጥ ወደ ሴት አስተሳሰብ ያዘነበለ ቢሆን ኖሮ ዓለም በአሁኑ ጊዜ የተሻለና ይበልጥም ሰላማዊ ቦታ ይሆን ነበር ብለው የሚያምኑ ይመስላል።
ይሁን እንጂ የእናት ሴት አምላክ አምልኰ ለጥንቱ ዓለም ሰላም አላመጣም፤ ዛሬም አያመጣም። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እየተባበሩ ያሉ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ እንዲያውም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስን ለመውለድና ለማሳደግ ግሩም መብት የነበራት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሴት በመሆኗ የቱንም ያህል ቢያከብሯትና ቢያፈቅሯትም ይህች ምድር የምትድነው በማርያም እንዳልሆነ አምነዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሴቶች ነፃ አውጪ ንቅናቄም ቢሆን ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም ሰላማዊ ዓለም ያመጣል ብለው አያምኑም። ያን ሰላማዊ ዓለም እንዲያመጣላቸው በተስፋ የሚጠባበቁት ጳውሎስ ለአቴናና ለኤፌሶን ሰዎች “ዓለሙንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ” በማለት ያወጀለትን አምላክ ነው። (ሥራ 17:24፤ 19:11, 17, 20) ስሙ ይሖዋ የሆነው ሁሉን ማድረግ የሚችለው ይህ አምላክ “ጽድቅ የሚኖርበትን” ክብራማ የሆነ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ ሰጥቷል። እሱ ቃል በገባልን ተስፋ ላይም በእርግጠኝነት እምነታችንን ልንጥል እንችላለን።—2 ጴጥሮስ 3:13
ሴቶች በአምላክና በወንድ ፊት ስላላቸው ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስን አመለካከት በሚመለከት በዚህ በዚህ መጽሔት ቀጥሎ ተብራርቷል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሽቶሬት—የከነዓናውያን የፍትወተ ሥጋና የጦርነት ሴት አምላክ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አርጤምስ—የኤፌሶናውያን የመራባት ሴት አምላክ
[ምንጭ]
Musei dei Conservatori, Rome
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሕዝበ ክርስትና “የእግዚአብሔር እናት”
[ምንጭ]
Chartres Cathedral, France