በልጆቻችን ውስጥ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን መገንባት
ባልዋ ጥሏት የሄደው የዋንዳ እናት በሴት ልጅዋ በዋንዳ ውስጥ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለመገንባት ትጥር ነበር። ዋንዳ 12 ዓመት ሲሆናት ይህ ማሠልጠኛ ፈተና ደረሰበት። በዚያ ጊዜ ዋንዳ፣ ታናሽ ወንድሟና እህቷ ለጥቂት ጊዜ ከእናታቸው ተነጥለው ከአባታቸው ጋር ለመኖር ተገደዱ። አባቷ አማኝ አልነበረም። ታዲያ እናትዋ አጠገብዋ ሆና እርስዋን ለማየት በማትችልበት በዚህ ሁኔታ ላይ ስትኖር ዋንዳ ምን ታደርግ ይሆን?
በሁሉም ክርስቲያን ወላጆች ላይ ልጆቻቸው ብቻቸውን ውሳኔ ለማድረግ የሚገደዱበትና የራሳቸው እምነት የሚፈተንበት ጊዜ ውሎ አድሮ መምጣቱ የማይቀር ነው። ልጆቹ እንደ ዋንዳ ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ተለይተው ለመኖር ይገደዱ ይሆናል። በትምህርት ቤትም መጥፎ ነገር እንዲያደርጉ የእኩዮቻቸው ግፊት ያጋጥማቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ ኃይለኛ የሆነ ወደ ክፉ የሚገፋፋ ፈተና ያጋጥማቸው ይሆናል። ያ ጊዜ ሲመጣ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ይኖራቸው ዘንድ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ይጸልያሉም።
ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ ጠንካራ ክርስቲያናዊ ባሕርዮችን ሊገነቡ የሚችሉት እንዴት ነው? ዋንዳ ምን እንዳደረገች ከማየታችን በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እንዴት እንደሚረዳን እንመልከት። ለመልሱ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች ከጻፈላቸው ከእነዚህ ቃላት መሠረት እናገኛለን፦ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም፣ በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል። በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።”—1 ቆሮንቶስ 3:11-13
መሠረቱ
ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው ለምንድን ነው? እርሱ በቆሮንቶስ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን የመገንባት ፕሮግራም ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ፕሮግራሙ የሚያሰናክል ችግር አጋጥመው። እርግጥ የጳውሎስ የግንባታ ፕሮግራም የራሱን ሥጋዊ ልጆች የሚመለከት አልነበረም። በእርሱ ስብከት አማካኝነት ክርስቲያን ለመሆን የቻሉትን የሚመለከት ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህን እንደ መንፈሳዊ ልጆቹ አድርጎ ስለሚቆጥራቸው እርሱ የተናገረው ነገር ለወላጆችም ቢሆን ጠቃሚ ነው።—1 ቆሮንቶስ 4:15
ጳውሎስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ወደ ቆሮንቶስ በመምጣት በዚያ አንድ የክርስቲያን ጉባኤ አቋቁሞ ነበር። ስብከቱን ሰምተው ጥሩ ምላሽ የሰጡት ሰዎች በባሕርያቸው ታላላቅ ለውጦችን አድርገዋል። ቀደም ሲል አንዳንዶቹ የጾታ ብልግና የሚፈጽሙ፣ ሌቦች፣ ጣዖት አምላኪዎችና ሰካራሞች ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ጥሩ መሠረት መሥርቶ ስለነበረ ወደ ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ችለዋል። ይህ መሠረት ምን ነበር? “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 3:11
ጳውሎስ እነዚህን አዲስ አማኞች በቆሮንቶስ ሲያስተምር ይህን መሠረት የጣለው እንዴት ነበር? እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “እኔም ወንድሞች ሆይ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ [የአምላክን ቅዱስ ምሥጢር (አዓት)] ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና።” (1 ቆሮንቶስ 2:1, 2፤ ሥራ 18:5) የሰዎች ትኩረት ወደ እርሱ እንዲሆን አላደረገም ወይም እውነትን ከውጭ ምሁራዊ መልክ እንዲኖረው አለባብሶ አላቀረበውም። ከዚህ ይልቅ ትኩረትን የሳበው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስና እርሱን አምላክ እንዴት እንደተጠቀመበት ነው።
እንዲያውም ኢየሱስ ለክርስቲያናዊው ግንባታ ድንቅ የሆነ ጠንካራ መሠረት ነው። ቤዛዊ መስዋዕት አስገኝቷል። እርሱ አሁን ሰማያዊ ንጉሥ ነው። በመሆኑም በቅርቡ የአምላክን ጠላቶች በአርማጌዶን ያጠፋቸዋል። ከዚያም በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ የአምላክን ጽድቅ ያስፈጽማል። የአምላክ ሊቀ ካህን እንደመሆኑም የሰውን ዘር ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ያደርሳቸዋል። ታዲያ አንድ ሰው ምን ሌላ መሠረት ሊያስፈልገው ይችላል?
ስለዚህ በልጆቻችን ውስጥ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ስንገነባ እነዚህን ዐበይት ቁም ነገሮች እንዲያስተውሉና እንዲያደንቁ በማድረግ ጳውሎስን ብንመስለው መልካም ነው። ኢየሱስ ስላደረገልንና አሁንም እያደረገልን ስላለው ነገር እንዲያፈቅሩት ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ልናስተምራቸው ይገባል።—1 ጴጥሮስ 1:8
ሕንፃው
ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንዲህ ያለ ጥሩ መሠረት ከጣለ በኋላ እርሱ ሲሄድ የሕንፃው የግንባታ ሥራ አንዳንድ መሰናክሎች አጋጥመውታል። (1 ቆሮንቶስ 3:10) ችግሩ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወላጆችን ከሚያጋጥማቸው የተለየ አልነበረም። ልጆቻቸውን በክርስትና እምነት ያሳድጋሉ፤ ልጆቹ እውነት ገብቷቸዋል ብለው እርግጠኝነት ይሰማቸዋል። ልጆቹ ሲያድጉ ግን ከእውነት ተንሸራትተው ይወጣሉ ወይም እምነቱን ይተዉታል። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ እነርሱ በተጠቀሙበት የግንባታ ዕቃ ምክንያት ነው።
ጳውሎስ ባሕርያት ውድ በሆኑ ነገሮች ይኸውም በወርቅ፣ በብር፣ ወይም በከበሩ ድንጋዮች ሊገነቡ እንደሚችሉ ተናግሯል። ወይም ርካሽ በሆኑ ነገሮች ማለትም በእንጨት፣ በሣር፣ ወይም በአገዳ ሊታነጹ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 3:12) ስለዚህ ገንቢው ሰው በወርቅ፣ በብርና በክቡር ድንጋዮች ከተጠቀመ ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ የላቀ ሕንፃ እየገነባ ነው ማለት ነው። ገንቢው በእንጨት፣ በሣርና በአገዳ ከተጠቀመ ግን እየገነባ ያለው ጊዜያዊና ርካሽ ሕንፃ ነው።
በቆሮንቶስ ውስጥ የማይረቡ መንፈሳዊ የግንባታ ዕቃዎች በሥራ ላይ ሳይውሉ አልቀሩም። የሐዋርያው ጳውሎስን የመሠረት አጣጣል የተከተሉ አንዳንድ ሰዎች ጠንካራና ቋሚ ሕንፃ ሳይሆን ርካሽና ጊዜያዊ ሕንፃ በመገንባት ላይ ነበሩ። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሰዎችን መመልከት ጀምረው ነበር፤ በዚህም ምክንያት በመካከላቸው መከፋፈል፣ ቅንዓትና ክርክር ነበረ። (1 ቆሮንቶስ 1:10-12፤ 3:1-4) ይህ ምን ቢደረግ ኖሮ ሊቀር ይችል ነበር? ጥራት ባለውና ጠንካራ በሆነ የግንባታ ዕቃ ቢጠቀሙ ይህ ሁኔታ ባልኖረም ነበር።
እነዚህም ለአንድ ክርስቲያን ጠባይ አስፈላጊ የሆኑትን ውድ ባሕርያት ያመለክታሉ። የትኞቹን ባሕርያት? ሐዋርያው ጴጥሮስ “ከሚጠፋ ወርቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ” በማለት አንዱን ጠቅሶታል። (1 ጴጥሮስ 1:6, 7) ንጉሥ ሰለሞንም ‘ወርቅና ብር ከማግኘት ይልቅ’ ጥበብና ማስተዋል ይሻላሉ በማለት ሌሎቹን ሁለት ባሕርያት ጠቅሶአል። (ምሳሌ 3:13-15) ንጉሥ ዳዊትም ይሖዋን መፍራትና ትዕዛዛቱን መረዳት ‘ከወርቅ ይልቅ በጣም የሚፈለጉ’መሆናቸውን አስታውሶናል።—መዝሙር 19:9, 10
እነዚህና ሌሎች ውድ የሆኑ የግንባታ ዕቃዎች ልጆቻችን ፈተናዎችን እንዲያልፉ ለመርዳት በክርስቲያን ጠባዮች ላይ ሊገነቡ ይችላሉ። ታዲያ እንደነዚህ ባሉት የግንባታ ዕቃዎች እየገነባን ስለመሆናችን እንዴት እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን? የልጆቻችንንም ሆነ የራሳችንን ልብ በመጠበቅ ነው።
የተሳካ የግንባታ ሥራ
የአንድ ወላጅ ልብ በዚህ የግንባታ ሥራ የሚጫወተው ሚና በጥንት እስራኤል ውስጥ ይሖዋ ለወላጆች ከሰጠው ትዕዛዝ ሊታይ ይችላል፦ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ።” ከዚያም በመቀጠል፦ “ለልጆችህም አስተምረው” ይላል። (ዘዳግም 6:6, 7) ስለዚህ ሌሎችን ለመገንባት ከመቻላችን በፊት ራሳችንን መገንባት ይኖርብናል ማለት ነው። ልጆቻችን በምንናገረውና በምናደርገው ነገር የእኛ ባሕርይ ከጥሩ የግንባታ ዕቃዎች የተሠራ መሆኑን ማየት ይኖርባቸዋል።—ቆላስይስ 3:9, 10
ከዚህም በኋላ የምንሰጣቸው ትምህርት የእነርሱን ልብ መንካት ይኖርበታል። የክርስቲያን ባሕርዮችን በመገንባት ከሁሉም በላይ የተሳካለት ኢየሱስ በምሳሌዎችና በጥያቄዎች በመጠቀም የሰዎችን ልብ ይነካ ነበር። (ማቴዎስ 17:24-27፤ ማርቆስ 13:34) ወላጆችም እንደነዚህ ያሉትን የማስተማር ዘዴዎች ውጤታማ ሆነው ያገኙአቸዋል። የክርስትና እውነቶች ለትንንሽ ልጆቻቸው ልብ ማራኪ እንዲሆኑ በምሳሌዎች ይጠቀማሉ፤ ትልልቅ ልጆቻቸው ምን እንደሚያስቡ፣ ነገሮችን በልባቸው እንዴት እንደሚረዱ ለማወቅ በደንብ የታሰበባቸው ጥያቄዎች ይጠይቃሉ።—ምሳሌ 20:5
ሙሴ በእስራኤላውያን ውስጥ ታማኝ ሆኖ የመቀጠልን ፍላጎት ለመገንባት በሞከረበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “መልካምም እንዲሆንልህ . . . [ የይሖዋን (አዓት)] ትዕዛዝና ሥርዓት” ጠብቅ። (ዘዳግም 10:13) በተመሳሳይም ወላጆች ለልጆቻቸው የአምላክ የአቋም ደረጃዎች ምን እንደሆኑ በግልጽ መናገራቸው ብቻ አይበቃም፤ ነገር ግን እንደ ሐቀኝነት፣ የስነ ምግባር ንጽሕናና መልካም ባልንጀርነት የመሳሰሉት ነገሮች ለምን ለእነርሱ ጥሩ እንደሆኑ በሚያሳምን መንገድ ቢያሳዩዋቸው ጥሩ ነው።
በመጨረሻም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) ልጆች ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ይሖዋን ካወቁ፣ ስለ ችግሮቻቸው ከእርሱ ጋር መነጋገርን ከተማሩ፣ ጸሎታቸውን እንደሰማላቸው ተሞክሮ ካላቸው ዋናውን የክርስቲያን ባሕርይ ክፍል ይኸውም ከፈጣሪያቸው ጋር የግል ዝምድና አሳድገዋል ማለት ነው።
እሳቱ
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ውስጥ የግንባታው ሥራ በትክክል ባልተሠራ ጊዜ እንደ መከፋፈል፣ ጠብ ያሉት ዓለማዊ ጠባዮች ሥር እንደሚሰዱ ተገንዝቦ ነበር። ይህ አደገኛ ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ እንደገለጸው “የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።”—1 ቆሮንቶስ 3:13
እሳቱ ምንድን ነው? ሰይጣን በአንድ ክርስቲያን ላይ የሚያመጣው ማንኛውም ዓይነት ፈተና ሊሆን ይችላል። የጓደኞች ግፊት፣ የሥጋ ፈተናዎች፣ ፍቅረ ነዋይ፣ ስደት፣ የሚሸረሽር ጥርጣሬ ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ያሉ ፈተናዎች መምጣታቸው የማይቀር ነው። “የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፣ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።” ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ፈተና እንደሚደርስባቸው በመጠበቅ የልጆቻቸውን ባሕርዮች ይገነባሉ። በይሖዋ እርዳታ ልጆቻቸው ፈተናውን ሊያልፉ እንደሚችሉ ትምክህት አላቸው። ወላጆች እንደዚህ ያለ አስተሳሰብ ካላቸው በከፍተኛ ይባረካሉ።
ለጥረቱ የሚያገኙት ዋጋ
ጳውሎስ፦ “ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ቢጸናለት ደመወዙን (የጥረቱን ዋጋ) ይቀበላል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 3:14) ሐዋርያው ጳውሎስ ለጥረቱ ዋጋውን ተቀብሏል። እርሱ የግንባታ ሥራ ባከናወነባት በተሰሎንቄ ከተማ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፎላቸው ነበር፦ “ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።”—1 ተሰሎንቄ 2:19, 20
የዋንዳ እናት ይህን የጥረት ዋጋ አግኝታለች። ዕድሜዋ 12 ዓመት የሆነው ዋንዳ ከእናቷ መለየቷን ስታውቅ እስከምትተኛ ድረስ አለቀሰች። በኋላም እናቷ ችግሯን በጸሎት ለይሖዋ እንድትነግረው የሰጠቻት ምክር ትዝ አላት። ጸለየች፤ ወዲያውኑም የስልክ ቁጥር ማውጫ መጽሐፍ ተመልክታ በአካባቢው የይሖዋ ምስክሮች እንዳሉ ለማወቅ መሞከር እንደምትችል ሐሳብ መጣላት። አገኘቻቸው፤ ከአባትዋ ቤት ዝቅ ብሎ በሚገኘው መንገድ ላይ የሚኖሩ አንድ ቤተሰብ እንዳሉ አወቀች። “ደስ አለኝ” አለች ዋንዳ።
ከዚህ ቤተሰብ ባገኘችው ማበረታቻ ዋንዳ ትንሽ ወንድሟንና እህቷን ወደ ክርስቲያናዊው እንቅስቃሴ እንዲመለሱ አዘጋጀቻቸው። “ራሳችንን ለስብሰባዎች የማዘጋጀቱ ኃላፊነት የእኔ ነበር” በማለት ገለጸች። “ልብሶቻችንን ማጠብ፣ ጸጉራችንን ማበጠር፣ ንጹሖችና በሰው ፊት ልንቀርብ የምንችል መሆናችንን ማረጋገጥ ነበረብኝ።” ይህ ለአንዲት ትንሽ ልጃገረድ የሚከብድ ሥራ ነው፤ ቢሆንም ሠርታዋለች። በአንድ ወቅት አባታቸው ስብሰባ እንዳይሄዱ ሊከለክላቸው ሞከረ፤ ሆኖም ልጆቹ ለመኑትና እንዲሄዱ ፈቀደላቸው።
ከጊዜ በኋላ ልጆቹ ከእናታቸው ጋር እንደገና ተገናኙ። ዋንዳ 15 ዓመት ሲሞላት የተጠመቀች ክርስቲያን ሆነችና ሚስዮናዊት ለመሆን ያላትን ፍላጎት ገለጸች። አዎ፤ የዋናዳ እናት ሥራ ፈተናውን አልፏል። ሴት ልጅዋ በራስዋ ለእውነት ጸንታ ስትቆም በማየት የጥረቷን ዋጋ አግኝታለች። ሁሉም ክርስቲያን ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ የክርስቲያን ባሕርዮችን ለመገንባት ሲጥሩ ተመሳሳይ የሆነ የተሳካ ውጤት የሚያገኙ ይሁኑ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ይህ ርዕሰ ትምህርት እንደሚያሳየው ወላጆች በልጆቻቸው ውስ የክርስቲያን ባሕርዮችን ለመገንባት ከፍተኛ ሙከራ ያደርጋሉ፤ ልጆችም ቢሆኑ ኃላፊነት አለባቸው። እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ሁሉ እነርሱም በውስጣቸው የግንባታ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 4:22-24) በዚህ በኩል ወላጆች አስደናቂ የሆነ የመርዳት አጋጣሚ ቢኖራቸውም በመጨረሻው ላይ እያንዳንዱ ግለሰብ ይሖዋን ለማገልገል የራሱን ወይም የራስዋን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል።