ሥራችሁ እሳቱን ይቋቋም ይሆን?
“እያንዳንዱ ግን [በመሠረቱ] ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ።”—1 ቆሮንቶስ 3:10
1. ታማኝ ክርስቲያኖች ወደፊት ደቀ መዛሙርት የሚሆኑትን በሚመለከት ምን ተስፋ ያደርጋሉ?
አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት አዲስ የተወለደ ሕፃን ልጃቸውን ትክ ብለው ይመለከታሉ። አንድ የመንግሥቱ አስፋፊ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ፊት ላይ ጉጉትና ፍላጎት ሲንጸባረቅ ይመለከታል። መድረክ ላይ ሆኖ እያስተማረ ያለ ክርስቲያን ሽማግሌ በአድማጮቹ መካከል የሚገኝ ፍላጎት ያሳየ አንድ አዲስ ሰው ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እያወጣ በጉጉት ሲከታተል ይመለከታል። እነዚህ የታመኑ የይሖዋ አገልጋዮች ልባቸው በተስፋ ተሞልቷል። ‘ይህ ሰው ይሖዋን ለመውደድና ለማገልገል ይበቃ ይሆን?’ እንዲሁም የታመነ ሆኖ እስከ መጨረሻው ይቀጥል ይሆን? ብለው ማሰባቸው አይቀርም። እርግጥ እንዲህ ያለው ውጤት እንዲሁ በራሱ የሚመጣ አይደለም። ጠንክሮ መሥራት ይጠይቃል።
2. ሐዋርያው ጳውሎስ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን የማስተማሩ ሥራ ያለውን አስፈላጊነት ያሳሰባቸው እንዴት ነበር? ይህስ በምን ረገድ ራሳችንን እንድንመረምር ያነሳሳናል?
2 የተዋጣለት አስተማሪ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ የማስተማሩንና ደቀ መዝሙር የማድረጉን ሥራ አስፈላጊነት አስምሮበታል:- “ከጊዜው የተነሣ አስተማሪዎች ልትሆኑ [ይገባችኋል]።” (ዕብራውያን 5:12) እንዲህ ብሎ የጻፈላቸው ክርስቲያኖች፣ አማኞች ሆነው ከቆዩበት ጊዜ አንጻር ሲታይ ያደረጉት እድገት አነስተኛ ነበር። ሌሎችን ለማስተማር ዝግጁ አለመሆን ብቻ አይደለም፤ የእውነትን መሠረታዊ ትምህርቶች እንደገና የሚከልስላቸው ሰው ያስፈልጋቸው ነበር። ዛሬ ሁላችንም የማስተማር ችሎታችንን በየጊዜው መገምገምና ማሻሻል የምንችልበትን መንገድ መፈለጋችን ተገቢ ነው። የብዙ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። ምን ማድረግ እንችላለን?
3. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት የማፍራቱን ሥራ ከምን ሂደት ጋር አመሳስሎታል? (ለ) ክርስቲያን ግንበኞች እንደመሆናችን መጠን ምን ታላቅ መብት አለን?
3 ጳውሎስ በርካታ ነገሮችን የሚዳስስ ምሳሌ በመጠቀም ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ከአንድ ሕንፃ ግንባታ ጋር አመሳስሎታል። እንዲህ ብሎ በመናገር ይጀምራል:- “የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።” (1 ቆሮንቶስ 3:9) ስለዚህ ሰዎችን በሚመለከት የግንባታ ሥራ እንካፈላለን፤ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳት እንገነባቸዋለን። እንዲህ የምናደርገው ‘ሁሉን ነገር የሠራው’ አምላክ የሥራ ባልደረቦች በመሆን ነው። (ዕብራውያን 3:4) ይህ እንዴት ያለ መብት ነው! ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ ተነሳስቶ የሰጠው ምክር ችሎታችንን ይበልጥ ለማዳበር እንዴት እንደሚረዳን ቀጥለን እንመልከት። በተለይም ደግሞ ‘በማስተማር ችሎታችን’ ላይ ትኩረት እናደርጋለን።—2 ጢሞቴዎስ 4:2
ትክክለኛውን መሠረት መጣል
4. (ሀ) በክርስቲያናዊው የግንባታ ሥራ ውስጥ ጳውሎስ የነበረው ሚና ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስም ሆነ አድማጮቹ የጥሩ መሠረትን አስፈላጊነት ያውቁ ነበር ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
4 አንድ ሕንፃ ምንም ሳይሆን ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ከተፈለገ ጥሩ መሠረት ሊኖረው ይገባል። በመሆኑም ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ [“የሥራ፣” NW] አለቃ መሠረትን መሠረትሁ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 3:10) ኢየሱስ ክርስቶስም ጠንካራ መሠረት መርጦ ቤቱን ስለገነባ ሰው የሚገልጽ ተመሳሳይ ምሳሌ ተናግሯል። ይህ ቤት በጠንካራ መሠረት ላይ ስለተገነባ በማዕበል ከመወሰድ ሊተርፍ ችሏል። (ሉቃስ 6:47–49) ኢየሱስ መሠረት ምን ያህል ወሳኝነት ያለው ነገር መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል። ይሖዋ ምድርን በመሠረተ ጊዜ አብሮት ነበር።a (ምሳሌ 8:29–31) የኢየሱስ አድማጮችም ቢሆኑ ጥሩ መሠረት አስፈላጊ መሆኑን ያውቁ ነበር። በፍልስጤም ምድር አልፎ አልፎ የሚከሰቱትን የጎርፍና የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ለመቋቋም የሚችሉት በጥሩ መሠረት ላይ የተገነቡ ቤቶች ብቻ ነበሩ። ሆኖም ጳውሎስ በአእምሮው ይዞት የነበረው መሠረት ምን ነበር?
5. የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት ማን ነው? ይህስ በትንቢት የተነገረው እንዴት ነበር?
5 ጳውሎስ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 3:11) ኢየሱስ ከመሠረት ጋር ተመሳስሎ ሲጠቀስ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም። እንዲያውም ኢሳይያስ 28:16 እንደሚከተለው በማለት ተንብዮአል:- “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፣ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፣ የከበረውን፣ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ።” ይሖዋ ከጥንት ጀምሮ ልጁ የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት እንዲሆን የማድረግ ዓላማ ነበረው።—መዝሙር 118:22፤ ኤፌሶን 2:19–22፤ 1 ጴጥሮስ 2:4–6
6. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ላይ ትክክለኛውን መሠረት የጣለው እንዴት ነበር?
6 የግለሰብ ክርስቲያኖች መሠረት ምንድን ነው? ጳውሎስ እንዳለው ለአንድ እውነተኛ ክርስቲያን በአምላክ ቃል ላይ ከተገለጸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ምንም መሠረት የለም። ጳውሎስ እንዲህ ያለውን መሠረት መጣሉ የተረጋገጠ ነው። ለፍልስፍና ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ ሰዎች በነበሩባት በቆሮንቶስ ከተማ ሰዎች ዘንድ ዓለማዊ ጥበብ በማንጸባረቅ ልቆ ለመታየት አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ አሕዛብ “ሞኝነት” በማለት ያጣጣሉትን “የተሰቀለውን ክርስቶስን” ሰብኳል። (1 ቆሮንቶስ 1:23) ጳውሎስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ኢየሱስ መሆኑን አስተምሯል።—2 ቆሮንቶስ 1:20፤ ቆላስይስ 2:2, 3
7. ጳውሎስ ራሱን ለመግለጽ ከተጠቀመበት ‘ብልሃተኛ የሥራ አለቃ’ ከሚለው አነጋገር ምን ለመማር እንችላለን?
7 ጳውሎስ የማስተማሩን ሥራ የሚያካሂደው “እንደ ብልሃተኛ የአናጺ [“የሥራ፣” NW] አለቃ” መሆኑን ገልጿል። ይህ አነጋገሩ ራሱን ከመጠን በላይ ከፍ ከፍ ማድረጉን የሚያሳይ አልነበረም። ይሖዋ ሥራውን የማደራጀት ወይም የመምራት አስደናቂ ስጦታ እንደሰጠው መግለጹ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 12:28) እኛ ዛሬ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ተአምራዊ ስጦታዎች እንደሌሉን የታወቀ ነው። እንዲሁም ልዩ የማስተማር ተሰጥኦ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ይህ ተሰጥኦ አለን ለማለት ይቻላል። እስቲ አስቡት፤ ይሖዋ እኛን ለመደገፍ ቅዱስ መንፈሱን ይሰጠናል። (ከሉቃስ 12:11, 12 ጋር አወዳድር።) እንዲሁም የይሖዋ ፍቅርና በቃሉ ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ ትምህርቶች እውቀት አለን። እነዚህ ነገሮች ሌሎችን ለማስተማር ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ድንቅ ስጦታዎች ናቸው። ትክክለኛውን መሠረት ለመጣል በእነዚህ ስጦታዎች ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።
8. ወደፊት ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ለሚችሉ ሰዎች ክርስቶስን መሠረት አድርገን ልናስቀምጥ የምንችለው እንዴት ነው?
8 ክርስቶስን መሠረት አድርገን ስናስቀምጥ በግርግም እንደሚገኝ አቅመ ቢስ ሕፃን ወይም ከይሖዋ ጋር እንደሚተካከል የሥላሴ ክፍል አድርገን እናስተምራለን ማለት አይደለም። እንዲህ ያለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ እምነት የሐሰተኛ ክርስቲያኖች መሠረት ነው። ከዚህ ይልቅ በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው መሆኑን፣ ፍጹም ሕይወቱን ለእኛ ሲል መስጠቱንና በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ የተሾመ በሰማይ ሆኖ የሚገዛ ንጉሥ መሆኑን እናስተምራለን። (ሮሜ 5:8፤ ራእይ 11:15) በተጨማሪም ተማሪዎቻችን የኢየሱስን ፈለግ እንዲከተሉና ባሕርያቱን እንዲኮርጁ ልናነሳሳቸው እንጥራለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ ለአገልግሎቱ በነበረው ቅንዓት፣ ለተናቁና በግፍ ለተደቆሱ ሰዎች ባሳየው ርኅራኄ፣ በጥፋተኝነት ስሜት ቅስማቸው ለተሰበረ ሰዎች ባሳየው ምሕረትና ፈተና ሲደርስበት ባሳየው የማይናወጥ አቋም ተማሪዎቻችን በጥልቅ እንዲነኩ እንፈልጋለን። በእርግጥም ኢየሱስ ዕጹብ ድንቅ መሠረት ነው። ሆኖም የሚቀጥለው ምንድን ነው?
በትክክለኛ የግንባታ ቁሳቁስ ተጠቅሞ ማነጽ
9. ጳውሎስ ዋነኛ ሥራው መሠረት መጣል ቢሆንም እሱ ያስተማረውን እውነት ለተቀበሉ ሰዎች እንደሚያስብላቸው ያሳየው እንዴት ነበር?
9 ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፣ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፣ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።” (1 ቆሮንቶስ 3:12, 13) ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር? ይህን የተናገረበትን ምክንያት ተመልከቱ። የጳውሎስ ተቀዳሚ ተግባር መሠረት መጣል ነበር። ባደረጋቸው የሚስዮናዊ ጉዞዎች ከከተማ ወደ ከተማ በመጓዝ ስለ ክርስቶስ ሰምተው ለማያውቁ ብዙ ሰዎች ሰብኳል። (ሮሜ 15:20) ሰዎች የሚያስተምረውን እውነት ሲቀበሉ ጉባኤዎች ይመሠረቱ ነበር። ጳውሎስ ለእነዚህ የታመኑ ሰዎች ከልብ ያስብ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:28, 29) ይሁን እንጂ ሥራው ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወርን ይጠይቅበት ነበር። ስለዚህ በቆሮንቶስ መሠረት በመጣል 18 ወራት ያህል ከቆየ በኋላ በሌሎች ከተሞች ለመስበክ ሄደ። ያም ሆኖ ግን እሱ ጀምሮት የሄደውን የስብከት ሥራ ሌሎች እንዴት እያከናወኑት እንዳሉ ለማወቅ ይፈልግ ነበር።—ሥራ 18:8–11፤ 1 ቆሮንቶስ 3:6
10, 11. (ሀ) ጳውሎስ ለግንባታ የሚያገለግሉ ሁለት ዓይነት ቁሳቁሶችን ያነጻጸረው እንዴት ነው? (ለ) በጥንቷ ቆሮንቶስ ቃል በቃል ምን ዓይነት ሕንፃዎች ኖረው ሊሆን ይችላል? (ሐ) በአብዛኛው እሳትን ሊቋቋሙ የሚችሉ ሕንፃዎች ምን ዓይነት ናቸው? ይህስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ለሚካፈሉ ሰዎች ምን ግሩም ትምህርት ይሰጣል?
10 ጳውሎስ በቆሮንቶስ በጣለው መሠረት ላይ እየገነቡ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች መናኛ የሆነ ሥራ እየሠሩ ነበር። ችግሩን በግልጽ ለማስቀመጥ እንዲያመች ሲል ጳውሎስ ሁለት ዓይነት የግንባታ ቁሳቁስ ማለትም ወርቅን፣ ብርንና የከበረ ድንጋይን ከእንጨት፣ ከሣርና ከአገዳ ጋር አነጻጽሯል። አንድ ሕንፃ ግሩም በሆኑ፣ ረዥም ጊዜ በሚቆዩና እሳትን መቋቋም በሚችሉ ነገሮች ሊገነባ ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ዘላቂነት በሌላቸው፣ ጊዜያዊና እሳት መቋቋም በማይችሉ ቁሳቁሶች መገንባት ይቻላል። እንደ ቆሮንቶስ የመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞች በሁለቱም ዓይነት የግንባታ ቁሳቁሶች የተገነቡ ሕንፃዎች በብዛት እንደሚኖሯቸው አያጠራጥርም። ግዙፍና ውድ ከሆኑ ጥርብ ድንጋዮች የተሠሩና ምናልባትም በፊት ለፊት በኩል ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በወርቅና በብር ያጌጡ አስደናቂ ቤተ መቅደሶች ነበሩ።b እነዚህ ጠንካራ መሠረት ያላቸው ሕንጻዎች በአጠገባቸው ከሚገኙት ከእንጨት ከተሠሩና የሣር ክዳን ካላቸው ደሳሳ ቤቶች እንዲሁም የገበያ ዳሶች በላይ ገዝፈውና ተውበው ሳይታዩ አይቀርም።
11 እሳት በሚነሣበት ጊዜ እነዚህ ሕንፃዎች ምን ይሆናሉ? መልሱ ለእኛም ሆነ በጳውሎስ ዘመን ለነበሩ ሰዎች ግልጽ ነው። እንዲያውም መሚየስ የተባለው የሮማ ጄኔራል በ146 ከዘአበ ቆሮንቶስን ድል ካደረገ በኋላ ከተማዋን በእሳት አቃጥሏት ነበር። በእንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ የተሠሩ ብዙ ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ የተረጋገጠ ነው። በድንጋይ ተሠርተው በብርና በወርቅ ያጌጡት ጠንካራ ሕንፃዎችስ? እነዚህ ከጥፋት እንደተረፉ ምንም አያጠራጥርም። በቆሮንቶስ የነበሩ የጳውሎስ ተማሪዎች በአካባቢያቸው የነበሩትን ጥንካሬ የሌላቸውን ቤቶች ያወደመውን ጥፋት የተቋቋሙትን ሕንፃዎች በየዕለቱ ሲያልፉ ሲያገድሙ ያዩ እንደነበር አያጠራጥርም። ስለዚህ ጳውሎስ ሊያጎላ የፈለገውን ነጥብ ግሩም በሆነ መንገድ ገልጾታል! በምናስተምርበት ጊዜ ራሳችንን እንደ ግንበኞች አድርገን ልንመለከት ይገባል። በተቻለ መጠን ምርጥና ጠንካራ በሆኑ ቁሳቁሶች ልንጠቀም እንፈልጋለን። በዚህ መንገድ ሥራችን ዘላቂነት ያለው የመሆን አጋጣሚ ሊኖረው ይችላል። ጠንካራ ቁሳቁስ የተባሉት ምንድን ናቸው? እነሱን መጠቀምስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ሥራችሁ እሳቱን ይቋቋም ይሆን?
12. አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ግዴለሽነት የሚታይበት የግንባታ ሥራ በማከናወን ላይ የነበሩት በምን መንገዶች ነው?
12 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኙ አንዳንድ ክርስቲያኖች መናኛ የሆኑ ግንባታዎችን እያካሄዱ እንዳሉ ተሰምቶት ነበር። ችግሩ ምን ነበር? የጥቅሱ ሐሳብ እንደሚያሳየው የጉባኤውን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ የሰዎችን ስብዕና በሚያወድሱ ግለሰቦች ጉባኤው ተከፋፍሎ ነበር። አንዳንዶች “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “እኔስ የአጵሎስ ነኝ” ይሉ ነበር። አንዳንዶች በራሳቸው ጥበብ ከሚገባው በላይ ተመክተው የነበሩ ይመስላል። በውጤቱም የሥጋዊ አስተሳሰብ አየር እንዲሰፍን፣ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዳይኖር እንዲሁም “ቅናትና ክርክር” እንዲበራከት ማድረጉ ምንም አያስደንቅም። (1 ቆሮንቶስ 1:12፤ 3:1–4, 18) እነዚህ አስተሳሰቦች በጉባኤና በአገልግሎት በሚሰጡ ትምህርቶች ላይ እንደሚንጸባረቁ አያጠራጥርም። በመሆኑም መናኛ በሆኑ ቁሳቁሶች እንደሚሠራ የግንባታ ሥራ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራቸው ግዴለሽነት የሚታይበት ነበር። ‘እሳቱን’ ሊቋቋም የማይችል ነበር። ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው እሳት ምንድን ነው?
13. በጳውሎስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው እሳት ምን ያመለክታል? ሁሉም ክርስቲያኖች ንቁ መሆን ያለባቸውስ ለምን ነገር ነው?
13 ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመን እሳት አለ። ይህም በእምነታችን ላይ የሚደርሱ ፈተናዎች ናቸው። (ዮሐንስ 15:20፤ ያዕቆብ 1:2, 3) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች፣ እውነትን የሚያስተምሩት እያንዳንዱ ሰው ወደፊት እንደሚፈተን ማወቅ አስፈልጓቸው ነበር። እኛም ብንሆን ይህን ማወቅ አለብን። በጥሩ ሁኔታ የማናስተምር ከሆነ ውጤቱ አሳዛኝ ይሆናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጐዳበታል፣ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል።”c—1 ቆሮንቶስ 3:14, 15
14. (ሀ) ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት አድራጊዎች ‘ጉዳት ሊደርስባቸው’ የሚችለው እንዴት ሊሆን ይችላል? ሆኖም በእሳት ውስጥ እንዳለፉ ሆነው መዳንን ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሊገጥመን የሚችለውን ጉዳት መቀነስ የምንችለው እንዴት ነው?
14 በእርግጥም ሊጤን የሚገባው አነጋገር ነው! አንድ ሰው ደቀ መዝሙር እንዲሆን ለመርዳት ብዙ ከደከምን በኋላ ግለሰቡ በፈተና ወይም በስደት ሲሸነፍ ብሎም ከእውነት መንገድ ሲወጣ መመልከት እጅግ የሚያሳዝን ሊሆን ይችላል። ጳውሎስም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ነገር መድረሱ ለገነባው ሰው ጉዳት መሆኑን ሲናገር ይህንኑ መግለጹ ነበር። ሁኔታው የሚያስከትልብን ሥቃይ ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል መዳናችን “በእሳት [“ውስጥ አልፎ፣” NW] እንደሚድን” ሰው ተደርጎ ተገልጿል። ይህም ንብረቱ ሁሉ ተቃጥሎበት ሕይወቱ ብቻ ከተረፈለት ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እኛ በበኩላችን የዚህ ዓይነቱን አሳዛኝ ሁኔታ መከሰት መቀነስ የምንችለው እንዴት ነው? ጠንካራ በሆኑ ቁሳቁሶች በመገንባት ነው! ተማሪዎቻችንን ልባቸውን በሚነካ መንገድ ካስተማርናቸውና እንደ ጥበብ፣ ማስተዋል፣ ይሖዋን መፍራትና እውነተኛ እምነት ማሳየት የመሳሰሉ ውድ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ የምናበረታታቸው ከሆነ ጠንካራ በሆኑና እሳትን መቋቋም በሚችሉ ቁሳቁሶች እየገነባን ነው ማለት ነው። (መዝሙር 19:9, 10፤ ምሳሌ 3:13–15፤ 1 ጴጥሮስ 1:6, 7) እነዚህን ባሕርያት ያዳበሩ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ይቀጥላሉ፤ እርግጠኛ የሆነው ለዘላለም ሕያው ሆኖ የመኖር ተስፋ የእነሱ ይሆናል። (1 ዮሐንስ 2:17) ሆኖም የጳውሎስን ምሳሌ ተግባራዊ ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከቱ።
15. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን በተመለከተ የግዴለሽነት የግንባታ ሥራ ከማከናወን ልንርቅ የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
15 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን በምናስተምርበት ጊዜ ትኩረታቸው ከይሖዋ አምላክ ይልቅ ወደ ሰዎች እንዲሆን ማድረግ አይገባም። ግባችን የጥበብ ምንጭ እኛ እንደሆን አድርገው እንዲመለከቱ ማስተማር መሆን የለበትም። መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ፣ ወደ ቃሉና ወደ ድርጅቱ ዘወር እንዲሉ እንፈልጋለን። በመሆኑም ለሚጠይቁን ጥያቄዎች የራሳችንን አስተያየት ከመስጠት እንቆጠባለን። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስንና “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመጠቀም መልሶችን እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ እናስተምራቸዋለን። (ማቴዎስ 24:45–47) በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ከእኛ ጋር ባላቸው ግንኙነት ብቻ እንዲወሰኑ ማድረግ የለብንም። ጥናቶቻችንን ሌሎች ሊቀርቧቸው ሲሞክሩ ቅር ከመሰኘት ይልቅ ጥናቶቻችን ራሳቸው ፍቅራቸውን ‘በማስፋት’ በተቻለ መጠን በጉባኤው ውስጥ ካሉት ወንድሞች ጋር እንዲተዋወቁና እንዲቀራረቡ ልናበረታታቸው ይገባል።—2 ቆሮንቶስ 6:12, 13
16. ሽማግሌዎች እሳትን መቋቋም በሚችሉ ነገሮች ሊገነቡ የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ደቀ መዛሙርትን በመገንባቱ ሥራ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። በጉባኤ ፊት ቆመው በሚያስተምሩበት ጊዜ እሳትን ሊቋቋሙ በሚችሉ ቁሳቁሶች ለመገንባት ይጥራሉ። የማስተማር ችሎታቸው፣ ተሞክሯቸውና ባሕርያቸው ይለያይ ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህን ልዩነቶች በመጠቀም ተከታዮች ለማፍራት አይጥሩም። (ከሥራ 20:29, 30 ጋር አወዳድር።) በቆሮንቶስ ይገኙ የነበሩ አንዳንዶች “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ወይም “እኔስ የአጵሎስ ነኝ” ይሉ የነበረው ለምን እንደሆነ በትክክል አናውቅም። ሆኖም ከእነዚህ ታማኝ ሽማግሌዎች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ እንዲህ ያለውን ከፋፋይ አስተሳሰብ እንዳላስፋፉ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስ እንዲህ ባሉት የስሜት መግለጫዎች አልተታለለም፤ በጽኑ አውግዟቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:5–7) በተመሳሳይም ዛሬ ያሉ ሽማግሌዎች በእረኝነት የሚጠብቁት “የእግዚአብሔርን መንጋ” መሆኑን አይዘነጉም። (1 ጴጥሮስ 5:2፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የማንም ሰው ንብረት አይደለም። ስለዚህ ሽማግሌዎች አንድ ሰው መንጋውንም ሆነ የሽማግሌዎችን አካል የመጫን አዝማሚያ እንዳይኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች ጉባኤውን ለማገልገል፣ ልብን ለመንካትና በግ መሰል ሰዎች ይሖዋን በሙሉ ነፍስ እንዲያገለግሉ ለመርዳት ቅን ፍላጎት ካላቸው እሳትን ሊቋቋሙ በሚችሉ ነገሮች ይገነባሉ።
17. ክርስቲያን ወላጆች እሳትን መቋቋም በሚችሉ ነገሮች ለመገንባት የሚጥሩት እንዴት ነው?
17 ይህ ጉዳይ ክርስቲያን ወላጆችንም በጥልቅ የሚያሳስብ ነው። ልጆቻቸው የዘላለም ሕይወት አግኝተው ለማየት በጣም ይጓጓሉ! ለዚህም ነው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ‘ለመቅረጽ’ ጠንክረው የሚሠሩት። (ዘዳግም 6:6, 7 NW) ልጆቻቸው እውነትን እንዲያውቁላቸው ይፈልጋሉ፤ እውነት እንዲያው የመመሪያዎች ክምችት ወይም የእውነታዎች ስብስብ እንደሆነ አድርገው ሳይሆን የተሟላ፣ የሚክስና የሚያስደስት የሕይወት መንገድ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይፈልጋሉ። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) አፍቃሪ ወላጆች ልጆቻቸው የታመኑ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑላቸው እሳትን መቋቋም በሚችሉ ነገሮች በመጠቀም ለመገንባት ይጥራሉ። ልጆቻቸው ይሖዋ የሚጠላቸውን ባሕርያት እንደ አረም ነቅለው እንዲጥሉና እሱ የሚወዳቸውን ባሕርያት ደግሞ እንዲያዳብሩ በመርዳት ከልጆቻቸው ጋር በትእግሥት ይሠራሉ።—ገላትያ 5:22, 23
በኃላፊነት የሚጠየቀው ማን ነው?
18. አንድ ደቀ መዝሙር ጤናማውን ትምህርት ቢተው ጥፋቱ ሊያስተምሩትና ሊያሰለጥኑት ጥረት ያደርጉ የነበሩት ሰዎች ነው ብሎ መደምደም የማይቻለው ለምንድን ነው?
18 ይህ ውይይት አንድ አስፈላጊ ጥያቄ እንዲነሣ ያደርጋል። ልንረዳው ጥረት እናደርግለት የነበረ ሰው እውነትን ቢተው በማስተማር ችሎታችን አልተዋጣልንም ወይም መናኛ በሆኑ ነገሮች ተጠቅመን ገንብተናል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። ደቀ መዛሙርትን በመገንባቱ ሥራ መካፈል ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑን የጳውሎስ ቃላት እንደሚያሳስቡን የተረጋገጠ ነው። አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል ጥሩ አድርገን ለመገንባት እንፈልጋለን። ሆኖም እንረዳቸው የነበሩ ሰዎች ከእውነት ዘወር በሚሉበት ጊዜ የአምላክ ቃል፣ ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ እንድንሸከምና በጥፋተኝነት ስሜት እንድንደቆስ እየነገረን አይደለም። ግንበኞች ሆነን ከምናከናውነው የሥራ ድርሻችን ጎን ለጎን የሚመጡ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ የማስተማር ችሎታው ጥራት ያልነበረውን አስተማሪ አስመልክቶ ሲናገር “ይጐዳበታል፣ እርሱ ራሱ ግን ይድናል” እንዳለ ልብ በሉ። (1 ቆሮንቶስ 3:15) ይህ ግለሰብ መጨረሻ ላይ ደህንነት የሚያገኝ ከሆነና በተማሪው ላይ ሊገነባ ይጥር የነበረው ክርስቲያናዊ ባሕርይ ግን በእሳታማ ፈተናዎች እንደ ‘ተቃጠለ’ ሆኖ ከተገለጸ ምን ብለን ለመደምደም እንገደዳለን? በእርግጥም የታማኝነት አካሄድ ለመከተል ወይም ላለመከተል በመምረጥ በግሉ ለሚወስዳቸው ውሳኔዎች ይሖዋ በዋነኝነት በኃላፊነት የሚጠይቀው ተማሪውን ነው።
19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንመረምረው ምንድን ነው?
19 በግል ተጠያቂ የመሆን ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እያንዳንዳችንን ይነካል። መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን ያስተምራል? የሚቀጥለው ርዕሳችን ይህን የሚመለከት ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ‘የምድር መሠረት’ የሚለው ሐሳብ ምድርን ደግፈው የያዟትን የተፈጥሮ ኃይላት እንዲሁም ቦታ ቦታቸውን ይዘው የሚገኙትን ሰማያዊ አካላት በሙሉ ሊያመለክት ይችላል። በተጨማሪም ምድር ራሷ የተሠራችው ለዘላለም “እንዳትናወጥ” ወይም እንዳትጠፋ ሆና ነው።—መዝሙር 104:5
b ጳውሎስ የጠቀሳቸው ‘የከበሩ ድንጋዮች’ የግድ እንደ አልማዝና ሩቢ ያሉ የከበሩ ማዕድናት መሆን የለባቸውም። እንደ እብነ በረድ የመሳሰሉ ለግንባታ የሚያገለግሉ በጣም ውድ ድንጋዮችም ሊሆኑ ይችላሉ።
c ጳውሎስ የመዳኑ ሁኔታ አጠራጣሪ ነው ያለው የሚገነባውን ሰው ሳይሆን ‘ሥራውን’ ነው። ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ጥቅሱን እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “የአንድ ሰው ሕንፃ ጸንቶ ከቆመ፣ ሽልማት ያገኝበታል። ከተቃጠለበት ግን ኪሳራውን ሊሸከም ይገባዋል፤ ቢሆንም ከእሳት እንደሚድን ሰው ሕይወቱን ብቻ ሊያተርፍ ይችላል።”
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ የአንድ እውነተኛ ክርስቲያን “መሠረት” ምንድን ነው? መሠረቱ የሚጣለውስ እንዴት ነው?
◻ የተለያየ ዓይነት የግንባታ ቁሳቁሶች መኖራቸው ምን ሊያስተምረን ይችላል?
◻ ‘እሳቱ’ ምንን ያመለክታል? በአንዳንዶች ላይ ‘ጉዳት ሊያደርስ’ የሚችለውስ እንዴት ነው?
◻ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፣ ሽማግሌዎችና ወላጆች እሳትን በሚቋቋሙ ቁሳቁሶች መገንባት የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በብዙ ጥንታዊ ከተሞች እሳትን መቋቋም የሚችሉ በድንጋይ የተገነቡ ሕንፃዎችና ደሳሳ ጎጆዎች ጎን ለጎን ይታዩ ነበር