የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 7/15 ገጽ 18-22
  • ፍቅራዊ ደግነትን ሁልጊዜ ተከታተል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፍቅራዊ ደግነትን ሁልጊዜ ተከታተል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ደግነት ራስ ወዳድ ከመሆን ጠብቆ እንግዳ ተቀባዮች ያደርገናል
  • ደግነት አሳቢዎች ያደርገናል
  • ደግነት ዝምድናን ያጠነክራል
  • ሴቶች ደግነት ሲያሳዩ
  • ፍቅራዊ ደግነትን መከታተልህን ቀጥል
  • እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ፍቅራዊ ደግነት አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • “የፍቅራዊ ደግነት ሕግ” አንደበታችሁን እንዲቆጣጠረው ፍቀዱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ከይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መጠቀም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ደግነት በማሳየት ይሖዋን አስደስት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 7/15 ገጽ 18-22

ፍቅራዊ ደግነትን ሁልጊዜ ተከታተል

“ጽድቅንና ምህረትን (ፍቅራዊ ደግነትን) የሚከታተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል።”​—ምሳሌ 21:21

1. በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሰዎች ደግነትን እንዲያሳዩ መጠበቅ ያለብን ለምንድነው?

ይሖዋ ደግና ርኅሩኅ ነው። እሱ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለብዙ [ፍቅራዊ ደግነትና] እውነት” የሆነ አምላክ ነው። (ዘዳግም 34:6, 7) እንግዲያውስ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ፍቅርንና ደግነትን ለምን እንደሚጨምር ሊገባን ይችላል።​—ገላትያ 5:22, 23

2. አሁን የምንመለከተው ምን ምሳሌዎችን ነው?

2 በይሖዋ መንፈስ ቅዱስ ወይም በአንቀሳቃሽ ኃይሉ የሚመሩ ሁሉ ከፍሬዎቹ አንዱ የሆነውን ደግነትን ያሳያሉ። ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ፍቅራዊ ደግነት ያሳያሉ። በእርግጥም “በደግነትና” በሌሎች መንገዶች ራሳቸውን እንደ አምላክ አገልጋዮች አድርገው በማቅረብ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ይከተላሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:3-10) የደግነት፣ የርኅራኄና የይቅር ባይነት መንፈሳቸው “ባለ ብዙ ፍቅራዊ ደግነት” ከሆነው ከይሖዋ ባሕርይ ጋር ይስማማል። ቃሉ ራሱ ብዙ የደግነት ምሳሌዎችን የያዘ ነው። (መዝሙር 86:15፤ ኤፌሶን 4:32) ከአንዳንዶቹ የደግነት ምሳሌዎች ምን ልንማር እንችላለን?

ደግነት ራስ ወዳድ ከመሆን ጠብቆ እንግዳ ተቀባዮች ያደርገናል

3. አብርሃም ደግነት በማሳየት በኩል ምሳሌ የነበረው እንዴት ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ ጳውሎስ ምን ማበረታቻ ሰጥቶናል?

3 “የይሖዋ ወዳጅ” ለሚያምኑ ሁሉ አባት” የሆነው የታላቅ ቤተሰብ አባት የነበረው አብርሃም (አብራም) ደግነትን በማሳየት መልካም ምሳሌ ትቶልናል። (ያዕቆብ 2:23፤ ሮሜ 4:11) እሱና ቤተሰቡ፣ የወንድሙ ልጅ ሎጥ ጭምር፣ በአምላክ ትዕዛዝ የከለዳውያንን ከተማ ዑርን ለቀው ወደ ከነዓን ገቡ። በዕድሜ የሚበልጠውና የቤተሰቡ ራስ የሆነው አብርሃም ቢሆንም ሎጥ ምርጥ የሆነውን ለም የግጦሽ መሬት እንዲወስድ በመፍቀዱና ለራሱ የተረፈውን በመውሰዱ ደግና ራስ ወዳድነት የሌለበት መሆኑን አሳይቷል። (ዘፍጥረት 13:5-18) ያው ዓይነት ደግነት እኛንም ሌሎች በእኛ ኪሳራ እንዲጠቀሙ እንድንፈቅድ ሊያነሳሳን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ራስ ወዳድነት የሌለበት ደግነት “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ” ከሚለው የጳውሎስ ምክር ጋር የሚስማማ ነገር ያደርጋል። ጳውሎስ ራሱ ‘ብዙዎች ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሱን ጥቅም ሳይፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ አሰኝቷል።’​—1 ቆሮንቶስ 10:24, 33

4. አብርሃምና ሣራ በእንግዳ ተቀባይነት መልክ ደግነትን በማሳየታቸው በአጸፋው የተባረኩት እንዴት ነው?

4 አንዳንድ ጊዜ ደግነት ከልብ የመነጨ የእንግዳ ተቀባይነትን መልክ ይይዛል አብርሃምን ሚስቱ ሣራ አንድ ቀን በመኖሪያቸው አጠገብ ያልፉ ለነበሩ ሦስት መንገደኞች ደጎችና እንግዳ ተቀባዮች ሆነዋል። እሱና ሣራ በጥድፊያ እንግዶቹን እንደምንም አግባብቶ ጥቂት ጊዜ እንዲቆዩ አደረገ፤ በኋላም እርሱና ሚስቱ ሣራ በችኰላ ለእንግዶቹ ምግብ አዘጋጁ። እነዚያ እንግዶች የይሖዋ መላዕክት ሆነው ተገኙ። ከእነሱም አንዱ ያረጀችውና መካኒቱ ሣራ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ የተስፋ ቃል ሰጣት። (ዘፍጥረት 18:1-15) በደግነት እንግዳ ተቀባይ በመሆናቸው በአጸፋው እንድት ዓይነት ካሣ አገኙ።

5. ጋይዮስ ደግነት ያሳየው በምን መንገድ ነበር? እኛስ ተመሳሳይ ነገር ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?

5 ሁሉም ክርስቲያኖች ደግነት ሊያሳዩ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ እንግዳ ተቀባይ መሆን ነው። (ሮሜ 12:13፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) በዚህ መሠረት የይሖዋ አገልጋዮች ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በደግነት የእንግዳ አቀባበል ያደርጋሉ። ይህም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኑ ጋልዮስ ያሳየውን ደግነት ያስታውሰናል። ጐብኚ ወንድሞችን በማስተናገድ “የታመነ ሥራ” ሠርቷል። እርሱ ያስተናገዳቸው ወንድሞች አንዳንዶቹ በፊት አይቷቸው አያውቅም ነበር። (3 ዮሐንስ 5-8) አብዛኛውን ጊዜ በደግነት እንግድነት የምንቀበላቸው የምናውቃቸውን ሰዎች ነው። ምናልባት አንዲት መንፈሳዊት እህት ተክዛ እንመለከት ይሆናል። የትዳር ጓደኛዋ የማያምን ወይም የተወገደ ሊሆን ይችላል። እሷን በጊዜው ከቤተሰባችን መንፈሳዊ ጓደኝነት እንድታገኝና አብራንም እንድትበላ ለመጋበዝ እንዴት ያለ ጥሩ አጋጣሚ ይኖረናል! ድግስ ባናዘጋጅም ለእንዲህ ዓይነቷ እህት ደግነት በማሳየት ቤተሰባችን ያለአንዳች ጥርጥር ደስታ ያገኛል። (ከምሳሌ 15:17 ጋር አወዳድር) እሷም አመስጋኝነቷን በቃልም ሆነ የምሥጋና ማስታወሻ በመጻፍ እንደምትገልጽ አያጠራጥርም።

6. ሊድያ ደግነት ያሳየችው እንዴት ነው? ለደግነት ሥራዎች አድናቆት ማሳየት ተገቢ የሆነው ለምንድነው?

6 ለአምላክ ያደረችው ሊድያ ከተጠመቀች በኋላ ጳውሎስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ‘በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ’ ወይም ሰንብቶ ብላ ለመነቻቸው። ሉቃስ በመጨመር ‘በግድም እንድንገባ አደረገችን’ ይለናል። ያለ ጥርጥር የሊድያ ደግነት አድናቆት አትርፏል። (ሥራ 16:14, 15, 40) አድናቆት ያለማሳየት ግን አጥፊ ሊሆን ይችላል። በአንድ ወቅት በጣም መጠነኛ የሆነ ጉልበትና ኑሮ ያላት አንዲት የ80 ዓመት ዕድሜ እህት ለጥቂት እንግዶች ምግብ አዘጋጀች። በተለይ አንዱ በዕድሜ አነስተኛ የሆነው ሰው መምጣት እንዳልቻለ ሳያስታውቃት በመቅረቱ አሳዘናት። በሌላ ወቅት ሁለት እህቶች አንዲት ወጣት ሴት በተለይ ለነሱ ባዘጋጀችው የምግብ ግብዣ ላይ ሳይገኙ ቀሩ። “አንዳቸውም ቢሆን ረስተው ስላልነበረ ቅስሜ ተሰበረ . . . ስለ ራት ጥሪው ረስተውት እንደሆነ ብሰማ እመርጥ ነበር። ከዚህ ይልቅ አንዳቸውም ለመንገር እንኳ ደግነትና ፍቅር አልነበራቸውም።” ታዲያ አንተስ በተመሳሳይ ሁኔታዎች አድናቂና አሳቢ እንድትሆን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነው ደግነት ይገፋፋሃል?

ደግነት አሳቢዎች ያደርገናል

7. ቀብርን በሚመለከት የያዕቆብን ፈቃድ ለመፈጸም በተደረገው ጥረት ስለደግነት የተገለጸው ነጥብ ምንድነው?

7 ደግነት ለሌሎች ሰዎችና ለተገቢ ምኞቶቻቸው አሳቢዎች እንድንሆን ያደርገናል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ያዕቆብ (እሥራኤል) ልጁን ዮሴፍን ‘ከሞትኩ በግብጽ ምድር ባለመቅበር ፍቅራዊ ደግነት አድርግልኝ’ ብሎ ጠየቀው። ይህም የያዕቆብን አስከሬን እስከ ሩቅ ቦታ ተሸክሞ መውሰድን የሚጠይቅ ቢሆንም ዮሴፍና ሌሎቹ የያዕቆብ ልጆች “ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት። ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻ ቀበሩት። እሷም በመምሬ ፊት ያለችው አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያውያን ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት።” (ዘፍጥረት 47:29፤ 49:29-31፤ 50:12, 13) ከዚያ ምሳሌ ጋር በመስማማት አንድ ክርስቲያን የሆነ የቤተሰባችን አባል የተመኘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ተቀባይነት ያለው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንድንፈጽም ፍቅራዊ ደግነት ሊገፋፋን አይገባምን?

8. የረዓብ ታሪክ ለደግነት ብድራት ስለመክፈል ምን ያስተምረናል?

8 ሌሎች ፍቅራዊ ደግነት ሲያሳዩን አድናቆታችንን መግለጽ ወይም በሆነ መንገድ ወሮታውን መመለስ አይገባንምን? በእርግጥ ይገባናል። ጋለሞታይቱ ረአብ እሥራኤላውያኑን ሰላዮች በመደበቅ ፍቅራዊ ደግነት አሳየች። ስለዚህ እሥራኤላውያን የኢያሪኰን ከተማ ሲያጠፉ እሷንና ቤተሰቧን በማዳን ፍቅራዊ ደግነት አሳዩአት። (ኢያሱ 2:1-21፤ 6:20-23) ራሳችን አሳቢዎችና ደጎች በመሆን ለደግነት ውለታ መመለስ እንደሚገባን የሚያመለክት ግሩም ምሳሌ ነው!

9. አንድ ሰው ፍቅራዊ ደግነት እንዲያሳየን መጠየቅ ተገቢ ነው የምትለው ለምንድነው?

9 ይህ ከተነሣ ዘንድ ሰው ለእኛ ፍቅራዊ ደግነት እንዲያሳይ መጠየቅ ተገቢ ነው። የእሥራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ የሳዖል ልጅ ዮናታን እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ አቅርቧል። ዮናታን የሚወደውን ወጣት ወዳጁን ዳዊትን ለሱና ለቤተሰቡ ፍቅራዊ ደግነት እንዲያደርግለት ጠየቀው። (1 ሳሙኤል 20:14, 15፤ 2 ሳሙኤል 9:3-7) ሳዖል ግፍ የፈጸመባቸውን ገባዖናውያንን ሲበቀላቸው ዳዊት ዮናታንን አስታውሷል። በእሱና በዮናታን መካከል የነበረውን “የይሖዋ መሐላ” በማስታወስ ዳዊት የዮናታንን ልጅ የሜምፊቦስቴን ሕይወት በማትረፍ ፍቅራዊ ደግነት አድርጓል። (2 ሳሙኤል 21:7, 8) እኛስ እንደዚሁ “አዎናችን አዎን” ነውን? (ያዕቆብ 5:12) የጉባኤ ሽማግሌዎች ብንሆን የእምነት ጓደኞቻችን ተመሳሳይ ፍቅራዊ ደግነት ልናሳያቸው በሚያስፈልግበት ጊዜ ርኅራኄ እናሳያለንን?

ደግነት ዝምድናን ያጠነክራል

10. የሩት ፍቅራዊ ደግነት በረከት ያስገኘው እንዴት ነበር?

10 ፍቅራዊ ደግነት የቤተሰብን ዝምድና ወይም አንድነት ያጠነክራል። ደስታንም ይጨምራል። ይህም በሞዓባዊቱ ሩት ሁኔታ ታይቷል። ሩት ለራሷና ባሏ ለሞተባት ድሃ አማቷ ለናዖሚ ቀለብ ለማቅረብ በቤተልሔም አጠገብ ባለው በዕድሜ ሸምገል ባለው በቦኤዝ እርሻ በመቃረም ትደክም ነበር። (ሩት 2:14-18) ቦኤዝ በኋላ ለሩት እንዲህ አላት፦ “ባለጠጋም ድሃም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ [ፍቅራዊ ደግነት] አድርገሻል።” (ሩት 3:10) በመጀመሪያ ሩት ለናዖሚ ፍቅራዊ ደግነት አሳይታ ነበር። “በመጨረሻው ጊዜ” ደግሞ ሞዓባዊቷ ለሞተው የባሏንና ያረጀችውን የናዖሚን ስም ለማስጠራት ስትል በዕድሜ የሸመገለውን ቦኤዝን ለማግባት ፈቃደኛ በመሆን ፍቅራዊ ደግነት አሳየች። በቦኤዝ በኩል ሩት የዳዊት አያት የሆነው የኢዮቤድ እናት ለመሆን ቻለች። አምላክም የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆንን “ፍጹም ደመወዝ” ሰጣት። (ሩት 2:12፤ 4:13-17፤ ማቴዎስ 1:3-6, 16፤ ሉቃስ 3:23, 31-33) የሩት ፍቅራዊ ደግነት ለሷና ለቤተሰቧ እንዴት ዓይነት በረከት ሆነ! በአሁኑ ጊዜም አምላካዊ በሆኑ ቤቶች (ቤተሰቦች) ውስጥ ፍቅራዊ ደግነት ሲያብብ በረከትና ደስታ ይኖራሉ፤ የቤተሰቡም መተሳሰር ይጠናከራል።

11. የፊልሞና ደግነት ምን ውጤት አስከተለ?

11 ደግነት በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ ያለውን መተሳሰር ያጠነክረዋል። ፊልሞና የተባለው ክርስቲያን ለእምነት ጓደኞቹ ፍቅራዊ ደግነት በማሳየት የታወቀ ሰው ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ብሎታል፦ “በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ። . . . የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስላረፈ ወንድሜ ሆይ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቻለሁና።” (ፊልሞና 4-7) የቅዱሳን ልብ በፊልሞና እንዴት እንዳረፈ ቅዱሳን ጽሑፎች አይነግሩንም። ይሁን እንጂ መንፈስን በሚያነቃቃ በተለያየ መንገድ ለቅቡዓን ጓደኞቹ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቶ መሆን አለበት። ይህም ያለጥርጥር በመካከላቸው የነበረውን መተሳሰር አጠናክሮታል። በአሁኑ ጊዜም ክርስቲያኖች ፍቅራዊ ደግነት ሲያሳዩ ተመሳሳይ ነገር ይፈጸማል።

12. በሄኔሲፎሩ ከተገለጸው ደግነት ምን ተገኘ?

12 የሄኔሲፎሩ ደግነትም ጥሩ ውጤት ነበረው። ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምህረትን ይስጥ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤ በሰንሰለቴም አላፈረበትም። ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ። በዚያን ቀን ከጌታ ምህረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው በኤፌሶንም እንዴት እንዳገለገለኝ አንተ በደህና ታውቃለህ።” (2 ጢሞቴዎስ 1:16-18) የይሖዋ አምላኪዎች ለሆኑት መሰሎቻችን ፍቅራዊ ደግነትን ለማሳየት ከጣርን ደስተኞች እንሆናለን፤ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም የወንድማማች መዋደድን እናጠነክራለን።

13, 14. የፊልጵስዩስ ጉባኤ ጥሩ አርዓያ የነበረው እንዴት ነው? ጳውሎስስ ለጉባኤው አድራጎት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

13 መላው ጉባኤ ለአምልኰ ጓደኞች ፍቅራዊ ደግነት ሲያሳይ ይህ በመካከላቸው ያለውን መተሳሰር ያጠነክረዋል። እንዲህ ዓይነት የቅርብ መተሳሰር በጳውሎስና በፊልጵስዩስ ከተማ በነበረችው ጉባኤ መካከል ተፈጥሮ ነበር። እንዲያውም ለፊልጵስዩስ ሰዎች ደብዳቤ ከጻፈበት ምክንያት አንዱ ለደግነታቸውና ለቁሳዊ እርዳታቸው ምስጋናውን ለመግለጽ ሲል ነበር። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ። በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። . . . ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል። የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ።”​—ፊልጵስዩስ 4:15-18

14 ደጐቹ የፊልጵስዩስ ሰዎች በጳውሎስ ጸሎት ሁልጊዜ የሚታሰቡ መሆናቸው እንግዲያውስ አያስደንቅም። እንዲህ አለ፦ “ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለሠራችሁ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ።” (ፊልጵስዩስ 1:3-5) እንዲህ ዓይነቱ ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ የሚደረግ ደግነትና ለጋስነት የተሞላበት ድጋፍ አንድን ጉባኤ ፈጽሞ ድሃ አያደርገውም። የፊልጵስዩስ ሰዎች በዚህ ረገድ የሚቻላቸውን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ጳውሎስ እንዲህ በማለት አረጋገጠላቸው፦ “አምላኬም እንደ ባለጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል።” (ፊልጵስዩስ 4:19) አዎን አምላክ የደግነትንና የለጋስነትን ውለታ መልሶ ይከፍላል። ቃሉ “እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድር እንዲቀበለው ታውቃላችሁና” ይላል።​—ኤፌሶን 6:8

ሴቶች ደግነት ሲያሳዩ

15, 16. (ሀ) የዶርቃ ደግነት የታሰበው እንዴት ነበር? በሞተች ጊዜስ ምን ሆነ (ለ) ዛሬ ያሉ ደግ ክርስቲያን ሴቶች መልካም ሥራ የሞላባቸው እንዴት ነው?

15 የደቀመዝሙሯ የኢዮጴይቱ ዶርቃ (ጣቢታ) ፍቅራዊ ደግነት ወሮታውን መልሶ ሳያገኝ አልቀረም። “እርስዋ መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች።” ‘በታመመችና በሞተች ጊዜ’ ደቀመዛሙርት ጴጥሮስን ለማስመጣት ወደ ልዳ ላኩ። እንደደረሰም “ወደ ሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ።” ትዕይንቱን እስቲ በዓይነ ህሊናህ ተመልከተው፦ ያዘኑና እንባ የተሞሉ መበለቶች ዶርቃ እንዴት ደግ እንደነበረች ነገሩትና ለፍቅሯና ለደግነቷ ማስረጃ እነዚህን ልብሶች ሁሉ አሳዩት። ሁሉንም ካስወጣ በኋላ ጴጥሮስ ለጸሎት ተንበረከከና ወደ አስከሬኑ ዘወር አለ። አዳምጥ! “ጣቢታ ሆይ ተነሽ” ለ። ተመልከት! “እርሷም ዓይኖቿን ከፈተች፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ። ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት።” (ሥራ 9:36-41) ይህስ ከአምላክ እንዴት ያለ በረከት ነበር!

16 በአንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የተፈጸመ ትንሣኤ በመዝገብ ላይ ከሠፈሩት የመጀመሪያው ይህ ነበር። ወደዚህ አስደናቂ ተአምር የመሩት ሁኔታዎች የተመሠረቱት በደግነት ላይ ነበር። ዶርቃ መልካም ሥራዎችና የምህረት ስጦታዎች ባለቤት ባትሆን ኖሮ ማለትም ፍቅራዊ ደግነት የሞላባት ባትሆን ኖሮ ወደ ሕይወት እንደምትመለስ ማለትም ትንሣኤ እንደምታገኝ ማን ሊናገር ይችላል? የዶርቃስ ትንሣኤ ተአምር ለእሷና ለመበለቶቹ በረከት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአምላክ ክብርም ምሥክርነት ሰጥቷል። አዎን “ይህም በኢዮጴ ሁሉ የታወቀ ሆነ። ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ።” (ሥራ 9:42) ዛሬም ለእምነት ጓደኞች ልብስ መስፋትም ሆነ በመካከላችን ለሚገኙ በዕድሜ ለገፉ ምግብ በማዘጋጀት፣ እንዲሁም ለሌሎች እንግድነት አቀባበልን የሚዘረጉ ደግ ክርስቲያን ሴቶች በመልካም ሥራ የተሞሉ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10) ይህን ለተመልካቾች እንዴት ያለ ምሥክርነት ነው! ከሁሉ ይበልጥ ይህ “ታላቅ የሴቶች ሠራዊት ለአምላካችን ለይሖዋ ክብር የምሥራች እንዲናገሩ” ለአምላክ ያደሩ መሆንና ፍቅራዊ ደግነት የሚገፋፋቸው በመሆኑ እንዴት ደስ ይለናል!​—መዝሙር 68:11

ፍቅራዊ ደግነትን መከታተልህን ቀጥል

17. በምሳሌ 21:21 ላይ ምን ተብሏል? እነዚያ ቃላትስ ለአምላካዊ ግለሰቦች የሚሠሩት እንዴት ነው?

17 የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ፍቅራዊ ደግነትን መከታተል አለባቸው። “ጽድቅን [ፍቅራዊ ደግነትን አዓት] የሚከተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል” ይላል ጥበብ የተሞላበት ምሳሌ። (ምሳሌ 21:21) አምላካዊ የሆነ ሰው የአምላክን ጽድቅ በትጋት ይከታተላል፤ ሁልጊዜ በመለኰታዊ የአቋም ደረጃዎች ይመራል። (ማቴዎስ 6:33) ለሌሎች በቁሳዊና በተለይ ደግሞ በመንፈሳዊ መንገዶች ባለማቋረጥ ታማኝ ፍቅር ወይም ፍቅራዊ ደግነት ያሳያል። በመሆኑም ጽድቅን ያገኛል፤ ምክንያቱም የይሖዋ መንፈስ በጽድቅ መንገድ እንዲኖር ይረዳዋል። እንዲያውም አምላካዊ እንደነበረው እንደ ኢዮብ “ጽድቅን ይለብሳል።” (ኢዮብ 29:14) እንደዚህ ዓይነት ሰው የራሱን ክብር ፈላጊ አይደለም። (ምሳሌ 25:27) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲቀበል የፈቀደለትን ማንኛውንም ክብር ያገኛል። ይህም ምናልባት ፍቅራዊ ደግነት ያደረገላቸው ሰዎች ለሱም በደግነት ውለታ እንዲመልሱለት በአምላክ ተገፋፍተው በሚሰጡት ክብር አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ በታማኝነት የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ብልጭ ብለው ለሚጠፉ ዓመታት ሳይሆን ለዘላለም ሕይወትን ያገኛሉ።

18. ፍቅራዊ ደግነትን መከታተል ያለብን ለምንድነው?

18 ስለዚህ ይሖዋ አምላክን የሚወዱ ሁሉ ፍቅራዊ ደግነትን መከታተላቸውን ይቀጥሉ። ይህ ባሕርይ በአምላክና በሌሎች ዘንድ ያስወድደናል። እንግዳ ተቀባይ መሆንን ያበረታታል፤ አሳቢዎችም ያደርገናል። ደግነት በቤተሰብ ውስጥና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍቅራዊ መተሳሰርን ያጠነክራል። ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳዩ ሴቶች አድናቆትንና ከፍ ያለ ክብርን ያገኛሉ። ይህን ግሩም ባሕርይ የሚከታተሉ ሁሉ የፍቅራዊ ደግነት ባለቤት ለሆነው አምላክ ለይሖዋ ክብርን ያመጣሉ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ አብርሃም ደግነትን በማሳየት በኩል ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

◻ የረዓብ ታሪክ ለደግነት ብድር ስለመመለስ ምን ያስተምረናል?

◻ የፊልጵስዩስ ጉባኤ ደግነት ያሳየው እንዴት ነው?

◻ በአሁኑ ጊዜ ደግ ክርስቲያን ሴቶች በመልካም ሥራ የተሞሉት እንዴት ነው?

◻ ፍቅራዊ ደግነትን መከታተል ያለብን ለምንድን ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ