ስለ ሰላምና ደኅንነት መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት
ብዙ ሰዎች በግልጽ እየታየ ያለውን ወደ ከፍተኛ የዓለም አንድነትና በእርሱም ምክንያት የሚገኘውን ሰላምና አስተማማኝ ኑሮ የማምጣት አዝማሚያ አምነው እየተቀበሉት ነው። እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ወደተሻለ ዓለም እንደሚመራ ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በውጭ የሚታየው መልክ በቂ ያለመሆኑን ያመለክታል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረ አንድ የክርስቲያን ጉባኤ በጻፈው ነገር ምክንያት የሰላምና የደኅንነት ጉዳይ በተለይ የክርስቲያኖችን ስሜት የሚስብ ነው። እርሱ የተናገራቸው ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ1 ተሰሎንቄ 5:3 ላይ እንደሚከተለው ተመዝግበው ይገኛሉ፦ “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” ይህ ጥቅስ ትልልቅ ጥያቄዎችን ያስነሣል።
ሰላምና ደኅንነት—የምን ነገር ዋዜማ ነው?
ከላይ በተጠቀሱት የጳውሎስ ቃላት ዙሪያ ያሉትን አሳቦች ብታነብ “ሰላምና ደኅንነት” እያሉ የሚናገሩት በጣም ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች ሳይሆኑ በእውን እየተፈጸመ ላለው ነገር ያንቀላፉት ሰዎች መሆናቸውን ትመለከታለህ። እነርሱ የሚገኙት በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው፤ ሆኖም ነገሮች እየተሻሻሉ እንደሆኑ አድርገው ስለሚያስቡ ይህን አልተገነዘቡትም። ክርስቲያኖችን በሚመለከት ግን ጳውሎስ “ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም” ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 5:1) አዎን፣ አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበትን የጊዜ ሰሌዳ መገንዘብ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም “የይሖዋ ቀን” ተብሎ የሚጠራ ድንገተኛ ጥፋት የሚሆንበት ጊዜ ልክ ‘እንደ ሌሊት ሌባ’ ይመጣል ሲል ጳውሎስ ተናግሯል።—1 ተሰሎንቄ 5:2
ይመጣል ተብሎ አስቀድሞ የተነገረለት የሰላምና የደኅንነት ንግግር ምንን ይጨምራል? ነገሩ በንግግር ብቻ እንደሚያበቃ ግልጽ ነው። የሰላም ውይይት የጦርነትን ያህል ለብዙ ዘመናት የቆየ ነገር ነው። የጳውሎስ ቃላት የሚያመለክቱት ግን ብሔራት በአንድ አስገራሚ መንገድ ሰላምንና አስተማማኝ ኑሮን ያገኙ የሚመስሉበትን ጊዜ መሆን ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ይህ ውጫዊ መልክ ብቻ ይሆናል። ወደ ድንገተኛ ጥፋት የሚመራው የሚታይ ሰላምና አስተማማኝ ኑሮ እውነተኛ ሰላም ወይም እውነተኛ አስተማማኝ ኑሮ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ኢየሱስም ስለዚህ ድንገተኛ ጥፋት ተናግሯል። ይህንንም “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ” ሲል ጠርቶታል። ከኢየሱስ አያሌ ዓመታት ቀደም ብሎ ነቢዩ ዳንኤልም ስለዚህ ጥፋት ተናግሮ ነበር፤ እርሱም “ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን” ሲል ገልጾታል።—ማቴዎስ 24:21፤ ዳንኤል 12:1
ታላቅ መከራም ይባል የመከራ ዘመን በትንቢቶቹ መሠረት የሰይጣንን ምድራዊ ሥርዓት በሙሉ ይጠራርጋል። ይህ በትንቢት የተነገረለት የሰላምና የደኅንነት ንግግር መለኮታዊውን ተቀባይነት ከማግኘት ይልቅ የሚያስከትለው ተቃራኒውን ውጤት ይሆናል።—ከሶፎንያስ 3:8 ጋር አወዳድር
ነገሮች የሚፈጸሙባቸው ጊዜያት ተገለጡ
በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ የዓለም አንድነትና እርሱ የሚያስከትላቸውን ሰላምና አስተማማኝ ኑሮ ለማግኘት የተደረጉት ግልጽ እንቅስቃሴዎች የጳውሎስ ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ ናቸውን? ይህ መጽሔት በተደጋጋሚ እንዳመለከተው ከ1914 ጀምሮ ኢየሱስ በሰማይ መንግሥታዊ ሥልጣን ይዞ ከመገኘቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ ተመልክተናል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ራእይ 6:1-8) ኢየሱስ በክፉዎች ላይ ድንገተኛ ጥፋት የሚመጣበት የይሖዋ ቀን፣ ይህ ትንቢት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈጸም ያየው ትውልድ አባላት ገና በሕይወት እያሉ እንደሚመጣ አመልክቷል።—ሉቃስ 21:29-33
ሐዋርያው ጳውሎስም ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ጠቁሟል። እንዲህ አለ፦ “ስለ ሰላምና ደኅንነት ሲናገሩ ጥፋት በአንድ ጊዜ ይመጣባቸዋል።” ይህ በኒው ኢንግሊሽ ባይብል ላይ የተተረጎመ የጳውሎስ ቃል ታላቁ መከራ የሚሆነው “ገና እየተናገሩ እያሉ” መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ልክ በሌሊት እንደሚመጣ ሌባ፣ የአብዛኞቹ ሰዎች ትኩረት ተስፋ በተደረገበት ሰላምና ደኅንነት ላይ እያለ ድንገተኛ የሆነው ጥፋት ባልተጠበቀበት ሰዓት ይመጣል። እንግዲያው ለጊዜው አሁን ያለው የሰላምና የደኅንነት ሁኔታ የጳውሎስ ቃላት ፍጻሜ ነው ብለን ለመደምደም ወይም የሰላምና የደኅንነቱ ንግግር ገና እስከ ምን ያህል እንደሚቀጥል ለመናገር ባንችልም ይህ ንግግር እስከ ዛሬ ተደርጎ በማይታወቅ መጠን እየተሰማ መሆኑ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ነቅተው የመጠበቅን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ነው።
በዓለም ኃያላን መካከል የሚደረግ ‘መገፋፋት’
ነቢዩ ዳንኤል ስለ መከራ ዘመን ሲናገር ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ጠቅሷል። የመከራ ዘመን የሚሆነው “የሰሜን ንጉሥ” ተብሎ በሚጠራውና “የደቡብ ንጉሥ” ተብሎ በሚጠራው ሁለት ኃይሎች መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው ግጭት በሚያበቃበት ጊዜ ላይ እንደሆነ አሳይቷል። (ዳንኤል 11:5-43) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እነዚህ ሁለት ኃይሎች በካፒታሊስቱ “የደቡብ ንጉሥ” እና በሶሻሊስቱ “የሰሜን ንጉሥ” ተወክለዋል።
ዳንኤል በእነዚህ ሁለት ኃይሎች መካከል የሚኖረውና ባለፉት 45 ዓመታት የታየው መራራ ተቀናቃኝነት ልክ የነፃ ትግል ታጋዮች የበላይነትን ለማግኘት እንደሚጣጣሩት የመሰለ “መገፋፋት” እንደሚሆን ተንብዮ ነበር። በቅርቡ ግን መገፋፋቱ እየቀነሰ የሄደ ይመስላል። በዚህም ምክንያት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የሶቪየቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቀዝቃዛው ጦርነት አልፏል ብለው አውጀዋል። በሰኔ ወር የወጣው ታይም መጽሔት በዩናይትድ ስቴትስና በሶቪየት ኅብረት መካከል የተደረገውን ልዩ ስብሰባ በመጥቀስ እንዲህ ሲል ገልጾ ነበር፦ “በጦር መሣሪያ ቁጥጥርና የኑክሌር ሙከራን በተመለከተ የተደረሰባቸው አንዳንድ ስምምነቶች ከጥቂት ዓመታት በፊት የማይሆኑ ክንውኖች መስለው ይታዩ ነበር። አሁን በአጠቃላይ ሲወሰዱ የመጨረሻውን ወሳኝ ግጭት ያስቀሩት መስለው ይታያሉ።”
ይህ በኃያላን መንግሥታት መካከል የሚታየው ወዳጅነት ጊዜያዊ ይሁን ዘላቂ ጊዜ ያሳየናል። ሆኖም አንድ ነገር ግልጽ ነው። ኢየሱስ የጠቀሰው ዘመን በጣም ወደፊት ገፍቷል። በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ያሉትም ሁኔታዎች ሐዋርያው ጳውሎስና ነቢዩ ዳንኤል ወደ ተነበዩአቸው ነገሮች እንደቀረብን ያመለክታሉ። በቅርብ ጊዜያት የታዩት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በተወሰነ ደረጃ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እጅ ያለባቸው ቢሆኑም ወደ ዘላቂ ሰላም የሚመሩ አይሆኑም። በማስረጃው መሠረት የዚህን ዓለም ብሔራት ወደ ተቃራኒው የሚመሩ ይሆናሉ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በሁለቱ ኃያላን መካከል ያለው የማስመሰያ ወዳጅነት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚዘልቅ ጊዜ ያሳየናል
[ምንጭ]
USSR Mission to the UN