የኑክሌር ስጋት ለዘለቄታው ይወገዳል!
አምላክ የሰው ዘር የፍርሃትን ማቅ ተከናንቦ እንዲኖር አይፈልግም። “ደስተኛ አምላክ” እንደመሆኑ መጠን ሰዎች ሰላምን እንዲያገኙና ተረጋግተው እንዲኖሩ ይፈልጋል፤ በአጭሩ ደስተኛ እንዲሆኑ ፍላጎቱ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) በኑክሌር ስጋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ግን ይህ የማይቻል ነው።
የይምሰል “ሰላምና ደህንነት”
የኑክሌር ስጋት አሁንም እንዳለ በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል። እስከ አሁንም ድረስ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መረጋጋት ባይኖርም መንግሥታት በጥቅሉ በወደፊቱ ጊዜ ላይ ተስፋቸውን የጣሉ ይመስላሉ። የተባበሩት መንግሥታት 1986ን ዓለም አቀፍ የሰላም ዓመት ብሎ ከሰየመው ወዲህ ስጋቱ እንዲከስም ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
ዘ ቡለቲን ኦቭ ዘ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው መጽሔት የኑክሌር ጦርነት ሊነሣ እንደሚችል የሚጠቁመውን የጥፋት ቀን ሰዓቱን ባለፉት አሥርተ ዓመታት ወደኋላ በመመለስ ለእኩለ ሌሊት (የኑክሌር ጦርነት ሊፈነዳ) 3 ደቂቃ ጉዳይ የነበረውን 17 ደቂቃ ጉዳይ አድርጎታል። በ1989 የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እልባት ለማግኘት ያለው ተስፋ ከየትኛውም ዓመት የተሻለ ጠንካራ መሠረት አለው” በማለት አመልክቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፋዊ ችግር በፈጠሩ የጦርነት አካባቢዎች አንዳንድ እርምጃዎችን ለመውሰድ አቋሙን አጠናክሯል። ምንም እንኳ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ጥረቱ የሰመረለት መሆኑ አጠቃላይ የሆነ ተስፋ የማድረግ መንፈስ እንዲኖር ለማድረግ አስችሎታል። የወደፊቱ ጊዜ ሌሎች አዳዲስ የታሪክ ምዕራፎችን ይከፍት ይሆናል። የ“ሰላምና ደህንነት” ልፈፋ ሊያይልና ሊጧጧፍ ይችላል። እንዲያውም እምነት የሚጣልበት እስከመሆን ደረጃ ሊደርስ ይችላል።
ነገር ግን ተጠንቀቁ! መጽሐፍ ቅዱስ “ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም” በማለት ያስጠነቅቃል። ስለዚህ የ“ሰላምና ደህንነት” ልፈፋ አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፉትን [በኑክሌርና በሌሎች ነገሮች የሚበክሉትን] የሚያጠፋበት’ ጊዜ መድረሱን የሚያሳይ ምልክት ይሆናል።—1 ተሰሎንቄ 5:3, 4፤ ራእይ 11:18
መጽሐፍ ቅዱስ መንግሥታት “ሰላምና ደህንነት”ን ይጨብጣሉ እንደማይል ልብ በል። ቀደም ሲል ያልነበራቸውን ተስፋና ትምክህት በመግለጽ ሆኖ በማያውቅ መንገድ ስለ ሰላምና ደህንነት ይናገራሉ። ሰላምንና ደህንነትን መጨበጥ የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች በወቅቱ ከምን ጊዜውም በበለጠ የተቃረቡ ይመስላሉ። የኑክሌር ስጋት እንዳለ ቢቀጥልም መንግሥታት በይስሙላ ደህንነት ይዘናጋሉ።
እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን አይታለሉም። የሰው ልጅ ለማምጣት ከሚዳክርለት ሰላምና ደህንነት የተሻለ ነገርን በከፍተኛ ስሜት አሻግረው ይመለከታሉ!
እውነተኛ ሰላምና ደህንነት
መዝሙር 4:8 በሚለው መሠረት እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ሊገኝ የሚችለው በይሖዋ አምላክ ዝግጅት ብቻ ነው፦ “በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፣ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።” ከይሖዋ መንግሥት ዝግጅት ውጪ የሆነ ማንኛውም የ“ሰላምና ደህንነት” ልፈፋ እንዲያው ለይስሙላ የሚደረግ ብቻ ነው። አንዳችም ዓይነት ዘላቂ ስኬት ሊኖረው አይችልም።
በክርስቶስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት ያልተሟላ መፍትሔን በማምጣት አትረካም። መለኮታዊ መንግሥት የኑክሌር መሣሪያዎችን ከመቀነስ የበለጠ ነገርን ታደርጋለች፤ እነርሱንም ሆነ ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን በሙሉ ጠራርጋ ታጠፋለች። መዝሙር 46:9 “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል” በማለት የተስፋ ቃል ይሰጣል።
ልክ እንደዚሁም የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች የሚያጋጥማቸው ብልሽትም ሆነ የሬዲዮአክቲቭ ጨረር ዝቃጮች ያስከተሉት የኑክሌር ስጋት ጊዜ ያለፈበት ይሆናል። አለዚያማ የሚከተለው ቃል ሐሰት ሊሆን ነው፦ “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርም አፍ ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።” አምላክ አይዋሽም። ቃሉን የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም።—ሚክያስ 4:4፤ ቲቶ 1:2
የኑክሌር ስጋት ለዘለቄታው በተወገደበት ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ተስፋ ብታገኝ ደስ ይልህ ነበርን? የአምላክ ቃል ለዚህ የሚያበቁትን ነገሮች ቁልጭ አድርጎ ያሰፈራቸው በመሆኑ ይህ ተስፋ ሲፈጸም ለማየት ትችላለህ። ስለ ብቃቶቹ በመማርና ከብቃቶቹ ጋር ተስማምተህ በመኖር አንድ ቀን እፎይ ተገላገልን፤ “የኑክሌር ስጋት በመጨረሻ አከተመለት!” በማለት ልትደሰት ትችላለህ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰላም ማንኛውም ዓይነት የኑክሌር ስጋት በሌለበት የአምላክ አዲስ ዓለም ላይ ድንኳኑን ይዘረጋል
[ምንጭ]
M. Thonig/H. Armstrong Roberts
[ምንጭ]
U.S. National Archives photo