የኑክሌር ስጋት አክትሞለታልን?
“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ሰላም በምድር ላይ የሚሰፍንበት የተሻለ ጊዜ አሁን የመጣ ይመስላል።” በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ በአንድ የዜና አቀባይ የተሰነዘረው ይህ ተስፋ የጦር መሣሪያ ቅነሳ ስምምነቶችና ያልተጠበቁ ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጦች በመጨረሻ ቀዝቃዛው ጦርነት እንዲያከትም ማስቻላቸውን በማስመርኮዝ የተነገረ ነበር። ይሁን እንጂ የቀድሞው ልዕለ ኃያል አገር ከባላንጣው ጋር ለነበረው ፍጥጫ ዋነኛ መንስኤ የነበረው የኑክሌር ስጋት አብሮ አክትሞለታልን? ዘላቂ የሆነ ሰላምና ደህንነትን መጨበጥ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷልን?
የኑክሌር መሣሪያ ያላቸው አገሮች መጨመር የሚያስከትለው አደጋ
በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ልዕለ ኃያላኑ አገሮች እርስ በእርስ ተፈራርቶ መኖር ሰላምን እንደሚፈጥር በማመን የኑክሌርን ኃይል ለሰላማዊ ግልጋሎት ለማዋል የሚፈልጉ አገሮች የኑክሌር እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ፈቅደውላቸው ነበር። ሆኖም የኑክሌር መሣሪያ መሥራት የሚችሉ አገሮችን ቁጥር ለመገደብ ተስማምተው ነበር። በ1970 የኑክሌር መሣሪያን መዛመት የሚያግደው ውል በሥራ ላይ ዋለ። ከጊዜ በኋላም ይህንኑ ውል 140 አገሮች ፈርመዋል። ሆኖም ኑክሌር የመሥራት አቅም ያላቸው እንደ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ህንድና እስራኤል የመሳሰሉ አገሮች እስከ አሁንም ድረስ ይህን ውል ለመፈረም አሻፈረኝ ብለዋል።
ይሁን እንጂ በ1985 የኑክሌር መሣሪያ የመሥራት አቅም ያላት ሌላ አገር ማለትም ሰሜን ኮርያ ውሉን ፈርማ ነበር። ሆኖም መጋቢት 12, 1993 ውሉን ማፍረሷ ይፋ ሲደረግ የዓለም ሕዝብ መደናገጡ አልቀረም። ዴር ሼፊጌል የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “የኑክሌር መሣሪያን መዛመት ከሚያግደው ውል ራሷን ማግለሏ ሌሎች አገሮችም ይህንኑ ለማድረግ እንዲነሳሱ ጥርጊያ መንገድ ከፍቷል። በአሁኑ ጊዜ በእስያ ውስጥ የኑክሌር መሣሪያ እሽቅድምድም ይነሣል የሚል ስጋት አለ። ይህም በልዕለ ኃያላኑ አገሮች መካከል ከነበረው የኑክሌር ቦምብ ክምችት ፉክክር የከፋ አደጋ ሊሆን ይችላል።”
ብሔራዊ ስሜት ለማመን በሚያዳግት መጠን አዳዲስ አገሮች ብቅ ብቅ እንዲሉ አድርጓል። ስለዚህ የኑክሌር መሣሪያ ያላቸው አገሮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል። (ሳጥኑን ተመልከት።) ቻርልስ ክራውትሃመር የተባሉ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፦ “ሶቭየት ፈጥራው የነበረው ስጋት ማክተሙ የኑክሌር አደጋ አክትሞለታል ማለት አይደለም። ትልቁ አደጋ የኑክሌር መሣሪያ ያላቸው አገሮች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ነው፤ የኑክሌር መሣሪያ መዛመት ጀምሯል።”
ለሽያጭ የቀረቡ ቦምቦች
የኑክሌር ኃይል ባለቤት ለመሆን የሚፈልጉ አገሮች እነዚህ መሣሪያዎች የሚያስገኙትን ክብርና ኃያልነት ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት አላቸው። አንዲት አገር ከካዛክስታን ቢያንስ ሁለት የኑክሌር አረሮችን ገዝታለች ተብሏል። ይህች የቀድሞዋ የሶቭየት ሪፑብሊክ የኑክሌር አረሮቹ “እንደጠፉባት” አድርጋ በይፋ አስመዝግባለች።
ጥቅምት 1992 በጀርመን ፍራንክፈርት ውስጥ የአንድን ከተማ የውኃ አቅርቦት በሙሉ መመረዝ የሚችል ከፍተኛ የሬድዮ አክቲቭ ጨረር ያለው 200 ግራም የሚመዝን ሴሲየም የተባለ ማዕድን የያዙ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ይህ ከሆነ ከአንድ ሳምንት በኋላ 2. 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዩራኒየም የያዙ ሰባት የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ሙኒክ ውስጥ ተይዘዋል። በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ ኑክሌርን በኮንትሮባንድ የሚነግዱ ሁለት የተደራጁ ቡድኖች መያዛቸው ባለ ሥልጣኖችን አስደንግጧቸዋል። ምክንያቱም ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ የተመዘገቡት እንዲህ ያሉ ወንጀሎች አምስት ብቻ ናቸው።
እነዚህ ግለሰቦች ለሽብር ፈጣሪዎች ቡድን ለመሸጥ አስበው ይሁን ወይ ለአንዳንድ አገሮች መንግሥታት የታወቀ ነገር የለም። የሆነው ሆኖ በኑክሌር አማካኝነት ሽብር ለመፍጠር የሚቻልበት አጋጣሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቷል። በአውሮፓ የኑክሌር መዛመት መረጃ ማዕከል የሚሠሩት ዶክተር ዴቪድ ሎውሪ አደጋውን እንዲህ በማለት ገልጸውታል፦ “አንድ ሽብር ፈጣሪ ማድረግ የሚያስፈልገው ነገር ብዙ ዩራኒየም አለን፣ ማስረጃውም ይኸውና በማለት ለአንድ የታወቀ ባለ ሥልጣን መርምሮ ማረጋገጥ እንዲችል መጠነኛ የዩራኒየም ናሙና መላክ ብቻ ነው። ይህም አንድ አፋኝ ያፈነውን ሰው ጆሮ ቆርጦ ለማስረጃነት እንደሚልከው ዓይነት ነው።”
ለበጎ ዓላማ የዋሉ “ውሎ አድሮ ግን አደጋ የሚያስከትሉ” እና “ሕይወትን ለሕልፈት የሚዳርጉ ነገሮች”
1992 ሲጀምር የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማመንጨት በጎ ዓላማ ሲባል 420 የኑክሌር ማመንጫዎች ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ሌሎች 76 የሚሆኑ ደግሞ በግንባታ ላይ ነበሩ። ሆኖም ላለፉት በርካታ ዓመታት በኑክሌር ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የደረሱ አደጋዎች ለበሽታ መጨመር፣ ለፀነሱ ሴቶች መጨንገፍና ልጆች አካለ ስንኩል ሆነው እንዲወለዱ ምክንያት ሆኗል። አንድ ሪፖርት በ1967 በሶቭየት ፕሉቶኒየም የተባለ ንጥረ ነገር ማምረቻ ጣቢያ ላይ በደረሰው አደጋ ወደ አየር የወጣው የሬዲዮ አክቲቭ ጨረር በቼርኖቢሉ ከደረሰው አሠቃቂ አደጋ ሦስት እጥፍ ይበልጣል ብሏል።
እርግጥ ሚያዝያ 1986 በዩክሬኑ ቼርኖቢል ላይ የደረሰው አደጋ የዜና አውታሮችን ትኩረት በእጅጉ ስቦ ነበር። በ1970ዎቹ በቼርኖቢል ጣቢያ ተቀዳሚ ምክትል የኑክሌር ኢንጂነር የነበሩት ግሪጎሪ ሜድቬዴፍ ወደ አየር የተበተነው “ከፍተኛ መጠን ያለውና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የሬዲዮ አክቲቭ ጨረር ቁስሉ ቶሎ የማይሽር በመሆኑ በሂሮሽማ ላይ እንደወረደው ቦምብ ያሉ አሥር ቦምቦችን ይተካከላል” በማለት ገልጸዋል።
ሜድቬዴፍ ቼርኖቢልስካያ ክሮኒካ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በ1980ዎቹ አጋማሽ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ውስጥ የተከሰቱ 11 ከባድ የኑክሌር ማመንጫ ጣቢያ አደጋዎችንና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተከሰቱ ሌሎች 12 አደጋዎችን በዝርዝር አስፍረዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ከተከሰቱት አደጋዎች መካከል በ1979 በስሪ ማይል አይላንድ የተፈጸመው አስደንጋጭ አደጋ ይገኝበታል። ሜድቬድፍ በዚያን ጊዜ ስለደረሰው ሁኔታ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የኑክሌር ኃይል የነበረውን ስም ያጎደፈና በሁሉም ሰዎች አእምሮ ውስጥ ያልነበረ ቢሆንም በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ የነበረውን የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ የሚለውን የተሳሳተ እምነት ውድቅ ያደረገ የመጀመሪያው አደጋ ነበር።”
ይህ እስከ አሁንም ድረስ ለምን ያልተጠበቁ አደጋዎች እንደሚደርሱ ይገልጻል። በ1992 ሩስያ ውስጥ እነዚህ አደጋዎች 20 በመቶ ጨምረዋል። ከእነዚህ አደጋዎች መካከል አንዱ በዚያው ዓመት በመጋቢት ወር በሩስያ ቅዱስ ፒትስበርግ ከተማ ውስጥ በሶስኖቪ ቦሬ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ከደረሰ በኋላ በእንግሊዝ ሰሜናዊ ምሥራቅ የሬዲዮ አክቲቭ ብናኞች መጠን ወደ 50 በመቶ ከፍ ብሏል፤ በኢስቶኒያና በደቡብ ፊንላንድ ለክፉ አይሰጥም ከሚባልለት ከፍተኛ መጠን በእጥፍ አድጓል። በኒውካስትል ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ጆን ኧርካርት ከዚህ ጋር በመስማማት እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ መጠን እንዲጨምር ምክንያት የሆነው ሶስኖቪ ቦሬ ነው ብዬ ማስረጃ ላቀርብ አልችልም። ግን ሶስኖቪ ቦሬ ካልሆነ ታዲያ ማን ሊሆን ነው?”
አንዳንድ ባለ ሥልጣኖች የቼርኖቢል ዓይነት አሠራር ያላቸው የኑክሌር ማመንጫ ጣቢያዎች አሠራራቸው ላይ ጉድለት ያላቸውና ሥራቸውንም ለማንቀሳቀስ በጣም አደገኛ ናቸው በማለት ይናገራሉ። ያም ሆኖ ግን ብዙዎቹ በጣም ከፍተኛ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ለማሟላት አሁንም ጥቅም ላይ እንደዋሉ ነው። እንዲያውም አንዳንድ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞች ጣቢያው የሚያመነጨውን ኃይል ለመጨመር ሲሉ የኃይሉን መጠን የሚቆጣጠሩትን መሣሪያዎች ያጠፏቸዋል የሚል ክስ ተሰንዝሮባቸዋል። እንዲህ ዓይነት ሪፖርቶች ከኤሌክትሪክ ፍጆታዋ መካከል 70 በመቶውን ለማመንጨት የኑክሌር ጣቢያዎችን የምትጠቀመውን ፈረንሳይ የመሰሉ አገሮችን ፍርሃት ለቀውባቸዋል። ሌላ “ቼርኖቢል” ከተከሰተ ብዙዎቹ በፈረንሳይ የሚገኙ የኑክሌር ጣቢያዎች የግድ እስከናካቴው ይዘጉ ይሆናል።
ሌላው ቀርቶ “አስተማማኝ” የተባሉት እንኳ ከጊዜ ብዛት አስጊ እየሆኑ ይሄዳሉ። በ1993 መጀመሪያ ላይ ጀርመን ውስጥ ከሚገኙት የቆዩ የኑክሌር ጣቢያዎች አንዱ በሆነው በብረንስቡቴል ጣቢያ እንደተለመደው መሣሪያዎቹ በደህና ሁኔታ ላይ ይገኙ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ምርመራ ሲካሄድ ከጠንካራ ብረት (ስቲል) በተሠራ ቧንቧ ላይ ከመቶ በላይ ስንጥቆች ተገኝተዋል። በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ በሚገኙት የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎችም ተመሳሳይ ስንጥቆች ተገኝተዋል። ጃፓን ውስጥ በሚገኘው የኑክሌር ጣቢያ ላይ በ1991 ለደረሰው የመጀመሪያው ከባድ አደጋ አንዱ መንስኤ ጣቢያው ረጅም ዕድሜ ማስቆጠሩ ሊሆን ይችላል። ይህም ከአሥርተ ዓመታት በላይ ካስቆጠሩት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚገኙት ለንግድ የዋሉ የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች መካከል በግምት ሁለት ሦስተኛዎቹ ተመሳሳይ አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል ይጠቁማል።
በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ በኑክሌር ማመንጫዎች ላይ አደጋ ሊደርስ ይችላል። የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች በበዙ ቁጥር ስጋቱም ያንኑ ያህል ይጨምራል። የኑክሌር ኃይል ማመንጫው እያረጀ በሄደ መጠን አደጋውም ያን ያህል ይጨምራል። አንድ ጋዜጣ ውለው አድረው አደጋ የሚያስከትሉና የሬዲዮአክቲቭ ጨረር ያላቸው ሕይወትን ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ ጣቢያዎች የሚል ቅጽል ስም የሰጣቸው አለምክንያት አይደለም።
ዝቃጩን የት ያፍስሱት?
በቅርቡ ፈረንሳይ ውስጥ ባለው የአልፕስ ተራራ አጠገብ በወንዝ ዳርቻ የሚገኝ አንድ የመዝናኛ ስፍራ በአጥር ታጥሮ በፖሊስ ሲጠበቅ በማየታቸው ሰዎች ተገርመው ነበር። ዘ ዩሮፕያን የተባለ ጋዜጣ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በዚህ አካባቢ የምትኖር አንዲት ሴት ቤሪሊየም በተባለ ንጥረ ነገር ተመርዛ ከሞተች ከሁለት ወር በኋላ በቦታው ያለው የሬዲዮ አክቲቭ ጨረር መጠን እንዲመረመር መመሪያ ተላልፎ የተደረገው ምርመራ በመዝናኛ ስፍራው ያለው የሬዲዮአክቲቭ ጨረር መጠን በዙሪያው ባሉት ሥፍራዎች ካለው የሬዲዮአክቲቭ ጨረር መጠን 100 ጊዜ እጥፍ በልጦ እንደተገኘ ገልጿል።”
በተለያዩ መንገዶች የሚመረተውና በጣም አነስተኛ ክብደት ያለው ቤሪልየም በአውሮፕላን ኢንዱስትሪ ውስጥ ጥቅም ላይ ውሏል። በጨረር እንዲመታ ተደርጎ ከተፈተነ በኋላም በኑክሌር ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ቤሪሊየም የሚያዘጋጅ ፋብሪካ አደገኛውን በጨረር የማስመታት ሂደት ካከናወነ በኋላ ዝቃጩን በመዝናኛ ስፍራው ወይም በአቅራቢያው አምጥቶ አራግፏል። “ቤሪሊየም በሬዲዮአክቲቭ ጨረር ሳይመታም እንኳ ብናኙ እጅግ መርዘኛ ከሆኑት የታወቁ የኢንዱስትሪ ዝቃጮች መካከል አንዱ ነው” በማለት ዘ ዩሮፕያን ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኑክሌር ሙከራ ለማድረግ ትጠቀምባቸው በነበሩት ኖቫያ ዜምላያ ተብለው በሚጠሩት ሁለት ደሴቶች የባሕር ዳርቻ አጠገብ በሚገኘው ባሕር ውስጥ በ30 ዓመታት 17,000 በርሜሎች ሙሉ የሬዲዮአክቲቭ ዝቃጮች እንዲፈሱ ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ የኑክሌር መሣሪያ ተሸካሚ የሆኑ ሰርጓጅ መርከቦች የሬድዮ አክቲቭ ጨረር ያላቸው ክፍሎቻቸውና ቢያንስ ቢያንስ 12 የሚሆኑ የኑክሌር ማመንጫዎች የተለያዩ መሣሪያዎቻቸው ወደዚህ በቋሚነት ወደሚጠቀሙበት የቆሻሻ ማከማቻ ተጥለዋል።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚደረግ የኑክሌር ብክለት አደገኛ ነው። ታይም መጽሔት በ1989 በኖርዌይ የባሕር ዳርቻ ስለሰጠመች አንዲት ሰርጓጅ መርከብ ሲናገር የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፦ “የሰጠመችው መርከብ ሴሲየም–137 የተባለውን ካንሰር ሊያስከትል የሚችል ኬሚካል ማፍሰስ ጀምራለች። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የፈሰሰው ኬሚካል ውኃ ውስጥ በሚኖሩ ነፍሳትና በሰው ጤና ላይ እምብዛም ጉዳት አያመጣም የሚል ግምት አለ። ይሁን እንጂ ኮምሶሞሌትስ የተባለችው ይህች የሰጠመች መርከብ 13 ኪሎ ግራም ፕሉቶኒየም የያዙ ሁለት የኑክሌር ቶርፒዶዎች (ከመርከብ ላይ የሚተኮሱ በባሕር ውስጥ ተጉዘው ዒላማቸውን የሚመቱ መሣሪያዎች) ተሸክማ ነበር። ፕሉቶኒየሙ ካለው የሬዲዮአክቲቭ መጠን መካከል ግማሹ እንዲከስም ለማድረግ 24,000 ዓመታት የሚፈጅ ሲሆን እጅግ መርዛማ በመሆኑ ትንሽ ብናኝ ብቻ እንኳ ሰውን ሊገድል ይችላል። የሩሲያ ጠበብቶች ይህ ፕሉቶኒየም ውኃው ውስጥ ሊፈስስ እንደሚችልና እስከ 1994 መጀመሪያ ድረስ የውቅያኖሱን ክልል ሊያዳርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።”
እርግጥ ነው የሬዲዮአክቲቭ ዝቃጮች የት ይፍሰሱ የሚለው ችግር ፈረንሳይና ሩስያ ብቻ የሚያጋጥማቸው ችግር አይደለም። ዩናይትድ ስቴትስ “የሬዲዮአክቲቭ ዝቃጮች ክምሮች አሏት። ዝቃጩን ለማከማቸት የሚያገለግል ቋሚ ቦታም የለም” በማለት ታይም መጽሔት ዘግቧል። ይኸው ታይም መጽሔት ገዳይ ንጥረ ነገሮችን የያዙ በሚልዮን የሚቆጠሩ በርሜሎች ጊዜያዊ በሆነ የማከማቻ ሥፍራ ተከማችተዋል፤ ይህም “ሊጠፋና ሊሰረቅ እንዲሁም በጥንቃቄ ሳይያዝ ቀርቶ አካባቢን ሊበክል ይችላል” የሚል የማያቋርጥ ስጋት ፈጥሯል ብሏል።
እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚያስከትለውን አደጋ ለማሳየት የተደረገ ይመስል ሚያዝያ 1993 በሳይቤርያ ቶምስክ ውስጥ ቀደም ሲል የጦር መሣሪያዎች ማምረቻ ጣቢያ በነበረ ሥፍራ አንድ የኑክሌር ዝቃጭ ማከማቻ ጋን ፈንድቶ ሌላ አስፈሪ የቼርኖቢል ምስልን በአእምሮ ውስጥ ቀርጾ ነበር።
በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ‘የኑክሌር ስጋት ስላከተመ ሰላምና ደህንነት ሊመጣ ነው’ የሚለው ልፈፋ ጥሩ መሠረት የለውም። ያም ሆኖ ግን ሰላምና ደህነንት የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል። እንዴት እናውቃለን?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ኑክሌር ያላቸው
12 አገሮች፤ ቁጥራቸው አሁንም እየጨመረ ነው
ኑክሌር እንዳላቸው በይፋ የሚነገርላቸው አገሮች፦ ቤሎሩስ፣ ብሪታንያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ህንድ፣ እስራኤል፣ ካዛክስታን፣ ፓኪስታን፣ ሩስያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩክሬን፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የኑክሌር መሣሪያ የመሥራት አቅም ያላቸው አገሮች፦ አልጄርያ፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሰሜን ኮርያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ሶሪያ፣ ታይዋን
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌላው ቀርቶ ለበጎ ዓላማ የዋለው የኑክሌር ኃይል እንኳ አደገኛ ሊሆን ይችላል
[ምንጭ]
Background: U.S. National Archives photo
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሽፋን: Stockman/International Stock
[ምንጭ]
U.S. National Archives photo