የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 10/1 ገጽ 23-28
  • ‘ይሖዋን በተስፋ የሚጠባበቁ ደስተኞች ናቸው’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ይሖዋን በተስፋ የሚጠባበቁ ደስተኞች ናቸው’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሚስዮናዊ ዘር ተዘራ
  • በስፔይን ውስጥ ያጋጠሙን ችግሮች
  • በካቶሊክ አምባገነን ገዥ ሥር ሆኖ መስበክ
  • ስደትና መባረር
  • ሌላ ምድብ ሌላ ቋንቋ
  • የችግር ጊዜ ጀመረ
  • የእስላም አገር በሆነችው በሞሮኮ መስበክ
  • ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ምድብ?
  • ፈተናዎችና በረከቶች
  • በኤል ሳልቫዶር የተገኘ ዕድገት
  • በይሖዋ አገልግሎት የገጠሙን ያልጠበቅናቸው ነገሮች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ከከፋ ድህነት ወደ ላቀ ብልጽግና
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • የአምላክን ጸጋ በተለያዩ መንገዶች ተመልክተናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ተሰጥቶን ነበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 10/1 ገጽ 23-28

‘ይሖዋን በተስፋ የሚጠባበቁ ደስተኞች ናቸው’

በዶሜኒክ ፒኮን የተነገረ

ወላጆቼ በ1920ዎቹ ዓመታት ከኢጣልያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ፈለሱና በመጨረሻው በዚያን ጊዜ ትንሽዋ ኢጣልያ ተብላ በምትታወቀው ደቡብ ፊላደልፊያ መኖር ጀመሩ። በ1927ም በኋላ የይሖዋ ምስክሮች ተብለው ከተጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ይሰበሰቡ ነበር።

የተወለድኩት በ1929 ስለነበረ ከሕፃንነቴ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን የመማር አጋጣሚ ነበረኝ። ምስክሮቹ የከሰል ማዕድን ማውጫ ባለባቸውና ወንድሞች ብዙ ጊዜ ይታሠሩባቸው በነበሩ በፔንስልቫንያ ግዛት በሚገኙ የማይበገሩ የሚመስሉ የሮማ ካቶሊክ ከተሞች ለመስበክ ከመሄዳቸው በፊት በቤታችን ይሰበሰቡ እንደነበር አስታውሳለሁ። በ1941 በሴንት ሉዊስ ሚሱሪ በተደረገው የይሖዋ ምስክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን ነገሮች መበላሸት ጀመሩ።

በጎረቤት ካሉ መጥፎ ዓይነት ወጣቶች ጋር መዋልና በየመንገዱም ዳር ሲጋራ ማጨስና ቁማር መጫወት ጀመርኩ። እንዳጋጣሚ ሆኖ ወላጆቼ ከቁጥጥራቸው ውጭ መሆኔን ሲመለከቱ ወደ ሌላው የከተማ ክልል ለመዛወር ወሰኑ። ሁሉንም የመንገድ ጓደኞቼን ስላጣሁ አልተደሰትኩም። ይሁን እንጂ ዛሬ መለስ ብዬ ስመለከተው አባቴን በጣም አመሰግነዋለሁ። ከእነዚያ አካባቢዎች እኔን ጎትቶ ለማውጣት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መስዋዕት ከፍሏል። ቀደም ሲል ወደ ሥራ የሚሄደው በእግሩ ነበር፤ አሁን ግን በባቡር ረጅም ጉዞ ማድረግ ግድ ሆኖበታል። ሆኖም ይህ ዝውውር ወደ ቲኦክራቲኩ ክልል መልሶ አስገባኝ።

የሚስዮናዊ ዘር ተዘራ

ቢያንስ በየዓመቱ በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ምረቃ ላይ ለመገኘት ወደ ደቡብ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ እንጓዝ ነበር። እነዚያ ሚስዮናውያን ወደ ሁሉም የዓለም ክፍል ሲላኩ ማየቴ በልቤ ውስጥ የሚስዮናዊነት አገልግሎት ምኞት ዘራብኝ። ስለዚህ ከከፍተኛ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ በኋላ ከግንቦት 1947 ጀምሮ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ለማገልገል ተመዘገብኩ።

በጉባኤያችን ኤልሳ ሽቫርዝ አንዲት ወጣት አቅኚ አለች። እርስዋም በስብከቱ ሥራ በጣም ቀናተኛ ነበረች። ወላጆችዋ ሚስዮናዊ እንድትሆን ሁልጊዜ ያበረታቷት ነበር። ውጤቱን ልትገምቱት ትችላላችሁ። በ1951 ተጋባን። አቅኚ ሆነን በፔንስልቫንያ ውስጥ አብረን በማገልገል ላይ እያለን በጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ኮርስ ለመካፈል አመለከትን። በ1953 በ23ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ኮርስ እንድንካፈል ተጋበዝን። በጊልያድም ለአምስት ወራት ከፍተኛ የሆነ ጥናትና ዝግጅት ካደረግን በኋላ በቶሮንቶ ካናዳ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ተመርቀን ስፔይን ተመደብን።

በስፔይን ውስጥ ያጋጠሙን ችግሮች

በ1955 ወደ ምድብ ቦታችን ለመሄድ ስንዘጋጅ ኤልሳና እኔ ብዙ ጥያቄዎች ተፈጠሩብን። ስፔይን! ምን ዓይነት ቦታ ይሆን? አገሪቱ በካቶሊኩ አምባገነን በጄኔራል ሲሞ ፍራንሲስኮ ፍራንኮ አገዛዝ ሥር ነበረች፤ የይሖዋ ምስክሮችም ሥራ ታግዶ ነበር። እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች ሥር እንዴት ለመሥራት እንችላለን?

በብሩክሊን በሚገኘው የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኙ ወንድሞች በዚያን ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት የነበረው ፍሬዴሪክ ፍራንዝና ከአርጀንቲና የመጣው ሚስዮናዊ አልቫሮ ቤርኮቺያ ከሌሎች ብዙ ወንድሞች ጋር ተይዘው መታሠራቸውን ነገሩኝ። በባርሴሎና አጠገብ በሚገኝ ጫካ ውስጥ አንድ የድብቅ ስብሰባ ተዘጋጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ ፖሊስ ይህንን የድብቅ ስብሰባ ደረሰበትና በዚያ የተገኙትን አብዛኞቹን በቁጥጥር ሥር አዋላቸው።a

ምናልባት ባርሴሎና ስንደርስ ልናገኘው የምንችል ማንም ሰው ላይኖር እንደሚችል ተነገረን። የተሰጠን መመሪያ፦ “የምታርፉበት ሆቴል ፈልጉ፣ ከዚያም አድራሻ ለማወቅ በኒው ዮርክ የሚገኘውን የማኅበሩን ቢሮ ጠይቁ” የሚል ነበር። የሚከተሉትን የኢሳይያስ ቃላት አስታወስን፦ “[ይሖዋን] በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። ጆሮችህ ከኋላህ፦ መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።” (ኢሳይያስ 30:18, 21) ይሖዋን በተስፋ መጠበቅና የድርጅቱን መመሪያ መከተል ነበረብን።

ወላጆቻችንና ሊሰናበቱን ወደ ኒው ዮርክ የመጡትን ጓደኞቻችንን ተሰናበትን። የምንጓዝባት መርከብ ሳቱርኒያ በሀድሰን ወንዝ ላይ ወደ አትላንቲክ ጉዞዋን ቀጠለች። አባቴን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በዚህ ጊዜ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ እኔ ሌላ አገር በነበርኩበት ጊዜ ለረጅም ጊዜ በቆየበት በሽታ ምክንያት ሞተ።

በመጨረሻ ምድብ ቦታችን ወደሆነችው የባርሴሎና የወደብ ከተማ ደረስን። ቀኑ የሚያስጠላና ዝናባማ ነበር፤ በግምሩክ ፍተሻው ስናልፍ ፈካ ያሉ ፊቶች “እንደ ፀሐይ” ሲያበሩ ተመለከትን። አልቫሮ ቤሬኮቻ ከሌሎች የስፔይን ወንድሞች ጋር ሆኖ ይጠብቀን ነበር። ወንድሞቻችን መፈታታቸውን በማወቃችን በጣም ተደሰትን።

አሁን የስፓኒሽ ቋንቋ መማር ነበረብን። በዚያን ዘመን ሚስዮናውያን ቋንቋ ይማሩ የነበረው ያለ መማሪያ መጻሕፍት ወይም ያለ አስተማሪ አስቸጋሪ በሆነ መንገድ ነበር። በዚያን ጊዜ የቋንቋ ኮርሶች አልነበሩም። በስብከቱ ሥራ የሚፈለግብንን ሰዓት እያሟላን ቋንቋውን መማር ነበረብን። በሥራው ላይ እንዳለን መሰልጠን ነበረብን ማለት ነው።

በካቶሊክ አምባገነን ገዥ ሥር ሆኖ መስበክ

በዚያ ጊዜ በስፔይን ውስጥ የነበረው የይሖዋ ድርጅት ገና በልጅነት ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር። በ1955 28 ሚልዮን ሕዝብ በሚኖርባት አገር ውስጥ የነበረው ከፍተኛው የአስፋፊዎች ቁጥር 366 ነበር። በመላዋ አገር ውስጥ የነበሩት አሥር ጉባኤዎች ብቻ ነበሩ። ሁኔታው በዚህ መልኩ ለረጅም ጊዜ ይቆይ ይሆንን? እኔና ሚስቴ ከቤት ወደ ቤት መስበካችንን ስንጀምር ስፔይን ምሥራቹን ለሚያስፋፉ ሰዎች እንደ ገነት መሆንዋን ተገነዘብን። አዎን፣ ሕዝቡ እውነትን የተራቡ ነበሩ።

ይሁን እንጂ እገዳ ስለነበረ ስብከቱ የሚከናወነው እንዴት ነበር? ብዙውን ጊዜ በመንገድ ላይ የሚገኙትን ሁሉንም ቤቶች፣ ወይም በአንድ ሕንፃ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም ክፍሎች አናንኳኳም ነበር። ባርሴሎና ብዙ ባለአምስትና ባለስድስት ፎቅ የአፓርትማ ሕንፃዎች የሚገኙባት ከተማ ነች፤ ከላይ ጀምረን ወደ ታች እንድንሠራም መመሪያ ተሰጥቶን ነበር። ምናልባትም በእያንዳንዱ ፎቅ ላይ የምናንኳኳው አንዱን ክፍል ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ወይም አያሌ ፎቆችን እንዘል ነበር። ይህ ዘዴ አክራሪ የሆነ የቤት ባለቤት አሳልፎ ሊሰጠን ቢፈልግ ፖሊስ እኛን ለመያዝ በጣም አስቸጋሪ እንዲሆንበት አድርጓል።

የጉባኤ ስብሰባዎች የሚከናወኑት በግል ቤቶች ውስጥ ነበር። ጉባኤዎች ከሦስት እስከ አራት የሚሆኑ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች ነበሯቸው። ይህም የጉባኤው አገልጋይ እነዚህን የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች በወር አንድ ጊዜ እንዲጎበኝ ያስችለዋል። የመጽሐፍ ጥናቱ መሪ ሁሉንም ስብሰባዎች ማለትም በሁለት የተለያዩ ምሽቶች የሚደረጉትን ከ10 እስከ 20 ሰዎች የሚገኙባቸውን ትንንሽ ቡድኖች ለመምራት ኃላፊነቱን ይወስዳል።

አዲስ የአኗኗር መንገድ መማር ነበረብን። በዚያን ጊዜ በስፔይን ውስጥ የሚስዮናውያን ቤት የሚባል አልነበረም። በሚቻልበት ጊዜ ሁሉ በወንድሞች ቤት እንኖር ነበር። በከሰል ምድጃ ላይ ምግብ ማብሰል መማር ለኤልሳ ግሩም ተሞክሮ ነበር! ውሎ አድሮ አንድ መጣጃ ያለው የጋዝ ምድጃ ለመግዛት ቻልን፤ ይህም ትልቅ መሻሻል ነበር።

ስደትና መባረር

ከጊዜ በኋላ አንድ ልዩ አቅኚ ተይዞ በታሠረባት በአንዳሉሲያ የስደት ማዕበል መነሣቱን ሰማን። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በመላው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙትን ወንድሞች ስምና አድራሻ የያዘ ትንሽ ደብተር ይዞ ነበር። በየከተማው ሁሉ ወንድሞቻችን ተይዘው መታሠራቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ያለ ማቋረጥ ይደርሱን ጀመር። በድንገት የመያዙ ነገር ወደ ባርሴሎናም እየተቃረበ መጣ። በመጨረሻም ስደት ባርሴሎናን መታት።

ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ፖሊሶች ለጥየቃ ወደ ዋናው መምሪያ ወሰዱኝ። ከአያሌ ሰዓታት በኋላም ተለቀቅሁ። ጉዳዩ በዚህ ያበቃ መስሎኝ ነበር። ከዚያም የአሜሪካ ኤምባሲ አገኘኝና በውርደት ከአገር ከመባረር በራሴ ፈቃድ እንድወጣ አሳብ አቀረበልኝ። ብዙም ሳይቆይ በአሥር ቀን ውስጥ አገሪቱን ለቀን እንድንወጣ ማስጠንቀቂያ ሰጠን። ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ደብዳቤ ለመጻፍ ጊዜ አልነበረንም፤ ታዲያ ምን እናድርግ? ለስፔይን ቅርብ ወደሆነው ሚስዮናዊ መስክ ማለትም ከስፔይን በስተምዕራብ ወደምትገኘው ወደ ፖርቹጋል ለመሄድ ሁኔታው አስገደደን።

ሌላ ምድብ ሌላ ቋንቋ

በሐምሌ 1957 ሊዝበን ፖርቹጋል ከደረስን በኋላ በሰሜናዊ ሊዝበን በምትገኘው በፖርቶ ከተማ በሚስዮናዊነት ተመደብን። ይህችም የአገሪቱ ሁለተኛ ዋና ከተማ ሆና ትቆጠር ነበር። በፖርት ወይን ጠጆቿ እውቅ በሆነ አካባቢ የምትገኝ ከተማ ነበረች። አንድ ታዳጊ ጉባኤ ስብሰባዎቹን በመሃል ከተማ በሚገኝ ሕንፃ ውስጥ ያደርግ ነበር። አገሪቱ በሳላዛር አገዛዝ ሥር ስለነበረች በፖርቹጋልም የስብከቱ ሥራ ታግዶ ነበር። ቢሆንም ሁኔታዎቹ በስፔይን ውስጥ ከነበረው ሙሉ በሙሉ የተለዩ ነበሩ። ስብሰባዎቹ የሚካሄዱት በወንድሞች ቤት ውስጥ ነበር፤ ከ40 እስከ 60 የሚሆኑ ሰዎችም ይገኙ ነበር። ቤቶቹ የይሖዋ ምስክሮች መሰብሰቢያ ቦታ እንደሆኑ የሚጠቁሙ ምልክቶች አልነበሩም። እኔ የፖርቹጋል ቋንቋ መናገር ባልችልም እንኳ የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። አሁንም እንደገና በአስቸጋሪ መንገድ ሌላ አዲስ ቋንቋ ተማርን።

ከአንድ ዓመት አካባቢ በኋላ በሊዝበን ተመደብን። እዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳችን የሆነ ቦታ ይኸውም በሊዝበን ከተማ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ አፓርትማ አገኘን። በመላዋ የፖርቹጋል ሪፓብሊክ ውስጥ የሚገኘውን ክልል እንድንመራ ተመደብን። ፖርቹጋል በገባንበት ጊዜ የነበሩት 305 አስፋፊዎችና አምስት ጉባኤዎች ብቻ ነበሩ።

የችግር ጊዜ ጀመረ

ፖርቹጋልንና ቅኝ ግዛቶችዋን በሚያሳዩ አንዳንድ ካርታዎች ላይ “በፖርቹጋል ግዛት ላይ ፀሃይ ፈጽሞ አትጠልቅም” የሚል አባባል ነበረ። ይህ የሆነበት ምክንያት ፖርቹጋል በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ቅኝ ግዛት አገሮች ስለነበሯት ነው፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ትልልቅ አገሮች በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙት ሞዛምቢክና አንጎላ ናቸው። በ1961 በእነዚህ የቅኝ ግዛት አገሮች ውስጥ ችግሮች ተፈጠሩ፤ ፖርቹጋልም የጦር ኃይሏን ማሳደጉ አስፈላጊ ሆኖ ተሰማት።

ታዲያ አሁን ወጣት ወንድሞች ለወታደራዊ አገልግሎት ሲመለመሉ ምን ያደርጉ ይሆን? አንዳንዶች በሐኪም ማስረጃ ነፃ መሆን ሲችሉ አብዛኞቹ ግን ለክርስቲያን ገለልተኝነት የጸና አቋም ይዘው ቆመዋል። ብዙም ሳይቆይ ከባድ የሆነ የስደት ማዕበል ጀመረ። ልዩ አቅኚዎች ተይዘው እንደታሠሩና ፒ.አይ.ዲ.ኢ. በተባለው የምሥጢር ፖሊስ ክፉኛ እንደተደበደቡ የሚገልጹ ሪፖርቶች ለቅርንጫፍ ቢሮው ደረሱት። ሚስዮናዊ ከሆንነው ውስጥ አንዳንዶቻችን ወደ ፖሊስ ዋና መምሪያ ለጥያቄ ተጠራን። ከዚያም ሦስት ባልና ሚስት አገሪቱን ለቀው እንዲሄዱ 30 ቀን ተሰጣቸው። ሁላችንም አመለከትን።

ሚስዮናውያኑ ባልና ሚስቶች አንድ በአንድ በምሥጢር ፖሊሱ ዳይሬክተር ጥያቄ ሊደረግላቸው ወደ ዋናው የፖሊስ መምሪያ ተጠሩ። በመጀመሪያ የተጠየቁት የቅርንጫፍ አገልጋይ የሆነው ኤሪክ ብሪተንና ሚስቱ ክርስቲና ነበሩ። ከዚያም ኤሪክ ቤቨራይጅና ሚስቱ ሃዜል እንዲሁም በመጨረሻ ኤልሳና እኔ ተጠየቅን። የፖሊስ አዛዡ በትምህርታችንና በገለልተኝነታችን የምዕራቡን ዓለም ለማዳከም የኮሚኒስቶች መሣሪያ እንደሆንን አድርጎ በሐሰት ከሰሰን። ማመልከቻችንም ከንቱ ሆነ።

ምክንያታዊ ባልሆነ አምባገነናዊ የጭካኔ አገዛዝ ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጠሙአቸውን 1,200 ወንድሞችና እህቶች ትቶ መውጣት በጣም አሳዛኝ ነገር ሆነብን። ወንድምና እህት ቤቨራይጅ ወደ ስፔይን፣ ወንድምና እህት ብሪተንስ ደግሞ ወደ እንግሊዝ አገር ሄዱ፤ የእኛስ የሚቀጥለው ምድብ ቦታችን የት ይሆን? የእስላም አገር የሆነችው ሞሮኮ ነበረች።

የእስላም አገር በሆነችው በሞሮኮ መስበክ

አሁንም እንደገና ይሖዋን በተስፋ ተጠባበቅን። አዲስ ምድብ ቦታ፣ አዲስ ባሕልና አዲስ ቋንቋዎች! አረብኛ፣ ፈረንሳይኛና የስፓኒሽ ቋንቋ የሞሮኮ መንግሥት የኦፊሲየል ቋንቋ ናቸው። በዚህም አገር ውስጥ በስምንት ጉባኤዎች 234 ምስክሮች ይገኙ ነበር። ሕጋዊ እውቅና ያለው የአገሪቱ ሃይማኖት እስልምና ነበር፤ ሃይማኖትን መቀየር በእስላሞች ዘንድ ሕገ ወጥ ድርጊት ነው። ስለዚህ ለመስበክ እንችል የነበረው በተለይ ለአውሮፓውያንና እስላም ላልነበረው ሕዝብ ብቻ ነበር።

በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ሚስዮናዊያን መምጣት ከጀመሩ ወዲህ ጭማሪ ታየ። ይሁን እንጂ የሞሮኮ መንግሥት በአውሮፓውያን ላይ ተጽዕኖ ማድረጉን ቀጠለ፤ ብዙ የውጭ አገር ሰዎች ብዙ ወንድሞቻችንም ጭምር እንዲባረሩ ተደረጉ።

የምናነጋግራቸው ሰዎች ቁጥር እያነሰ ሲሄድ እስላሞችን ለማነጋገር የጥበብ መንገዶችን ለመፈለግ ተገደድን። በዚህም ምክንያት ሰዎች ቅሬታቸውን ለፖሊሶች ማሰማት ጀመሩ። እንደነዚህ ያሉት ቅሬታዎች በታንጂርና በሌሎች ከተሞች በመሰማታቸው ምክንያት በ30 ቀን ውስጥ አገሩን ለቅቀን እንድንወጣ ተነገረን። በግንቦት 1969 ኤልሳና እኔ አሁንም ከተመደብንበት አገር እንድንወጣ ተደረግን።

ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ምድብ?

ወደ ብሩክሊን እንድንመለስ ተነገረን፤ በዚያኑ ጊዜ በበጋ ወራት ለቅርንጫፍ አገልጋዮች በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ እንድሳተፍ ግብዣ ቀረበልኝ። እዚያ በነበርኩበት ጊዜ የአሁኑ አዲስ የሥራ ምድባችን የማዕከላዊ አሜሪካ አገር የሆነችው ኤል ሳልቫዶር እንደሆነችና እዚያም የቅርንጫፍ አገልጋይ ሆኜ እንደማገለግል ተነገረኝ። ሥራችን በዚህ አገር ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ስላልነበረው እዚያ የምቆይበት ጊዜ ሚስዮናውያን በአገሩ ውስጥ እንዲቆዩ ለሚፈቀድበት የመጨረሻ ከፍተኛ ጊዜ ማለትም ለአምስት ዓመታት ብቻ እንደሚሆን ተረዳሁ።

ኤል ሳልቫዶር​—እንዴት ያለ የሥራ ምድብ ነበር! በየወሩ በአማካይ ሪፖርት የሚያደርጉ 114 አቅኚዎችን ጨምሮ 1,290 አስፋፊዎች ነበሩ። የአገሩ ሕዝቦች አምላክን የሚፈሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚወዱና እንግዳ ተቀባይ ናቸው። በየበራቸውም ላይ እንድናነጋግራቸውና ወደ ቤት እንድንገባ ይጋብዙን ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምንችለው በላይ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አገኘን።

በዚያ ያለውን ጭማሪና ከፍተኛ ፍላጎት ከተመለከትን በኋላ ከአምስት ዓመት በኋላ ይህንን ምድብ ቦታ ትተን መሄድ እንደሚኖርብን ስናስብ በጣም አዘንን። ስለዚህ የይሖዋ ምስክሮች ሥራ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ መሞከር እንደሚኖርብን ወሰንን። በታህሣስ 1971 ለመንግሥት ማመልከቻችንን አቀረብን፤ በሚያዝያ 26, 1972 መንግሥታዊ በሆነው ጋዜጣ በዳያሪኦ ኦፊሲያል ላይ ያቀረብነው አቤቱታ ተቀባይነት ማግኘቱን ስናነብ በጣም ተደሰትን። ከዚያ በኋላ ሚስዮናውያን ከአምስት ዓመት በኋላ እንዲሄዱ በመገደድ ፋንታ በአገሩ ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ የመኖር ፈቃድ ሊያገኙ ቻሉ።

ፈተናዎችና በረከቶች

ባለፉት ዓመታት በተመደብንባቸው የተለያዩ ቦታዎች ብዙ ጥሩ ወዳጆችን አፍርተናል፤ ከአገልግሎታችንም ፍሬ አግኝተናል። ኤልሳ በሳን ሳልቫዶር አንዲት መምህርትና ወታደር ባልዋን የሚመለከት አንድ ጥሩ ተሞክሮ አጋጥሟታል። በተጨማሪም ከመምህርዋ ጓደኞች ውስጥ አንዷ ለእውነት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች። በመጀመሪያ ላይ ባልየው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት አላሳየም ነበር፤ ሆኖም በሆስፒታል በነበረበት ጊዜ ሄደን ጠየቅነው፣ የሚቀረብ ዓይነት ሰው ነበር። ውሎ አድሮም መጽሐፍ ቅዱስን አጠና፤ የወታደርነት ሥራውን ተወ፤ ከዚያም ከእኛ ጋር መስበክ ጀመረ።

ትንሽ ቆየት ብሎ አንዲት ሴትዮ ወደ መንግሥት አዳራሹ መጥታ ወታደር የነበረውን ሰው ታስጠናው የነበረችው እርስዋ እንደሆነችና እንዳልሆነች ኤልሳን ጠየቀቻት። ለካስ ሴትዮዋ ቀደም ሲል ቁባቱ ነበረች! እርስዋም ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠናች። በወረዳ ስብሰባ ላይ ወታደር የነበረው ሰው፣ ሚስቱ፣ ጓደኛዋና የቀድሞ ቁባቱ ሁሉም ተጠመቁ!

በኤል ሳልቫዶር የተገኘ ዕድገት

በተገኘው ከፍተኛ ዕድገት ምክንያት ብዙ የመንግሥት አዳራሾች ተሠሩ፤ አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ከ18,000 የሚበልጡ ንቁ ምስክሮች አሏት። ሆኖም ይህ ዕድገት የተገኘው ያለ ምንም ፈተናና ችግር አልነበረም። ለአሥር ዓመታት ወንድሞች በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ነበረባቸው። ይሁን እንጂ እነርሱ ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው ለይሖዋ መንግሥት ታማኝ ሆነዋል።

እኔና ኤልሳ በድምሩ ለ85 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አቅኚነት ቆይተናል። ይሖዋን በተስፋ ከተጠባበቅንና ከኋላም “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል” ከሰማን በፍጹም ተስፋ የሚያስቆርጥና የሚያበሳጭ ሁኔታ እንደማያጋጥመን ለማየት ችለናል። የይሖዋ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በመሆናችን በእርግጥም አርኪና አስደሳች የሆነ የሕይወት ዘመን ለማሳለፍ ችለናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሙሉውን ሐሳብ ለማግኘት የ1978 የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ፣ ገጽ 177-9 ተመልከት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስፔይን ውስጥ በአንድ ጫካማ ቦታ የተደረገ ትልቅ ስብሰባ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሞሮኮ ውስጥ እስላም ላልሆኑ ሰዎች እንሰብክ ነበር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኤል ሳልቫዶር የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ፣ የአሁኑ ምድብ ቦታችን

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ