ከከፋ ድህነት ወደ ላቀ ብልጽግና
ማንዌል ዲ ዘዙሽ አልሜይዳ እንደተናገረው
የተወለድኩት ጥቅምት 1916 ሲሆን ከ17 ልጆች መካከል የመጨረሻ ልጅ ነበርኩ። ዘጠኝ ታላላቅ ወንድሞቼና እህቶቼ በበሽታና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ስለሞቱ ጭራሽ አላውቃቸውም ነበር። የተቀረነው ስምንት ልጆች ከወላጆቻችን ጋር በፖርቱጋል ፖርቶ አቅራቢያ በምትገኝ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ እንኖር ነበር።
ትንሿ ቤታችን አንድ አነስተኛ ሳሎንና አንድ መኝታ ቤት ነበራት። የሚጠጣ ውኃ የምናገኘው ወደ ግማሽ ኪሎ ሜትር ከሚጠጋ ርቀት ላይ ሲሆን ምግብ ለማብሰል የምንገለገልባቸው ዕቃዎች ደግሞ በጣም ኋላ ቀር ነበሩ።
ታላላቅ ወንድሞቼ ትንሽ ከፍ ሲሉ በበቆሎ እርሻ ላይ ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ። እነርሱ የሚያገኙት ገቢ ለቤተሰቡ ምግብ ለመደጎም ይረዳ ነበር። በእነርሱ እርዳታ አማካኝነት ከልጆች መካከል ጥቂት ፊደል የቆጠርኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። ምንም እንኳ ኑሯችን አስቸጋሪ ቢሆንም በሆነ መንገድ ኑሯችንን ለማሻሻል ይረዳናል በሚል ተስፋ አጥባቂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ነበርን።
በግንቦት ወር ቤተ ክርስቲያኒቱ ኖቬና የሚባል ለዘጠኝ ቀን የሚቆይ የአምልኮ ሥርዓት ነበራት። ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ገና ጎሕ ሳይቀድ በማለዳ ወደ ቤተ ክርስቲያን በእግር እንሄድ ነበር። እዚያም ስንደርስ የአምላክን በረከት ያስገኝልናል በሚል እምነት ጸሎት እናቀርባለን። እንዲሁም ቄሱን የአምላክ ወኪል እንደሆኑ ቅዱስ ሰው አድርገን እንመለከታቸው ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ አመለካከታችን ተለወጠ።
የተሻለ ነገር ለማግኘት መፈለግ
ለቤተ ክርስቲያን የሚከፈለውን ግብር መክፈል ሲያቅተን ቄሱ ለነበረብን ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ትንሽ እንኳ አስተያየት አላደረገልንም። ይህ ተስፋ አስቆረጠን። ለቤተ ክርስቲያኑ የነበረኝ ጥሩ አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። በመሆኑም 18 ዓመት ሲሆነኝ በሕይወት ውስጥ በግብርና ሥራ ከመሰማራትና ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ከመጣላት ይልቅ የተሻለ ነገር ካለ ፈልጌ ለማግኘት ስል ከቤተሰቦቼ ተለይቼ ለመሄድ ወሰንኩ። በ1936 የፖርቱጋል ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ሊዝበን ሄድኩ።
እዚያም ከኤድሚኒያ ጋር ተዋወቅሁ። ምንም እንኳ በሃይማኖት እንደተታለልኩ ቢሰማኝም በባሕሉ መሠረት ጋብቻችንን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፈጸምን። ከዚያም በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ። በጦርነቱ ወቅት 18 የጦር መሣሪያ መጋዘኖችን እቆጣጠር የነበረ ሲሆን በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ የጦር መሣሪያ የጫኑ ወደ 125 የሚደርሱ የጭነት መኪናዎች እንልክ ነበር።
የጦርነቱ አሰቃቂነትና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጦርነቱ ያደረገችው ሰፊ ተሳትፎ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳደረ። ‘አምላክ በእርግጥ ለሰው ልጆች ያስባል? እርሱን ማምለክ ያለብን እንዴት ነው?’ ስል ራሴን ጠየቅሁ። ከዓመታት በኋላ በ1954 ጥሩ ጠባይ ያለው አንድ አረጋዊ የይሖዋ ምሥክር በአእምሮዬ ይመላለሱ የነበሩትን ጥያቄዎች በሚመለከት አነጋገረኝ። ያደረግነው ውይይት መላ ሕይወቴን ለወጠው።
መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ተስፋ አስደሰተኝ
ጃሽዋ የሚባለው ይህ ደግ ሰው በዓለም ላይ ላሉ ችግሮች ብቸኛ መፍትሔ የአምላክ መንግሥት መሆኑንና ሰላምና ደኅንነት ሊገኝ የሚችለው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ አማካኝነት ብቻ እንደሆነ አስረዳኝ። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14) እርሱ የነገረኝ ነገር ቢያስደስተኝም እንኳ ከዚህ ቀደም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ባጋጠመኝ ነገር የተነሳ የሰጠኝን ማብራሪያ መቀበል ከበደኝ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ያቀረበልኝን ሐሳብ የተቀበልኩት ገንዘብ እንዳይጠይቀኝና ስለ ፖለቲካ እንዳያነሳብኝ ቃል ካስገባሁት በኋላ ነበር። እሱም ሊያስጠናኝ ግብዣ ያቀረበልኝ ያለ ምንም ክፍያ መሆኑን በማረጋገጥ ባቀረብኩት ሐሳብ ተስማማ።—ራእይ 22:17
በጃሽዋ ላይ ያለኝ ትምክህት በጥቂት ጊዜ ውስጥ አደገ። በመሆኑም ከልጅነቴ አንስቶ ስመኘው የነበረውን ነገር እንዲሰጠኝ በማሰብ “የግሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማግኘት እችላለሁ?” ስል ጠየኩት። መጽሐፍ ቅዱሱን ከሰጠኝ በኋላ ከራሱ ከፈጣሪያችን ቃል እንደሚከተለው ያሉ ተስፋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሳነብ በጣም ተደሰትኩ:- “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ [ከሰው ልጆች] ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና”!—ራእይ 21:3, 4
በተለይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ድህነትና በሽታ እንደሚወገድ ከሚሰጣቸው ተስፋዎች ማጽናኛ አገኘሁ። ታማኙ ኤሊሁ አምላክን በተመለከተ “ብዙም ምግብ ይሰጣል” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 36:31) እንዲሁም በአምላክ መንግሥት የጽድቅ አገዛዝ ስር ‘የሚቀመጥ ታምሜአለሁ እንደማይል’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 33:24) ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ፍቅራዊ አሳቢነት አለው። እርሱ ለሰጣቸው ተስፋዎች ያለኝ ጉጉት በጣም ጨመረ!
ሚያዝያ 17, 1954 በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኘሁ። ስብሰባው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ የሚከበርበት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስብሰባ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ዘወትር በስብሰባዎች ላይ እገኝ ጀመር። ብዙም ሳልቆይ የተማርኳቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ጀመርኩ። በዚያን ጊዜ ፖርቱጋል ውስጥ በየወሩ ለሽርሽር ወደ ባሕር ዳርቻ እንሄድና የጥምቀት ሥርዓት እናከናውን ነበር። ጃሽዋ በመጀመሪያ ካነጋገረኝ ከሰባት ወር በኋላ ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን ባሕር ውስጥ በመጠመቅ አሳየሁ።
በ1954 መጀመሪያ ላይ በመላው ፖርቱጋል ወደ አንድ መቶ ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። በመሆኑም በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው የሚሠሩ ወንዶች በጣም ያስፈልጉ ነበር። ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አደረግሁና ብዙም ሳይቆይ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶች ተረከብኩ። በ1956 ሊዝበን ውስጥ በሚገኝ በሁለተኛው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ በዚያን ጊዜ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች በሚጠራበት ስያሜ መሠረት የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። ዛሬ በዚህ ከተማና በአካባቢው ከአንድ መቶ በላይ ጉባኤዎች ይገኛሉ።
እንግዳ ተቀባይ በመሆን ያገኘነው ጥቅም
ምንም እንኳ እኔና ኤድሚኒያ የነበረን የገንዘብ አቅም ውስን ቢሆንም ምንጊዜም ክርስቲያን ወንድሞቻችንን በእንግድነት እንቀበል ነበር። በ1955 አንድ አቅኚ (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን መጠሪያ ነው) ከመኖሪያው ከብራዚል ተነስቶ ጀርመን ላይ በሚደረገው “ድል አድራጊው መንግሥት” በተባለ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲጓዝ እግረ መንገዱን ፖርቱጋል አርፎ ነበር። በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ለአንድ ወር ያህል እኛ ጋር ያረፈ ሲሆን እኛ ጋር በመቆየቱ ከፍተኛ መንፈሳዊ ጥቅም አግኝተናል!
በዚያን ጊዜ ቤታችን ካረፉት እንግዶች መካከል በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አባላት የሆኑት እንደ ሁጎ ሬይመርና አብሮት የሚኖረው ቻርለስ ኢከር የመሳሰሉት ይገኙበታል። ከእኛ ጋር እራት የበሉ ሲሆን የፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ወንድሞች ደግሞ በአስተርጓሚ ንግግር ሰጥተዋል። አፋቸውን ከፍተው እንደሚጠባበቁ ትንንሽ ጫጩቶች ሁሉ እኛም እነዚህን የመሰሉ ወንድሞች የሚሰጡንን አርኪ የሆነ ጣፋጭ መንፈሳዊ ምግብ ለማግኘት እንጓጓ ነበር።
በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤያችንን በሚጎበኙበት ጊዜ እኛ ቤት ያርፉ ነበር። በ1957 ወንድሞችን ለማበረታታት ፖርቱጋልን እንዲጎበኝ የተላከው የሞሮኮ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ወንድም አልቫሮ ባሬኮቻ ያደረገልኝ ጉብኝት ፈጽሞ የማይረሳ ነው። እቤታችን በሚደረገው የመጽሐፍ ጥናት ላይ የተገኘ ሲሆን በፖርቱጋል የሚያሳልፈውን ቀሪውን ጊዜ እኛ ጋር እንዲቆይ ለመንነው። አንድ ወር በሚፈጀው የጉብኝቱ ቆይታ ከፍተኛ በረከት ያገኘን ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ሁኔታ ፋፍተን ነበር። ወንድም አልቫሮ ደግሞ ውዷ ባለቤቴ ኤድሚኒያ የምትሠራውን ገንቢ ምግብ በመመገብ የሰውነት ክብደት ጨምሮ ነበር።
በልጅነቴ ያሳለፍኩት ዓይነት ከፍተኛ ድህነት በአንድ ሰው ላይ የማይሽር ጠባሳ ሊተው ይችላል። ሆኖም ለይሖዋና ለታማኝ አገልጋዮቹ ይበልጥ በሰጠን መጠን ይሖዋ አብልጦ እንደሚባርከን ተገንዝቤአለሁ። አቅማችን በፈቀደልን ጊዜ ሁሉ ለወንድሞች እንግዳ ተቀባይነት ባሳየን መጠን ተባርከናል።
በ1955 በፖርቶ ባደረግነው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በ1958 ኒው ዮርክ ውስጥ በያንኪ ስቴዲዮም ሊደረግ ስለታቀደው ብሔራት አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር። በስብሰባው ለመገኘት ከፖርቱጋል ለሚላኩ ልዑካን የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን በወቅቱ በአገሪቱ በነበሩት ጥቂት የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ የመዋጮ ሣጥኖች ተቀምጠው ነበር። እኔና ባለቤቴ ከእነዚህ ልዑካን መካከል እንድንሆን ስንመረጥ ምን ያህል እንደተደሰትን መገመት ትችላላችሁ! ለስብሰባው በዩናይትድ ስቴትስ በነበርንበት ወቅት በብሩክሊን የሚገኘውን ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት መጎብኘታችን በጣም አስደስቶን ነበር!
የደረሰብንን ስደት በጽናት ማሳለፍ
በ1962 ፖርቱጋል ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ ታገደ። ከዚህ የተነሳ ኤሪክ ብሪትን፣ ዶሚኒክ ፒኮን፣ ኤሪክ ቢቨሪጅንና ሚስቶቻቸውን ጨምሮ ሁሉም ሚስዮናውያን ከአገሪቱ ተባረሩ። ከዚያም በመንግሥት አዳራሾቻችን ውስጥ መሰብሰብ ስለተከለከልን በምስጢር በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እንሰበሰብ ጀመር። በተጨማሪም ፖርቱጋል ውስጥ ትልልቅ ስብሰባዎች ማድረግ ተከለከልን። በመሆኑም ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶቻችን እነዚህን ስብሰባዎች በሌሎች አገሮች መካፈል እንዲችሉ መጓጓዣ የማዘጋጀቱ ኃላፊነት በእኔ ላይ ወደቀ።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሌሎች አገሮች የሚያደርጉትን ጉዞ ማደራጀት ቀላል አልነበረም። ሆኖም የፖርቱጋል ወንድሞች ከሚያገኟቸው አስደናቂ መንፈሳዊ በረከቶች ጋር ሲነጻጸር የተደረገው ጥረት የሚክስ ነበር። እነዚህ ወንድሞች በስዊትዘርላንድ፣ በእንግሊዝ፣ በኢጣልያና በፈረንሳይ በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸው ምንኛ የሚያንጽ ተሞክሮ ሆኖላቸዋል! በተጨማሪ እነዚህ ስብሰባዎች ወደ አገራቸው ጽሑፎች ይዘው እንዲመለሱ አጋጣሚ ሰጥተዋቸዋል። በእነዚያ ዓመታት ፖርቱጋል ውስጥ በሃይማኖታዊ ድርጅት ስም ለመመዝገብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ያደረግነው ሙከራ ሁሉ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
በ1962 መጀመሪያ ላይ ሚስዮናውያኑ ከተባረሩ በኋላ የሕዝብ ደኅንነት የስብከት ሥራችንን ለማስቆም የተጠናከረ ዘመቻ ማካሄድ ጀመረ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ። በዚህ መጽሔትና አብሮት በሚታተመው ንቁ! መጽሔት ላይ ከእነዚህ አጋጣሚዎች አብዛኞቹን በተመለከተ የተጠናቀሩ ዘገባዎች ታትመው ወጥተው ነበር።a
በመስበካቸው ምክንያት ከታሰሩት መካከል የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሰበኩለት አንድ አቅኚ ይገኝበት ነበር። ፖሊሶቹ የእርሱን ንብረቶች ሲፈትሹ የእኔን አድራሻ ስላገኙ ተጠርቼ ለምርመራ ቀረብኩ።
ከጊዜ በኋላ ሁለት ፖሊሶች መጥተው ቤቴን በረበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችንና 13 የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ወሰዱብኝ። በድምሩ በተለያዩ ሰባት ጊዜያት ቤታችንን ለመፈተሽ እየመጡ ማወካቸውን ቀጠሉ። በመጡ ቁጥር በጥያቄ ያፋጥጡን ነበር።
በርካታ ጊዜያት መሰል የይሖዋ ምሥክሮችን ወክዬ ፍርድ ቤት ለምሥክርነት ቀርቤያለሁ። ምንም እንኳ ያን ያህል ዓለማዊ ትምህርት ባይኖረኝም ይሖዋ ‘ተቃዋሚዎች ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን ጥበብ’ ሰጥቶኛል። (ሉቃስ 21:15) በአንድ ወቅት ዳኛው በሰጠሁት የምሥክርነት ቃል ከመገረማቸው የተነሳ ምን ያህል ዓለማዊ ትምህርት እንደተከታተልኩ ጠየቁኝ። የተማርኩት እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ብቻ መሆኑን ስነግራቸው ፍርድ ቤት ውስጥ የነበሩት ሁሉ ሳቁብኝ።
ስደቱ እየተጋጋለ ሲሄድ የዚያኑ ያህል ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ቁጥር ይጨምር ነበር። በመሆኑም በ1962 በፖርቱጋል የነበሩት ከ1,300 የማይበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥራቸው አድጎ በ1974 ከ13,000 በላይ ደርሰው ነበር! በመሀሉ በግንቦት 1967 የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በዚህ ሥራ ስካፈል የይሖዋ ምሥክሮችን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ጉባኤዎችን እጎበኝ ነበር።
ከሁሉ በሚበልጠው ሀብት መደሰት
በታኅሣሥ 1974 ፖርቱጋል ውስጥ ለይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ሕጋዊ እውቅና ባስገኘው ምዝገባ ላይ ተካፋይ የመሆን መብት አግኝቼ ነበር። በቀጣዩ ዓመት እኔና ባለቤቴ በኤሽተሪል የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆንን። በተጨማሪም በፖርቱጋል የሚገኘው የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ።
የስብከቱ ሥራ በፖርቱጋልም ሆነ በእኛ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተቆጣጣሪነት ስር ባሉ አገሮች ውስጥ ተስፋፍቶ ማየቱ ምንኛ ያስደስታል! እነዚህ አገሮች አንጎላን፣ አዞሬስን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ማዴይራንና ሳኦ ቶሚ እና ፕሪንሲፒን ያጠቃልላሉ። ባለፉት ዓመታት ለመንግሥቱ መልእክት ከፍተኛ ፍላጎት በታየባቸው በእነዚህ አገሮች እንዲያገለግሉ ከፖርቱጋል ሚስዮናውያን ሲላኩ ማየቱ በጣም አስደሳች ነበር። አሁን በእነዚህ አገሮች ውስጥ ከ88,000 በላይ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመኖራቸውና ፖርቱጋል ውስጥ ደግሞ ከ47,000 በላይ በመኖራቸው ምን ያህል እንደምንደሰት ገምቱ! በ1998 በእነዚህ አገሮች የነበረው የመታሰቢያው በዓል የተሰብሳቢዎች ቁጥር 245,000 የደረሰ ሲሆን እኔ የይሖዋ ምሥክር በሆንኩበት በ1954 የነበረው የተሰብሳቢዎች ቁጥር ግን ከ200 ያንስ ነበር።
እኔና ኤድሚኒያ “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች” ሲል ከተናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙራዊ ጋር በሙሉ ልብ እንስማማለን። (መዝሙር 84:10) ትንሽ ከነበረው አጀማመሬ አንስቶ ያገኘኋቸውን መንፈሳዊ ብልጽግናዎች ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ነቢዩ ኢሳይያስ የነበረው ዓይነት ስሜት ይሰማኛል:- “አቤቱ፣ አንተ አምላኬ ነህ፤ ድንቅን ነገር . . . አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናለሁ። ለድሀው መጠጊያ፣ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ . . . ሆነሃል።”—ኢሳይያስ 25:1, 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የግንቦት 22, 1964 ንቁ! ገጽ 8-16 እና የጥቅምት 1, 1966 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 581-92 (እንግሊዝኛ) ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከላይ:- በሊዝበን ወንድም አልሜይዳ በ1958 ኒው ዮርክ ላይ ለሚካሄደው ስብሰባ ልዑካን ለመላክ ዝግጅት መደረጉን ሲያስታውቅ
መካከል:- ፓሪስ ውስጥ በተደረገው “ሰላም በምድር” የተባለ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለናሙና የቀረበ የሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ስብሰባ ሲመራ
ከታች:- በኮንትራት የተያዙ አውቶቡሶች በፈረንሳይ ወደሚደረግ የአውራጃ ስብሰባ ለማምራት ተዘጋጅተው እያሉ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፖርቱጋል በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የጠዋት አምልኮ ስመራ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1988 ለአምላክ የተወሰነው የፖርቱጋል ቅርንጫፍ ቢሮ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ጋር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንድም ሁጎ ሬይመር ከብሩክሊን ቤቴል ሊጎበኘን መጥቶ የሰጣቸው ንግግሮች አበረታተውናል