የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 10/15 ገጽ 25-28
  • ለመሰል ክርስቲያኖች ገነዘብ ማበደር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለመሰል ክርስቲያኖች ገነዘብ ማበደር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መበደር የሚያስከትለውን ችግር ማመዛዘን
  • ለአበዳሪዎች “እውነትን መናገር”
  • በንግድ ጉዳዮችህ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ
  • ጥንቁቅ አበዳሪዎች
  • አለመሳካት
  • ወንድሜን ብድር ልጠይቀውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ገንዘብ መበደር ይኖርብኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • የንግድ ሥራህ ምን መሥዋዕት እንድትከፍል ያስገድድሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 10/15 ገጽ 25-28

ለመሰል ክርስቲያኖች ገንዘብ ማበደር

ፔድሮና ካርሎስ ጥሩ ወዳጆች ነበሩ።a ሁለቱም ክርስቲያኖች ናቸው። ቤተሰቦቻቸውም ይጠያየቁና ብዙ ጊዜ አብረው በመሆን ይደሰቱ ነበር። ስለዚህ ካርሎስ ለንግዱ ማካሄጃ ገንዘብ ባስፈለገው ጊዜ ፔድሮ ለማበደር ወደ ኋላ አላለም። ፔድሮ “ጥሩ ወዳጆች ስለነበርን ምንም ቅር አላለኝም ነበር” አለ።

የሆነ ሆኖ ከሁለት ወር በኋላ የካርሎስ ንግድ ከሠረና የዕዳው ክፍያ ተቋረጠ። ካርሎስ ከፔድሮ ከተበደረው ገንዘብ የሚበዛውን ከንግዱ ውጭ የሆኑ ዕዳዎችን ለመክፈልና ቅንጦት ለሆኑ ጉዳዮች እንደተጠቀመበት ፔድሮ ሲያውቅ ተገረመ። ፔድሮ አንድ ዓመት ያህል እየተመላለሰና ደብዳቤ እየጻፈ ቢጠይቅ እንኳ ጥሩ ምላሽ ለማግኘት አልቻለም። ፔድሮ በመበሳጨት ወደ ባለሥልጣኖች ሄደና ወዳጁና ክርስቲያናዊ ወንድሙ የሆነውን ካርሎስን አሳሰረው።b ይህ ሊወሰድ የሚገባው ተገቢ እርምጃ ነበርን? እስቲ እንመልከት።

በገንዘብ ብድር የተነሣ መጨቃጨቅን አለመግባባት በዓለም ዙሪያ ባሉ ሕዝቦች መሃል ለሚነሱ የወዳጅነት መበላሸቶች ዋናው መንስኤ ሆኗል። ይህ ጉዳይ አንዳንዴ በመሰል ክርስቲያኖች መሃልም ሳይቀር አለመስማማትን ሊያስከትል ይችላል። በብዙ አገሮች የባንክ ብድር ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የገንዘብ ድጎማ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ወዳጆችንና ዘመዶችን ቀርበው መጠየቃቸው የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ የፔድሮና የካርሎስ አሳዛኝ ገጠመኝ አበዳሪም ሆነ ተበዳሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ሥርዓቶችን በጥንቃቄ የማይከተሉ ከሆነ ከባድ ችግሮች ሊነሱ እንደሚችሉ ያሳያል። ታዲያ ለክርስቲያኖች ገንዘብ የማበደር ጥያቄ ሲነሣ ምን ማድረግ ይገባል?

መበደር የሚያስከትለውን ችግር ማመዛዘን

መጽሐፍ ቅዱስ ሳያስፈልግ መበደርን ይከለክላል። “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ በጥብቅ ያሳስባል። (ሮሜ 13:8) ስለዚህ ዕዳ ከመግባትህ በፊት መበደር የሚያስከትለውን ችግር አመዛዝን። (ሉቃስ 14:28) በእርግጥ መበደር ያስፈልግሃልን? የምትበደረው ላንተና ለቤተሰብህ የዕለት ጉርስ ለማቅረብ ስትል ነውን? (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ወይስ የስስት ምኞት ወይም በቅንጦት የመኖር ምኞት ስላለህ ነው?​—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው ቁም ነገር ዕዳ መግባት ለረዥም ሰዓቶች እንድትሠራ ያስገድድህ እንደሆነና ምናልባትም ስብሰባዎችንና የመስክ አገልግሎትን ችላ እንድትል ያደርግህ እንደሆነና እንዳልሆነ ከግምት ማስገባት ነው። በተጨማሪም የሌላ ሰው ገንዘብ ማባከኑስ አይጎዳህምን? ንግድህ ወይም ውጥንህ ቢከስርስ? “ኃጢአተኛ ይበደራል፣ አይከፍልምም” የሚለውን ቃል አስታውስ።​—መዝሙር 37:21

ለአበዳሪዎች “እውነትን መናገር”

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ካሰብክባቸው በኋላ ለንግድ ሥራህ ማስኬጃ መበደር አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ከባንክ ቤት ብድር ልታገኝ ካልቻልክ ኢየሱስ በሉቃስ 11:5 ላይ እንደገለጸው በችግር ጊዜ ወደ ወዳጆች መሄድ የተለመደ ስለሆነ ከመሰል ክርስቲያን መጠየቁ የግድ ስህተት ነው ማለት አይደለም። ሆኖም አንድ ሰው “እውነትን የመናገርን” ግዴታ መቀበል አለበት። (ኤፌሶን 4:25) ታማኝነት ሊደርሱ ወይም ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ ኪሳራ ሊደርስ መቻሉንም ጭምር መግለጽን ይጠይቃል። እንዲያበድርህ የጠየቅኸው ሰው እርግጡን ለማወቅ ብሎ ብዙ መርማሪ ጥያቄዎችን ቢጠይቅህ አትቀየም።c

ታዲያ ለአንድ ጉዳይ ተበድሮ ገንዘቡን ለሌላ ጉዳይ ማዋል እውነትን መናገር ይሆናልን? ሊሆን አይችልም። አንድ የላቲን አሜሪካ ባለ ባንክ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ በጊዜው ካልከፈልክ “ባንኩ ብድርህን ይሠርዝና ንብረትህን ለመያዝ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊያወጣ ይችላል” የገንዘብ ብድር የተሰጠው የንግዱን ትርፍ ለመጨመር ከሆነ ገንዘቡን ለሌላ ዓላማ ማዋል አበዳሪው ገንዘቡ እንዲመለስለት የሚያስችለውን ዋስትና እንዲያጣ ማድረግ ነው። እውነት ነው ከመሰል ክርስቲያን ስትበደር የፍርድ ቤት ቅጣት ይደርስብኛል ብለህ ላትፈራ ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ “ተበዳሪ ያበዳሪው ባሪያ ነው።” ስለዚህ ለአበዳሪህ ታማኝ የመሆን ግዴታ አለብህ።​—ምሳሌ 22:7

በንግድ ጉዳዮችህ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ

ኢየሱስ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) ከአንድ መሰል አማኝ ጋር የንግድ ሥራ በምንጀምርበት ጊዜ ይህን ደንብ መከተል በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድም ብድር ጠይቀኸው እምቢ ቢልህ ምን ይሰማሃል? ጓደኛነትህን እንደካደ ይሰማሃልን? ገንዘብ ለራሱ እንደሚያስፈልገው በመገንዘብ ወይም ከአንተ ይልቅ የኪሳራውን ጉዳይ ከበድ አድርጎ ተመልክቶት ሐሳብህን ሳይቀበል ቢቀር መብቱን ትጠብቅለታለህን? ገንዘቡን ውጤት በሚያስገኝ መንገድ ልትጠቀምበት ስለመቻልህ ሊጠራጠር ይችላል። ከዚህ አንጻር እምቢ ማለቱ ተገቢም ፍቅራዊም ሊሆን ይችላል። ​—ምሳሌ 27:6

ወዳጅህ ገንዘብ ሊያበድርህ ቢስማማ የብድሩ መጠን ምን ያህል መሆኑን፣ ገንዘቡ ለምን አገልግሎት እንደሚውል፣ ለብድሩ መያዣ የሚሆን ምን ንብረት እንዳለና እንዴትና መቼ ተመልሶ እንደሚከፈል ጭምር ዝርዝር ጉዳዮቹ በጽሑፍ መሥፈር አለባቸው። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውሉ በአንድ ሕግ አዋቂ አዋዋይነት ተፈርሞ ከባለሥልጣኖች ዘንድ እንዲቀመጥ ቢደረግ ጥበብ ነው። ያም ሆነ ይህ አንድ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ “ቃላችሁ አዎን አዎን (አዎን የሆነው አዎን) ወይም አይደለም አይደለም (አይደለም የሆነው አይደለም) ይሁን።” (ማቴዎስ 5:37) ለባንክ እንደምታደርገው ያህል ለወዳጅህ ያለህን ግዴታ አጥብቀህ ሳታስብበት በመቅረት በጎ ፈቃዱን አትዳፈር።

ጥንቁቅ አበዳሪዎች

ብድር እንድትሰጥ ብትጠየቅስ? የተለያዩ ሁኔታዎችን ማመዛዘን አስፈላጊ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን ወንድም የራሱ ጥፋት ባልሆነ ምክንያንት ኪሳራ ላይ ሊወድቅ ይችላል። አቅም ካለህ “ለሰውነቱ የሚያስፈልገውን እንድትሰጠው” ክርስቲያናዊ ፍቅር ይገፋፋሃል።​—ያዕቆብ 2:15, 16

አንድ ወንድም መከራ ሲደርስበት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ወለድ ማስከፈል ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው። ኢየሱስ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ መልካም አድርጉ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም (ያለወለድ) አበድሩ” በማለት በጥብቅ አሳስቧል። ​—ሉቃስ 6:35፤ ዘሌዋውያን 25:35-38

ግን ብድር የተጠየቀው አንድን ንግድ ለማካሄድ ወይም ብድሩን የሚመልስ ለመሆኑ መያዣ የሚሆን ገንዘብ እንድትከፍልለት ብቻ ከሆነስ? ባጠቃላይ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ገንዘብን በሥራ ላይ እንደማዋል ተደርጎ መታየት ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ “እጃቸውን አጋና እንደሚመቱ ለባለ ዕዳዎችም እንደሚዋሱ (ከሚዋሱ መሃል) አትሁን” በማለት በጥብቅ ያሳስባል።​—ምሳሌ 22:26

ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ገንዘብህን ሥራ ላይ ለማዋል ከማሰብህ በፊት አቅም እንዳለህ መወሰን አለብህ። ንግዱ ከከሰረ ገንዘቡን ፈጽሞ ያጠፋብህ ወይም ኪሳራ ያስከትልብህ ይሆን? ወይም ተበዳሪው ብድሩን በሰዓቱ መመለስ አይችል ይሆን? ለማበደር አቅምህ ከፈቀደና ትርፍ የሚገኝ ከሆነ ላበደርከው ገንዘብ መጠነኛ ወለድ በማስከፈል ከትርፍ ለመካፈል መብት አለህ። (ሉቃስ 19:22, 23 ጋር አወዳድሩ) ምሳሌ 14:15፦ “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” በማለት ያስጠነቅቃል። አንዳንድ በሌሎች ጊዜያት ብልህ ወይም አዋቂ የሆኑ ነጋዴዎች ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ሲነግዱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሳይወስዱ ቀርተዋል። የከፍተኛ ወለድ ክፍያ ማራኪነት አንዳንዶች ገንዘባቸውንም ሆነ ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት ባጡበት ጉዳይ ላይ ገንዘባቸውን እንዲያውሉ ገፋፍቷቸዋል።

ባለባንኰች አንድ ብድር ምን ያህል የመክሰር አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ለመገመት ብዙውን ጊዜ የሚያጤኗቸውን ሦስት ጉዳዮች እኛም በትኩረት ማመዛዘን ይኖርብናል። (1) ብድሩን የጠየቀው ሰው ጠባይ (2) የመክፈል አቅሙ (3) በንግድ ዘርፍ ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች ናቸው። ታዲያ ደክመህ ያገኘኸውን ገንዘብ ለሰው ለማበደር በምታስብበት ጊዜ ነገሮችን በተመሳሳይ ሁኔታ መገምገሙ “ተግባራዊ ጥበብን” አያይምን?​—ምሳሌ 3:21

ለምሳሌ ያህል ገንዘቡን የጠየቀው ወንድም በሰዎች ዘንድ ያለው ስም ምንድን ነው? እምነት የሚጣልበትን ቁም ነገረኛ በመሆኑ የሚታወቅ ነው ወይስ ግድየለሽና ተለዋዋጭ ነው? (ከ1 ጢሞቴዎስ 3:7 ጋር አወዳድር) ንግዱን ለማስፋፋት የሚፈልግ ከሆነ እስከዚህ ድረስ ንግዱን በተሳካ ሁኔታ ሲያካሂደው ቆይቷልን? (ሉቃስ 16:10) ካልሆነ ያለአግባብ ሊያባክነው የሚችለው ገንዘብ ከማበደር ይልቅ የራሱን ገንዘብ እንዴት ሊይዝ እንደሚገባው ተግባራዊ እገዛ ማድረጉ ለኋላ ኋላው የሚጠቅመው ሊሆን ይችላል።

ሌላው ጉዳይ ወንድም መልሶ ለመክፈል ያለው ችሎታ ነው። ገቢው ምን ያህል ነው? ምን ዕዳዎችስ አሉበት? በግልጽ ሊነግርህ ይገባል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ክርስቲያናዊ ፍቅር ሊሰፍን ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ለብድሩ መያዣ እንዲሆን የወንድምን ንብረቶች በመያዣ ልትወስድ ትፈልግ ይሆናል። የሙሴ ሕግ የአንድን ሰው መተዳደሪያ ወይም መሠረታዊ ንብረቶች በብድር መያዣነት መውሰድን አውግዟል። (ዘዳግም 24:6, 10-12) ስለዚህም አንድ ነጋዴ የሆነ የደቡብ አፍሪካ ወንድም የአንድን ወንድም ሊሸጡ የሚችሉ ንብረቶች እኩሌታ የሚሆን መጠን ብቻ እንደሚያበድር ተናገረ። “የንግዱንም ሆን የቤቱን ዕቃዎች ሊሸጡ እንደሚችሉ ንብረቶች አድርጌ አልቆጥርም” በማለት ይገልጻሉ። “ያለ ጥርጥር ገንዘቤን መልሼ ለማግኘት ብዬ የወንድሜን ቤት በመያዝ እሱን ከቤቱ አውጥቼ ወደ መንገድ አልወረውርም” ብሏል።

በመጨረሻም በምትገኝበት አካባቢ ያለውን አጠቃላይ የንግድ ሁኔታ በማመዛዘን ከግምት ማስገባት ይኖርብሃል። የምንኖረው ሰዎች “ገንዘብን የሚወዱና. . ከዳተኞች” በሆኑበት “የመጨረሻ ቀን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) ወዳጅህ የሆነው ወንድም ታማኝ ቢሆንም ሸሪኮቹ፣ ሠራተኞቹና ደንበኞቹ ግን ታማኞች ላይሆኑ ይችላሉ። ክርስቲያን በመሆኑ የንግድ ተወዳዳሪዎቹ በሚጠቀሙበት ጉቦና ውሸት ሊጠቀም አይችልም። “የጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ” አውዳሚነትም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት። (መክብብ 9:11) የሸቀጣ ሸቀጦቹ ዋጋ በድንገት ሊወድቅ ይችላል። መረን የለቀቀው የገንዘብ ዋጋ ማጣት ንግድን ሊያበላሽ ወይም የተበደርከውን ገንዘብ ዋጋ ሊያወድመው ይችላል። ስርቆት፣ አደጋና ዝርፊያ፣ ወይም መጥፎ የንግድ አጋጣሚዎች ናቸው። ውሳኔ ስታደርግ እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ ከግምት ማስገባት ይኖርብሃል።

አለመሳካት

አንዳንዴ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ ከተደረገ በኋላ አንድ ክርስቲያን ብድሩን መመለስ ያቅተው ይሆናል። ወርቃማው ሕግ ከአበዳሪው ጋር አዘውትሮ እንዲነጋገር ሊገፋፋው ይገባል። ምናልባት ለጊዜው መጠነኛ ክፍያ ማድረግ ይቻል ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ለስሙ ያህል ብቻ ትንሽ መክፈሉ ግዴታውን ለመፈጸም እውነተኛ መስዋዕት ከማድረግ ነፃ እንደሚያደርገው ሊሰማው አይገባም። (መዝሙር 15:4) አንድ ክርስቲያን የሆነ አበዳሪ ፍቅር የማሳየት ግዴታ አለበት። እንደተጭበረበረ ከተሰማው የማቴዎስ 18:15-17ን ምክር ሊጠቀምበት ይችላል።

በመጀመሪያው ላይ የተጠቀሰው ፔድሮ እንዳደረገው ዓለማዊ ባለሥልጣኖችን ጣልቃ ማስገባት እምብዛም አያስፈልግም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ አንዱ በባልንጀራው ላይ ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዐመጸኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? . . . በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?”​—1 ቆሮንቶስ 6:1-7

በዓለማዊ ፍርድ ቤት ወይም በመንግሥታዊ ድርጅቶች አማካኝነት ማለቅ ያለባቸው የሚመስሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ማለትም የማያምኑ የንግድ ሸሪኮችን፣ ዓለማዊ ዕቃ አቅራቢዎችን፣ ወይም ኢንሹራንስ (የመድን) ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በአብዛኞቹ ጉዳዮች ረገድ አንድ ክርስቲያን ባልተመለሰ ብድር ምክንያት አንድን ወንድም በሕግ ፊት በማቅረብ በጉባኤው ላይ ውርደትን ከማምጣት ይልቅ ገንዘቡን እንዳጣ ሊቀር ይመርጣል።

አብዛኛውን ጊዜም እንደዚህ ዓይነት አስከፊ ውጤቶች ማስወገድ ይቻላል። እንዴት? ከአንድ ወንድም ከመበደር ወይም ለአንድ ወንድም ከማበደር በፊት ሊደርሱ የሚችሉትን አደጋዎች አስቀድመህ እወቅ። ጠንቃቃና ጥበበኛ ሁኑ። ከሁሉ በላይ የንግድ ጉዳይን ጨምሮ “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።”—1 ቆሮንቶስ 16:14

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተለውጠዋል።

b በአንዳንድ አገሮች መክሰርና ብድርን በጊዜ አለመክፈል እስካሁን ድረስ የሚያሳስር ጉዳይ ነው።

c አንዳንድ ሰዎች ከብዙ አበዳሪዎች አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በየተራ ተበድረዋል። ስለዚህ እያንዳንዱ አበዳሪ ጠቅላላውን ሁኔታ ሳይገነዘብ ገንዘቡ በቀላሉ የሚመለስለት ሊመስለው ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ