የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 11/15 ገጽ 24-27
  • ወንድሜን ብድር ልጠይቀውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወንድሜን ብድር ልጠይቀውን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወጪውን አስሉ
  • ገንዘቡን የፈለግህበትን ምክንያት ግለጽ
  • በጽሑፍ አስፍሩት
  • ገንዘብ ማበደርን በተመለከተ ጠንቃቃ ሁን
  • የምትወስዷቸውን እርምጃዎች በጥንቃቄ መርምሩ
  • ለመሰል ክርስቲያኖች ገነዘብ ማበደር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ገንዘብ መበደር ይኖርብኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ገንዘብ መቆጠብ ያለብኝ ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 11/15 ገጽ 24-27

ወንድሜን ብድር ልጠይቀውን?

ስምኦን የመጨረሻ ልጁ ታሞበታል፤ በአፋጣኝ ሕክምና ማግኘት አለበት። ሆኖም ስምኦን በጣም ድሀ ስለሆነ ማሳከሚያ ገንዘብ የለውም። ምን ቢያደርግ ይሻለዋል? ሚካኤል የተባለው ክርስቲያን ወንድሙ በገንዘብ ረገድ ከእሱ የተሻለ አቅም አለው። ምናልባት ሚካኤል ለስምኦን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ያበድረው ይሆናል። ይሁን እንጂ ስምኦን ብድሩን መልሶ መክፈል የመቻሉ ጉዳይ የማይመስል ነገር መሆኑን ያውቃል።a

ስምኦን ብድር በጠየቀው ጊዜ ሚካኤል ምን እንደሚያደርግ ግራ ገባው። ሚካኤል ገንዘቡ በእርግጥ ለስምኦን እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል፤ ሆኖም ስምኦን ገንዘቡን መልሶ መክፈል ስለመቻሉ ጥርጣሬ አድሮበታል። ምክንያቱም ቤተሰቡን ለመመገብ ብቻ እንኳ ምን ያህል ከባድ ትግል እንዳለበት ያውቃል። ሚካኤል ምን ቢያደርግ ይሻለዋል?

በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች በድንገት መተዳደሪያቸውን ሊያጡና የሕክምና ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስችል ገንዘብ ወይም ኢንሹራንስ ላይኖራቸው ይችላል። ከባንክ መበደር የማይቻል አሊያም ከፍተኛ ወለድ የሚጠይቅ ይሆናል። ድንገተኛ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከጓደኛ መበደር ይሆናል። ሆኖም ብድር ከመጠየቅ በፊት ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮች አሉ።

ወጪውን አስሉ

ቅዱሳን ጽሑፎች ለአበዳሪውም ሆነ ለተበዳሪው የሚጠቅሙ መመሪያዎች ይዘዋል። እነዚህን ምክሮች በመከተል ብዙ አለመግባባቶችንና በስሜት መቆሳሰልን ማስቀረት እንችላለን።

ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ የመበደርን ጉዳይ አቅልለን እንዳንመለከት ይመክረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል:- “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፣ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና።” (ሮሜ 13:​8) በመሠረቱ፣ አንድ ክርስቲያን ከፍቅር በስተቀር የሌሎች ዕዳ ሊኖርበት አይገባም። ስለሆነም ለመበደር ስናስብ በመጀመሪያ ‘በእርግጥ ይህ ብድር የግድ ያስፈልገኛልን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።

መልሱ አዎን፣ ያስፈልገኛል የሚል ከሆነ ባለ ዕዳ መሆን የሚያስከትላቸውን መዘዞች ማጤኑ ጥበብ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት የሆኑ ውሳኔዎች በጥንቃቄ ማጤንንና ዕቅድ ማውጣትን እንደሚጠይቁ ገልጿል። ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል ጠይቋቸዋል:- “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?” (ሉቃስ 14:​28) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት አንድን ወንድም ብድር ለመጠየቅ ወይም ላለመጠየቅ በሚታሰብበት ጊዜም ይሠራል። መበደር የሚጠይቀውን ወጪ ማስላት ሲባል ብድሩን እንዴትና መቼ እንደምንከፍል ማስላት ማለት ነው።

አበዳሪው ብድሩ እንዴትና መቼ እንደሚከፈለው የማወቅ መብት አለው። ጉዳዮቹን በጥሞና በማመዛዘን ተጨባጭ የሆኑ መልሶች ልንሰጠው እንችላለን። የተበደርነውን ገንዘብ ምክንያታዊ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ከፍሎ ለመጨረስ የሚጠይቀውን ወጪ አስልተናል? እርግጥ ነው ለወንድማችን “በተቻለኝ መጠን ወዲያውኑ እከፍልሃለሁ። እሱን በኔ ላይ ተወው” ብሎ መናገሩ በጣም ቀላል ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ይበልጥ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መያዝ አይገባንምን? ይሖዋ የተበደርነውን እንድንከፍል ስለሚጠብቅብን ገና ከመበደራችን በፊት ለመክፈል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። መዝሙር 37:​21 “ኃጢአተኛ ይበደራል አይከፍልምም” ይላል።

የተበደርነውን ገንዘብ እንዴትና መቼ እንደምንከፍል በማስላት የምንገባው ቃል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ራሳችንን እናስገነዝባለን። እንዲህ ማድረጋችን አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ የመግባቱን አጋጣሚ ይቀንሰዋል። ዕዳ ውስጥ የመግባት አጋጣሚውን ማስወገድ መቻላችን ጥቅሞች አሉት። ምሳሌ 22:​7 እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።” ሌላው ይቅርና አበዳሪውም ሆነ ተበዳሪው መንፈሳዊ ወንድማማቾች በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ገንዘብ መበደር በመጠኑም ቢሆን ግንኙነታቸውን ሊነካባቸው ይችላል። ብድርን በተመለከተ የተፈጠሩ አለመግባባቶች የአንዳንድ ጉባኤዎችን ሰላም እስከማናጋት ደርሰዋል።

ገንዘቡን የፈለግህበትን ምክንያት ግለጽ

አበዳሪው የተበደርነውን ገንዘብ ለምን ዓላማ እንደምናውለው የማወቅ መብት አለው። ከዚህ ብድር በተጨማሪ ከሌሎች ሰዎችም ገንዘብ እንበደራለን? ይህ ከሆነ ብድሩን ለመክፈል በሚኖረን አቅም ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድር ጉዳዩን ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል።

በተለይ ደግሞ ለንግድ በሚውልና ለአንዳንድ ድንገተኛ ጉዳዮች በሚያስፈልግ ብድር መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ወንድም ለንግድ ጉዳይ የሚውል ገንዘብ የማበደር ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ የለበትም። ይሁን እንጂ አንድ ሌላ ወንድም ከቁጥጥሩ ውጪ በሆነ ምክንያት እንደ ምግብ፣ ልብስ ወይም አስፈላጊ የሕክምና ወጪዎች ለመሳሰሉ መሠረታዊ ነገሮች መክፈል ቢያቅተው ገንዘብ የሚያበድረው ወንድም እሱን ለመርዳት ይገፋፋ ይሆናል። በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ አለመግባባቶችን ለማስወገድ ግልጽ መሆንና እውነቱን መናገር ይረዳናል።​—⁠ኤፌሶን 4:​25

በጽሑፍ አስፍሩት

ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን ማስቀረት እንዲቻል ስምምነቱን በጽሑፍ ማስፈር አስፈላጊ ነው። ስምምነቱ በጽሑፍ ካልሰፈረ አንዳንድ የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች በቀላሉ ሊረሱ ይችላሉ። የብድሩን መጠንና መቼ እንደሚከፈል በጽሑፍ ማስፈር ይኖርብናል። ተበዳሪውም ሆነ አበዳሪው ስምምነቱ ላይ መፈረማቸውና እያንዳንዳቸውም የግል ቅጂ መያዛቸው የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ዝውውሮች በጽሑፍ መያዝ እንዳለባቸው ያሳያል። ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ከመደምሰስዋ ከጥቂት ጊዜ በፊት ይሖዋ ኤርምያስን ከዘመዶቹ መካከል ከአንዱ መሬት እንዲገዛ ነግሮት ነበር። እርሱ የተከተለውን አሠራር በመከለስ ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

ኤርምያስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በዓናቶትም ያለውን እርሻ ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፣ አሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት። በውሉም ወረቀት ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፣ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት። የታተመውንና የተከፈተውን የውል ወረቀት ወሰድሁ፤ የአጎቴም ልጅ አናምኤል፣ የውሉንም ወረቀት የፈረሙ ምስክሮች፣ በግዞትም ቤት አደባባይ የተቀመጡ አይሁድ ሁሉ እያዩ የውሉን ወረቀት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።” (ኤርምያስ 32:​9-12) ምንም እንኳ ከላይ ያለው ምሳሌ ግዢን እንጂ ብድርን ባያመለክትም የገንዘብ ዝውውሮችን ግልጽና አሻሚ ባልሆነ መንገድ የመያዝን አስፈላጊነት ያሳያል።​—⁠የግንቦት 1, 1973 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 287-8ን ተመልከት።

ችግሮች ከተከሰቱ ክርስቲያኖች በማቴዎስ 18:​15-17 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው የኢየሱስ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት መጣር አለባቸው። ይሁን እንጂ እነዚህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ እርዳታ ለማበርከት የሞከረ አንድ ሽማግሌ የሚከተለውን ሐሳብ ተናግሯል:- “በእያንዳንዱ አጋጣሚ ማለት ይቻላል በጽሑፍ የሰፈረ ስምምነት አልነበረም። ከዚህ የተነሳ ብድሩ በምን መልክ መከፈል እንዳለበት በሁለቱ ወገኖች መካከል ግልጽ የሆነ መግባባት አልነበረም። እነዚህን ጉዳዮች በጽሑፍ ማስፈሩ የፍቅር እንጂ የአለመተማመን ምልክት አለመሆኑን ተቀብያለሁ።”

አንዴ ስምምነት ካደረግን በኋላ ዝንፍ ሳንል ቃላችንን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧል:- “ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው።” (ማቴዎስ 5:​37) አንድ ያልጠበቅነው ችግር ብድሩን በፕሮግራሙ መሠረት ከመክፈል ካገደን ሳንዘገይ ሁኔታውን ለአበዳሪው ማስረዳት ይኖርብናል። ምናልባትም ብድሩን ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ በትንሽ በትንሹ እንድንከፍል ሊፈቅድልን ይችላል።

ሆኖም የሁኔታዎች አለመመቻቸት ከኃላፊነቶቻችን ነፃ አያደርጉንም። ይሖዋን የሚፈራ ሰው ቃሉን ለመጠበቅ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። (መዝሙር 15:​4) ምንም እንኳ ያሰብናቸው ነገሮች እንደተጠበቁት ሳይሆኑ ቢቀሩም ክርስቲያናዊ ግዴታችን እስከሆነ ድረስ ዕዳችንን ለመክፈል ስንል መሥዋዕቶች ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን።

ገንዘብ ማበደርን በተመለከተ ጠንቃቃ ሁን

እርግጥ ነው ጉዳዩን በጥንቃቄ ማመዛዘን ያለበት ተበዳሪው ብቻ አይደለም። ብድር የተጠየቀው ወንድምም ወጪውን ማስላት አለበት። ገንዘብ ከማበደራችን በፊት ነገሮቹን በጥንቃቄና ባልተዛባ መንገድ ለመመርመር ጊዜ መውሰዳችን የጥበብ እርምጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥንቃቄ የመውሰድን አስፈላጊነት እንዲህ በማለት ያሳስባል:- “እጃቸውን አጋና እንደሚማቱ፣ ለባለ ዕዳዎች እንደሚዋሱ አትሁን።”​—⁠ምሳሌ 22:​26

ቃል ከመግባትህ በፊት ብድር የጠየቀህ ወንድም መክፈል ቢያቅተው ምን ሊከሰት እንደሚችል አስብ። በዚህ ጊዜ አንተ ራስህ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ይገጥምህ ይሆን? ምንም እንኳን ወንድም በእርግጠኝነት መልሶ እንደሚከፍል በማሰብ ብድር ቢጠይቅም ሁኔታዎች ሊቀየሩ ወይም እሱ ባሰበው መንገድ ላይሄዱ ይችላሉ። ያዕቆብ 4:​14 ሁላችንንም እንዲህ በማለት ያሳስበናል:- “ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።”​—⁠ከመክብብ 9:​11 ጋር አወዳድር።

በተለይም ብድሩ ለንግድ ሥራ የሚውል በሚሆንበት ጊዜ ተበዳሪው በሌሎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም እንዳለው ለማወቅ መጣሩ ጥበብ ይሆናል። የሚታወቀው ታማኝና እምነት የሚጣልበት ሰው እንደሆነ ነው? ወይስ ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች አያያዝ እንደማይችል? በጉባኤ ውስጥ ወዳሉ ወደተለያዩ ወንድሞች እየሄደ ገንዘብ የመጠየቅ ልማድ አለውን? የሚከተሉትን ቃላት ማስታወሱ ጥበብ ነው:- “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።”​—⁠ምሳሌ 14:​15

ማበደርህ አንዳንድ ጊዜ ተበዳሪውን የባሰ ችግር ውስጥ የሚከተው ሊሆን ይችላል። ለእርሱም ቢሆን ደስታውን የሚያሳጣ ሸክም ሊሆንበት ይችላል። ይህ ዓይነቱ ወንድም የእኛ “አገልጋይ” እንዲሆን እንፈልጋለን? ብድሩን መክፈል ካቃተው የመሸማቀቅ ብሎም የኃፍረት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ዝምድናችንን ሊጎዳብን ይችል ይሆን?

በእርግጥ ገንዘቡ አስፈልጎት ከሆነ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ብድር ከመስጠት ይልቅ በስጦታ መልክ ለመስጠት አቅሙ እንዳለን መገምገም እንችላለን? ቅዱሳን ጽሑፎች ወንድማችን ተቸግሮ ስናይ ርኅራሄ እንድናሳይ ያበረታቱናል። መዝሙራዊው ‘ጻድቅ ይራራል ይሰጣልም’ ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 37:​21) ፍቅር በችግር ላይ ላሉ ወንድሞቻችን አቅማችን የሚፈቅድልንን ያህል ተግባራዊ እርዳታ እንድንሰጥ ሊያነሳሳን ይገባል።​—⁠ያዕቆብ 2:​15, 16

የምትወስዷቸውን እርምጃዎች በጥንቃቄ መርምሩ

ብድር መቃቃርን ሊፈጥር የሚችል ነገር ስለሆነ ሌላ አማራጭ ካልጠፋ በቀር እንዲሁ በቀላሉ የሚገባበት ነገር አለመሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል። ከላይ እንደተጠቀሰው ተበዳሪው ብድሩን እንዴትና መቼ እንደሚከፍል በጽሑፍ በማስፈር ከአበዳሪው ጋር በግልጽ መግባባት አለበት። እውነተኛ ችግር በሚከሰትበት ጊዜ ደግሞ ከሁሉ የተሻለው መፍትሄ በስጦታ መልክ መስጠት ሊሆን ይችላል።

ሚካኤል፣ ስምኦን የጠየቀውን ገንዘብ አላበደረውም። ከዚህ ይልቅ ሚካኤል አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በስጦታ መልክ ሰጠው። ስምኦን ልጁን ማሳከም እንዲችል ለተደረገለት ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነበር። ሚካኤልም ወንድማዊ ፍቅሩን ተግባራዊ በሆነ መንገድ መግለጽ በመቻሉ ተደስቷል። (ምሳሌ 14:​21፤ ሥራ 20:​35) ሚካኤልም ሆነ ስምኦን ክርስቶስ በመንግሥቱ ግዛት ሥር ‘ችግረኛውን ከቀማኛ እጅ የሚያድንበትንና’ ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” የማይልበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (መዝሙር 72:​12፤ ኢሳይያስ 33:​24) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ወንድማችንን የግድ ብድር መጠየቅ እንዳለብን ከተሰማን የምንወስዳቸውን እርምጃዎች በጥንቃቄ እናመዛዝን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ በሌላ ተተክተዋል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የብድር ስምምነቶችን በጽሑፍ ማስፈር የፍቅር እንጂ የአለመተማመን ምልክት አይደለም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ