ሰዎች እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩትን ቅርሳ ቅርሶች በአምልኮ የሚጠቀሙባቸው ለምንድን ነው?
እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በኔፕልስ ኢጣልያ እንዳለህ አድርገህ ገምት። በካቴድራሉ ውስጥ ጆርጅ በርክሌይ የተባለው የአየርላንድ ፈላስፋ በአንድ ዝነኛ ሃይማኖታዊ ቅርስ ፊት ቆሟል። የካቶሊክ ቅዱስ የሆነውን ጀኑዋሪየስን ማለትም የ“ሳን ጄናሮ”ን ፈሳሽ ደም የሚመስል ነገር በጥርጣሬ ይመለከታል።
ኔፕልስ በዚህ ረገድ እምብዛም አልተለወጠችም። ለምሳሌ ያህል በቅርብ ዓመት በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ተአምር ተፈጽሟል በመባሉ ምክንያት የነበረውን መጥፎ የአየር ሁኔታ ሁሉ ተቋቁሞ የመጣው ብዙ ሕዝብ ይተራመስ ነበር። ቅርሱንና በዋናው ሊቀ ጳጳስ የሚመራውን ሰልፍ ሕዝቡ በሞቀ ጭብጨባ ሰላምታ ሰጠው። አዎን ይህ የ“ሳን ጄናሮ” ደም ሲፈስ ታየ ከተባለባቸው ብዙ ጊዜያት አንዱ ነው። ከ14ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በዚህ ሃይማኖታዊ ቅርስ ላይ ተአምር ሲፈጸም ቆይቷል ይባላል።
(ሬሊንኩዌሬ ከሚባለው የላቲን ቃል የመጣውና ትርጉሙ “ወደኋላ መተው” ማለት የሆነው) ሲወርድ ሲዋረድ ለመጣው የካቶሊክ ልማድ መሠረት ቅዱስ ነው ተብሎ በሚታሰብ ሰው የተተወ ዕቃ ነው። ዲዚዮናሪዮ ኤክለሲያስቲኮ እንደሚያመለክተው ሬሊክስ (ቅዱስ ተደርጎ የሚታይ ቅርስ) “በደንበኛው የቃሉ አባባል መሠረት የቅዱሱ ሰው አካል ወይም የአካል ክፍል ወይም የቅዱሱ አካል አመድ ሲሆን ባጠቃላይ አባባል ደግሞ ከቅዱስ አካል ጋር የተነካካና ሊመለክ የሚገባው ዕቃ ሊሆን ይችላል።”
የጳጳሱ ድጋፍ
ብዙዎች ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በአክብሮት የሚያዩት ቅርሶቹ ፈጸሙአቸው በሚባሉት ተአምራት ምክንያት መሆኑ አያጠራጥርም። ለቅርሶቹ ዝነኛነት ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች አንዱ የሊቀ ጳጳሳቱ ድጋፍ ነው።
ባለፉት 70 ዓመታት ከተነሡት ሊቃነ ጳጳሳት ቢያንስ አራቱ እንደ ቅዱስ ተደርገው ለሚታዩ ቅርሶች የተለየ ትኩረት ሰጥተዋል። ፓፓ ፓየስ 12ኛ ከሳቸው በፊት እንደነበሩት ፓፓ ፓየስ 11ኛ የቅዱስ ሊሲዩክስን ቅርሶች ይዘው ይዞሩ እንደነበረ፣ ጳውሎስ 4ኛ በቢሮአቸው ውስጥ የሐዋርያው [ቶማስን] ጣት በዴስካቸው ላይ እንደሚያስቀምጡ እና ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በራሳቸው መኖሪያ ቤት ውስጥ የ“ቅዱስ ቤነደክት”ንና የ“ቅዱስ እንድርያስን” “. . . ቁርጥራጭ አጽም እንዳስቀመጡ” አንድ የካቶሊክ መጽሔት ይገልጻል።—30 ጂዮርኒ መጋቢት 1990፣ ገጽ 50
እንዲህ ዓይነቱን የሊቃነ ጳጳሳት ድጋፍ ስንመለከት ለግልም ሆነ ለሕዝባዊ አምልኰ የቅርሶች ተፈላጊነት መጨመሩ አያስደንቀንም። ነገር ግን ለሃይማኖታዊ ቅርሶች አክብሮት ማሳየት አምላክን ያስደስታልን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩ ሃይማኖታዊ ቅርሶች የሚቀመጡበት ዕቃ
[ምንጭ]
Courtesy of The British Museum