እንደ ቅዱስ ተደርገው ለሚታዩ ቅርሳ ቅርሶች አክብሮት ማሳየት አምላክን ያስደስተዋልን?
ደሙ በዓመት ሦስት ጊዜ ይፈስሳል የሚባልለት “ሳን ጄኔሮ” እንደ ቅዱስ ተደርገው ከሚታዩት ቅርሳ ቅርሶች አንዱ ነው። የኢየሱስ አስከሬን የተጠቀለለበት ነው የሚባለው ጨርቅም እንደ ቅዱስ ተደርጎ የሚታይ ሌላው ቅርስ ነው። ከኢየሱስ ጋር ዝምድና እንዳላቸው ከሚጠቀሱት ቅርሶች መሃል የሕፃንነት አልጋው (በሮም ትልቅ ባሲሊካ የሚገኝ)፣ ይደግምበት የነበረው መጽሐፍ፣ በሞተበት ጊዜ ተቸንክረውበታል የሚባሉት ከሺህ የሚበልጡ ምስማሮች ይገኛሉ። ከሃይማኖታዊ ቅርሶች መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው የዮሐንስ መጥምቁ ራስና በአውሮፓ የተለያዩ ቦታዎች “የሳንታ ሉሲያ” አስከሬኖች ናቸው የተባሉ አራት አስከሬኖች ይገኛሉ።
እንደ ቅዱስ ተደርገው ከሚታዩት ቅርሳ ቅርሶች ረገድ ዝነኛ ከሆኑት ከተሞች መሃል “ቅዱስ ልብሶች” ኢየሱስ ከውስጥ ይለብሳቸው ነበር ከሚባሉት ቀሚሶች አንዱ የሆነው “ቅዱስ ልብስ” የሚገኝበት አገር የምትገኘው የትራየር ከተማ አንዷ ነች። በቫቲካን ከተማ ብቻ በአንድ ልዩ ግምጃ ቤት ውስጥ ከሺህ በላይ የሆኑ ቅርሶች አሉ። በጀርመን ኮሎኝ ከተማ ቃል በቃል በሺህ የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ቅርሶች “በቅዱስ ኡርሱላ” ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠዋል። በኢጣሊያ ብቻ ሃይማኖታዊ ቅርሶች የሚገኙባቸው 2,468 ቅዱስ ቦታዎች የሚባሉ አሉ!
ለቅርሶች አምልኮታዊ ክብር መስጠትም ሆነ ለ“ቅዱሳን” አምልኮታዊ ክብር መስጠት የተጀመረው ከ4ኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ጀምሮ ነው ተብሎ ይታመናል። በሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና እንዲያውም በፖለቲካዊ ምክንያት ሳይቀር የቅርሶች ቁጥር ባለፉት መቶ ዓመታት በሙሉ ቀስ በቀስ ሲጨምር ቆይቶ በዛሬው ጊዜ በብዙ ሺህ በሚቆጠርበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ቤተ ክርስቲያኗ በልማድዋና በወግዋ መሠረት ለቅዱሳን አምልኮታዊ ክብር ትሰጣለች፤ እውነተኛ ቅርሶቻቸውንና ምስሎቻቸውንም ታከብራለች” በማለት አረጋግጧል። (ኮንስቲትዩሽን “ሳክሮሳንክታይም ኮንሲሊየም” ሱላ ሳክራ ሊተርጂያ ኢን 1 ዶክመንቲ ዴል ኮንሲሎ ቫቲካኖ2, 1980፣ ኢዲዚዮኒ ፖኦሊኔ) “በጣም እውቅ የሆኑትና ምዕመናን በከፍተኛ ቅድስና የሚያከብሩአቸው ቅርሶች” በ1983 ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ባወጡት ኮዴክስ አይዩሪስ ካኖኒቼ (የጥንት ሕግና ደንብ) ላይ ተጠቅሰዋል። (ካኖን 1190) በተጨማሪም አንግሊካውያንና የኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት አባሎች ቅርሶችን ያከብራሉ።
ክርስቶስ የተሰቀለባቸው ናቸው የተባሉና የዮሐንስ መጥምቁ ራሶች ናቸው የተባሉ ብዙ ምስማሮችና ራሶች መኖራቸው ብቻ ሃይማኖታዊ ቅርሶች ሐሰት መሆናቸውን ያሳያል። ለምሳሌ ያህል ክርስቶስ የተከፈነበት ነው የተባለውን ጨርቅ የራዲዮ ካርቦን የዘመን መለኪያ መሣሪያ የውሸት ጨርቅ መሆኑን አረጋግጧል። የሚያስደንቀው ነገር በ1988 የጋለ ክርክር ይደረግ በነበረበት ወቅት እውቁ የቫቲካን ታዛቢ ማርኮ ቶሳቲ “በከፈኑ ላይ የተደረገው ሳይንሳዊ ምርመራ በሌሎቹም በከፍተኛ የሕዝብ ፍቅር በሚከበሩ ዕቃዎችም ላይ ቢደረግ ምን ውሳኔ ላይ ይደረስ ነበር?” ብለው ጠይቀዋል።
በግልጽ እንደሚታየው አዋቂ የሆነ ማንም ሰው የሐሰት ቅርስ ለማክበርና ለማምለክ አይፈልግም። ግን ከግምት ሊገባ የሚገባው ጉዳይ ቅርሱ የሐሰት መሆኑ ብቻ ነውን?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች የነበሩት እስራኤላውያን በግብጽ በባርነት በነበሩበት ጊዜ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ያከብሩ ነበር ብሎ አይነግረንም። እውነት ነው፣ አባታቸው የነበረው ያዕቆብ በግብጽ አገር ሞቶ ሬሣውን “በኤፍሮን እርሻ በምትገኘው ዋሻ” ለመቅበር ወደ ከነዓን ምድር ወስደውታል። ልጁ ዮሴፍም በግብጽ ሞቶ አጽሙ ወደ ከነዓን ተወስዶ ተቀብሯል። (ዘፍጥረት 49:29-33፤ 50:1-14, 22-26፤ ዘፀአት 13:19) ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች እሥራኤላውያን የያዕቆብንና የዮሴፍን አጽሞች ሃይማኖታዊ ቅርስ አድርገው እንደተጠቀሙባቸው አያመለክቱም።
እንደዚሁም በነቢዩ ሙሴ ረገድ የተፈጸመውን አስብ። ሙሴ በአምላክ መመሪያ መሠረት እስራኤላውያንን ለ40 ዓመታት መርቷል። ከዚያም በ120 ዓመት ዕድሜው ወደ ናባው ተራራ ወጥቶ የተስፋይቱን ምድር አየና ሞተ። የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስለሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር ተከራከረና ሰይጣን እስራኤላውያንን በቅርስ አምልኮ ለማጥመድ እንዳይጠቀምበት ያደረገውን ሙከራ አከሸፈበት። (ይሁዳ 9) ልንረዳ እንደምንችለው ሙሴ በመሞቱ ምክንያት ቢያለቅሱም ለአጽሙ አምልኮታዊ ክብር አልሰጡም። እንዲያውም አምላክ የሙሴን አስከሬን ሰዎች ሊያውቁና ሊያገኙት በማይችሉበት ቦታ ስለቀበረው አጽሙን እንደ ቅርስ አድርገው ለማምለክ እንዳይችሉ አድርጓል።—ዘዳግም 34:1-8
አንዳንድ ቅርሶች መከበር ይገባቸዋል ብለው የሚከራከሩ ሰዎች፦ “ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ። ሬሣውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት። የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ” የሚለውን 2 ነገሥት 13:21ን ይጠቅሳሉ። ይህ ከአምላክ ነቢያት አንዱ የነበረው ነቢይ በድን አጽም የፈጸመው ተአምር ነበር። ነገር ግን ኤልሳዕ ተአምሩ በተፈጸመበት ጊዜ ሞቶ ስለነበረ “አንዳች የማያውቅ” ሰው ነበር። (መክብብ 9:5, 10) ስለዚህ ይህ ትንሣኤ በመንፈስ ቅዱስ ወይም በአምላክ ሠራተኛ ኃይል አማካኝነት የተፈጸመ የይሖዋ ተአምር መሆን አለበት። ቅዱሳን ጽሑፎች የኤልሳዕ አጽሞች ይከበሩ ነበር እንደማይሉም መታወስ አለበት።
በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች በሥራ 19:11, 12 ላይ “እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር። ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር። ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር። ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር” ስለተባለ ቅርሶችን ማክበርን አጥብቀው ይደግፋሉ። እነዚያን ተአምራት በጳውሎስ በኩል ያደርግ የነበረው አምላክ ነው መባሉን አስተውሉ። ሐዋርያው እንዲህ ዓይነቶቹን ተአምራት የፈጸመው በራሱ ችሎታ አልነበረም። እርሱ የሰዎችን አክብሮት ተቀብሎ አያውቅም።—ሥራ 14:8-18
ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ይጋጫል
እንደ እውነቱ ከሆነ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ማምለክ በርካታ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የሚቃረን ነው። ለምሳሌ ያህል ለዚህ አምልኮ በጣም አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ በነፍስ አለመሞት ማመን ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ለሃይማኖታቸው ያደሩ የቤተክርስቲያን አባሎች የ“ቅዱስነት” ማዕረግ የተሰጣቸው ሰዎች ነፍሳት በሰማይ ሕያው ሆነው ይኖራሉ ብለው ያምናሉ። እነዚህ ቅን ሰዎች እነዚህ “ቅዱሳን” እንዲጠብቋቸውና ከአምላክ ጋር እንዲያማልዷቸው ወደነሱ ይጸልያሉ። እንዲያውም አንድ የቤተክርስቲያን ጽሑፍ እንደሚገልጸው “ቅዱሱ ከአምላክ ጋር ለማማለድ ያለውን ኃይል ለቅርሱ ይሰጡታል። ማለትም ቅርሱ ራሱ የሚያማልዳቸው ይመስላቸዋል።”
ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሰው ነፍስ የማትሞት አይደለችም። ሰዎች ከሞቱ በኋላ ከሥጋ ተለይተው መኖር የሚችሉ የማይሞቱ ነፍሶች በውስጣቸው የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሉት “ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው። በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበትና ሰው ሕያው ነፍስ ሆነ” ነው። (ዘፍጥረት 2:7) መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የማይሞቱ ነፍሶች አሏቸው ብሎ በማስተማር ፈንታ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” ይላል። (ሕዝቅኤል 18:4) ይህም በሁሉም ሰዎች ላይ፣ “ቅዱስ” የሚል ስያሜ በተሰጣቸውም ላይ ጭምር ይሠራል። ምክንያቱም ሁላችንም ኃጢአትንና ሞትን ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ወርሰናል።—ሮሜ 5:12
ለቅዱሳን አምልኮ መሰል አክብሮት መስጠት ተገቢ የማይሆነው እነዚህን ቅዱሳን ናቸው የሚባሉ ሰዎች ሰውን ከአምላክ ጋር የማማለድ ሥልጣን ፈጽሞ ስለሌላቸው ነው። ይሖዋ አምላክ የማማለድ ሥልጣን የሰጠው ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ “ለእኛ መሞቱ ብቻ ሳይሆን ከሙታንም ተነሥቷል። በአምላክ ቀኝ በመሆንም ስለ እኛ ይለምንልናል” ብሏል።—ሮሜ 8:34 እንደ ኢየሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከዮሐንስ 14:6, 14 ጋር አወዳድሩ።
ለ“ቅዱሳን”ና ለሃይማኖታዊ ቅርሶች አምልኮ መሰል አክብሮት ከመስጠት የምንርቅበት ሌላው ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጣዖት በሚናገረው ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። ለእስራኤላውያን ከተሰጡት አሥር ትዕዛዛት አንዱ “በላይ በሰማይ ካለው በታችም በምድር ካለው ከምድርም በታች በውሃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸባቸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም። ... እኔ ይሖዋ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና” ይላል። (ዘፀአት 20:4, 5) ብዙ መቶ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ለመሰል ክርስቲያኖች “ወዳጆች ሆይ ጣኦትን ከማምለክ ሽሹ” ብሎ ነግሯቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:14) በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ ከጣኦታት ራሳችሁን ጠብቁ” ብሎ ጽፎአል።—1 ዮሐንስ 5:21
እንግዲያው “ቅዱስ” የሚባል ስያሜ የተሰጣቸውንም ሰዎች ሆነ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን አምልኮታዊ አክብሮት መስጠት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም ድጋፍ አያገኝም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች እንደ ቅዱስ የሚቆጠሩት ሊታይና ሊዳሰስ የሚችልና የማዳን ኃይል አለው የሚባል ነገር እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። በእርግጥም ብዙ ሰዎች ሃይማኖታዊ ቅርሶችን የሚመለከቷቸው በሰማይና በምድር መሃል አገናኝ እንደሆኑ የሚታዩ ሰንሰለቶች አድርገው ነው። እስቲ ይህን ነጥብ ለአንድ አፍታ አስብ።
አንድ ሰው አምላክ ስለሚፈልገው አምልኮ ኢየሱስ ከተናገረው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ሊያመልክ የሚችለው ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በማየትና በመዳሰስ አይደለም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። አሁንም ሆኗል። አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና። እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” (ዮሐንስ 4:23, 24) ይሖዋ አምላክ ለሰው ዓይን የማይታይ “መንፈስ” ነው። እሱን “በመንፈስ” ማምለክ ማለት ደግሞ የምናቀርብለት ፍቅርና እምነት በተሞላ ልብ ተገፋፍተን ለእሱ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ ማለት ነው። (ማቴዎስ 22:37-40፤ ገላትያ 2:16) አምላክን “በእውነት” የምናመልከው ቅርሶችን በማክበር ሳይሆን ሃይማኖታዊ ውሸቶችን አስወግደን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ፈቃዱን በመማርና በማድረግ ነው።
እንግዲያውስ ምሁሩ ጀምስ ቤንትለይ “የጥንት ዕብራውያን ቅርሶችን የማክበር ልማድ አልነበራቸውም” በማለት ማረጋገጣቸው አያስደንቅም። እንደዚሁም እስጢፋኖስ በሞተበትና አስከሬኑ በሉሲያን ተቆፍሮ በወጣበት ጊዜ መሃል በነበሩት አራት መቶ ዓመታት ወቅት ክርስቲያኖች ለቅርስ የነበራቸው ዝንባሌ ሙሉ በሙሉ እንደተለወጠም ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በአምስተኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከሐዲዋ ሕዝበ ክርስትና ስለ ጣዖት፣ ስለሙታን ሁኔታ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ለእኛ በማማለድ’ ረገድ ስላለው ሚና የሚናገሩትን ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ቀደም ሲል ጀምሮ መከተሏን አቁማ ነበር።—ሮሜ 8:34፤ መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11-14
አምልኮታችን አምላክን እንዲያስደስተው ከፈለግን ከማንኛውም ዓይነት ጣኦት አምልኮ ጋር የማዛመድ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። አምልኰታችን ተቀባይነት ለማግኘት ወደማንኛውም ዓይነት ቅርስ ወይም ፍጡር ሳይሆን ፈጣሪአችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ መቅረብ አለበት። (ሮሜ 1:24, 25፤ ራእይ 19:10) የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት ማግኘትና ጠንካራ እምነት መገንባት አለብን። (ሮሜ 10:17፤ ዕብራውያን 11:6) በእውነተኛ የአምልኰ መንገድ የምንመላለስ ከሆነ እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩትን ቅርሳ ቅርሶች ማምለክ አምላክን እንደማያስደስተው ከሚገልጹት ብዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ጋር መስማማት ይኖርብናል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኤልሣዕ አጥንት ከትንሣኤ ጋር በተያያዘ ቢጠቀስም እንደ ቅዱስ ተደርጎ የሚታይ አልነበረም