“የበላይ ተመልካች . . . ራሱን የሚገዛ ሊሆን ይገባዋል”
“የበላይ ተመልካች . . . ራሱን የሚገዛ ሊሆን ይገባዋል።”—ቲቶ 1:7, 8
1, 2. የኦሬንጁ ዊሊያም ምን ራስን የመግዛት ምሳሌ አሳይቷል? ምንስ ጠቃሚ ውጤት አገኘ?
ስሜትን በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ታሪክ አለ። በ16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የዳች አገር የኦሬንጅ መስፍን የነበረው ወጣቱ ዊሊያም ከፈረንሳዩ ንጉሥ ዳግማዊ ሄንሪ ጋር አደን ሄዶ ነበር። ንጉሥ ሄንሪ እሱና የእስፓኝ ንጉሥ በፈረንሳይና በኔዘርላንድ አገሮች፣ እንዲያውም በሁሉም የሕዝበ ክርስትና አገሮች በሙሉ ያሉትን ፕሮቴስታንቶች በሙሉ ለማጥፋት ያወጡትን ዕቅድ ለዊሊያም ገለጸለት። ንጉሥ ሄንሪ ወጣቱ ዊሊያም እንደ እሱ ግትር የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነ ስለመሰለው የሴራውን ዝርዝር ምስጢር ሁሉ ገለጸለት። ዊሊያም የቅርብ ወዳጆቹ ሁሉ ፕሮቴስታንቶች ስለነበሩ የሰማው ነገር አሰቀቀው። ሆኖም ስሜቱ አልተለወጠበትም። ከዚህ ይልቅ ንጉሡ የነገረውን ዝርዝር በሙሉ በትኩረት አዳመጠ።
2 ይሁንና ዊሊያም በተቻለው ፍጥነት ሴራውን ለማክሸፍ ጥረት ማድረግ ጀመረ። ይህም ጥረቱ በመጨረሻ ላይ ኔዘርላንድን ከእስፓኝ የካቶሊክ አገዛዝ ነፃ ሊያደርግ ችሏል። ዊልያም መጀመሪያ ሴራውን ሲሰማ ራሱን በመግዛቱ “ዝምተኛው ዊሊያም” በመባል ታውቋል። የኦሬንጁ ዊሊያም በጣም የተሳካ ውጤት በማስገኘቱ “የዳች ሪፑብሊክ ነፃነትና ታላቅነት እውነተኛ መሥራች ነበር” ተብሏል።
3. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ራስን የመግዛት ባሕርይ ሲያሳዩ ማን ይጠቀማል?
3 ዊሊያም ዝምተኛው ራሱን በመግዛቱ ራሱንና ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ ጠቅሟቸዋል። ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ከዚህ ጋር በሚመሳሰል የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነውን ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት ይገባቸዋል። (ገላትያ 5:22, 23) ይህን ጠባይ በማሳየትም ራሳቸውንም ሆነ ጉባኤዎቻቸውን ይጠቅማሉ። በሌላ በኩል ግን ራስ የመግዛትን ባሕርይ ሳያሳዩ ቢቀሩ መጠን የሌለው ጉዳት ሊደርስ ይችላል።
ራስን መግዛት ከሽማግሌዎች የሚፈለግ ባሕርይ ነው
4. ሽማግሌዎች ራሳቸውን መግዛት እንደሚያስፈልጋቸው አጥብቆ የሚያሳስበው የትኛው የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ነው?
4 ራሱ ሽማግሌ የነበረው ጳውሎስ የራስ መግዛትን ጠቃሚነት ተገንዝቧል። ከኤፌሶን ወደሱ የመጡትን ሽማግሌዎች ሲመክራቸው “ለራሳችሁና ለመንጋው ተጠንቀቁ” በማለት ነግሯቸዋል። ለራሳቸው መጠንቀቅ ማለት ከሌሎች ነገሮች መሃል ራስ የመግዛትን ባሕርይ ማሳየት አስፈላጊ መሆኑንና በአኗኗራቸው ረገድ መጠንቀቅን ይጨምራል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ” በማለት ይህንኑ ጉዳይ አመልክቷል። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መምከሩ አንዳንድ ሰዎች የሚሰብኩትን ነገር በተግባር ከመግለጽ ይልቅ ስለመስበክ ብቻ በመጨነቅ የሚያሳዩትን ሰብአዊ ዝንባሌ እንደተገነዘበ ያሳያል። ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ለራሳቸው የመጠንቀቅን አስፈላጊነት አጥብቆ አሳሰበ።—ሥራ 20:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16
5. ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሾሙት እንዴት ነው? ብቃታቸውስ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የት ነው?
5 ባለፉት ዓመታት ሁሉ የሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ የሥራ ድርሻ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ዛሬ ሽምግልና የሹመት ሥራ መሆኑን አውቀናል። ሽማግሌዎች የሚሾሙት በይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል ወይም በአስተዳደር አካሉ ቀጥተኛ ተወካዮች ነው። ይህም የአስተዳደር አካል “ታማኝና ልባም ባሪያን” የሚወክል ነው። (ማቴዎስ 24:45-47) ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ወይም ሽማግሌ ለመሆን የሚያስችሉት ብቃቶች በመጀመሪያ የተገለጹት በሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን በ1 ጢሞቴዎስ 3:1-7 እና ቲቶ 1:5-9 ላይ ይገኛሉ።
6, 7. ራስ መግዛትን የሚጠይቁት በተለይ የትኞቹ የሽማግሌዎች ብቃቶች ናቸው?
6 ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3 ላይ አንድ የበላይ ተመልካች በልማዶቹ ሁሉ ልከኛ መሆን እንዳለበት ይናገራል። ይህና አንድ ሽማግሌ በሥርዓት እንዲመላለስ አስፈላጊ መሆኑ ራሱን እንዲገዛ ያስገድደዋል። ለበላይ ተመልካችነት ብቁ የሚሆን ሰው ተናዳፊ ወይም ጠብ ወዳድ አይደለም። በተጨማሪም እነዚህ ብቃቶች አንድ ሽማግሌ ራሱን የሚገዛ እንዲሆን ይጠይቃሉ። ከዚህም በላይ አንድ ሽማግሌ ሰካራምና ለወይን ጠጅ የሚጐመጅ እንዳይሆን ራሱን መግዛት ይኖርበታል።
7 ጳውሎስ በቲቶ 1:7 ላይ አንድ የበላይ ተመልካች ራሱን የሚገዛ መሆን እንዳለበት ለይቶ ተናግሯል። ይሁን እንጂ እነዚህ ቁጥሮች ላይ ከተጠቀሱት ብቃቶች ስንቶቹ ራስ መግዛትን የሚጠይቁ እንደሆኑ ልብ በሉ። ለምሳሌ ያህል የበላይ ተመልካች ከክስ ነፃ የሆነ አዎ የማይነቀፍ መሆን አለበት። በእርግጥ አንድ ሽማግሌ ራስ የመግዛትን ባሕርይ ካላሳየ በቀር እነዚህን ብቃቶች ሊያሟላ አይችልም።
ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት
8. ራስ የመግዛትን ባሕርይ በጣም አስፈላጊ የሚያደርጉት ሽማግሌዎች ምክር ሲሰጡ የሚያስፈልጓቸው የትኞቹ ጠባዮች ናቸው?
8 በተጨማሪም አንድ የበላይ ተመልካች ታጋሽና ከመሰል አማኞች ጋር ባለው ግንኙነት ትዕግሥተኛ መሆን አለበት። ይህንንም ለማድረግ ራሱን መግዛት ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል በገላትያ 6:1 ላይ “ወንድሞች ሆይ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ መንፈሳውያን (በይበልጥ ሽማግሌዎች) የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት (አስተካክሉት) አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ” የሚል እናነባለን። የየዋህነት መንፈስ ለማሳየት ራስን መግዛት ያስፈልጋል። እንዲያውም ራስን ለመቆጣጠር ራስን የመግዛት ባሕርይም አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም አንድ ሽማግሌ አንድ የተጨነቀ ሰው ለእርዳታ በሚጠራው ጊዜ ራስን መግዛት በጣም ያስፈልገዋል። ሽማግሌው ስለግለሰቡ የሚያስበው መጥፎም ይሁን ደግ፣ ታጋሽና ችግር የሚገባው መሆን አለበት። ሽማግሌው ምክር ለመስጠት ከመቸኮሉ በፊት ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆንና ግለሰቡ ከሚናገረው ነገር የሚያስጨንቀው ነገር ምን እንደሆነ መረዳት አለበት።
9. ሽማግሌዎች የተጨነቁ ወንድሞችን ሲያነጋግሩ በአእምሯቸው መያዝ ያለባቸው ምክር ምንድን ነው?
9 በተለይም በተጨነቁ ሰዎች ጉዳይ ረገድ በያዕቆብ 1:19 ላይ ያለው ምክር በጣም ጠቃሚ ነው፦ “ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቁጣም የዘገየ ይሁን።” አዎን አንድ ሽማግሌ በተለይ የንዴት ወይም ስሜታዊ ምላሽ ሲሰጠው አጸፋውን እንዳይመልስ መጠንቀቅ አለበት። በስሜት ግንፋሎት የሚነገሩ ቃሎችን ተመሳሳይ በሆነ የስሜት ግንፋሎት ላለመመለስና “ክፉ በክፉ ፋንታ ላለመመለስ” ራስን መግዛት ያስፈልጋል። (ሮሜ 12:17) በተመሳሳይ ሁኔታ አጸፋ መመለስ ነገሮችን ያባብሳል። ስለዚህ እዚህ ላይም የአምላክ ቃል ለሽማግሌዎች “የለዘበች መልስ ቁጣን እንደምትመልስ” በማሳሰብ መልካም ምክር ይሰጣቸዋል።—ምሳሌ 15:1
ራስን መግዛት በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይና የፍርድ ጉዳይ በሚሰማበት ጊዜ
10, 11. በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ የራስ መግዛትን አስፈላጊነት የሚያሳይ ምን ሁኔታ አጋጥሟል?
10 ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ራስን የመግዛትን ባሕርይ ማሳየት የሚኖርባቸው ሌላው ዘርፍ በሽማግሌዎች ስብሰባ ጊዜ ነው። ለእውነትና ለፍትሕ ሲባል በረጋ መንፈስ ለመናገር ራስን መግዛት ያስፈልጋል። እኔ ብቻ ልደመጥ ከማለት ለመቆጠብም ራስን መግዛት ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያለው ሽማግሌ ካለ ሌላው ሽማግሌ ምክር ቢለግሰው ደግነት ነው።—ከ3 ዮሐንስ 9 ጋር አወዳድር።
11 ከዚህም ሌላ በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ከልክ በላይ ነገር አክራሪ የሆነ ሽማግሌ ስሜታዊ ለመሆን ሊፈተንና ጮክ ብሎ ሊናገር ይችላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች የራስ መግዛት ባሕርይ የጐደለ መሆኑን ያጋልጣሉ! ውጤት ከማስገኘት ይልቅ ድርብ ጉዳት ያስከትላሉ። በአንድ በኩል አንድ ሰው ራሱን መግዛት በተሳነው መጠን የስሜት ግንፋሎቱ ትክክለኛ አስተሳሰቡን እንዲጋረድበት በማድረግ የራሱን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያዳክማል። በሌላ በኩል ደግሞ ግለሰቡ ስሜታዊ በሆነበት ልክ መሰሎቹን (አብረውት የተሰበሰቡትን) ሽማግሌዎች ሊያበሳጫቸው አልፎ ተርፎም የጥላቻ መንፈስ ሊያሳድርባቸው ይችላል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ካልተጠነቀቁ ጉልህ የሆነ የአስተያየት ልዩነት ተፈጥሮ በመካከላቸው መከፋፈልን ሊያስከትል ይችላል። ይህም ለእነሱ ለራሳቸውና ለጉባኤው ጉዳት ያመጣል።—ከሥራ 15:36-40 ጋር አወዳድር።
12. ሽማግሌዎች ራስ መግዛትን ለማሳየት መጠንቀቅ ያለባቸው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ነው?
12 ሽማግሌዎች አድልዎ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ወይም ሥልጣናቸውን ያለአግባብ እንዳይጠቀሙ ራሳቸውን መግዛት በጣም ያስፈልጋቸዋል። በፈተና መሸነፍና አንድ ሰው የሚናገረውን ወይም የሚያደርገውን ነገር ፍጹም ያልሆነው ሰብአዊ አስተሳሰብ እንዲመራው ማድረግ በጣም ቀላል ነው። ሽማግሌዎች ልጆቻቸው ወይም ሌላ ዘመዳቸው መጥፎ ተግባር ፈጽሞ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ በቆራጥነት እርምጃ መውሰድ አቅቷቸዋል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የሥጋ ዝምድና ትክክለኛ እርምጃ ከመውሰድ እንዳያግድ ለማድረግ ራስን መግዛት ያስፈልጋል።—ዘዳግም 10:17
13. ሽማግሌዎች በፍርድ ጉዳይ ላይ ይበልጥ ራሳቸውን መግዛት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
13 ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላው ሁኔታ የፍርድ ጉዳይ በሚያዳምጡበት ጊዜ ነው። ሽማግሌዎች ከልክ ያለፈ በስሜት እንዳይነዱ ከፍተኛ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት አለባቸው። እንባ በማየታቸው ብቻ ስሜታቸው በቀላሉ የሚነካ መሆን የለበትም። በተመሳሳይም አንድ ሽማግሌ ከከሐዲዎች ጋር ሲነጋገር እንደሚያጋጥመው የሐሰት ክስና ስም አጥፊነት ሲሰነዘርበት እርጋታውን እንዳያጣ መጠንቀቅ አለበት። እዚህ ላይ “የጌታ ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም” የሚሉት የጳውሎስ ቃላት በጣም ተገቢ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ግፊት በሚኖርበት ጊዜ ገርነት ለማሳየት ራስን መግዛት ያስፈልጋል። ጳውሎስ በመቀጠል “የጌታ ባሪያ በትዕግሥት የሚጸና” (ራሱን የሚገታ) “የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚቀጣ” መሆን እንዳለበት ይገልጻል። ተቃውሞ በሚያጋጥምበት ጊዜ ራስን ለመግታትና የየዋህነትን ባሕርይ ለማሳየት ራስን መግዛት ያስፈልጋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25
በተቃራኒ ጾታ ረገድ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት
14. ሽማግሌዎች ለተቃራኒ ጾታ የእረኝነት ጉብኝት ሲያደርጉ የትኛውን መልካም ምክር ማስታወስ ይገባቸዋል?
14 ሽማግሌዎች ከተቃራኒ ጾታዎች ጋር ጉዳይ በሚኖራቸው ጊዜ ራሳቸውን ለመግዛት ጠንቃቆች መሆን አለባቸው። አንድ ሽማግሌ ለእረኝነት ጉዳይ ወደ አንዲት እህት ብቻውን ቢሄድ ጥሩ አይሆንም። ሽማግሌው ሌላ ሽማግሌ ወይም ዲያቆን አስከትሎ መሄድ ይኖርበታል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን፦ “የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች ቆነጃጅቱን እንደ እህቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው” በማለት የመከረው ይህን ችግር ተገንዝቦ ሳይሆን አይቀርም። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) አንዳንድ ሽማግሌዎች የአባትነት ስሜት ያሳዩ መስሎአቸው እጃቸውን በእኅት ትከሻ ላይ ሲጥሉ ታይተዋል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን የሰውነት እንቅስቃሴ ያነሣሣው ንጹሕ ክርስቲያናዊ የወንድምነት ፍቅር ሳይሆን የማሽኮርመም ስሜት ሊሆን ስለሚችል ራሳቸውን ማታለላቸው ሊሆን ይችላል።—ከ1 ቆሮንቶስ 7:1 ጋር አወዳድር።
15. አንድ የተፈጸመ ሁኔታ አንድ ሽማግሌ ራሱን ሳይገዛ ሲቀር በይሖዋ ስም ላይ ሊመጣ ስለሚችለው ውርደት ያሳየው እንዴት ነው?
15 አንዳንድ ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ ካሉ እኅቶች ጋር ባላቸው ቀረቤታ ራስ መግዛትን ባለማሳየታቸው በእውነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ችሏል። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ሽማግሌ ባሏ ምሥክር ካልሆነ አንዲት ክርስቲያን እህት ጋር ስላመነዘረ ተወግዶ ነበር። የዚህ ቀድሞ ሽማግሌ የነበረ ሰው መወገድ ማስታወቂያ በተነገረ ዕለት የተበደለው ባል ሽጉጥ ይዞ ወደ መንግሥት አዳራሹ ገሥግሦ በመምጣት በሁለቱም በዳዮች (በሚስቱና በተወገደው ሰው) ላይ ተኮሰባቸው። አንዳቸውም አልተገደሉም። እሱም ወዲያውኑ መሣሪያውን ተነጠቀ። ነገር ግን ይህ ድርጊት በማግሥቱ በዋነኛ ጋዜጣ መጀመሪያው ገጽ ላይ “ተኩስ በቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ ወጣ። የዚህ ሽማግሌ የራስ መግዛት ጉድለት በጉባኤው ላይና በይሖዋ ስም ላይ ከፍተኛ ሐፍረት አምጥቷል!
በሌሎች ዘርፎች ራስን መግዛት
16. ሽማግሌዎች የሕዝብ ንግግር ሲሰጡ ራስን የመግዛትን ባሕርይ ለማሳየት መጠንቀቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
16 አንድ ሽማግሌ የሕዝብ ንግግር በሚሰጥበት ጊዜም ራሱን መግዛት በጣም ያስፈልገዋል። አንድ የሕዝብ ተናጋሪ ለልበ ሙሉነትና ለእርጋታ መንፈስ ምሳሌ የሚሆን መሆን ይኖርበታል። አንዳንድ የሕዝብ ተናጋሪዎች አድማጮቻቸውን ለማሳቅ በታሰቡ የቀልድ አነጋገሮች ለማሳቅ ይጥራሉ። ይህም አድማጮቻቸውን ለማስደሰት በመጣር ስሜት እንዲሸነፉ ሊያደርጋቸው ይችላል። በእርግጥ ማንኛውንም ዓይነት ፈታኝ ስሜት መሸነፍ የራስ መግዛት ጉድለት ነው። ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ የተወሰነለትን ሰዓት ጠብቆ አለመጨረስና በቂ ዝግጅት አለማድረግም የራስ መግዛት ጉድለትን የሚያሳይ ነው ሊባል ይችላል።
17, 18. ራስን የመግዛት ባሕርይ አንድ ሽማግሌ የተለያዩ ኃላፊነቶቹን በሚዛናዊነት ለማከናወን በመርዳት ረገድ ምን ድርሻ አለው?
17 ማንኛውም ታታሪ ሽማግሌ በጊዜውና በጉልበቱ ላይ የሚጫኑበትን የተለያዩ ኃላፊነቶች ለመወጣት ሚዛኑን ለመጠበቅ መታገል አለበት። አንደኛውን ችላ ብሎ በሌላው ላይ ከልክ በላይ ብዙ ጊዜ እንዳያሳልፍ ራሱን መግዛት ያስፈልገዋል። አንዳንድ ሽማግሌዎች ለጉባኤ ጉዳዮች ሲለፉ ቤተሰባቸውን ችላ ብለዋል። ስለዚህ አንዲት እህት ለአንድ ሽማግሌ ሚስት ጥሩ የእረኝነት ጉብኝት እንዳደረገላት ስትነግራት የሽማግሌው ሚስት “ለእኔም አንድ ቀን የእረኝነት ጉብኝት ቢያደርግልኝ እንዴት ደስ ባለኝ!” ብላ መልሳላታለች።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 4, 5
18 አንድ ሽማግሌ በግል ጥናት የሚያሳልፈውን ጊዜ በመስክ አገልግሎት ወይም በእረኝነት ጉብኝት ከሚያሳልፈው ጊዜ ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ለማድረግ ራሱን መግዛት ያስፈልገዋል። የሰው ልብ አታላይ በመሆኑ አንድ ሽማግሌ የሚበዛውን ጊዜውን ከሚገባው በላይ ለራሱ ደስ በሚለው ነገር ላይ ለማዋል በጣም ይቀለዋል። መጻሕፍት ማንበብ የሚወድ ከሆነ የሚበዛውን ጊዜውን ከሚገባው በላይ በግል ጥናት ላይ ሊያሳልፍ ይችል ይሆናል። ከቤት ወደ ቤት ማገልገል አስቸጋሪ ሆኖ ካገኘው በእረኝነት ጉብኝት በማሳበብ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን አገልግሎት ችላ ሊል ይችላል።
19. ሽማግሌዎች ራስ የመግዛትን ባሕርይ በጣም አስፈላጊ የሚያደርግ ምን ኃላፊነት አለባቸው?
19 ምስጢር የመጠበቅ ግዴታም አንድ ሽማግሌ ራሱን እንዲገዛ የሚያስገድደው ሁኔታ ነው። “የሌላ ሰው ምሥጢር አትግለጥ” የሚለው ምክር አግባብነት ያለው ምክር ነው። (ምሳሌ 25:9) ይህ ጉዳይ ሽማግሌዎች አብዛኛውን ጊዜ ከሚጥሷቸው አስፈላጊ ደንቦች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ተሞክሮ ያመለክታል። አንድ ሽማግሌ በጥሩ ሁኔታ የሚያወያያት ብልህና አፍቃሪ ሚስት ያለችው ከሆነ ምሥጢራዊ ጉዳዮችን የማዋየት ወይም ጠቀስ የማድረግ ዝንባሌ ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ይህ የማይገባና ጥበብ የጐደለው አድራጎት ነው። መጀመሪያ ነገር መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል። መንፈሳዊ ወንድሞችና እኅቶች ወደ ሽማግሌዎች የሚመጡትና ምሥጢራቸውን የሚናገሩት ጉዳዩ በምሥጢርነት እንደሚያዝላቸው እምነት ስላላቸው ነው። ምሥጢራዊ ጉዳዮችን ለሚስት ማካፈል ስሕተት ነው። ጥበብና ፍቅር የጐደለው ነው። ምክንያቱም በሷ ላይ አስፈላጊ ያልሆነ ሸክም ይጥልባታል።—ምሳሌ 10:19፤ 11:13
20. ሽማግሌዎች ራሳቸውን መግዛታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
20 ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም። በተለይ ደግሞ ለሽማግሌዎች በጣም አስፈላጊ ነው! ሽማግሌዎች በይሖዋ ሕዝቦች መሃል አመራር የመስጠት ልዩ መብትና አደራ የተጣለባቸው በመሆኑ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ብዙ ስለተሰጣቸውም ብዙ ይፈለግባቸዋል። (ሉቃስ 12:48፤ 16:10 ከያዕቆብ 3:1 ጋር አወዳድር) ለሌሎች መልካም ምሳሌ መሆን የሽማግሌዎች መብትና ግዴታ ነው። ከዚያም በላይ ለሌሎች ብዙ ጥሩ ነገር ለማድረግ ወይም በሌሎች ላይ ብዙ ጉዳት ለማስከተል በሚያስችል ቦታ ላይ የሚገኙ ናቸው። ይህም በአብዛኛው የተመካው ራሳቸውን በመግዛታቸውና ባለመግዛታቸው ላይ ነው። እንግዲያውስ ጳውሎስ “የበላይ ተመልካች ራሱን የሚገዛ ሊሆን ይገባዋል” ማለቱ አያስደንቅም።
ታስታውሳላችሁን?
◻ ሽማግሌዎች ራሳቸውን መግዛት እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳዩት የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ናቸው?
◻ ሽማግሌዎች ከመሰል አማኞች ጋር ባላቸው ግንኙነት ራሳቸውን መግዛት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
◻ በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ራስን የመግዛት ባሕርይ መታየት ያለበት እንዴት ነው?
◻ ሽማግሌዎች ምሥጢር ጠባቂዎች በመሆን ረገድ ምን ፈተና ያጋጥማቸዋል?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሽማግሌዎች ስብሰባዎች ላይ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሽማግሌዎች ራስን የመግዛት ባሕርይን የሚያሳዩና ምሥጢራዊ የሆኑ ነገሮችን የሚጠብቁ መሆን ይገባቸዋል