የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የዘመን አቆጣጠር መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው በሉቃስ 3:1 ላይ የተጠቀሰው የጢባርዮስ ቄሣር ግዛት የጀመረበት 14 እዘአ ሳይሆን 29 እዘአ የሆነው ለምንድን ነው?
የጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት የጀመረበት ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። ተጠቅሶ የምናገኘው በ15ኛው ዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ ላይ የሆነው ነገር ነው። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህ ድርጊት የተፈጸመው በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር እንደ መነሻ ዓመት ሊቆጠር በሚችለው በ29 እዘአ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል።
ሁለተኛው የሮም ንጉሠ ነገሥት የሆነው የጢባርዮስ ቄሣር ዘመነ መንግሥት በታሪክ በሚገባ የታወቀ ነው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “ነሐሴ 19 14 ዓ.ም. (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር)መጀመሪያው ንጉሠ ነገሥት የነበረው አውግስጦስ ሞተ። የበላይነት ሥልጣን አግኝቶ የነበረው ጢባርዮስ የሮማ ምክር ቤት በሰጠው የንጉሠ ነገሥትነት ሹመት በቃኝ ሳይል ለአንድ ወር ያህል ሲከራከር ከቆየ በኋላ መስከረም 17 ቀን አልጋውን ወረሰ።”a
የጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት የጀመረበት ይህ ዓመት የመነሻ ዓመት መሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር አግባብነት ያለው ነው። ምክንያቱም በሉቃስ 3:1-3 ላይ ስለ ዮሐንስ መጥምቁ አገልግሎት እንዲህ ተብሏል፦ “ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት ጴንጤናዊው ጲላጦስ በይሁዳ ሲገዛ . . . የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። . . . ለኃጢአት ሥርየት የዮሐንስን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ።”
ዮሐንስ መስበክና ማጥመቅ የጀመረው ጢባርዮስ እንደነገሠ ሳይሆን “ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት” ነው። ይህም 15ኛ ዓመት ከ28 እዘአ እስከ 29 እዘአ ያለው የበልግ ወራት ነው። ይሁን እንጂ ይህን ማወቃችን ዮሐንስ መጥምቁ በዚያ ዓመት በየትኛው ወር አገልግሎቱን እንደጀመረ ወይም ከዚያ ጋር የሚዛመዱ ነገሮች የተፈጸሙበትን ትክክለኛውን ወር እንድናውቅ አያስችለንም።
ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል የዳንኤል “የሰባ ሱባኤ” ትንቢት መሲሑ የሚገለጠው በ29 እዘአ መሆኑን አመልክቷል። የኢየሱስ አገልግሎት ለሦስት ዓመት ተኩል የሚቆይ መሆኑንም አመልክቷል። (ዳንኤል 9:24-27) በዚህ ላይ የሚከተሉትን መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን ዝርዝሮች ጨምሩበት፦ ኢየሱስ የተወለደው ዮሐንስ መጥምቁ ከተወለደ ከስድስት ወራት በኋላ መሆኑ፣ ኢየሱስ ሲጠመቅ “ሰላሳ ዓመት ያህል የሆነው” መሆኑና ኢየሱስ የሞተው በ33 1/2 ዕድሜው፣ በ33 እዘአ በጸደይ ወራት (የማለፍ በዓል ጊዜ) ላይ መሆኑ ነው።—ሉቃስ 1:24-38፤ 3:23፤ 22:14-16, 54b
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዲህ ዓይነቱን ትክክለኛ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ፣ ዓለማዊ ታሪክ የጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት ስለጀመረበት ዘመን ከሚናገረው መረጃ ጋር አጣምረው ዮሐንስ መጥምቁ አገልግሎት የጀመረው በ29 እዘአ ጸደይ ወራት ላይ መሆኑንና ከዚያ በኋላ ስድስት ወር ቆይቶ በበልግ ወራት ኢየሱስን እንዳጠመቀው ለማስላት ችለዋል። ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የዘመን አቆጣጠር መነሻ ወይም መሽከርከሪያ ሆኖ የሚቆጠረው 14 እዘአ ሳይሆን 29 እዘአ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጁሊያን ቀን አቆጣጠር መሠረት መስከረም 17 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር መሠረት መስከረም 15 ነው። በዛሬው ጊዜ በሠፊው የሚሠራበት ይህ ጎርጎሮሳዊ ቀን አቆጣጠር ነው።
b በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ከተሰኘው መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 458፤ 467፤ ጥራዝ 2 ገጽ 87, 899-902, 1099, 1100 ጋር አወዳድር።