የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች
ጌንሳሬጥ—‘አስደናቂና ውብ’ ሥፍራ
“በጌንሳሬጥ የባሕር ዳርቻ በባሕርዩ አስደናቂና ውብ የሆነ በዚሁ ስም የሚጠራ ሠፊ አገር አለ። አፈሩ በጣም ለም ስለሆነ በዚህ አካባቢ የማይበቅል ተክል የለም። ነዋሪዎቹ የፈለጉትን ተክል ሁሉ ያበቅሉበታል። አየሩ ልዩ ልዩ ዓይነት ተክል ለማብቀል የሚስማማና ነፋሻ ነው። . . . ልዩ ልዩ ዓይነት ፍራፍሬዎችን በአስደናቂ ሁኔታ ከማብቀሉም በላይ የማያቋርጥ ምርትም ያስገኛል። . . . ከፍተኛ የሆነ የማዳበሪያነት ኃይል ያለው ውሃ ይፈስበታል።
ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ አብዛኛውን ጊዜ የገሊላ ባሕር በመባል በሚታወቀው ሰሜናዊ ምዕራብ ዳርቻ ያለውን ባለሦስት ማዕዘን ሜዳ የገለጸው እንዲህ በማለት ነበር። ከላይ ያሉት ፎቶ ግራፎች ይህ ሜዳ ምን ያህል ምርታማ እንደሆነ ይጠቁሟችሁ ይሆናል። በገሊላ አካባቢ ካለው መሬት ሁሉ የበለጠ ለም ሥፍራ ነው።a ይህ አካባቢ በጥንት ዘመን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስለነበረ የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ በአካባቢው ያለውን ፈሳሽ ባሕር “የጌንሳሬጥ ባሕር” ሲል ጠርቶታል።
ሉቃስ ይህን ስያሜ የተጠቀመው ኢየሱስ ወደዚህ አካባቢ እንደመጣና በኋላ ሐዋርያት የሆኑ አራት ሰዎች እንዳገኘ ሲናገር ነው። እነዚህ አራት ሰዎች በሙሉ ለም የሆነውን መሬት በማረስ ወይም ለውዝ፣ ወይራና በለስ በማምረት የሚተዳደሩ ገበሬዎች ነበሩን? አልነበሩም። እንዲህ ዓይነት ሰብሎች በጌንሳሬጥ ሜዳ ሞልተው ነበር። እነዚህ ሰዎች ግን አሣ አጥማጆች ነበሩ። ለምን ዓሣ አጥማጆች እንደነበሩም በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል።
በሜዳው ላይ ፈስሰው ወደ ባሕሩ የሚገቡት ጅረቶች ለዓሣዎቹ ቀለብ የሚሆን ሣርና ቅጠል ይወስዱላቸው ነበር። ስለዚህ ወንዞቹ መጠነኛ ለሆነ የዓሣ ማጥመድ ኢንዱስትሪ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዓይነት ዓሣዎች ይርመሰመሱባቸዋል። ጴጥሮስና እንድርያስ በዚያ ስፍራ ዓሣ እያጠመዱ ይሸጡ ነበር። የዘብዴዎስ ልጆች የነበሩት ያዕቆብና ዮሐንስም ሥራቸው ዓሣ ማጥመድ ነበር።—ማቴዎስ 4:18-22፤ ሉቃስ 5:2-11
ብዙውን ጊዜ አሣ የማጥመዱ ሥራ የሚከናወነው ከጀልባ ላይ በሚጣል መረብ አማካኝነት ነበር። ኢየሱስ የደረሰው ጴጥሮስና እንድርያስ መረባቸውን ሲጥሉ ነበር። ረዥም መረብ በክበብ አጋማሽ ቅርጽ ይጣል ነበር። ተንሳፋፊ እንጨቶች የመረቡን ላይኛ ክፍል ከላይ እንዲንሳፈፍ ሲያደርጉ ከሥረኛው ክፍል ላይ የሚታሠሩ ከባድ ነገሮች ደግሞ የመረቡ ታችኛ ክፍል ከባሕሩ ሥር እንዲውል ያደርጉ ነበር። በእንዲህ ዓይነቱ መረብ በርካታ ቁጥር ያለው ዓሣ ሊጠመድ ይችል ነበር። ከዚያም በባሕሩ ዳር እንዲራገፍ ወደ ጀልባው ወይም ጥልቀት ወደሌለው ውኃ ይጐተት ነበር። ለምግብነት ተስማሚ የሆነው ዓሣ ተስማሚ ካልሆነው ይለይ ነበር። በሉቃስ 5:4-7 እና በዮሐንስ 21:6-11 ላይ የሠፈረው ዝርዝር መግለጫ ትክክል መሆኑን አስተውሉ። ኢየሱስ ይህን ዓይነቱን አጠማመድ ስለ መረብ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደጠቀሰ ታስታውሳላችሁን? (ማቴዎስ 13:47, 48) በተጨማሪም ማቴዎስ 4:21 ዓሣ አጥማጆች በዓለት ወይም በዓሣ ምክንያት የተቀደዱ መረቦችን የሚያበጁበት ጊዜ እንደነበረ ገልጾአል።
በጌንሳሬጥ የባሕር ዳርቻ ተጉዘህ ብታውቅ ኖሮ በኢየሱስ አገልግሎት ዘመን አንዳንድ ጉዳይ የተፈጸመባቸው ናቸው የሚባሉ ሁለት ቦታዎችን ትመለከት ነበር። አንደኛው ሥፍራ ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን የሰጠበት ነው ተብሎ በአፈታሪክ የሚነገርለት አረንጓዴ ጉብታ ነው። ይህ ሥፍራ ከወንጌል ትረካዎቹ ጋር አይጋጭም። ምክንያቱም ኢየሱስ ያን ስብከት ባቀረበበት ጊዜ በጌንሳሬጥ ሜዳ አጠገብ ነበር።—ማቴዎስ 5:1–7:29፤ ሉቃስ 6:17–7:1
ጥንት የነበረ ቦታ ነው የሚባለው ሌላ ሥፍራ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው መግለጫ ጋር የሚስማማ አይደለም። ኢየሱስ በሰባት እንጀራና በጥቂት ዓሣ 4,000 ሰዎችን የመገበበት ቦታ ነው በሚባለው በዚህ ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶበታል። (ማቴዎስ 15:32-38፤ ማርቆስ 8:1-9) የማርቆስ ትረካ እንደሚያመለክተው ይህ ሥፍራ የሚገኘው በጌንሳሬጥ ሜዳ ላይ ሳይሆን “ዲካፖሊስ (አሥር ከተማ)” በሚባለው ከባሕሩ ባሻገር 11 ኪሎሜትር ርቆ የሚገኝ ሥፍራ ነው።—ማርቆስ 7:31
ማቴዎስና ማርቆስ ኢየሱስ ይህን ተዓምር ከፈጸመ በኋላ በጀልባ ወደ መጌዶል ወይም ወደ ዳልማህ እንደተጓዘ ይናገራሉ። ምሁራን ይህን ሥፍራ በጌንሣሬጥ ሜዳ በስተደቡብ ወደ ጢባሪያስ ሲጠጋ ካለው መጌዶል የሚባል ሥፍራ ጋር ያያይዙታል። በማክሚላን ባይብል አትላስ መሠረት መጌዶል “ዓሣ እንዳይበላሽ በቅመም ወይም በጨው በማሸት ወይም በማድረቅ ኢንዱስትሪዋ የታወቀች” ሥፍራ ነበረች። በዚህኛው የባሕሩ ወገን ያለው የዓሣ ብዛት ይህን ኢንዱስትሪ ተግባራዊና ትርፍ የሚያስገኝ እንዳደረገው አያጠራጥርም።
በ1985/86 የነበረው ድርቅ በገሊላ ባሕር የነበረውን የውኃ መጠን ስለቀነሰው የባሕሩ ወለል ተጋልጦ ነበር። በጌንሳሬጥ ሜዳ አጠገብ ሁለት ሰዎች አንዲት ጥንታዊ ጀልባ አግኝተው ነበር። የመሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች ይህ ከእንጨት የተሠራ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባ እዚያ የተተወው ኢየሱስ ባሕሩንና የጌንሳሬጥን ሜዳ በጐበኘበት ጊዜ አካባቢ በነበረው ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከዚህ በላይ ያለውን ባለቀለም ፎቶግራፍ በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ተመልከቱ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Garo Nalbandian
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.