የጐርፍ መጥለቅለቅ በዓለም አፈ ታሪኮች ውስጥ
የኖህ ዘመን የውኃ መጥለቅለቅ በጣም አጥፊ መቅሰፍት ከመሆኑ የተነሣ የሰው ልጅ ሊረሳው አልቻለም። 2,400 ዓመታት ካለፉ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የውኃ መጥለቅለቁ የታሪክ ሐቅ መሆኑን ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:37-39) ይህ አስፈሪ ሁኔታ በሰው ዘር ላይ የማይፋቅ ምልክቶች ትቶ በማለፉ ምክንያት በዓለም ዙሪያ በጣም የታወቀ አፈ ታሪክ ሆኗል።
ፊሊፕ ፍሮይንድ “ሚዝስ ኦፍ ክርኤሽን” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ከ250 በሚበልጡ ጐሣዎች የሚነገሩ ከ500 የሚበልጡ ስለውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈታሪኮች እንዳሉ ገልጸዋል። መገመት እንደሚቻለው ብዙ መቶ ዓመታት ባለፉ ቁጥር እነዚህ አፈታሪኮች ሐሳብ ወለድ በሆኑ ሁኔታዎችና ገጸ ባሕርያት ተቀባብተዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም የሚመሳሰሉባቸው መሠረታዊ ነገሮች አሉ።
የሚመሳሰሉባቸው ነጥቦች
ከጐርፍ መጥለቅለቁ በኋላ ሰዎች ከሜሶፖታሚያ ሲፈልሱ የመቅሰፍቱን ታሪክ ወደ ሁሉም የምድር ክፍሎች ይዘው ሄዱ። ስለዚህ የእስያ፣ የደቡብ ፓሲፊክ ደሴቶች፣ የሰሜን አሜሪካ፣ የማዕከላዊ አሜሪካና የደቡብ አሜሪካ ነዋሪዎች ስለዚህ አስደናቂ ሁኔታ የሚገልጹ ታሪኮች አሏቸው። እነዚህ ስለውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈታሪኮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ባልተዋወቁ ሕዝቦች ዘንድ የሚገኙ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሚባል ነገር ሊያዩ ከመቻላቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ የኖሩ ናቸው። ሆኖም አፈታሪኮቹ መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጥለቅለቁ ከሚገልጸው ታሪክ ጋር የሚመሳሰሉባቸው አንዳንድ መሠረታዊ ነጥቦች አሏቸው።
አንዳንድ አፈ ታሪኮች ከውኃ መጥለቅለቁ በፊት በምድር ላይ ኃይለኛ ግዙፍ ሰዎች እንደነበሩ ይጠቅሳሉ። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ ከውኃ ጥፋቱ በፊት ዓመፀኛ መላእክት ሥጋዊ አካል በመልበስ ከሴቶች ጋር ተጋብተው ኔፊሊም የሚባሉ ግዙፍ ዘሮችን እንደወለዱ ያመለክታል።—ዘፍጥረት 6:1-4፤ 2 ጴጥሮስ 2:4, 5
ስለውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች አብዛኛውን ጊዜ የውኃ መጥለቅለቅ ከአምላክ ዘንድ እንደሚመጣ ለአንድ ሰው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ እንደነበረ ይገልጻሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ይሖዋ አምላክ ክፉዎችንና ዓመፀኞችን እንደሚያጠፋ ለኖህ አስጠንቅቆታል። አምላክ ለኖህ “የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሷል። ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ” ብሎታል።—ዘፍጥረት 6:13
አፈ ታሪኮች የውኃ መጥለቅለቁን በሚመለከት አጠቃላይ የሆነ ዓለም አቀፍ ጥፋት እንደመጣ ያመለክታሉ። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ውኃውም በምድር ላይ እጅግ አሸነፈ። ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ። በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ።”—ዘፍጥረት 7:19, 22
አብዛኞቹ የውኃ መጥለቅለቅ አፈታሪኮች አንድ ሰው ከአንድ ወይም ከዚያ በላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሆኖ ከጥፋት ውኃው እንደዳነ ይናገራሉ። ብዙ አፈታሪኮች ሰውየው የዳነው በሠራት መርከብ ተጠልሎ መሆኑንና መርከቢቱም በተራራ ላይ እንድትቆም መደረጓን ይናገራሉ። በተመሳሳይም ቅዱሳን ጽሑፎች ኖህ መርከብ እንደሠራ ይናገራሉ። “ኖህ አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ” በማለትም ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 6:5-8፤ 7:23) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ከውኃ መጥለቅለቁ በኋላ መርከቧ ኖህና ቤተሰቡ ከመርከብ በወጡበት “የአራራት ተራሮች ላይ አረፈች።” (ዘፍጥረት 8:4, 15-18) አፈታሪኮች ከመርከብ የወጡት ሰዎች በምድር ላይ እንደተራቡ ይገልጻሉ። መጽሐፍ ቅዱስም ከዚህ ጋር በመስማማት የኖኅ ቤተሰብ በምድር ላይ እንደተባዛ ይናገራል።—ዘፍጥረት 9:1፤ 10:1
ስለጐርፍ መጥለቅለቅ የሚገልጹ ጥንታዊ አፈ ታሪኮች
ከላይ ያሉትን ነጥቦች በአእምሮአችን በመያዝ አንዳንድ ስለ ውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈ ታሪኮችን እንመልከት። እስቲ በሜሶፖታሚያ ይኖሩ ከነበሩት ጥንታዊ ሕዝቦች፣ ከሱሜሪያውያን እንጀምር። የእነሱ ስለጐርፍ መጥለቅለቅ የሚገልጽ ታሪክ በኒፑር ፍርስራሾች ውስጥ በቁፋሮ በተገኘ የሸክላ ሰሌዳ ላይ ተጽፎ ተገኝቷል። ይህም ሸክላ የሱሜሪያውያን አማልክት አኑና ኤንሊል የሰውን ዘር በአንድ ታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ ለማጥፋት እንደወሰኑ ይናገራል። ዚየሱድራና ቤተሰቡ ኤንኪ በተባለው አምላክ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው በአንድ ትልቅ መርከብ ውስጥ ሆነው ለመትረፍ ቻሉ።
ስለባቢሎናዊው ጊልጋሜሽ ጀግንነት የሚገልጽ ግጥም ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል። በዚህ ጽሑፍ መሠረት ጊልጋሜሽ ቅድመ አያቱ የሆነውን ከጐርፍ መጥለቅለቁ ድኖ የዘላለም ሕይወት ዕድል የተሰጠውን ኡትናፒሽቲምን ለመጠየቅ ሄደ። ከእርሱም ጋር ባደረገው ጭውውት ኡትናፒሽቲም መርከብ እንዲሠራና ከብቶችን፣ የዱር አራዊትንና ቤተሰቡን ወደ መርከቡ እንዲያስገባ ተናግሮት እንደነበረ ገልጾለታል። መርከቧም ሁለቱም ጎኖቿ 200 ጫማ የሆኑ ባለስድስት ጐን ትልቅ መርከብ እንደሆነች ገልጿል። ኃይለኛው ዝናብ የቆየው ስድስት ቀንና ስድስት ሌሊት መሆኑን ለጊልጋሜሽ ነገረውና እንዲህ አለው፦ “ሰባተኛው ቀን ሲመጣ አውሎ ነፋሱ፣ የጐርፍ መጥለቅለቁ፣ ልክ እንደ ጦር ሠራዊት የሚማታው የጦርነት ድንጋጤ በረደ። ባሕሩ ጸጥ አለ፤ ውሽንፍሩም አባራ፤ ጐርፉም አቆመ። ወደ ባሕሩ ስመለከት ምንም ድምጽ የለም። የሰው ልጆችም ሁሉ ወደ አፈር ተለውጠው ነበር።”
መርከቧ በኒሲር ተራራ ላይ ካረፈች በኋላ አትናፒሽቲም ርግብን አውጥቶ ሰደደና ማረፊያ ስፍራ ስታጣ ተመልሳ መጣች። ሌላ ወፍም ልኮ እሷም ተመለሰች። ከዚያም ቁራን ሰደደና ሳትመለስ ስትቀር ውኃው እንደደረቀ አወቀ። ከዚያ በኋላም ኡትናፒሽቲም እንስሶቹን አወጣቸውና መሥዋዕት አቀረበ።
ይህ በጣም ጥንታዊ የሆነ አፈ ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱሱ የውኃ መጥለቅለቅ ታሪክ ጋር የሚመሳሰል ነው። ይሁን እንጂ አተራረኩ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽና ቀላል አይደለም። የመርከቧ ወርድና ቁመት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አልተገለጸም። ወይም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው ጊዜያትን ለይቶ አያመለክትም። ለምሳሌ ያህል የጊልጋሜሽ የጀግንነት ግጥም ኃይለኛው ዝናብ የቆየው ስድስት ቀንና ስድስት ሌሊት ነው ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ዝናብም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ” በማለት መላዋን ምድር በውኃ ለመሸፈን የቻለ የማያቋርጥ ከባድ ዝናብ መውረዱን ይገልጻል።—ዘፍጥረት 7:12
መጽሐፍ ቅዱስ ከውኃ መጥለቅለቁ የዳኑት ሰዎች ስምንት መሆናቸውን ሲገልጽ የግሪካውያን አፈ ታሪክ የዳኑት ዴዩካሊዮንና ሚስቱ ፒርሃ ብቻ እንደሆኑ ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 2:5) በዚህ የግሪካውያን አፈታሪክ መሠረት ከውኃ መጥለቅለቁ በፊት በምድር ላይ የነሐስ ሰዎች በመባል የሚጠሩ ኃይለኛ ግለሰቦች እንደነበሩ ይናገራል። ዚየስ የተባለው አምላክ በታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ ሊያጠፋቸው እንደወሰነና ለዲዩካሊዮን ትልቅ መርከብ እንዲሠራና ወደሷ እንዲገባ እንደነገረው ይገልጻል። ጐርፉ ሲጐድል መርከቧ በፓርናስስ ተራራ ላይ እንዳረፈች ይናገራል። ዲዩካሊዮንና ፒርሃ ከተራራው ወርደው እንደገና በመዋለድ የሰው ዘሮችን አስገኙ።
የሩቅ ምሥራቅ አፈ ታሪኮች
በሕንድ አገር ማኑ የሚባል ሰው ስለዳነበት የውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጽ አፈታሪክ አለ። ይህ ሰው አድጎ ትልቅ ዓሣ ሊሆን የቻለ የአንድ ትንሽ ዓሣ ወዳጅ ሆነና ዓሣው ስለ አጥፊው የውኃ መጥለቅለቅ አስጠነቀቀው። ማኑ መርከብ ሠራና በሂማልያ ያሉ ተራሮች ላይ እስኪያርፍ ድረስ ዓሣው ጐትቶ ወሰደው። የውኃ መጥለቅለቁ ሲጐድል ማኑ ከተራራው ወረደና የመሥዋዕቱ ምሳሌ ከሆነችው ከኢዳ ጋር ሆኖ የሰው ዘሮችን አስገኘ።
የቻይናውያን ስለጐርፍ መጥለቅለቅ የሚገልጽ አፈታሪክ ደግሞ የነጐድጓድ አምላክ ኑውና ፉክሲ ለተባሉ ሁለት ልጆች አንድ ጥርስ ሰጣቸው። ይህንንም ጥርስ እንዲተክሉና ከእሱ በሚበቅለው ቅል ውስጥ እንዲጠለሉ ነገራቸው። ከጥርሱም ወዲያውኑ ዛፍ በቀለና አንድ ትልቅ ቅል ተገኘ የነጎድጓድ አምላክ ኃይለኛ ዝናብ ሲያመጣ ልጆቹ ወደቅሉ ውስጥ ገቡ። ዝናቡ ያስከተለው ጐርፍ የቀሩትን የመሬት ነዋሪዎች በሙሉ ሲያጥለቀልቃቸው ኑዋና ፉክሲ ግን ድነው በምድር ላይ እንደገና ተራቡ።
በአሜሪካዎች
የሰሜን አሜሪካ ሕንዶች ከጥቂት ሰዎች በቀር ሁሉንም ያጠፋ የጐርፍ መጥለቅለቅ እንደነበረ የሚገልጹ ልዩ ልዩ አፈታሪኮች አሏቸው። ለምሳሌ ያህል አሪካራ የተባሉ የካዶ ሕዝቦች በአንድ ወቅት በምድር ላይ በአማልክት ላይ የሚያፌዙ ኃይለኛ የሰው ዘሮች ይኖሩ እንደነበረ ይናገራሉ። ኒሳሩ የተባለ አምላክ በውኃ መጥለቅለቅ አማካኝነት እነዚህን ግዙፍ ሰዎች ሲያጠፋ የራሱን ሕዝብ እንስሳትንና የበቆሎ ዘርን በዋሻ ውስጥ እንዲድኑ አደረገ። የሀቫሱፓይ ሕዝብ ደግሞ ሆኮማታ የተባለ አምላክ የሰው ዘርን ያጠፋ የጐርፍ መጥለቅለቅ እንዳመጣ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ቶኮፖ የተባለ ሰው ሴት ልጁን ውስጡ በተቦረቦረ ግንድ ውስጥ አስገብቶ አዳናት ይላሉ።
በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ የሚኖሩ ሕንዳውያን መሠረታዊ ተመሳሳይነት ያላቸው ስለውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች አሏቸው። የማዕከላዊ አሜሪካ ማያዎች አንድ ትልቅ የዝናብ እባብ ዓለምን በኃይለኛ ውኃ እንዳጠፋ ያምኑ ነበር። በሜክሲኮ የቺማልፓፓካ አፈታሪክ ደግሞ ጐርፍ ተራሮችን እንዳለበሰ ይናገራል። ቴዝካትሊፓካ የተባለ አምላክ ናታ የተባለውን ሰው አስጠነቀቀውና ግንድን ቦርቡሮ እሱና ሚስቱ ነና ውኃው እስኪጐድል ድረስ ተጠለሉ።
በፔሩ ቺንቻ የተባሉ ሕዝቦች አንድ የሚናገር ላማ ወደ ተራራ መርቶ በመውሰድ ካዳነው አንድ ሰው በቀር ሁሉም ሰዎች ስለጠፉበት የአምስት ቀን የጐርፍ መጥለቅለቅ የሚናገር አፈታሪክ አላቸው። የፔሩና የቦሊቪያ አይማራ ሕዝቦች ቪራኮቻ የተሰኘ አምላክ ከቲቲካካ ባሕር ወጥቶ በመምጣት በዓለም ላይ ከመጠን በላይ ግዙፋን የሆኑና ጠንካራ ሰዎችን እንደፈጠረ ይናገራሉ። እነዚህ የመጀመሪያ የሰው ዘሮች ስላናደዱት ቪራኮቻ በጐርፍ አጠፋቸው።
የብራዚል ቱፒናምባ ሕንዶች በጀልባዎችና በረዣዥም ዛፎች አናት ላይ ተንጠልጥለው ከዳኑት በስተቀር ቅድመ አያቶቻቸውን ሁሉ ስላሰጠመ የጐርፍ መጥለቅለቅ ይናገራሉ። የብራዚል ካሺናዋ፣ የጉያና ማኩሺ፣ የማዕከላዊ አሜሪካና በደቡብ አሜሪካ የምትገኘው የቴራዴል ፉጐ ብዙ ጐሣዎች ስለ ውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈታሪኮች አሏቸው።
ደቡብ ፓስፊክና እስያ
በደቡብ ፓስፊክ አገሮች በሙሉ ጥቂቶች ስለዳኑበት የውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች ሞልተዋል። ለምሳሌ ያህል በሳሞአ ከፒሊና ከሚስቱ በስተቀር ሁሉንም ሰዎች ስላጠፋ የቀድሞ ዘመን ጐርፍ የሚናገር አፈታሪክ አለ። ተጠልለው የዳኑት በአንድ ዓለት ላይ ሲሆን ከውኃ መጥለቅለቁ በኋላ በምድር ላይ ተዋለዱ። በሃዋይ ደሴቶች ካኔ የተባለ አምላክ በሰዎች ላይ ተናደደና እነሱን ለማጥፋት የጐርፍ መጥለቅለቅ ሰደደ። ኑኡ የተባለ ሰው ብቻ በአንድ ትልቅ መርከብ ላይ ሆኖ እንደዳነና መርከቡም በመጨረሻ ተራራ ላይ እንዳረፈ ይገልጻል።
በፊሊፒንስ ሚንዳናኖ ኦታ የተባሉ ጐሣዎች ምድር በአንድ ወቅት ከሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት በስተቀር ሁሉንም ሰው ባጠፋ ውኃ ተሸፍና እንደነበር ይናገራሉ። የቦርኒዮ ሳራዋክ ኗሪዎች የሆኑት የኢባን ጐሣዎች ጥቂት ሰዎች ብቻ በጣም ረዥም ወደሆነ ተራራ ሸሽተው በመውጣት ከመጥለቅለቁ እንደዳኑ ይናገራሉ። በፊሊፒንስ በኢጉሮት አፈ ታሪክ መሠረት በፖኪስ ተራራ ላይ በመጠለል የዳኑት አንድ ወንድምና እህቱ ብቻ እንደሆኑ ተገልጿል።
የሳይቤሪያ ሩሲያ ሕዝቦች ምድርን ደግፎ የያዘ አንድ ትልቅ እንቁራሪት ስለተነቃነቀ ምድር እንደተጥለቀለቀች ይናገራሉ። አንድ ሽማግሌ ሰውና ሚስቱ በሠሩት ታንኳ ላይ ሆነው ዳኑ። ውኃው ሲቀልል ታንኳይቱ በአንድ ትልቅ ተራራ ላይ አረፈች። የምዕራብ ሳይቤሪያ ኡግሪን ሕዝቦችና ሀንጋሪ ከውኃው መጥለቅለቅ የዳኑት ሰዎች ታንኳ እንደተጠቀሙና ከዚያ በኋላም ወደ ሁሉም የምድር ክፍሎች እንደተበታተኑ ይናገራሉ።
የአፈታሪኮቹ የጋራ መነሻ
ከእነዚህ ስለውኃ መጥለቅለቅ ከሚገልጹት ብዙ አፈታሪኮች ምን ልንደመድም እንችላለን? በዝርዝር ጉዳዮች ረገድ ብዙ ልዩነት ቢኖራቸውም አንዳንድ የጋራ የሆኑ ገጽታዎች አሏቸው። እነዚህ ገጽታዎችም አፈታሪኮቹ የመነጩት ከአንድ ዓይነት ግዙፍና የማይረሳ መቅሰፍት መሆኑን ያመለክታሉ። ባለፉት መቶ ዓመታት ሁሉ የተለያየ ለውጥ ቢደረግባቸውም የአፈታሪኮቹ ዋና መልእክት እንደ ክር ከአንድ ዓቢይ ሁኔታ ጋር ያስተሳስራቸዋል። ይህም ዐቢይ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተነገረው ቀላልና ያልተቀባባው ስለ ዓለም አቀፍ የውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጸው ታሪክ ነው።
ስለጐርፍ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈታሪኮች ባጠቃላይ የሚገኙት እስከ ቅርብ መቶ ዓመታት ድረስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ባልተገናኙ ሕዝቦች ዘንድ ስለሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች ታሪክ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል ብሎ መከራከር ስህተት ይሆናል። ከዚህም በላይ ዘ ኢንተርናሽናል እስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “ስለጐርፍ መጥለቅለቅ የሚገልጹ ታሪኮች በየትም ቦታ ያሉ መሆናቸው የሚያመለክተው የሰው ዘር ዓለም አቀፍ በሆነ ጐርፍ ጥፋት ደርሶበት እንደነበረ ነው። . . . ከዚህም በላይ አንዳንድ የጥንት ታሪኮች የተጻፉት የዕብራውያንንና የክርስቲያኖችን ባሕል ወይም ልማድ አጥብቀው በሚቃወሙ ሰዎች ነው።” (ጥራዝ 2 ገጽ 319) ስለዚህ ስለውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈታሪኮች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ እውነትነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለን በእርግጠኝነት ለመደምደም እንችላለን።
በዚህ በዓመፅና በብልግና በተሞላ ዓለም ውስጥ ስለምንኖር በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 እስከ 8 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ የጐርፍ መጥለቅለቅ ታሪክ ብናነብ መልካም እናደርጋለን። ይህ ዓለም አቀፍ ጥፋት የመጣው ሰዎች በአምላክ ዓይን ክፉ የሆነውን ነገር በማድረጋቸው ምክንያት መሆኑን ካሰብን ታሪኩ አስፈላጊ የሆነ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጠን እንገነዘባለን
በቅርቡ የአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት የአምላክን አስፈሪ ፍርድ ይቀምሳል። ከጥፋቱ የሚተርፉ ሰዎች መኖራቸው ግን ያስደስተናል። “(በኖህ) ዘመን የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ። አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሣት ቀርተዋል። . . . ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል?” የሚሉትን የሐዋርያው ጴጥሮስን ቃላት ከተከተልክ ከሚድኑት መሃል ልትሆን ትችላለህ።—2 ጴጥሮስ 3:6-12
የይሖዋ ቀን ቅርብ እንደሆነ በአእምሮህ ታስባለህን? እንዲህ ካደረግህና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነገር ካደረግህ ታላላቅ በረከቶችን ታገኛለህ። ስለዚህ ይሖዋ አምላክን የሚያስደስቱ ሰዎች ጴጥሮስ ቀጥሎ “ጽድቅ የሚኖርባቸውን አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ሲል በጠቀሰው አዲስ ዓለም እምነት ሊኖራቸው ይችላል።—2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የባቢሎን የውኃ መጥለቅለቅ አፈታሪኮች ከአንድ ትውልድ ወደሌላው ይተላለፉ ነበር።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን ቀን በአእምሮህ በመያዝ የጴጥሮስን ማስጠንቀቂያ ትከተላለህን?