የማይረሳው ጐርፍ
ከ4,300 ዓመታት በፊት ድንገተኛ አጥፊ ጐርፍ ምድርን አጥለቅልቋት ነበር። ማንኛውንም ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ በአንድ ጊዜ መጥለቅለቅ ጠራርጎ አጠፋ ሊባል ይቻላል። ይህን ያህል ከፍተኛ ጎርፍ በመሆኑ በሰው ልጆች ላይ የማይፋቅ ትዝታ ጥሎ ስላለፈ እያንዳንዱ ትውልድ ታሪኩን ለመጪው ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
ጎርፉ ካለፈ ከ850 ዓመታት ገደማ በኋላ ዕብራዊው ጸሐፊ ሙሴ የምድር አቀፉን የውኃ መጥለቅለቅ ታሪክ በጽሑፍ አሠፈረው። ዝርዝር ታሪኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ከምዕራፍ 6 እስከ 8 ባለው ክፍል ውስጥ ተመዝግቦ ስለቆየልን ልናነበው እንችላለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውኃው መጥለቅለቅ የሚገልጸው ታሪክ
የዘፍጥረት መጽሐፍ የዓይን ምስክር የሆነ ሰው የተረከውን የሚከተለውን መግለጫ ይሰጠናል፦ “በኖህ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት በዚያ ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ። የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ። የጥፋትም ውኃ ምድር ላይ አርባ ቀን ነበር። ውኃውም በዛ። መርከቢቱንም አነሳ። ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች። ውኃውም አሸነፈ። በምድር ላይም እጅግ በዛ። መርከቢቱም በውኃ ላይ ሄደች። ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ። ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ።”—ዘፍጥረት 7:11, 17, 19
የውኃው መጥለቅለቅ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ያስከተለውን ውጤት በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ ወፉም፣ እንስሳውም፣ አራዊቱም፣ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውም ሁሉ ጠፋ።” ይሁን እንጂ ኖህና ሌሎች ሰባት ሰዎች ከእንስሳቱ፣ ከሚበሩ ፍጥረታትና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ ለናሙና ከተወሰዱት ፍጥረታት ጋር ከጥፋቱ ተርፈዋል። (ዘፍጥረት 7:21, 23) ሁሉም በሕይወት የተጠበቁት 437 ጫማ ርዝመት፣ 73 ጫማ ስፋትና 44 ጫማ ከፍታ ባለው አንድ ትልቅ የሚንሳፈፍ መርከብ ውስጥ በመሆን ነበር። የመርከቡ አገልግሎት ውሃ የማይገባው ሆኖ ተንሳፍፎ መቆየት ብቻ ስለነበር ከሥሩ ክብ ወይም ሾጣጣ ቅርጽ አልነበረውም። ወደፊት እንዲሄድ የሚያደርግ ሞተር ዓይነት ነገር ወይም መቅዘፊያ መሣሪያ አልነበረውም። የኖህ መርከብ ባለአራት ማዕዘን ሲሆን የትልቅ ሣጥን ቅርጽ ያለው ነበር።
የውኃው መጥለቅለቅ ከጀመረ ከአምስት ወራት በኋላ መርከቧ በአሁኗ ቱርክ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኙት የአራራት ተራሮች ላይ አረፈች። ኖህና ቤተሰቡ የውኃው መጥለቅለቅ ከጀመረ ጀምሮ ሲቆጠር ከአንድ ዓመት በኋላ ከመርከቧ ወደ ደረቁ ምድር ላይ በመውጣት የተለመደውን ዕለታዊ ኑሮ እንደ አዲስ ጀመሩ። (ዘፍጥረት 8:14-19) ከጊዜ በኋላ የሰው ልጅ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የባቢሎንን ከተማና ስመ ጥፉ የሆነውን ግንቧን መሥራት ለመጀመር እስከሚችል ድረስ ተባዛ። ከዚያም አምላክ ቋንቋቸውን ባዘበራረቀው ጊዜ ቀስ በቀስ ወደ ምድር ክፍሎች በሙሉ ተበታተኑ። (ዘፍጥረት 11:1-9) ታዲያ መርከቧስ ምን ሆነች?
መርከቧን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
ከ19ኛው መቶ ዓመት ጀምሮ በአራራት ተራሮች ላይ መርከቧን ፈልጐ ለማግኘት በርካታ ሙከራዎች ተደርገው ነበር። እነዚህ ተራሮች አንዱ 16,950 ጫማ ከፍታ ያለውና ሌላው ደግሞ 12,840 ጫማ ከፍታ ያላቸው ጐላ ብለው የሚታዩ ሁለት ጫፎች አሉት። ከሁለቱ ጫፎች ከፍተኛ የሆነው አንዱ ጫፍ ሁልጊዜ በበረዶ የተሸፈነ ነው። ከውኃው መጥለቅለቅ በኋላ በተከተሉት የአየር ጠባይ ለውጦች ምክንያት መርከቧ ወዲያው በግግር በረዶች ተሸፍና ይሆናል። አንዳንድ ተመራማሪዎች መርከቧ በበረዶ ተሸፍና አሁንም እዚያው አለች ብለው በጥብቅ ያምናሉ። መርከቧ በከፊል ተገልጣ ለመታየት እስክትችል ድረስ በረዶው የሟሟባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ይናገራሉ።
የኖህ መርከብ ፍለጋ የተሰኘው መጽሐፍ አራራት ተራራ ላይ ወጥቶ በ1902 እና እንደገናም በ1904 መርከቧን እንዳየ የተናገረውን አርመናዊ ጆርጅ ሀጐፒያን ይጠቅሳል። በመጀመሪያው ጉብኝቱ ላይ መርከቧ ላይ በትክክል ወጥቶ እንደነበረ ተናግሯል። “በመርከቧ ላይ ቀጥ ብዬ ቆሜ ሙሉ በሙሉ ተመልክቻታለሁ። ረዥም ነበረች። ከፍታዋ አርባ ጫማ ያህል ነው።” በኋላ ባደረገው ጉብኝቱ ስለተመለከተው ነገር እንዲህ ብሏል፦ “የክብነት ቅርጽ አላየሁባትም። ካየኋቸው ሌሎች መርከቦች ሁሉ የተለየች ነበረች። ከሥሯ ጠፍጣፋ የሆነች የጭነት መርከብ ወደመምሰል የምታደላ ነች።”
ከ1952 እስከ 1969 ባለው ጊዜ ፈርናንድ ናቫና ስለመርከቧ ማስረጃ የሚሆን ምልክት ለማግኘት አራት ሙከራዎች አድርጓል። ወደ አራራት ባደረገው ሦስተኛ ጉዞ ላይ በግግር በረዶው ላይ በበረዶው ውስጥ የተተከለ ጥቁር እንጨት ወዳገኘበት አንድ ጐድጐድ ያለ ቦታ እንደገባ ይናገራል። “በጣም ረዥም መሆን አለበት። ምናልባት አሁንም ከመርከቧ አውታር ሌሎች ክፍሎች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። አምስት ጫማ ርዝመት ያለው ቁራጭ ብቻ ሰንጥቄ ለመውሰድ ችያለሁ” አለ።
እንጨቱን ከመረመሩት አያሌ ሊቃውንት አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ብሊስ “የናቫራ የእንጨት ናሙና የሕንፃ ጠርብ ሲሆን በቅጥራን የተለቀለቀ ወይም የተነከረ ነው። ሌሎች ጠርቦች የሚሰኩባቸው የተቦረቦሩ ቀዳዳዎች አሉበት። በእጅ የተጠረበና አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ነው” ብለዋል። የእንጨቱ ዕድሜ አራት ወይም አምስት ሺህ ዓመት ተገምቷል።
መርከቧን በአራራት ተራራ ላይ ፈልጐ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ከውኃው መጥለቅለቅ መቅሰፍት ለመዳን ያገለገለ ስለመሆኑ እርግጠኛ ማስረጃ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በተመዘገበው ታሪክ ውስጥ ነው። ይህ ታሪክ ትክክለኛ መሆኑን በዓለም ዙሪያ ባሉ ጥንታዊ ሕዝቦች ዘንድ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስለ ውኃ መጥለቅለቅ የሚገልጹ አፈ ታሪኮች በመኖራቸው ሊረጋገጥ ይችላል። ምሥክርነታቸውን በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ውስጥ ተመልከቱ።
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመርከቧ የመያዝ አቅም እያንዳንዳቸው 25 የአሜሪካ ፉርጎዎች ያሏቸው 10 የጭነት ባቡሮችን ያህል ነው።