የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w09 7/1 ገጽ 13-14
  • የኖኅ መርከብ ተገኝቷል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የኖኅ መርከብ ተገኝቷል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለእምነት ጠንካራ መሠረት ሊሆን ይችላል?
  • የማይረሳው ጐርፍ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ስምንት ሰዎች ከጥፋት ውኃው ተረፉ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • የኖኅ መርከብ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ኖኅ መርከብ ሠራ
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
w09 7/1 ገጽ 13-14

የኖኅ መርከብ ተገኝቷል?

መገናኛ ብዙኃን፣ የኖኅን መርከብ ለማግኘት የሚደረገውን ፍለጋ አስመልክተው በየጊዜው ብዙ ሲናገሩ ይሰማል። ይህ ጉዳይ ያን ያህል ትኩረት የሚስብ የሆነበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም። ኖኅና ቤተሰቡ በ2370-2369 ዓ.ዓ. ከጥፋት ውኃ የዳኑበት ግዙፍ መርከብ ቢገኝ አስደናቂ የአርኪኦሎጂ ግኝት እንደሚሆን ግልጽ ነው። ይሁንና እስከ ዛሬ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም የኖኅን መርከብ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት መቋጫ ያለው አይመስልም። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ብዙ ግምታዊ አስተያየቶችና ቀልብ የሚስቡ ሐሳቦች የተሰጡ ቢሆንም በእርግጥ ስለ ኖኅ መርከብ ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኖኅ መርከብ “በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:4) የአራራት ክልል፣ በቱርክ ምሥራቃዊ ክፍል ያለውንና በአሁኑ ጊዜ አራራት ተብሎ የሚጠራውን ረጅም ተራራ ይጨምራል፤ ይህ ተራራ የሚገኘው በአርሜኒያና በኢራን ድንበር አቅራቢያ ነው።

በርካታ ሰዎች በዚህ አካባቢ የኖኅን መርከብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ በኋላ አስገራሚ ሐሳቦችን የሰነዘሩ ቢሆንም ተጨባጭ ማስረጃ ያቀረበ አንድም ሰው የለም። ከአውሮፕላን ላይ የተነሱ አስገራሚ ፎቶግራፎችና መርከቡ እንደታየ የሚናገሩ ሪፖርቶች መኖራቸው እንዲሁም በቅጥራን የተሸፈኑ የእንጨት ቁርጥራጮች መገኘታቸው ሰዎች ይበልጥ ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ ለማግኘት እንዲነሳሱ አድርገዋቸዋል። ይሁንና ፍለጋው ቀላል አልሆነም። በመጀመሪያ ደረጃ መርከቡ አርፎበታል ተብሎ በአብዛኛው የሚጠቀሰው የአራራት ተራራ ክፍል ወደ 4,600 ሜትር ከፍታ አለው። በሁለተኛ ደረጃ በአካባቢው ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የውጭ አገር አሳሾች ወደ ተራራው ለመውጣት ፈቃድ የሚያገኙት ሁልጊዜ አይደለም።

ያም ሆኖ መርከቡ እንዲገኝ በጣም የሚጓጉ በርካታ ሰዎች፣ በተራራው ላይ ተጨማሪ አሰሳ እንዲደረግ ይፈልጋሉ። እነዚህ ሰዎች የመርከቡ የተወሰነ ክፍል በበረዶ በተሸፈነው የአራራት ተራራ ላይ አሁን ድረስ ሳይፈራርስ እንደሚገኝና አብዛኛውን የዓመቱን ክፍል በበረዶ ተሸፍኖ እንደሚቆይ ይናገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ መርከቡን የማየትም ሆነ ወደ መርከቡ የመቅረብ አጋጣሚ የሚኖረው ሞቃታማ የሆኑ የበጋ ወራት ባሏቸው ዓመታት ውስጥ ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በርካታ ሪፖርቶች ይህ ተስፋ እንዲለመልም አድርገዋል። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ፣ በአራራት ክልል ባሉ ተራሮች ላይ መርከቡ እንደሚታይ ስለተናገሩ የተለያዩ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች ጠቅሷል። እንዲያውም ሰዎች በቅጥራን የተሸፈኑ የእንጨት ቁርጥራጮችን ለማስታወሻነት ይወስዱ እንደነበር የሚገልጹ ሪፖርቶችም አሉ። ጆሴፈስ ከጠቀሳቸው ሰዎች መካከል በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ባቢሎናዊው ታሪክ ጸሐፊ በራሰስ ይገኝበታል።

የብዙዎችን ትኩረት ከሳቡት ሪፖርቶች መካከል አንዱ፣ ባለፈው መቶ ዘመን ጆርጅ ሃጎፕያን የተባሉ አርመናዊ የተናገሩት ነገር ነው። እኚህ ሰው፣ ልጅ ሳሉ ማለትም በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከአጎታቸው ጋር ሆነው መርከቡ ያለበት ቦታ እንደሄዱ አልፎ ተርፎም መርከቡ ላይ እንደወጡ ተናግረዋል። ሃጎፕያን በ1972 የሞቱ ቢሆንም እሳቸው የተናገሩት ነገር አሁንም ድረስ ብዙዎች የኖኅን መርከብ ለማግኘት እንዲጓጉና ስለ መርከቡ እንዲጠይቁ አነሳስቷቸዋል።

ለእምነት ጠንካራ መሠረት ሊሆን ይችላል?

አሳሾች መርከቡን እንዳገኙት ለማመን አሊያም ደግሞ ወደፊት እንደሚያገኙት ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል መሠረት አለ? ይኖር ይሆናል፤ ይሁንና ስለ ኖኅ መርከብ መገኘት የሚቀርቡት ማስረጃዎች በአብዛኛው ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ይመስላሉ። መጀመሪያ ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውኃው ሲጎድል መርከቡ የት እንዳረፈ ለይቶ በግልጽ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ የሚሰጠው መረጃ መርከቡ “በአራራት ተራሮች” ላይ እንዳረፈ ብቻ ነው።

ስለ ኖኅ መርከብ ግምታዊ ሐሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎችና አሳሾች በአካባቢው ካሉት ተራሮች ሁሉ ከፍተኛ በሆነው ተራራ ላይ እንደሚያነጣጥሩ ግልጽ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአሁኑ ጊዜ ከባሕር ወለል በላይ ወደ አምስት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ከፍታ ባለውና በጣም ቀዝቃዛ በሆነው የአራራት ተራራ አናት ላይ መርከቡ እንዲያርፍ አምላክ እንዳደረገ አይናገርም።a ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡ ተራራው ላይ ካረፈ በኋላ ለብዙ ወራት እዚያው መርከቡ ውስጥ እንደቆዩ አስታውስ። (ዘፍጥረት 8:4, 5) ከመርከቡ ከወጡ በኋላም ቢሆን ልክ ተራራ እንደሚወጡ ስፖርተኞች እንስሳቱን ይዘው ከረጅሙ ተራራ አናት ላይ ቁልቁል መውረድ ነበረባቸው ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። እንግዲያው መርከቡ ያረፈበት ቦታ አንዳንድ ዘመናዊ አሳሾች ከሚገምቱት የበለጠ ለመሬት ቅርብ ሳይሆን አይቀርም። እንደዚያም ሆኖ በዘፍጥረት 8:4, 5 ላይ ከሚገኘው መግለጫ አንጻር መርከቡ ያረፈበት ቦታ ከመሬት የተወሰነ ከፍታ ያለው መሆንም አለበት። መርከቡ ያረፈው በአራራት አካባቢ የትም ይሁን የት ሰዎች ቀስ በቀስ ከመርከቡ ላይ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ነገር ሲወስዱ ወይም በመበስበሱ ምክንያት ከዘመናት በፊት ጠፍቶ ሊሆን አይችልም?

ከዚህም በተጨማሪ አሳሾች የኖኅን መርከብ ማግኘታቸው ከሃይማኖት አንጻር ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታ በተመለከተ አንዳንድ ጊዜ የሚሰነዝሩት ሐሳብ ጥርጣሬ የሚፈጥር ነው። በርካታ አሳሾችን ያቀፈን አንድ ቡድን የሚመሩ ሰው፣ መርከቡ መገኘቱ “በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እምነታቸው ትክክለኛ መሆኑን እንደሚያረጋግጥላቸው . . . እንዲሁም ብዙዎች አማኞች እንዲሆኑ እንደሚረዳ” ተናግረዋል። እኚሁ ሰው በ2004 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መርከቡ ቢገኝ “ከክርስቶስ ትንሣኤ ወዲህ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ክስተት” ይሆን እንደነበር ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እኚህ ሰው ሊያደርጉት ያሰቡት ጉዞ በኋላ ላይ ተሰረዘ።

የኖኅ መርከብ መገኘቱ በእርግጥ እምነትን የሚያጠናክር አልፎ ተርፎም አማኞች ያልሆኑ ሰዎች እምነት እንዲኖራቸው የሚረዳ ይመስልሃል? እውነተኛ እምነት የተመካው ማየትና መዳሰስ የምንችላቸው ነገሮች በመኖራቸው ላይ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 5:7) አንዳንድ ሰዎች እጅግ ተጠራጣሪ ከመሆናቸው የተነሳ የሚታይ ማስረጃ እስካላገኙ ድረስ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ እምነት ማሳደር እንደማይችሉ ይናገራሉ። ይሁንና እውነታውን ስንመለከት እንደነዚህ ያሉት ግለሰቦች የቱንም ያህል ብዙ ማስረጃ ቢቀርብላቸው እምነት እንዲኖራቸው አይረዳቸውም። ኢየሱስ እንደተናገረው አንዳንድ ሰዎች ሙታን ሲነሱ ቢያዩ እንኳ መንፈሳዊ እውነቶችን አምነው አይቀበሉም!—ሉቃስ 16:31

በሌላ በኩል ግን እውነተኛ እምነት፣ ሁሉንም ነገር በጭፍን መቀበልን የሚያመለክት ሳይሆን ተጨባጭ በሆኑ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው። (ዕብራውያን 11:1) ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ምክንያታዊ ሰዎች ስለ ጥፋት ውኃ በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ የሚረዳቸው ተጨባጭ ማስረጃ አለ? አዎን፣ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ኖኅ ወደ መርከቡ እንደገባና የጥፋት ውኃ እንደመጣ’ በግልጽ ተናግሯል። (ሉቃስ 17:26, 27) ይህ ደግሞ ከየትኛውም ማስረጃ የሚበልጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር ነበር። (ዮሐንስ 8:58) መርከቡ ሲሠራም ሆነ የጥፋት ውኃው ሲመጣ ተመልክቷል። ለአንተ ይበልጥ አሳማኝ የሆነው የትኛው ማስረጃ ነው? እምነት የሚጣልበትና የአምላክ ልጅ መሆኑን ያስመሠከረው ኢየሱስ በዓይኑ ስለተመለከተው ነገር የሰጠው የምሥክርነት ቃል ነው? ወይስ አሳሾች በበረዶ ከተሸፈነ የተራራ አናት ላይ አንዳንድ ጥንታዊ የእንጨት ቁርጥራጮችን እንደሚያገኙ የሚሰጡት የተስፋ ጭላንጭል ነው? ከዚህ አንጻር የኖኅ መርከብ በአንድ ወቅት እንደነበር የሚያሳየው ማስረጃ በራሱ ከበቂ በላይ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በአሁኑ ጊዜ አራራት ተብሎ የሚጠራው ተራራ ከ1840 ወዲህ ምንም እንቅስቃሴ የማይታይበት እሳተ ገሞራ ነው። ከፍታው 5,165 ሜትር የሚደርስ ሲሆን ዓመቱን ሙሉ በበረዶ የተሸፈነ ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ አለ?

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ኖኅ ወደ መርከቡ እንደገባና የጥፋት ውኃ እንደመጣ’ በግልጽ ተናግሯል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ