አምላካዊ ባሕርይ ያላቸው ሰጪዎች ዘላለማዊ ደስታ ተጠብቆላቸዋል
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”—ዮሐንስ 3:16
1, 2. (ሀ) ታላቁ ሰጭ ማነው? ለሰው ልጅ የሰጠው ከፍተኛ ስጦታስ ምንድን ነው? (ለ) ይህን ከፍተኛ ስጦታውን በመስጠቱ ምን ባሕርይ አሳይቷል?
ከሁሉም የበለጠው ታላቅ ሰጪ ይሖዋ አምላክ ነው። ደቀመዝሙሩ ያዕቆብ “በጐ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ከላይ ናቸው መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ” በማለት የጻፈው የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነውን አምላክ በሚመለከት ነው። (ያዕቆብ 1:17) በተጨማሪም ይሖዋ ማንም ሰጥቶ የማያውቀውን ከፍተኛ ስጦታ ሰጥቷል። ለሰው ልጅ ስለሰጠው ከፍተኛ ስጦታ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” ተብሏል።—ዮሐንስ 3:16
2 እነዚህን ቃላት የተናገራቸው የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ራሱ ነበር። የአንድ አባት አንድያ ልጅ የሆነ ሰው ይህን አባቱን ለሕይወቱና ለደስታው አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ሁሉ ምንጭ እንደሆነ አድርጎ ማድነቁና ማፍቀሩ የተፈጥሮ ባሕርይ ነው። ይሁን እንጂ የአምላክ ፍቅር በዚህ በአንድ ልጁ ላይ ብቻ አልተወሰነም። ለልጁ የሰጠውን ዓይነት ስጦታ ለሌሎች ፍጥረቶቹም መዘርጋቱ አምላክ ተወዳዳሪ በሌለው መጠን ፍቅር ማሳየቱን ያመለክታል። (ከሮሜ 5:8-10 ጋር አወዳድር) “ሰጠ” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ ምን ማለት መሆኑን ስንመረምር ወደር በሌለው መጠን ፍቅር ያሳየ መሆኑ ይበልጥ ግልጥ ይሆንልናል።
አምላክ “የፍቅሩን ልጅ” መስጠቱ
3. “ከፍቅሩ ልጅ” በተጨማሪ የሰማያዊውን አባት ፍቅር ያገኙት ሌሎች እነማን ናቸው?
3 አምላክ ቁጥሩ ላልተገለጸ ዘመን ከዚህ ከአንድያ ልጁ ማለትም “ከፍቅሩ ልጅ” ጋር በሰማይ አብሮ ኖሯል። (ቆላስይስ 1:13) በዚያ ሁሉ ጊዜ አባትና ልጁ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር በከፍተኛ ደረጃ ያሳደጉ ከመሆናቸው የተነሣ የእነሱን የሚመስል የእርስ በርስ ፍቅር ሊኖር አይችልም። አምላክ በዚህ በአንድያ ልጅ አማካኝነት ወደ ሕልውና ያመጣቸው ሌሎች ፍጥረቶችም የይሖዋ መለኮታዊ ቤተሰብ በመሆናቸው የተወደዱ ናቸው። በመሆኑም በመላው የአምላክ ቤተሰብ መሃል ፍቅር ሰፍኖ ነበር። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “አምላክ ፍቅር ነው” ተብሎ በትክክል ተነግሯል። (1 ዮሐንስ 4:8) ስለዚህ መለኮታዊው ቤተሰብ አባት የሆነው ይሖዋ አምላክ በሚወዳቸው አባሎች የተገነባ ነበር።
4. አምላክ ልጁን መስጠቱ አብሮ መሆንን ከማጣቱ የበለጠ ነገር የሚጨምረው እንዴት ነው? ይህስ የሆነው ለእነማን ተብሎ ነው?
4 በይሖዋና በበኩር ልጁ መሃል ያለው መተሣሠር በጣም ጥብቅ ከመሆኑ የተነሣ አብረው መኖራቸው መቅረቱና መራራቃቸው ራሱ ትልቅ ጉዳት ይሆንባቸው ነበር። (ቆላስይስ 1:15) ይሁን እንጂ አንድያ ልጁን “መስጠቱ” አምላክ “ከፍቅሩ ልጅ” ጋር አብሮ የመኖር መብቱን ከመንፈግ የበለጠ ነገር የሚጠይቅበት ነበር። ልጁ እንዲሞትና ለጊዜውም ቢሆን ከጽንፈ ዓለማዊው ቤተሰብ አባልነት ተሰርዞ ከሕልውና ውጭ እንዲሆን እስከመፍቀድ የሚደርስ ነበር። የሞተውም የአምላክ ቤተሰብ አባል ሆነው ለማያውቁ ሰዎች ሲባል ነበር። ይሖዋ ቅዱሳን ጽሑፎች “በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው” በማለት ከሚገልጹት ከራሱ አንድያ ልጅ የበለጠ ስጦታ ለምስኪኖቹ የሰው ዘሮች ሊሰጥ አይችልም።—ራእይ 3:14
5. (ሀ) የአዳም ዘሮች ችግር ምንድን ነው? የአምላክ ፍትሕስ ከታማኝ ልጆቹ አንዱ ምን እንዲያደርግ የሚጠይቅ ሆነ? (ለ) የአምላክ ከፍተኛ ስጦታስ ምን የሚጠይቅበት ሆነ?
5 የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት፣ አዳምና ሔዋን የአምላክ ቤተሰብ አባሎች የመሆን ቦታቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። በአምላክ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ከኤደን ገነት ከተባረሩ በኋላ ከአምላክ ቤተሰብ አባልነት ተወገዱ። ከዚያ በኋላ የአምላክ ቤተሰብ አባል ካለመሆናቸውም በተጨማሪ በሞት ፍርድ ስር የሚኖሩ ፍጥረቶች ሆኑ። ስለዚህ ችግሩ የእነሱን ዘሮች እንደገና የአምላክ ቤተሰብ አባሎች እንዲሆኑ በማድረግ ወደእሱ ሞገስ መመለስ ብቻ ሳይሆን መለኮታዊውን የሞት ፍርድ ከእነሱ ላይ ማንሣትም ጭምር ነበር። በመለኮታዊው ፍትሕ አሠራር መሠረት ከይሖዋ አምላክ ታማኝ ልጆች አንዱ በምትክነት ወይም በቤዛነት ሞትን እንዲቀምስ የሚጠይቅ ሁኔታ ነበር። ታዲያ ትልቁ ጥያቄ ለዚህ ጉዳይ የሚመረጠው ልጅ ለኃጢአተኞች ሰዎች ሲል በምትክነት ለመሞት ፈቃደኛ ይሆናልን? የሚለው ነበር። ከዚህም በላይ ይህን ለማድረግ ሁሉን የሚችለው አምላክ ተአምር እንዲያደርግ ያስፈልግ ነበር። እንደዚሁም መለኮታዊ ፍቅሩን ተወዳዳሪ በሌለው መጠን እንዲገልጽ የሚጠይቅ ነበር።—ሮሜ 8:32
6. የአምላክ ልጅ ኃጢአተኞቹ የሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ብቁ የነበረው ለምንድን ነው? እሱስ በዚህ ረገድ ምን ብሏል?
6 ኃጢአተኛው የሰው ልጅ የሚገኝበት ሁኔታ የሚጠይቀውን ልዩ ብቃት የሚያሟላው የይሖዋ በኩር ልጅ ብቻ ነበር። በመለኮታዊ ኃይል ለተፈጠረው ቤተሰብ ፍቅር በማሳየት በኩል የሰማያዊ አባቱ ፍጹም ነጸብራቅ በመሆኑ ረገድ በአምላክ ልጆች መሃል አቻ አይገኝለትም። ሌሎቹ አስተዋይ ፍጡሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡት በኢየሱስ አማካኝነት ስለሆነ ለእነዚህ ፍጡሮች ያለው ፍቅር ያለጥርጥር ታላቅ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ “(የአምላክ) የክብር ነፀብራቅና የባሕርዩ ምሳሌ” ስለሆነ ከይሖዋ አንድያ ልጅ ታላላቅ ባሕርያት አንዱ ፍቅር ነው። (ዕብራውያን 1:3) ኢየሱስ ለኃጢአተኛ የሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን በመስጠት በከፍተኛ ደረጃ ፍቅሩን ለማሳየት ፈቃደኛ መሆኑን ለ12 ሐዋርያቱ ሲገልጽ እንዲህ አላቸው፦ “እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”—ማርቆስ 10:45፤ በተጨማሪም ዮሐንስ 15:13ን ተመልከት
7, 8. (ሀ) ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሰው ልጆች ዓለም እንዲልክ ያነሣሳው ምንድን ነው? (ለ) አምላክ አንድያ ልጁን የላከው ለምን ዓይነት ዓላማ ነው?
7 ይሖዋ አምላክ ወደዚህ በድህነት የተራቆተ የሰው ልጆች ዓለም ኢየሱስን የላከበት ልዩ ምክንያት ነበረው። ልጁን እንዲልክ ያነሣሳው መለኮታዊ ፍቅሩ ነበር። ይህንንም ኢየሱስ ራሱ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም” በማለት ገልጿል።—ዮሐንስ 3:16, 17
8 ይሖዋ አንድያ ልጁን በፍቅር ተነሣስቶ የላከው የማዳን ተልዕኮ እንዲፈጽም ነበር። አምላክ ልጁን ወደዚህ ዓለም የላከው በዓለም እንዲፈርድ አልነበረም። የአምላክ ልጅ የተላከው ለፍርድ ቢሆን ኖሮ የሰው ልጆች ሁሉ የወደፊት ተስፋ ከንቱ ይሆን ነበር። ኢየሱስ የፍርድ ውሳኔ ቢሰጥ መላው የሰው ልጆች ከሞት ሞት ፍርድ ሊያመልጥ አይችልም ነበር። (ሮሜ 5:12) በመሆኑም አምላክ በዚህ ልዩ የሆነ የመለኮታዊ ፍቅሩ መግለጫ አማካኝነት ፍትሕ የሚጠይቀውን የሞት ፍርድ ሽሯል።
9. መዝሙራዊው ዳዊት ስለ ይሖዋ ሰጪነት የተሰማው እንዴት ነበር?
9 ይሖዋ አምላክ በሁሉ ነገር ፍቅር ከፍተኛ የሆነ የባሕርዩ አንድ ገጽታ መሆኑን አሳይቷል። አምላክ በምድር ላይ ላሉት ታማኝ አምላኪዎቹ በፍቅር ተነሣስቶ በምድር ላይ ለሚኖሩት ታማኝ አምላኪዎቹ ከሚያስፈልጋቸው አስበልጦ መልካም ነገሮችን ይሰጣቸዋል መባሉ ትክክል ነው። መዝሙራዊው ዳዊት “በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት ቸርነትህ እንደምን በዛች!” ብሎ ሲናገር ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ሰጪነት ይህን የመሰለ ስሜት ተሰምቶት ነበር። (መዝሙር 31:19) ዳዊት በእሥራኤል ሕዝብ ላይ በነገሠበት ዘመን ሁሉ የአምላክ ልዩ ምርጥ ሕዝብ አባል በመሆን ባሳለፈው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ የይሖዋን ጥሩነት ብዙ ጊዜ ቀምሷል። ዳዊት የይሖዋን ጥሩነት ብዙ ሆኖ አግኝቶታል።
የእስራኤል ሕዝብ ከአምላክ የተሰጠውን ትልቅ ስጦታ አጣ
10. የጥንቱ የእሥራኤል ሕዝብ በምድር ላይ ከነበረው ከማንኛውም ሕዝብ የተለየ የነበረው ለምንድን ነው?
10 የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ ይሖዋ ስለነበረ በምድር ላይ ከነበሩት ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ነበረ። ይሖዋ ነቢዩ ሙሴን መካከለኛ በማድረግ የአብርሃም፣ የይሥሐቅንና የያዕቆብን ዘሮች ከራሱ ጋር ወደ ቃል ኪዳን ዝምድና አስገባቸው። ከሌላ ከማንም ሕዝብ ጋር እንዲህ አላደረገም። ስለዚህ በመንፈስ ተመርቶ የጻፈው መዝሙራዊ “ቃሉን ለያዕቆብ ሥርዓቱንና ፍርዱን ለእሥራኤል ይናገራል። ለሌሎች አሕዛብ ሁሉ እንዲህ አላደረገም። ፍርዱንም አልገለጠላቸውም” በማለት ሊናገር ችሏል።—መዝሙር 147:19, 20
11. እሥራኤል ከአምላክ ጋር በተወደደ ልዩ ዝምድና የኖረው እስከመቼ ነበር? በዝምድናቸው ረገድ ለውጥ መምጣቱን ኢየሱስ የገለጸው እንዴት ነበር?
11 የሥጋዊው እስራኤል ሕዝብ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሕ መሆኑን አንቀበልም እስካለበት እስከ 33 እዘአ ድረስ ከአምላክ ጋር በዚያ ልዩ ዝምድና ውስጥ ሆኖ ነበር። ኢየሱስ “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ብሎ በኀዘን የተናገረበት ጊዜ ቀን ለእሥራኤል ሕዝብ በእርግጥ የኀዘን ቀን ነበር። (ማቴዎስ 23:37, 38) የእሥራኤል ሕዝብ ከዚያ በፊት በይሖዋ የተመረጠና የተወደደ ሕዝብ ቢሆንም ከዚያ ወዲህ ግን የአምላክን ልዩ ስጦታ እንዳጣ የኢየሱስ ቃላት ያመለክታሉ። እንዴት?
12. የኢየሩሳሌም “ልጆች” እነማን ናቸው? ኢየሱስ እነሱን መሰብሰቡ ምን ማለት ይሆናል?
12 ኢየሱስ “ልጆችሽን” ሲል በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩትንና ጠቅላላውን የአይሁድ ሕዝብ የሚወክሉትን በሥጋ የተገረዙ አይሁዶች ማመልከቱ ነበር። ኢየሱስ “የኢየሩሳሌምን ልጆች” ቢሰበስብ ኖሮ እነዚህን “ልጆች” በይሖዋና በሥጋዊ አይሁዳውያን መሃል እሱ ራሱ መካከለኛ በመሆን ከአምላክ ጋር ወደ አዲስ ቃል ኪዳን ያስገባቸው ነበር። (ኤርምያስ 31:31-34) ኃጢአታቸውን በሙሉ ይቅር ይላቸው ነበር። የአምላክ ፍቅር እስከዚህ ደረጃ ለመድረስ የሚችል ነበር። (ከሚልክያስ 1:2 ጋር አወዳድሩ) በእርግጥም ትልቅ ስጦታ በሆነ ነበር።
13. የእሥራኤል ሕዝብ የአምላክን ልጅ አለመቀበሉ ምን ነገር አሳጣው? የይሖዋ ደስታ ግን ያልተቀነሰው ለምንድን ነው?
13 ይሖዋ ከትንቢታዊ ቃሉ ጋር በመስማማት አይሁድ ላልሆኑ ሕዝቦች የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋዮች የመሆንን ስጦታ ከመዘርጋቱ በፊት መጠነኛ ለሆነ ጊዜ አይሁዳውያንን ጠብቋል። ሥጋዊ የእሥራኤል ሕዝብ ግን የአምላክ ልጅ የሆነውን መሲሕ ባለመቀበሉ ይህን ትልቅ ስጦታ አጣ። ስለዚህ ይሖዋ ይህን ስጦታ ከአይሁድ ሕዝብ ውጭ ላሉ ሕዝቦች በመዘርጋት ልጁን አለመቀበላቸው ያስከተለውን ውጤት ሽሮታል። በዚህ መንገድም ይሖዋ በታላቅ ሰጪነቱ ያገኘው ደስታ አልተቀነሰበትም።
መስጠት የሚያስገኘው ደስታ
14. ኢየሱስ ክርስቶስ በጽንፈ ዓለሙ ሁሉ ካሉት ፍጥረታት የበለጠ ደስተኛ ፍጡር የሆነው ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ከሚያስደስቱትም ነገሮች አንዱ ለሌሎች መስጠት ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም አንድያ ልጁ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 20:35) ኢየሱስም ከዚህ ደንብ ጋር በመስማማት ከጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ከይሖዋ ፍጥረታት በሙሉ ከሁሉ የበለጠ ደስተኛ ፍጡር ሆኗል። እንዴት? ከይሖዋ አምላክ ቀጥሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ጥቅም ሲል ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ ከሁሉ የበለጠውን ስጦታ ሰጥቷል። እንዲያውም ኢየሱስ “ደስተኛ ገዥ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:15) ስለዚህ ኢየሱስ ራሱ በመስጠት ስለሚገኘው ከፍተኛ ደስታ ምሳሌ ሆኗል።
15. ይሖዋ የምን ምሳሌ መሆኑን ፈጽሞ አያቆምም? አስተዋይ የሆኑ ፍጡሮቹስ የሱን ደስታ በመጠኑ ሊቀምሱት የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ይሖዋ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለአስተዋይ ፍጡሮቹ በሙሉ ለጋስ ሰጪ መሆኑን አይተውም። ሁልጊዜም በመስጠት ረገድ ከሁሉ የበለጠ ምሳሌያቸው ሆኖ ይኖራል። አምላክም እንኳ ለሌሎች ጥሩ ስጦታዎችን በመስጠት የሚደሰት መሆኑ በምድር ላይ ባሉት አስተዋይ ፍጡሮቹ ልብ ውስጥ የለጋስነትን መንፈስ አኑሯል። በዚህ መንገድም የሱን ባሕርይ በማንጸባረቅና እሱን በመምሰል የሱን ደስታ በመጠኑ ይቀምሳሉ። (ዘፍጥረት 1:26፤ ኤፌሶን 5:1) ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ስጡ፣ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መሥፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና የተጨቆነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መሥፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል” ማለቱ ተገቢ ነበር።—ሉቃስ 6:38
16. ኢየሱስ በሉቃስ 6:38 ላይ ስለምን ዓይነት መስጠት ተናገረ?
16 ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ የመስጠትን ወይም የለጋስነትን ባሕርይ ልማዳቸው እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው ግሩም ምሳሌ ሆኗል። እንዲህ ዓይነቱ መስጠት በተቀባዮቹ ዘንድ መልካም አጸፋ እንደሚኖረው ተናግሯል። በሉቃስ 6:38 ላይ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሥጋዊ ስጦታ ስለመስጠት ማመልከቱ አልነበረም። ደቀመዛሙርቱ ራሳቸውን በሥጋዊ ረገድ የሚያደኸያቸውን ጐዳና እንዲከተሉ መናገሩ አልነበረም። በዚህ ፋፈንታ መንፈሳዊ ምልአት የሚሰጣቸውን መንገድ እንዲከተሉ ማመልከቱ ነበር።
ለዘላለማዊ ደስታ ዋስትና ተሰጥቷል
17. በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች አምላክ ለምስክሮቹ የሰጠው አስደናቂ ስጦታ ምንድን ነው?
17 የፍጥረት ሁሉ ራስ የሆነው ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ለምሥክሮቹ በጣም አስደናቂ የሆነ ስጦታ ሰጥቷል። የመንግሥቱን ምሥራች ሰጥቶናል። በመግዛት ላይ ባለው ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ የተቋቋመችው የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የመሆን ታላቅ መብት አግኝተናል። (ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10) በአንደበታችን የምንናገር የልዑል አምላክ ምሥክሮች እንድንሆን መደረጋችን ተወዳዳሪ የሌለው ስጦታ ነው። ሰጪዎች ወይም ለጋሶች በመሆን አምላክን ከምንመስልባቸው መንገዶች ሁሉ የተሻለው መንገድ የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማካፈል ነው።
18. የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ለሌሎች መስጠት ያለብን ምንድን ነው?
18 ሐዋርያው ጳውሎስ የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ሲያውጅ የደረሰበትን መከራ አመልክቷል። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27) የይሖዋ ዘመናዊ ምሥክሮችም የመንግሥቱን ተስፋ ለሌሎች ለመስጠት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ የግል ምቾቶቻቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ። ብዙ ችግሮችም ይደርሱባቸዋል። በተለይ ደግሞ ዓይንአፋሮች ከሆንን ወደ ሰዎች ቤት መሄድ አንወድ ይሆናል። ይሁንና የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናችን “ይህን የመንግሥት ወንጌል” በመስበክ ለሌሎች መንፈሳዊ ነገሮችን የመስጠትን መብት ረግጠን ለማለፍ ወይም ችላ ለማለት አንችልም። (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ የነበረው ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ያስፈልጋል። ኢየሱስ ሞት በተደቀነበት ጊዜ “አባቴ ሆይ . . . አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን” በማለት ጸልዮአል። (ማቴዎስ 26:39) የይሖዋ አገልጋዮች ለሌሎች ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች ሲሰብኩ ማድረግ የሚኖርባቸው የአምላክን ፈቃድ እንጂ የራሳቸውን ፈቃድ አይደለም። እሱ የሚፈልገውን እንጂ እነሱ የሚፈልጉትን አይደለም።
19. “የዘላለም ቤቶች” ባለቤቶች እነማን ናቸው? ከእነሱ ጋር መወዳጀት የምንችለው እንዴት ነው?
19 እንዲህ ዓይነቱ መስጠት ጊዜያችንንና ሀብታችንን ጭምር እንድንሰጥ ይፈልግብናል። ይሁንና አምላካዊ ሰጪዎች ስንሆን ደስታችን ዘላለማዊ እንደሚሆን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ “የዓመፅጽ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለማዊ ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ ለራሳችሁ ወዳጆች አድርጉ ስለሚለን ነው። (ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን “በዓለማዊ ሀብት” ይላል።) (ሉቃስ 16:9) የዓመጽ ሀብት የዘላለም ቤቶች ባለቤቶች ከሆኑት ጋር ለመወዳጀት መጠቀም ግባችን መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ ፈጣሪ በመሆኑ የማንኛውም ነገር ባለቤት ነው። የበኩር ልጁም የሁሉም ነገሮች ወራሽ በመሆኑ በዚህ ባለቤትነት ይካፈላል። (መዝሙር 50:10-12፤ ዕብራውያን 1:1, 2) ከእነሱ ጋር ለመወዳጀት ሀብታችንን የእነሱን ሞገስ በሚያስገኝልን መንገድ መጠቀም አለብን። ይህም ቁሳዊ ነገሮችን ለሌሎች ጥቅም በማዋል ረገድ ትክክለኛ ዝንባሌ መያዝን ይጨምራል። (ማቴዎስ 6:3, 4፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7) ገንዘባችንን ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነታችንን ለማጠናከር ተገቢ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። ይህንንም የምናደርገው ያለንን ነገር ችግረኞች የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት በመጠቀምና ሀብታችንንም የአምላክን መንግሥት ፍላጎቶች ለማራመድ በማዋል ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 19:17፤ ማቴዎስ 6:33
20. (ሀ) ይሖዋና ኢየሱስ “በዘላለም ቤቶች” ሊያስተናግዱን የሚችሉት ለምንድን ነው? እነዚህ ቦታዎችስ የት ይሆናሉ? (ለ) ለዘላለምስ ምን መብት ይኖረናል?
20 ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ የማይሞቱ በመሆናቸው ለዘላለም ወዳጆቻችን ሊሆኑና “በዘላለማዊ ቤት” ሊያስተናግዱን ይችላሉ። የሚያስተናግዱበትም ቦታ በሰማይ ከቅዱሳን መላእክት ሁሉ ጋር ወይም በዚህ ምድር ላይ ዳግመኛ በምትመለሰው ገነት ላይ ይሆናል። (ሉቃስ 23:43) ይህን ሁሉ ነገር እንዲፈጸም ያስቻለው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን በፍቅር መስጠቱ ነው። (ዮሐንስ 3:16) ይሖዋ አምላክም ኢየሱስን ለራሱ ልዩ ደስታ ሲል ለፍጥረቱ ሁሉ በመስጠት እንዲቀጥል ይጠቀምበታል። እንዲያውም እኛ ራሳችን ጭምር በይሖዋ አምላክ ጽንፈ ዓለማዊ የበላይ ገዥነትና በአንድያ ልጁ፣ ጌታችንና አዳኛችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ንግሥና ሥር የመስጠት መብት ይኖራል። ይህም ለአምላካዊ ሰጪዎች ዘላለማዊ ደስታ ያስገኝላቸዋል።
ታስታውሳላችሁን?
◻ የአምላክ ከፍተኛ ስጦታ ከአምላክ ከራሱ ምን ነገር ጠይቆበታል?
◻ አምላክ ልጁን የላከው ለምን ዓይነት ዓላማ ነበር?
◻ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የበለጠው ደስተኛ ፍጡር ማን ነው? ለምንስ?
◻ አምላካዊ ሰጪዎች ዘላለማዊ ደስታ የሚቀምሱት እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱን ታደንቃለህን?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የምሥራቹን በመስበክና ይህን የስብከት ሥራ በሀብትህ በመደገፍ የአምላክን መንግሥት ታደንቃለህን?