የቀድሞዋ ቤተክርስቲያን አምላክ ሥላሴ ነው ብላ አስተምራ ነበርን?
ክፍል 2—ሐዋርያዊ አባቶች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን?
ህዳር 1, 1991 በወጣው መጠበቂያ ግንብ ላይ የዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ክፍል 1 ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ማለትም አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እኩል የሆኑ ሦስት አካላት ሆነው ግን ሦስት አምላኮች ሳይሆኑ አንድ አምላክ ናቸው የሚለውን ሐሳብ አስተምረው እንደሆነና እንዳልሆነ አብራርቶአል። ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከታሪክ ጸሐፊዎችና ከሃይማኖታዊ ሊቃውንትም ሳይቀር የተገኘው ግልጽ ማስረጃ ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ይህን ትምህርት ወይም ሐሳብ እንዳላስተማሩ አሳይቷል። ከመጀመሪያዎቹ ሐዋርያትና ደቀመዛሙርት ቀጥሎ በነበረው ዘመን የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶችስ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን?
“ሐዋርያዊ አባቶች” የሚባሉት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያና በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ እዘአ ላይ ስለ ክርስትና የጻፉ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከል የሮሙ ክሌመንት፣ ኢግናቲየስ፣ ፖሊካርፕ፣ ሄርማስና ፓፒያስ ይገኙበታል።
ከእነዚህ ሐዋርያዊ አባቶች አንዳንዶቹ በሐዋርያት ዘመን የኖሩ ናቸው ይባላል። በመሆኑም ሐዋርያት ካስተማሩአቸው ትምህርቶች ጋር ይተዋወቁ ነበር ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ስለጻፉአቸው ጽሑፎች ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፦
“ሐዋርያዊ አባቶች የጻፉአቸው ጽሑፎች በአጠቃላይ ሲወሰዱ ከአዲስ ኪዳን ውጭ ከተጻፉት ከማንኛውም ሌሎች የክርስቲያን ጽሑፎች የበለጠ ታሪካዊ ጠቀሜታ አላቸው” ይላል።1
ሐዋርያት የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረው ከነበረ እነዚህ ሐዋርያዊ አባቶችም ማስተማር ይገባቸው ነበር። ለሰዎች አምላክ ማን መሆኑን ከመናገር የበለጠ አስፈላጊ ነገር ስለማይኖር የሥላሴ ትምህርት ዋነኛው የትምህርታቸው ክፍል መሆን ነበረበት። ታዲያ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን?
ጥንታዊ የእምነት መግለጫ
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ከሚገኙ የጥንት የክርስትና እምነት መግለጫዎች አንዱ የሚገኘው ዘ ዲዳክ ወይም የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ትምህርት በተሰኘ 16 አጫጭር ምዕራፎች ባሉት መጽሐፍ ውስጥ ነው። አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች ይህ መጽሐፍ የተጻፈበት ዘመን ከ100 እዘአ በፊት ወይም በዚህ ዓመት አካባቢ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ደራሲው አይታወቅም።2
ዘ ዲዳክ ክርስቲያን የሚሆኑ ሰዎች ማወቅ ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይገልጻል። በ7ኛው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19 ላይ ከተጠቀመባቸው ቃላት ጋር አንድ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ እንደሚያስፈልግ ያዝዛል።3 ነገር ግን ሦስቱ በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃና በጥበብ እኩል ስለመሆናቸው የሚናገረው ነገር የለም። ዘ ዲዳክ በ10ኛው ምዕራፍ ላይ በጸሎት መልክ የቀረበውን የሚከተለውን የእምነት መግለጫ ጨምሯል፦
“ቅዱስ አባት ሆይ በልባችን ስላኖርኸው ስለ ቅዱስ ስምህና በአገልጋይህ በኢየሱስ በኩል ስላሳወቅኸን ዕውቀት፣ እምነትና የአለመሞት ባሕርይ እናመሰግንሃለን። ክብር ለዘላለም ለአንተ ይሁን! አንተ ሁሉን ቻይ የሆንክ ጌታ ሁሉንም ነገር ለስምህ ስትል ፈጥረሃል . . . ለእኛም መንፈሳዊ ምግብና መጠጥ፣ እንዲሁም በአገልጋይህ በኢየሱስ በኩል የዘላለምን ሕይወት በለጋስነት ሰጥተኸናል።”4
ስለ ሥላሴ የተነገረ ምንም ነገር የለም። ዘ ኢንፍሉዌንስ ኦቭ ግሪክ አይዲያስ ኦን ክርስቲያኒቲ (የግሪክኛ ሐሳቦች በክርስትና ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ) በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ኤድዊን ሃች ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ቃል በመጥቀስ የሚከተለውን ብለዋል፦
“በመጀመሪያው የክርስትና ዓለም ውስጥ ከእነዚህ ያልተወሳሰቡ ቀላል ጽንሰ ሐሳቦች የሚያልፍ ነገር አልተጨመረም ነበር። ከፍ ያለ ግምት ይሰጠው የነበረው መሠረተ ትምህርት አምላክ አንድ፣ ሁሉን ቻይና ዘላለማዊ መሆኑ፣ ዓለምን መፍጠሩ፣ ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ መሆኑ ነበር። የግሪካውያንን ፍልስፍና ለመቅዳት የተደረገ ሙከራ አልነበረም።”5
የሮሙ ክሌመንት
የሮማ ከተማ ጳጳስ ነበር ተብሎ የሚታሰበው የሮሙ ክሌመንትም ስለ ክርስትና ከጻፉት የጥንት ሰዎች አንዱ ነበር። የሞተው በ100 እዘአ አካባቢ እንደሆነ ይታመናል። በክሌመንት የተጻፈ ነው በሚባለው ጽሑፍ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለ ሥላሴ የተናገረው ነገር የለም። ለቆሮንቶስ ሰዎች በተጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ፦
“ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።”
“ሐዋርያት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን ወንጌል ሰብከውልናል። ኢየሱስ ክርስቶስም የሰበከው ከአምላክ የተቀበለውን ነው። እንግዲያውስ ክርስቶስ በአምላክ የተላከ ሲሆን ሐዋርያት ደግሞ በክርስቶስ የተላኩ ናቸው።”
“ሁሉንም ነገር የሚያይ አምላክ፣ የመናፍስት ሁሉ ገዥና የሥጋ ሁሉ ጌታ፣ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንና በእርሱ በኩልም እኛን የእሱ ልዩ ሕዝቦች አድርጎ የመረጠ፣ ክብራማና ቅዱስ ስሙን ለሚጠራ ማንኛውም ነፍስ እምነትንና ፍርሐትን፣ ሠላምን፣ ትዕግሥትንና መከራ ቻይነትን ይስጥ።”6
ክሌመንት ኢየሱስም ሆነ መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ ጋር እኩል ናቸው አላለም። ሁሉን የሚችለው አምላክ (“አብ” ብቻ ሳይሆን) ከወልድ የተለየ መሆኑን ገልጿል። ክርስቶስ በአምላክ “የተላከ” እና በአምላክ የተመረጠ ስለሆነ አምላክና ክርስቶስ ሁለት የተለያዩ እኩል ያልሆኑ አካላት መሆናቸውን በመግለጽ ክሌመንት እንደሚከተለው ብሏል፦
“የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ በመላው ዓለም ያሉ ምርጦቹን በሙሉ በተወዳጁ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አጠንክሮ ይጠብቃቸው ዘንድ በልባዊ ጸሎትና ምልጃ እንለምነዋለን . . . አንተ (አምላክ) ብቻ የልዑሎች ልዑል እንደሆንክ እንገነዘባለን። . . . አንተ ብቻ የመናፍስት ጠባቂና የሥጋ ሁሉ አምላክ ነህ።”
“አሕዛብ ሁሉ አንተ ብቻ አምላክ እንደሆንክና ኢየሱስ ክርስቶስም ልጅህ እንደሆነ ይወቁ።”7
ክሌመንት አምላክን የጠራው (“አብ” ብቻ በማለት ሳይሆን) “ከፍ ያልክ ልዑል” በማለት ነው። ኢየሱስንም የአምላክ “ልጅ” ሲል ጠርቶአል። በተጨማሪም ኢየሱስ “የአምላክን ክብር ስለሚያንጸባርቅ ማዕረጉም ከመላእክት የላቀ እንደመሆኑ መጠን ከእነሱ የበላይ ነው” ብሎአል።8 ጨረቃ የጸሐይን ብርሃን ብታንጸባርቅም የብርሃን ምንጭ ከሆነችው ከጸሐይ ጋር እንደምትተካከል ሁሉ ኢየሱስም የአምላክን ክብር ያንጸባርቃል እንጂ ከአምላክ ጋር አይተካከልም።
የእግዚአብሔር ልጅ ሰማያዊ አባት ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ቢሆን ኖሮ ክሌመንት ኢየሱስ የመላእክት የበላይ ነው ማለት አያስፈልገውም ነበር። ምክንያቱም አምላክ የመላእክት የበላይ መሆኑ ግልጽ ነውና። የቃላት አመራረጡም ኢየሱስ የመላእክት የበላይ ሲሆን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ግን የበታች እንደሆነ የተገነዘበ መሆኑን ያሳያል።
የክሌመንት አቋም በጣም ግልጽ ነው፦ ወልድ የአብ የበታችና በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ነው። ክሌመንት ኢየሱስ እንደ ሥላሴ ትምህርት አባባል አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ ክፍል እንደሆነ አድርጎ አልተመለከተም። ልጁ የአባቱ ማለትም የአምላክ ጥገኛ መሆኑን ገልጿል። በእርግጠኝነትም አብ ሥልጣኑን ከማንም ጋር የማይጋራ ‘ብቻውን አምላክ የሆነ’ እንደሆነ ተናግሯል። ክሌመንት መንፈስ ቅዱስን ከአምላክ ጋር ያስተካከለበት ቦታ የለም። በመሆኑም በክሌመንት ጽሑፎች ውስጥ የሥላሴ ትምህርት ጨርሶ አይገኝም።
ኢግናቲየስ
የአንጾኪያ ጳጳስ የነበረው ኢግናቲየስ የኖረው ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ነው። እሱ የጻፋቸው ናቸው የሚባሉትን ጽሑፎች ሁሉ በእርግጥ የእሱ ጽሑፎች ናቸው ብለን ብንቀበል እንኳ በየትኛውም ጽሑፍ ውስጥ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ እኩልነት አልተገለጸም።
ኢግናቲየስ ወልድ ከአብ ጋር በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን በደረጃና በጥበብ እኩል ነው ቢልም እንኳን ስለ ሥላሴ አስተምሮአል ለማለት አይቻልም። ምክንያቱም የትም ቦታ ላይ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዓይነት መንገድ ከአምላክ ጋር እኩል ነው ብሎ አልተናገረም። ይሁን እንጂ ኢግናቲየስ ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ከላይ በተገለጹት መንገዶችም ሆነ በሌሎች መንገዶች እኩል ነው ብሎ አልተናገረም። በዚህ ፈንታ ወልድ የበላዩ ለሆነው ሁሉን ቻይ አምላክ ተገዥ እንደሆነ ገልጾአል።
ኢግናቲየስ በአምላክና በልጁ መሃል ያለውን ልዩነት በማመልከት ሁሉን የሚችለውን አምላክ “እውነተኛው አምላክ፣ ያልተወለደና ሊደረስበት የማይችል፣ የሁሉም ጌታ፣ የአንድያ ልጁ አባትና ወላጅ”9 በማለት ጠርቶታል። “እግዚአብሔር አብና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ”10 በማለት ሁለቱን ለያይቶ ጠርቶአል። “በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን የገለጠ አንድ ሁሉን ቻይ አምላክ አለ”11 አለ በማለት ተናግሯል።
ኢግናቲየስ ወልድ ለዘላለም የነበረ ሳይሆን የተፈጠረ መሆኑን በመግለጽ ወልድ “ጌታ [ሁሉን ቻይ አምላክ] የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ”12 እንዳለ ጽፏል። በተመሳሳይም ኢግናቲየስ “የጽንፈ ዓለሙ አምላክና የክርስቶስ አባት እንዲሁም ‘ሁሉም የእርሱ የሆነ አንድ አለ።’ ‘ሁሉም ነገር በእርሱ በኩል የሆነ’ አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ”13 ብሏል። በተጨማሪም እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦
“ጌታችን ደግሞ ከአብ የተቀበላቸውን ነገሮች እንዳስታወቀን . . . መንፈስ ቅዱስም የሚናገረው የራሱን ሳይሆን የክርስቶስን ነው። ምክንያቱም እሱ [ወልድ] ‘የምትሰሙት ቃል የእኔ ሳይሆን የላከኝ የአብ ነው’ ብሎአል።”14
“በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን የገለጠ አንድ አምላክ አለ። እሱም [ኢየሱስ] ዝምታ ከሰፈነበት ሁኔታ የወጣና የላከውን [አምላክ] በሁሉም መንገድ ያስደሰተ የአምላክ ቃል ነው። . . . ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ተገዥ ነበር።”15
እርግጥ ነው ኢግናቲየስ “ቃል የሆነው አምላክ” በማለት ጠርቶታል። ይሁን እንጂ ወልድ “አምላክ” መባሉ ሁሉን ከሚችለው አምላክ ጋር እኩል አያደርገውም። መጽሐፍ ቅዱስ ወልድን በኢሳይያስ 9:6 ላይ “አምላክ” ብሎ ይጠራዋል። ዮሐንስ 1:18 ወልድን “አንድያ ልጅ የሆነ አምላክ” ብሎ ጠርቶታል። ወልድ ከአብ ማለትም ከይሖዋ አምላክ ኃይልና ሥልጣን ስለተሰጠው “ኃያል” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። “አምላክ (god)” የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉምም ኃያል ማለት ነው።—ማቴዎስ 28:18 1 ቆሮንቶስ 8:6፤ ዕብራውያን 1:2
ይሁን እንጂ የኢግናቲየስ ጽሑፎች ናቸው የሚባሉት 15 ደብዳቤዎች በእርግጥ የእርሱ ጽሑፎች መሆናቸው ተቀባይነት አግኝቶአልን? የቅድመ ኒቂያ አባቶች በተሰኘው መጽሐፍ ላይ አዘጋጆቹ አሌክሳንደር ሮበርትስ እና ጀምስ ዶናልድሰን በጥራዝ 1 ኣይ እንዲህ በማለት አትተዋል፦
“የኢግናቲየስ ደብዳቤዎች ናቸው ከተባሉት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ጽሑፎች የእርሱ አለመሆናቸው ሠፊ ተቀባይነት አግኝቶአል። በኋለኞቹ ዘመናት የተጻፉ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። . . . በአሁኑ ጊዜ ሐሰተኛና በማስመሰል የተጻፉ ጽሑፎች ስለመሆናቸው አጠቃላይ ስምምነት ላይ ተደርሶአል።
“ዩሲቢየስ አምኖ ከተቀበላቸው ሰባት መልእክቶች ውስጥ . . . በምርምር የጸደቁ አንድ ረዥምና አንድ አጭር የጽሑፎች ስብስብ አለን። . . . አጭሩ . . . ባጠቃላይ ከረዥሙ የበለጠ ተቀባይነት ቢያገኝም እሱም እንኳ ቢሆን በኋላ በተጨመሩ ጽሑፎች ከመበከል ነፃ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር አልቻለም። በማያጠራጥር ሁኔታ እውነተኛ ስለመሆኑ በምሁራን መካከል አሁንም ብዙ ጥርጣሬ አለ።”16
አጭሩን የኢግናቲየስ ጽሑፍ እንደ እውነተኛ አድርገን ከተቀበልን (በረዥሙ ትርጉም ውስጥ ያሉ) ክርስቶስ ከአምላክ የበታች መሆኑን የሚያሳዩ አንዳንድ ሐረጎች ወጥተዋል። ይሁንና በአጭሩ ትርጉም ውስጥ የተቀሩትም ቢሆኑ ስለ ሥላሴ አይገልጹም። እውነተኛው ጽሑፍ የትኛውም ቢሆን ማለትም ረዥሙም ይሁን አጭሩ እጅግ ቢበዛ የሚያመለክተው ኢግናቲየስ በአምላክና በልጁ ሁለትነት ያምን እንደነበረ ነው። ይህ ሁለትነትም በእርግጥ የአቻዎች ወይም የእኩያዎች ሁለትነት አይደለም። ምክንያቱም ወልድ የተገለጸው ምንጊዜም ከአባቱ ያነሰና የበታች እንደሆነ ተደርጎ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው የኢግናቲየስን ጽሑፎች በፈለገው መንገድ ቢመለከት በውስጣቸው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አይገኝም።
ፖሊካርፕ
የስሚርናው ፖሊካርፕ የተወለደው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጨረሻ ሲሶ ላይ ሲሆን የሞተው በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው። ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተገናኝቶ ነበር ይባላል። እንዲሁም የፖሊካርፕ መልእክት ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የተባለውን ጽሑፍ የጻፈው እሱ ነው ይባላል።
ታዲያ በፖሊካርፕ ጽሑፍ ውስጥ ሥላሴን የሚያመለክት አንዳች ነገር ይገኛልን? የሥላሴ ሐሳብ ፈጽሞ አልተጠቀሰም። እንዲያውም እሱ የሚናገረው ነገር ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ካስተማሩት ጋር የሚስማማ ነው። ለምሳሌ ያህል ፖሊካርፕ በመልእክቱ፦
“የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዲሁም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ . . . በእምነትና በእውነት ያንጿችሁ”17 በማለት ተናግሯል።
ፖሊካርፕ እንደ ክሌመንት ሁሉ ሥላሴ ስለሆነ አምላክ ወይም አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ እኩል ክፍሎች ስለሆኑ የ“አባትና” የ“ልጅ” ዝምድና እንዳልተናገረ ልብ በሉ። ከዚህ ይልቅ “የኢየሱስ አባት” ብቻ ሳይሆን የኢየሱስ “አምላክና አባት” እንደሆነ ይናገራል። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በተደጋጋሚ እንዳደረጉት አምላክን ከኢየሱስ ለይቶአል። ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 1:3 ላይ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” ይላል። ጳውሎስ “የኢየሱስ አባት ይባረክ” ብቻ ሳይሆን የኢየሱስ “አምላክና አባት” ብሎአል።
ፖሊካርፕ “ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክና ከአዳኛችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሠላም ለእናንተ ይሁን”18 ብሎአል። እዚህ ላይም ኢየሱስ የተገለጸው ሁሉም እኩል የሆኑ አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ አንድ አካል እንደሆነ ተደርጎ ሳይሆን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ተለይቶ ነው።
ሄርማስና ፓፒያስ
ሌላው በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የጻፈ ሐዋርያዊ አባት ሄርማስ ነው። እረኛው ወይም ፓስተሩ በተሰኘው ጽሑፉ ላይ ሄርማስ አምላክን ሥላሴ እንደሆነ ያምን እንደነበረ የሚገልጽ አንዳች ነገር ተናግሯልን? ከተናገራቸው ውስጥ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከቱ፦
“መንፈስ ቅዱስ የሚናገረው አንድ ሰው መንፈሱ እንዲናገር ሲፈልግ ሳይሆን አምላክ ሲያናግረው ወይም መንፈሱ እንዲናገር ሲፈልግ ብቻ ነው። . . . የወይኑን ተክል የተከለው አምላክ ነው። ይህም ማለት ሕዝቡን ከፈጠረ በኋላ ለልጁ ሰጣቸው። ልጁም እንዲጠብቋቸው መላእክትን መደበላቸው።”19
“የእግዚአብሔር ልጅ በዕድሜ ከፍጥረቱ ሁሉ ይበልጣል።”20
እዚህ ላይ ሄርማስ አምላክ (አብ ብቻ አላለም) መንፈስ እንዲናገር ሲፈልግ መንፈስ ይናገራል ሲል አምላክ ከመንፈሱ የሚበልጥ መሆኑን አሳይቷል። እንደዚሁም አምላክ ከልጁ የሚበልጥ መሆኑን ሲያሳይ አምላክ ለልጁ የወይን አትክልቱን ሰጠው ይላል። “በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ (በክርስቶስ) ተፈጥረዋልና።” ሄርማስም “የእግዚአብሔር ልጅ ከፍጥረቶቹ ማለትም የእግዚአብሔር ልጅ የአምላክ ዋና ሠራተኛ በመሆን ከፈጠራቸው ከልጁ ፍጥረቶች በዕድሜ ይበልጣል” ብሏል። (ቆላስይስ 1:15, 16) ወልድ ዘላለማዊ አለመሆኑ ተገልጾአል። በእሱ አማካኝነት ከተፈጠሩት እንደ መላእክት ከመሳሰሉት ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረቶች ሁሉ በፊት ከፍተኛ ማዕረግ ያለው መንፈሳዊ ፍጡር በመሆን ተፈጥሮአል።
ጄ ኤን ዲ ኬሊ የቀድሞ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች በተሰኘው ጽሑፍ ውስጥ ሄርማስ ስለ አምላክ ልጅ የነበረውን አመለካከት ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፦
“በጽሑፎቹ በርካታ ክፍሎች ውስጥ የአምላክ ምክር ቤት አባላት ሆነው ከሚያገለግሉት ስድስት መላእክት መሃል የበላይ የሆነውን አንድ መልአክ “እጅግ የተከበረ” “ቅዱስ” እና “በክብር ታላቅ የሆነ” በማለት ደጋግሞ ገልጾታል። ይህ መልአክ ሚካኤል የሚል ስም ተሰጥቶታል። ሄርማስ ይህን መልአክ እንደ እግዚአብሔር ልጅ አድርጎ ይመለከተውና ከመላእክት አለቃ ሚካኤል ጋር አንድ እንደሆነ አድርጎ ያየው ነበር ከማለት ሌላ ምንም መናገር ያዳግታል።”
“ክርስቶስን እንደ ታላቅ ወይም ከፍተኛ መልአክ አድርጎ የመቁጠር ሙከራ . . . እንደነበረ የሚያመለክት ማስረጃ አለ።. . . የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ስለመኖሩ ግን ምንም አይነት ምልክት የለም።”21
ፓፒያስም ሐዋርያው ዮሐንስን ያውቀው ነበር ተብሏል። የጻፈውም በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የሚገኘው ያልተሟሉ የመጽሐፉ ቁርጥራጮች ብቻ ናቸው። በእነርሱም ውስጥ ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት ምንም አልተናገረም።
የማይጋጭ ትምህርት
ሐዋርያዊ አባቶች ስለአምላክ የበላይነትና ከልጁ ጋር ስላለው ዝምድና ያስተማሩት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ከሚገኘው ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱና ሐዋርያቱ ካስተማሩት ትምህርት ጋር በትክክል ይስማማል። ሁሉም የተናገሩት ስለ ሥላሴ ሳይሆን አምላክ ለብቻው የተለየ አካል ያለው፣ ዘላለማዊ፣ ሁሉን ቻይና ሁሉን አዋቂ መሆኑን ነው። ስለ እግዚአብሔር ልጅም የተናገሩት አምላክ ዓላማውን ለማከናወን እንዲያገለግል የፈጠረው ከራሱ ከአምላክ የተለየ አካል ያለው፣ ከአምላክ ያነሰና የበታች የሆነ መንፈሳዊ ፍጡር መሆኑን ነው። መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ ጋር እኩል እንደሆነ ተደርጎ የተጠቀሰበት ቦታ የለም።
በመሆኑም በአንደኛው መቶ ዘመን መጨረሻና በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሐዋርያዊ አባቶች በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ሕዝበ ክርስትና ለምታስተምረው ሥላሴ ድጋፍ የሚሆን ማስረጃ የለም። ስለ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ መንፈስ ቅዱስ የተናገሩት ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ሥራ 7:55, 56ን ተመልከቱ፦
“እስጢፋኖስ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦ እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ።”
እስጢፋኖስ አምላክንና ኢየሱስን በራእይ ተመልክቷል። ወልድ ወይም ልጁ “አብ” ብቻ ሳይሆን “አምላክ” ወይም “እግዚአብሔር” ተብሎ ከተጠራው ከኢየሱስ ፈጽሞ የተለየ አካልና ሕልውና ካለው አምላክ ጐን ቆሞ ነበር። እስጢፋኖስ በተመለከተው ራእይ ላይ ሌላ ሦስተኛ አካል አልነበረም። መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስና ከአባቱ ጋር በሰማይ አልታየም።
ይህም በራእይ 1:1 ላይ “እግዚአብሔር ለኢየሱስ የሰጠው ራእይ ነው” (እንደ ጀሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ) ከተባለው ራዕይ ጋር ይመሳሰላል። እዚህም ላይ ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ከአምላክ ሙሉ በሙሉ የተለየ ሆኖ በሰማይ የታየ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ግን አልተጠቀሰም። ኢየሱስ ሁሉንም ነገር የሚያውቅ የሥላሴ ሁለተኛ አካል ቢሆን ኖሮ ራእዩ እንዴት ‘ሊሰጠው’ ቻለ?
እነዚህን የመሳሰሉት ጥቅሶች ሥላሴ እንደሌለ በግልጽ ያሳያሉ። አምላክ ሥላሴ እንደሆነ የሚያመለክት አንድም ጥቅስ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። የሐዋርያዊ አባቶችም ጽሑፎች ይህንን አረጋግጠዋል። የሕዝበ ክርስትናን ሥላሴ እንዳላስተማሩ በጣም እርግጠኛ ነገር ነው።
ከእነዚህ ጽሑፎች ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ የክርስትና ጽሑፎች የተጻፉት በሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ነበር። እነዚህን ጽሑፎች የጻፉት የቤተ ክርስቲያን ሰዎች አፖሎጂስት ተብለው የሚጠሩት ፀሐፊዎች ናቸው። ታዲያ እነዚህስ ፀሐፊዎች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን? ወደፊት በሚወጣ እትም ላይ የሚወጣው ተከታዩ ክፍል 3 እነዚህ ፀሐፊዎች ስላስተማሩት ትምህርት የሚያትት ይሆናል።
በእንግሊዝኛ የሚገኙ ማጣቀሻዎች
1. The New Encyclopædia Britannica, 15th Edition, 1985, Micropædia, Volume 1, page 488.
2. A Dictionary of Christian Theology, edited by Alan Richardson, 1969, page 95; The New Encyclopædia Britannica, 15th Edition, 1985, Micropædia, Volume 4, page 79.
3. The Apostolic Fathers, Volume 3, by Robert A. Kraft, 1965, page 163.
4. Ibid., pages 166-7.
5. The Influence of Greek Ideas on Christianity, by Edwin Hatch, 1957, page 252.
6. The Ante-Nicene Fathers, Alexander Roberts and James Donaldson, editors, American Reprint of the Edinburgh Edition, 1885, Volume I, pages 5, 16, 21.
7. The Library of Christian Classics, Volume 1, Early Christian Fathers, translated and edited by Cyril C. Richardson, 1953, pages 70-1.
8. Ibid., page 60.
9. The Ante-Nicene Fathers, Volume I, page 52.
10. Ibid., page 58.
11. Ibid., page 62.
12. Ibid., page 108.
13. Ibid., page 116.
14. Ibid., page 53.
15. The Apostolic Fathers, Volume 4, by Robert M. Grant, 1966, page 63.
16. The Ante-Nicene Fathers, Volume I, pages 46-7; Cyclopedia of Biblical, Theological, and Ecclesiastical Literature, by John McClintock and James Strong, reprinted by Baker Book House Co., 1981, Volume IV, pages 490-3; The Catholic Encyclopedia, 1910, Volume VII, pages 644-7.
17. The Ante-Nicene Fathers, Volume I, page 35.
18. Ibid., page 33.
19. The Ante-Nicene Fathers, Volume II, pages 27, 35.
20. The Apostolic Fathers (Loeb’s Classical Library) with an English Translation by Kirsopp Lake, 1976, page 249.
21. Early Christian Doctrines, by J. N. D. Kelly, Second Edition, 1960, pages 94-5.