የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ሥላሴ ነው ብላ አስተምራለችን?
ክፍል 1—ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የሥላሴን መሠረት ትምህርት አስተምረዋልን?
ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን? በቀጣዮቹ ምዕተ ዓመታት የነበሩ የቤተክርስቲያን መሪዎችስ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረው ነበርን? ስለዚህ እምነት እውነቱን ማወቅ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው? መጠበቂያ ግንብ በዚህ ዕትሙ ላይ ከቀረበው ከክፍል 1 ጀምሮ በተከታታይ ዕትሞቹ እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራል። ሌሎቹ ርዕሰ ትምህርቶች በሚቀጥሉት ተከታታይ ዕትሞች ላይ ይወጣሉ።
መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው የሚቀበሉ ሰዎች ስለ ፈጣሪ ለሌሎች ሰዎች የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። በተጨማሪም ስለ አምላክ የሚያስተምሩት ፍሬ ነገር እውነት መሆን እንደሚገባው ይገነዘባሉ።
አምላክ የኢዮብን “አጽናኞች” ስለ አምላክ ቅን ወይም ትክክል የሆነ ነገር ባለማስተማራቸው ገስጾአቸዋል። “ይሖዋ፣ ቴማናዊውን ኤልፋዝን ‘እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለእኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነዷል።’”—ኢዮብ 42:7
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ሲገልጽ ስለ አምላክ ሥራዎች እውነት ያልሆነን ነገር ከተናገርን “ሐሰተኛ የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:15) ስለ ትንሣኤ ማስተማር ይህን ያህል ከባድ ከሆነ ስለ አምላክ ማንነት ለማስተማር ስንቀርብ ምን ያህል ጠንቃቆች መሆን ይገባናል?
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት
ሁሉም የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አምላክ ሥላሴ ነው ብለው ያስተምራሉ። የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ የሥላሴን ትምህርት “የክርስትና ሃይማኖት ዋነኛ መሠረተ ትምህርት ” ነው ይላል። ይህንንም መሠረተ ትምህርት እንደሚከተለው በማለት ይገልጸዋል፦
“በአንድ አምላክ ውስጥ አባት፣ ልጅና መንፈስ ቅዱስ የሆኑ የሦስት አካላት ኅብረት አለ። እነዚህ ሦስቱም አንዱ ከሌላው ፈጽሞ የተለዩ አካላት ናቸው። ስለዚህ በአትናቴዎስ እምነት አባባል ‘አባት አምላክ ነው፤ ልጅ (ወልድ) አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው። ሆኖም አንድ አምላክ ነው እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም። . . . ሦስቱም አካላት እኩል ዘላለማውያንና አንዱ ከሌላው የማይበልጥ ማለትም ሁሉ ያልተፈጠሩና ሁሉን ቻዮች ናቸው።”1
የባብቲስት ኢንሳይክሎፒዲያ ተመሳሳይ ገለጻ ይሰጣል። እንዲህ ይላል፦
“[ኢየሱስ] . . . ዘላለማዊው ይሖዋ ነው። መንፈስ ቅዱስ ይሖዋ ነው. . . ልጁና (ወልድ) መንፈሱ ከአብ ጋር ተተካካይ የሆነ የእኩልነት ቦታ አላቸው። አብ ይሖዋ ከሆነ እነሱም ይሖዋ ናቸው።”2
በተቃዋሚዎች የተነገሩ ውግዘቶች
በ325 እዘአ በትንሹ እስያ በምትገኘው በኒቂያ ጉባኤ ጳጳሶች ተሰብስበው እግዚአብሔር “እውነተኛ አምላክ” እንደሆነ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅም “እውነተኛ አምላክ” ነው የሚል እምነት ደነገጉ። ያ እምነት በከፊል እንዲህ ይላል፦
“ነገር ግን (ወልድ) ያልነበረበት (ጊዜ) ነበር፤ ሳይፈጠር በፊት አልነበረም፤ ካለመኖር ወደ መኖር የመጣ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የተለየ ሕላዌ አለው፤ ወይም የተፈጠረ ነው፤ ወይም ሊለወጥ የሚችል ነው የሚሉትን ሰዎች የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታወግዛቸዋለች።”3
ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ ከአባቱ ጋር እኩል አልነበረም፤ ወይም ወልድ የተፈጠረ ወይም ፍጡር ነበር ብሎ የሚያምን ማንኛውም ሰው ለዘላለማዊ ኩነኔ ይመደብ ነበር። ይህ ውግዘት ተራው ሰው ከዚህ እምነት ጋር እንዲስማማ የሚያስገድደው ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያመጣበት መገመት ይቻላል።
በ381 እዘአ ሌላ ጉባኤ በኮንስታንቲኖፕል (ቁስጥንጥኒያ) ተሰባሰበና ልክ አብና ወልድ እንደሚመለኩና እንደሚከበሩት መንፈስ ቅዱስም መመለክና መከበር አለበት ብሎ ደነገገ። አንድ ዓመት ቆይቶም በ382 እዘአ ሌላ ሲኖዶስ በዚያው በኮንስታንቲኖፕል ተሰበሰበና የመንፈስ ቅዱስን ፍጹም መለኮታዊነት አረጋገጠ።4 በዚያም ዓመት ፓፓ ዳምሱስ በሮም በተሰበሰበ ጉባኤ ፊት ተነስተው በቤተክርስቲያኗ መወገዝ የሚኖርባቸውን የትምህርቶች ስብስብ አቀረቡ። የዳማሱስ መጽሐፍ የተሰኘው ሠነድ የሚከተለውን ቃል ይጨምራል፦
“አብ ዘላለማዊ መሆኑን፣ ወልድ ዘላለማዊ መሆኑና መንፈስ ቅዱስ ዘላለማዊ መሆኑን የሚክድ ማንኛውም ሰው መናፍቅ ነው”
“ማንም ሰው የአምላክ ልጅ ልክ እንደ አብ ሙሉ ኃይል ያለው፣ ሁሉን የሚያውቅና ከአባቱ ጋር እኩል የሆነ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ቢክድ መናፍቅ ነው።”
“ማንም ሰው መንፈስ ቅዱስ ሙሉ ኃይል ያለውና ሁሉን ነገር የሚያውቅ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ቢክድ መናፍቅ ነው።”
“ማንም ሰው ሦስቱ አካሎች ማለትም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እውነተኛ አካሎች፣ እኩል፣ ዘላለማዊ፣ የሚታዩትንና የማይታዩትን ነገሮች ሁሉ የያዙ ሁሉን ቻይ . . . መሆናቸውን ከካደ መናፍቅ ነው።”
“ማንም ሰው ሥጋ የሆነው ወልድ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከአብ ጋር በሰማይ ነበር ብሎ ካላመነ መናፍቅ ነው”
“ማንም ሰው አብ አምላክ ነው፤ ወልድ አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ብሎ ሳለ . . . ሦስቱም አንድ አምላክ ናቸው ካላለ . . . መናፍቅ ነው።”5
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ቃላት ከላቲን የተረጎመው አንድ ካቶሊክ ኢየሱሳዊ ምሁር የሚከተለውን አስተያየት እንዲህ በማለት ጨምሮአል፦ “በግልጽ እንደሚታየው ፓፓ ቅዱስ ሴለስቲን (422-32)እነዚህን ድንጋጌዎች እንደ ሕግ ይቆጥሯቸው ነበር። በተጨማሪም የእምነት ፍችዎች እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ።”6 ምሁሩ ኢድመንድ ጂ. ፎርትማንም መጽሐፉ “በእውነት ላይ የተመሠረተና ጠንካራ የሥላሴ መሠረተ ትምህርትን” ያመለክታል በማለት ተናግረዋል።7
የሥላሴን ትምህርት የሚቀበል ቤተክርስቲያን አባል ከሆንክ እነዚህ ቃሎች ለአንተም እምነቶች ፍች ወይም ትርጉም የሚሰጡ ናቸውን? አብያት ክርስቲያናቱ በሚያስተምሩት መሠረት በሥላሴ መሠረተ ትምህርት የምታምን ከሆንክ ኢየሱስ በምድር በነበረ ጊዜ በሰማይም እንደነበር ወይም በአንድ ጊዜ በሁለቱም ቦታ ይኖር ነበር ብለህ ማመን እንደሚኖርብህ ተገንዝበሃልን? ይህ ትምህርት የ4ኛው መቶ ዘመኑ የቤተ ክርስቲያን ሰው አትናቴዎስ ኦን ዘ ኢንካርኔሽን በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው በማለት ከገለጹት ጋር ይመሳሰላል፦
“ቃል (ኢየሱስ) በሥጋው አልተገደበም ነበር። በሥጋ መገኘቱ በሌላ ቦታው እንዳይሆን አያግደውም ነበር። አካሉን ወደ ምድር ሲያዛውር ጽንፈ ዓለሙን በአእምሮውና በኃይሉ ማስተዳደሩን አላቆመም ነበር።. . . .እስከ አሁንም የመላው ጽንፈ ዓለም የሕይወት ምንጭ ነው። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ባለው ነገር ሁሉ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ከሁሉም ውጭ ነው።”8
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ምን ማለት እንደሆነ
አንዳንዶች የሥላሴ ትምህርት ማለት ለኢየሱስ የአምላክነት ባሕርይ መስጠት ወይም ኢየሱስ አምላክ ነው ማለት ብቻ ነው ብለው ይደመድማሉ። ሌሎች ደግሞ በሥላሴ ማመን ማለት በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ማመን ማለት ነው ይላሉ።
ይሁን እንጂ የሕዝበ ክርስትናን እምነት ቀረብ ብሎ መመርመሩ እነዚህ አስተሳሰቦች ከመደበኛው የሥላሴ ትምህርት አንጻር ሲታዩ ምን ያህል በአሳዛኝ ሁኔታ የተለዩና ከምኑም የማይደርሱ መሆናቸውን ያረጋግጣል። መደበኛው ወይም ደንበኛው ፍች የሥላሴ ትምህርት እንዲህ ቀላል ሐሳብ እንዳልሆነ ያሳያል። የሥላሴ ትምህርት ለረዥም ጊዜ ሲተበተብ የቆየ የተጠላለፈና በኋላ አንድ ላይ የተሰባሰበና ውስብስብ የሆነ የሐሳቦች ስብስብ ነው።
ከኮንስታንቲኖፕል ጉባኤ በኋላ በ381 እዘአ ከወጣው፣ በ382 እዘአ ከዳማሱስ መጽሐፍ ከወጣው፣ ከዚያም ጥቂት ቆይቶ ከአትናቴዎስ እምነት ከወጣውና ከሌሎችም ሰነዶች እንደሚታየው፣ የሕዝበ ክርስትና የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ምን ማለት እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን። ቀጥሎ ያሉትን የተረጋገጡ ሐሳቦች ይጨምራል፦
1. በአንድ አምላክ መለኮታዊ አካል ውስጥ ሦስት አካላት ማለትም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አሉ ተብለዋል።
2. እነዚህ የተለያዩ አካላት እያንዳንዳቸው ዘላለማዊ ማለትም በዘመናቸው የማይቀዳደሙ ናቸው ተብለዋል።
3. እያንዳንዳቸው ሁሉን ቻይና እርስ በርሳቸው የማይበላለጡ ናቸው ተብለዋል።
4. እያንዳንዳቸው ሁሉን አዋቂ ናቸው ተብለዋል።
5. እያንዳንዳቸው እውነተኛ አምላክ ናቸው ተብለዋል።
6.ይሁን እንጂ አንድ አምላክ ነው እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም ተብሎአል።
በግልጽ እንደምናየው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ቢያንስ ቢያንስ ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ነገሮችና በዝርዝር ሲመረመር ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ሐሳቦችን የሚያጠቃልል የተወሳሰበ የሐሳብ ስብስብ ነው። ነገር ግን ከላይ የሠፈሩትን ዋና ዋና ሐሳቦች ብንመለከት ከስድስቱ አንዱ እንኳ ቢጎድል የቀሩት ሐሳቦች የሕዝበ ክርስትና ሥላሴን ሊገልጹ የማይችሉ ይሆናሉ። ሙሉውን መግለጫ ለማግኘት ከተፈለገ እነዚህ ቁርጥራጦች በሙሉ መገኘት አለባቸው።
“ሥላሴ” ለሚባለው ቃል ይህን የተሻለ ግንዛቤ ከያዝን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ሥላሴ ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ያስተማሩት ትምህርት ነበርን? ከሆነ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅሮ በአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ መውጣት ነበረበት ማለት ነው። እነሱ ያስተማሩትን ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ ስለሚገኝ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው ወይም አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ ደግሞ ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የሰፈረ መሆን ይኖርበታል።
ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ስለ አምላክ ለሰዎች ሲያስተምሩ በተለይም አንዳንድ አማኞች ሕይወታቸውን ሳይቀር ስለ አምላክ ሲሉ ለሞት አሳልፈው መስጠት እንደሚኖርባቸው ሲናገሩ ስለ አምላክ ማንነት ግን አላስተማሯቸውም ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። ስለዚህ ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ለዚህ ዋነኛ የአምላክን ማንነት የሚመለከት መሠረተ ትምህርት ለማስተማር ሥራ ከፍተኛውን ቅድሚያ ሰጥተውት መሆን ይኖርበታል።
ቅዱሳን ጽሑፎችን መርምሩ
ሰዎች በሥራ ምዕራፍ 17 ቁጥር 11 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ያስተማረውን ነገር “ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጽሐፍትን ይመረምሩ” ስለነበር “ልበ ሰፊዎች” ተብለው መጠራታቸው ተገልጿል። የሐዋርያትን ትምህርት እንኳ ሳይቀር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲመረምሩ ተነግሯቸው ነበር። አንተም እንደነርሱ ማድረግ አለብህ።
ቅዱሳን ጽሑፎች “በአምላክ መንፈስ የተጻፉ” መሆናቸውንና “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ እንደሚጠቅሙ” አስታውስ።(2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ለመሠረት ትምህርት ነክ ጉዳዮች የተሟላ መግለጫ ይሰጣል። የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እውነት ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መገኘት አለበት።
ኢየሱስና የሱ ደቀመዛሙርት ስለ ሥላሴ አስተምረው እንደሆነ ራስህ ማየት እንድትችል መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም ደግሞ 27ቱ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱስን ጽሑፎች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። በምትመረምርበት ጊዜ ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦
1. ስለ “ሥላሴ” የሚናገር ጥቅስ ላገኝ እችላለሁን?
2. አምላክ ከሦስት የተለያዩ አካሎች ማለት ከአብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ የተሠራ ሆኖ ግን ሦስቱም አንድ አምላክ ብቻ ናቸው የሚል ጥቅስ ላገኝ እችላለሁን?
3. አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በሁሉም መንገዶች ለምሳሌ ያህል በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃ በጥበብና በመሳሰሉት እኩል ናቸው ብሎ የሚናገር ጥቅስ ላገኝ እችላለሁን?
የቱንም ያህል ብትመረምር ሥላሴ የሚለው ቃል የሚገኝበት ወይም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በሁሉም መንገዶች ለምሳሌም በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃና በጥበብ እኩል ናቸው የሚል አንድም ጥቅስ አታገኝም። በእነዚህ ረገድ ወልድ ከአብ ጋር እኩል ነው የሚል አንድም ጥቅስ የለም። እንዲህ የሚል የሚመስል ጥቅስ ቢኖርም እንኳ የሚናገረው ስለ ሥላሴ ወይም ሦስትነት ሳይሆን ቢበዛ ስለ “ሁለትነት” ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ጋር አያስተካክልም።
ብዙ ምሁራን ምን እንደሚሉ
ብዙ ምሁራን በሥላሴ የሚያምኑትን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሥላሴ መሠረት ትምህርት እንደሌለ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ አፍ ሪሊጅን እንዲህ በማለት ይናገራል፦
“በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎችና የሃይማኖት ሊቃውንት በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንደማይገኝ ይስማማሉ። . . . ምንም እንኳ የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እንደ እስራኤላውያን አባት አድርጎ ቢገልጸውና ቃል (ዳዋር)፣ መንፈስ (ሩሕ)፣ ጥበብ (ሆክማህ) እና መገኘት (ሼክናህ) በመሰሉት ቃላት ስብዕናውን ቢገልጹም እነዚህን ሐሳቦች በኋላ ከመጣው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ጋር ማገናዘብ ከብሉይ ኪዳን ዓላማና መንፈስ የራቀ ነው።
“ከዚህም በተጨማሪ ተመራማሪዎቹና የሃይማኖት ሊቃውንት አዲስ ኪዳንም ቢሆን ግልጽ የሆነ የሥላሴ ትምህርት እንደማይገኝበት ያምናሉ። አባት የሆነው አምላክ (ፓንቶክሬተር) የሁሉ ነገር ምንጭና የኢየሱስ ክርስቶስም አባት ነው። ‘አብ (አባት)’ የመጀመሪያው የሥላሴ ክፍል የማዕረግ ስም ሳይሆን ሌላው የአምላክ ስም ነው። . . .
“በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሥላሴ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የትም ቦታ ተሰራጭቶ ይገኛል የሚል አስተሳሰብ የለም። ወይም ደግሞ አዲስ ኪዳን በኋላ የመጡት የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ቴክኒካዊ ቋንቋዎች (ሁፖስታሲስ፣ ኦሲያ፣ ሰብስታንሺያ፣ ስብሲስቴንሺያ፣ ፕሮስፖን፣ ፐርሶና) የመሳሰሉት ቃላት የሉበትም። . . . መሠረተ ትምህርቱ በቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ላይ ብቻ ሊመሠረት የማይችል መሆኑ አሌ ሊባል አይችልም።”9
በዚህ ጉዳይ ላይ ታሪካዊ ሐቆችን በሚመለከት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦
“ሥላሴ የሚለው ቃልም ሆን የሥላሴ ትምህርት በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። . . .
“መሠረተ ትምህርቱ የዳበረው በብዙ መቶ ዘመናትና በብዙ ክርክሮች ነው። . . .
“እስከ 4ኛው መቶ ዘመን ድረስ የሦስቱ ልዩነትና አንድነት አንድ ባሕርይና ሦስት አካላት በሚል አንድ መሠረተ ትምህርት አልተቀመረም ነበር።”10
ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ የሥላሴን አመጣጥ በተመለከተ ተመሳሳይ ገለጻ ሰጥቷል፦
“በተመራማሪዎችና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ የሃይማኖት ሊቃውንት እንዲሁም ባለማቋረጥ ቁጥራቸው እያደገ በመጣ የሮማ ካቶሊኮች ዘንድ ያለው ግንዛቤ አንድ ሰው ከፍ ያለ ብቃት ከሌለው አዲስ ኪዳንን መሠረት አድርጎ ስለ ሥላሴ መናገር እንደሌለበት ነው። በተመሳሳይም የሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች ታሪክ ሊቃውንትና የሥርዓታዊ ሃይማኖት ሊቃውንት አንድ ሰው እዚህ ቀረሽ ስለማይባል ሥላሴያዊነት ሲናገር ከክርስቲያናዊ መሠረቱ ለቆ ወደ አራተኛው መቶ ዘመን የመጨረሻዎቹ አሥር ዓመታት መምጣቱ እንደሆነ ተገንዝበዋል። “አንድ አምላክ በሦስት አካላት” ተብሎ የሚጠራው የመጨረሻው የሥላሴ ድንጋጌ ከክርስትና ሕይወትና አስተሳስብ ጋር በሚገባ የተዋሃደው በዚያ ጊዜ ነበር። . . .
“የድንጋጌው ቀመር ራሱ ያመጣጡ ዘመን መታወቁን አይገልጽም። የሦስት መቶ ዘመናት የመሠረት ትምህርታዊ ዕድገት ውጤት ነበር።”11
“በተዘዋዋሪ መንገድ ተገልጿልን”?
የሥላሴ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ “ሥላሴን” በተዘዋዋሪ መንገድ ይገልጸዋል ይሉ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ዓይነቱ አባባል የመጣው መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው። የኋላ ዘመን ቀሳውስት በገዛ ፈቃዳቸው መሠረተ ትምህርት መሆን አለበት ብለው የደነገጉትን ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማንበብ ወይም በግድ ለማስገባት የተደረገ ከንቱ ሙከራ ነው።
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ማንነት የሚገልጸውን እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እንዲሁ በተዘዋዋሪ ብቻ የሚገልጸው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች መሠረታዊ ትምህርቶች ላይ ግልጽ ሲሆን በዚህ እጅግ አስፈላጊ በሆነ ትምህርት ላይ ግልጽ ያልሆነው ለምንድን ነው? የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ሥላሴ ከሆነ ስለዚሁ ጉዳይ ግልጽ የሆነ ትምህርት የሚሰጥ መጽሐፍ አይጽፍም ወይም አያስጽፍም ነበርን?
መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴን መሠረት ትምህርት የማያስተምርበት ምክንያት ቀላል ነው፦ ሥላሴ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ስላልሆነ ነው። አምላክ ሥላሴ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስና የእሱ ደቀመዛሙርት ለሌሎች እንዲያስተምሩት ጉዳዩን ግልጽ ያደርግላቸው ነበር። እንዲህ ቢሆን ኖሮ ይህ እጅግ አስፈላጊ የሆነ መረጃ በአምላክ መንፈስ በተጻፈው ቃሉ ውስጥ ይጨመር ነበር። በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን እንዲያታግል አይተውም ነበር።
የሥላሴ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ “ሥላሴን” በተዘዋዋሪ መንገድ ይገልጻል ብለው በማስረጃነት የሚያቀርቧቸውን ጥቅሶች ስንመረምራቸው ምን እናገኛለን? ትክክለኛው ግምገማ የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች ስለ ሕዝበ ክርስትና ሥላሴ የማይናገሩ መሆናቸውን ይገልጻል። የሃይማኖት ሊቃውንት የሥላሴ ጽንሰ ሐሳባቸውን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በግድ ለማስገባት ይጥራሉ። ነገር ግን እነዚህ ሐሳቦች በቅዱስ ጽሑፉ ጥቅሶች ውስጥ አይገኙም። እንዲያውም ሥላሴያዊ ሐሳቦች መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ ከሚሰጠው ምስክርነት ጋር ይጋጫሉ።
ሥላሴን በተዘዋዋሪ መንገድ ይጠቅሳሉ ከሚባሉት ጥቅሶች መሃል አንዱ የሚገኘው በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ነው። እዚህ ላይ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ ተጠቅሰዋል። አንዳንዶች ይህ ጥቅስ በተዘዋዋሪ መንገድ ሥላሴን ይገልጻል ብለው ይናገራሉ። ነገር ግን ቁጥሮቹን ራስህ አንብባቸውና ሦስቱ በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃና በጥበብ እኩል የሆነ አንድ አምላክ ናቸው የሚል ነገር እንዳለ ተመልከት። ፈጽሞ የለም። ሦስቱን አንድ ላይ በሚጠቀሱ ሌሎች ጥቅሶችም ረገድ ተመሳሳይ ነው።
በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ለአብ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ “ስም” የሚለው ነጠላ አጠራር ብቻ በመጠቀሱ ሥላሴን በተዘዋዋሪ ይጠቅሳል ብለው ለሚያስቡ ሰዎች ለአብርሃምና ለይስሐቅ “ስም” በሚለው ነጠላ ቃል ከተጠቀመው ከዘፍጥረት 48:16 ጋር አወዳድር።—ኪንግ ጀምስ ቨርሺን፣ ኒው ወርልድ ትራንስሌሽን ኦፍ ሆሊ እስክሪፕቸርስ
የሥላሴ አማኞች በአንዳንድ ትርጉሞች “ቃል” “በእግዚአብሔር ዘንድ” እና ራሱም “እግዚአብሔር” እንደሆነ የተነገረበትን የዮሐንስ 1:1 ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቃል አምላክ (“a god”) ወይም “መለኮት” ማለት የግድ (God) እግዚአብሔር ሳይሆን ኃይል መሆኑን እንደሚገልጽ ይናገራሉ። ከዚህም በላይ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ “ቃል” ከእግዚአብሔር “ዘንድ” እንደነበረ ይናገራል። ይህም ምክንያታዊ እንሁን ከተባለ ያው አምላክ ራሱ ከራሱ ጋር ሊሆን አይችልም። ስለ “ቃል” ምንም ዓይነት መደምደሚያ ቢሰጠው ሐቁ በዮሐንስ 1:1 ላይ የተጠቀሱት ሦስት ሳይሆን ሁለት አካላት መሆናቸው ነው። የሥላሴን መሠረት ትምህርት ለመደገፍ በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ሁሉም ጥቅሶች በሐቀኝነት ሲመረመሩ በምንም መንገድ ትምህርቱን እንደማይደግፉ መረዳት ይችላል።a
ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ይህ ነው፦ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ አስተምረውት ከነበረ ከእነሱ በኋላ ወዲያውኑ የተተኩት የቤተክርስቲያን ሰዎችም አስተምረውት ነበር ማለት ነው። ነገር ግን እነዚህ በአሁኑ ጊዜ ሐዋርያዊ አባቶች የተባሉት ሰዎች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን? ይህ ጥያቄ ከዚህ በኋላ በሚወጣው መጠበቂያ ግንብ በዚህ ተከታታይ ርዕስ ትምህርት ክፍል 2 ላይ ይብራራል።
ማመሳከሪያዎች
1. ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ 1912 ጥራዝ 15 ገጽ 47
2. ዘ ባፕቲስት ኢንሳይክሎፒዲያ በዊሊያም ካት ካርት የተዘጋጀ፣ 1883፣ ገጽ 1168-9
3. ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦፍ ክርስቲያን ዶክትሪን በበረሃርድ ሎስ 1980 እትም ገጽ 53
4. ከላይ ቁጥር ሦስት ላይ የተጠቀሰው ሥር ገጽ 64-5.
5. ዘ ቸርች ቲችዝ በጆን ኤፍ ክላርክሰን፣ ኤስ ጄ ጆን ኤች ኤድዋርድስ፣ በኤስ ጄ ዊልያም ጄ ኬላ፣ በኤስ ጄ እና ጆን ጄ ዌልች ተተርጉሞ የተዘጋጀ፣ 1955, ገጽ 125-7
6. በቁጥር 5 ላይ የተጠቀሰው ሥራ ገጽ 125
7. ዘ ትሪዩን ጎድ በኢድመንድ ጄ ፎርትማን፣ የ1982 እትም ገጽ 126
8. ኦን ዘ ኢንካርኔሽን በፔሎፕ ለውስን የተተረጎመ፣ 1981 እትም ገጽ 27-8
9. ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ሪሊጅን ሚርሴ ኤሊዲያ ዋና አዘጋጅ 1987 ጥራዝ 15 ገጽ 54
10. ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ 15ኛው እትም 1985፣ ጥራዝ 11 ማይክሮፒድያ 1967 ጥራዝ 14፥ገጽ 928
11. ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ 1967 ጥራዝ 14 ገጽ 295
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እንደነዚህ ስላሉት የቅዱስ ጽሑፍ ጥቅሶች የተሟላ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በሥላሴ ማመን አለብህን? የሚለውን በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር የታተመውን ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Church at Tagnon, France