የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ሥላሴ ነው ብላ አስተምራለችን?
ክፍል 4—የሥላሴ መሠረተ ትምህርት የተስፋፋው መቼና እንዴት ነበር?
የመጀመሪያዎቹ የዚህ ተከታታይ ሦስት ርዕሰ ትምህርቶች ኢየሱስና ሐዋርያቱም ሆኑ የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት እንዳላስተማሩ አሳይተዋል። (የህዳር 1, 1991፣ የየካቲት 1, 1992 እና የሚያዚያ 1, 1992 የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን ተመልከቱ።) ይህ የመጨረሻ ርዕሰ ትምህርት ደግሞ የሥላሴ ቀኖና እንዴት እንደተስፋፋና በ325 እዘአ የተደረገው የኒቂያ ጉባኤ በዚህ ረገድ የተጫወተውን ሚና ይገልጻል።
በ325 እዘአ የሮማው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በትንሹ እስያ በምትገኘው የኒቂያ ከተማ የአቡኖችን ጉባኤ ሰበሰበ። ዓላማውም በእግዚአብሔር ልጅና ሁሉን በሚችለው አምላክ መካከል ስላለው ዝምድና ለነበረው የማያባራ ሃይማኖታዊ ክርክር እልባት ለማስገኘት ነበር። የዚያን ጉባኤ ውጤት በተመለከተ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንደሚከተለው ይላል፦
“ውይይቱን በንቃት በመምራት ስብሰባውን በቁንጮነት የመራውና በጉባኤው በወጣው ቀኖና ላይ ክርስቶስ ከአብ ጋር ያለውን ዝምድና ለመግለጽ ‘ከአብ ጋር የባሕርይ አንድነት (ሆሙዎሲዮስ) አለው’ የሚል ዋና ረቂቅ . . . ሐሳብ ያቀረበውም ቆስጠንጢኖስ ራሱ ነበር። . . . ከሁለት አቡኖች ብቻ በቀር አብዛኞቹ አቡኖች ንጉሡን በመፍራት ከፍላጎታቸው ውጭ ረቂቁን ፈረሙ።”1
ይህ አረማዊ ንጉሠ ነገሥት ጣልቃ የገባው ጽኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ስለነበረው ነውን? አልነበረም። የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርት አጭር ታሪክ የተሰኘ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ “ቆስጠንጢኖስ በግሪክኛ መንፈሳዊ ትምህርት ላይ ስለሚነሱ ማንኛቸውም ጥያቄዎች የሚያውቀው ነገር አልነበረም” ይላል።2 የሚያውቀው ነገር ቢኖር ሃይማኖታዊ ክርክሮች ለግዛቱ አንድነት ስላሰጉት እነዚህ ክርክሮች እልባት እንዲያገኙ መፈለጉ ነበር።
የኒቂያ ጉባኤ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት መሥርቷልን?
የኒቂያ ጉባኤ ሥላሴ የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርት እንዲሆን መሥርቷልን ወይም አጽድቋልን? ብዙዎች የሚያስቡት የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በኒቂያ ጉባኤ እንደተመሠረተ ወይም እንደጸደቀ ነው። ሐቁ የሚያሳየው ግን ሌላ ነው።
በጉባኤው የወጣው ረቂቅ ስለ እግዚአብሔር ልጅ የተለያዩ ካህናት ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በአንድ ዓይነት መንገድ እኩል እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት የሚያስችሏቸውን ነገሮች ተናግሯል። ሆኖም የኒቂያ ጉባኤ ያልተናገረውን ነገር ስንመለከት ጥሩ እውቀት እናገኛለን። በመጀመሪያ ላይ የቀረበው ሙሉ ድንጋጌ የሚከተለው ነበር፦
“የሚታዩትንና የማይታዩትን ሁሉ በሠራው ሁሉን ቻይ አብ በሆነው አንድ አምላክ እናምናለን፤
“እንዲሁም በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እርሱም ከአብ በተወለደው፣ የአብ የባሕርይ ልጅ በሆነው አንድያ ልጅ፣ አምላክ ከአምላክ፣ ብርሃን ከብርሃን፣ እውነተኛ አምላክ ከእውነተኛ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ የተሠራ ባልሆነው፣ ከአብ ጋር አንድ ባሕሪ በሆነው፣ በሰማይና በምድር ላይ ያሉት ሁሉ በእርሱ በኩል ወደ ሕልውና በመጡበት፣ በእኛ በሰዎችና በመዳናችን ምክንያት ወደ ምድር ወርዶ ሥጋ ለብሶ ሰው በመሆን በተሠቃየውና በሦስተኛው ቀን እንደገና በተነሳው፣ ወደ ሰማይ በአረገውና ሙታንንና ሕያዋንን ሊፈርድ በሚመጣው እናምናለን፤
“በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን።”3
ታዲያ ይህ ድንጋጌ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአንድ አምላክ ውስጥ ያሉ ሦስት አካሎች ናቸው ይላልን? ሦስቱ በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃና በጥበብ እኩል ናቸው ይላልን? አላለም። እዚህ ላይ ስለ አንድነት በሦስትነት የሚገልጽ ምንም ፍንጭ የለም። የመጀመሪያው የኒቂያ ድንጋጌ ሥላሴን አልመሠረተም ወይም አላጸደቀም።
ይህ ድንጋጌ ግፋ ቢል ወልድ ከአብ ጋር “አንድ ባሕሪ ያለው” ነው በማለት ወልድን ከአብ ጋር እኩል አድርጎ ያያል። ስለ መንፈስ ቅዱስ ግን እንዲህ የመሰለ ነገር አልተናገረም። የሚለው “በመንፈስ ቅዱስም . . . እናምናለን” ብቻ ነው። ይህም የዛሬው የሕዝበ ክርስትና የሥላሴ ትምህርት ከሚያስተምረው የተለየ ነው።
“አንድ ባሕሪ (ሆሙዎሲዮስ)” የሚለው አባባልም እንኳን ጉባኤው አብንና ወልድን በቁጥር አንድ እንደሆኑ ያምን እንደነበር ያመለክታል ለማለት አያስደፍርም። ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደሚከተለው ይላል፦
“ጉባኤው የአብንና የወልድን ባሕሪ በቁጥርም አንድ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አስቦ ይሁን አይሁን ያጠራጥራል።”4
ጉባኤው ወልድና አብ በቁጥር አንድ ናቸው ማለቱ ቢሆን ኖሮም እንኳን ሥላሴ አይሆንም ነበር። ሁለትነት በአንድነት የያዘ አምላክ ይሆን ነበር እንጂ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት እንደሚለው ሦስትነት በአንድነት ያለው አምላክ አይሆንም ነበር።
“የጥቂቶች አመለካከት”
በኒቂያ ጉባኤ አቡኖቹ ባጠቃላይ ወልድ ከአብ ጋር እኩል ነው ብለው አምነው ነበርን? አላመኑም፣ ተፃራሪ አመለካከቶች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የአንዱ አመለካከት ወልድ በጊዜ ረገድ የተወሰነ መጀመሪያ ያለው ስለሆነ ከአብ ጋር እኩል አይደለም፤ እንዲያውም ከሁሉም አንፃር ከአብ የበታች ነው ብሎ ባስተማረው በአርዮስ የተገለጸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አትናቴዎስ ወልድ በአንዳንድ መንገዶች ከአብ ጋር እኩል ነው ብሎ ያምን ነበር። ሌሎች አመለካከቶችም ነበሩ።
ወልድ ከአብ ጋር አንድ ዓይነት ባሕሪ አለው የሚለውን የጉባኤውን ውሳኔ በተመለከተ ማርቲን ማርቲ “እንደ እውነቱ ከሆነ ኒቂያ የወከለው የጥቂቶችን አመለካከት ነበር፤ ስምምነቱ ያልሠመረና ከአርዮስ የተለየ አመለካከት በነበራቸው በብዙዎች ዘንድ እንኳን ተቀባይነት ያላገኘ ነበር” ብለዋል።5 በተመሳሳይም ኧ ሴሌክት ላይብረሪ ኦቭ ናይሲን ኤንድ ፖስት ኒኬን ፋዘርስ ኦቭ ዘ ክሪስቺየን ቸርች የተሰኘው መጽሐፍ “ምንም እንኳን የወቅቱ አሸናፊዎች የሆኑት በቁጥር አነስተኞቹ ቢሆኑም በመሠረተ ትምህርት ረገድ ከአርዮስ የሚለየውን በግልጽ የተደነገገ አቋም የያዙት እነዚያው አነስተኞቹ ወገኖች ነበሩ” በማለት ይገልጻል።6 የክርስትና መሠረተ ትምህርቶች አጭር ታሪክ የተሰኘው መጽሐፍም እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦
“በተለይ በብዙ አቡኖችና በምሥራቅ መንፈሳዊ ሊቃውንት ዘንድ በጣም ተነቃፊ የመሰላቸው ተቀባይነት ባገኘው መሠረተ ትምህርትና ከእርሱ በሚለየው መናፍቅነት ተብሎ በተጠራው መካከል የኋላ ኋላ ለተነሳው ጥል መነሻ የሆነው ሆሙዎሲዮስ [“የባሕሪ አንድነት”] የሚለው በራሱ በቆስጠንጢኖስ በድንጋጌው ውስጥ የገባው ጽንሰ ሐሳብ ነበር።”7
ከጉባኤው በኋላ ክርክሩ ለብዙ ዓመታት ቀጠለ። ወልድን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል አድርጎ መመልከትን ይደግፉ የነበሩ ሰዎች ለጊዜው ተቀባይነት አጥተው ነበር። ለምሳሌ ያህል ማርቲን ማርቲ ስለ አትናቴዎስ እንዲህ ብለዋል፦ “ታዋቂነቱ ከፍ ብሎ ነበር በኋላ ግን ዝቅ አለ፤ [ከጉባኤው በኋላ በነበሩት ዓመታት] ብዙ ጊዜ ይታሰር ስለነበር ተቅበዝባዥ ሆኖ ነበር።”8 አትናቴዎስ ብዙ ዓመታትን በእሥር ያሳለፈው ወልድ ከአምላክ ጋር እኩል ነው የሚለውን አመለካከቱን የፖለቲካና የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣኖች ስለተቃወሙ ነበር።
ስለዚህ በ325 እዘአ የተደረገው የኒቂያ ጉባኤ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት መሠረተ ወይም አጸደቀ ብሎ መናገር ትክክል አይደለም። የኋላ ኋላ የሥላሴ ትምህርት የሆነው ጽንሰ ሐሳብ በዚያን ጊዜ አልነበረም። አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳቸው እውነተኛ አምላክና በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃና በጥበብ እኩል የሆኑ፣ ነገር ግን ሦስትነት በአንድነት ያለው አንድ አምላክ ነው የሚለው ሐሳብ በዚያ ጉባኤም ሆነ በቀደሙት የቤተ ክርስቲያን አበው አልተስፋፋም ነበር። የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል፦
“በዘመናችን በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት . . . ከጀስቲን [ማርቲር] አነጋገር ምንም ድጋፍ አያገኝም። ከኒቂያ ጉባኤ በፊት ስለተነሱ አባቶችም እንደዚሁ ሊባል ይቻላል፣ ይህም ማለት ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት ሦስት መቶ ዘመናት የተነሱት ክርስቲያን ጸሐፊዎች በሙሉ ከጀስቲን [ማርቲር] የተለዩ አልነበሩም ሊባል ይቻላል። እውነት ነው፣ ስለ አብ፣ ስለ ወልድና ስለ ትንቢታዊው ወይም ስለመንፈስ ቅዱስ ተናግረዋል። ይሁንና ዛሬ በሥላሴ አማኞች እንደሚታመነው እኩያሞች እንደሆኑ ወይም በቁጥር አንድ የመሆን ባሕሪ እንዳላቸው፣ ወይም ሦስትነት በአንድነት እንዳላቸው አድርገው በምንም ዓይነት መንገድ አልተናገሩም። ሐቁ የዚህ ተቃራኒ ነው። እነዚህ አበው የገለጹት የሥላሴ ትምህርት በዘመናችን ከሚገኘው መሠረተ ትምህርት ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህን የምንለው በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንደሚገኝ እንደማንኛውም ሐቅ በበቂ ማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችል ስለሆነ ነው።”
“በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት የኖረና በዘመናዊ መልኩ የምናውቀውን ይህን [የሥላሴ] መሠረተ ትምህርት ያመነ ጸሐፊ የጻፈውን ቅንጣት ማስታወሻ አቀርባለሁ የሚል ሰው ካለ እንዲያቀርብ ጥሪ እናቀርብለታለን።”9
ይሁን እንጂ ኒቂያ አንድ ትልቅ ለውጥ የተደረገበትን ጊዜ ያመለክታል። ወልድ ከአብ ጋር እኩል ነው የሚለው አመለካከት በይፋ ተቀባይነት እንዲያገኝ በር ከፍቷል፤ ይህም በኋላ ለተስፋፋው የሥላሴ ትምህርት መንገድ ጠርጓል። በጄ ኤ ባርክሌይ የተዘጋጀው ዘ ሰከንድ ሴንቸሪ ኦርቶዶክሲ የተሰኘ መጽሐፍ እንደሚከተለው ይገልጻል፦
“ቢያንስ እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ድረስ ዓለም አቀፏ ቤተ ክርስቲያን በአንድ መሠረተ ሐሳብ የተባበረች ሆና ቆይታለች፤ ሁሉም የአብን የበላይነት ይቀበሉ ነበር። ሁላቸውም ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሔር አብ ብቻውን የሁሉም የበላይ፣ የማይለወጥ፣ እንከን ሊወጣለት የማይችልና መጀመሪያ የሌለው እንደሆነ አድርገው ይመለከቱ ነበር። . . .
“እነዚያ የሁለተኛው መቶ ዘመን ጸሐፊዎችና መሪዎች ሲሞቱ ቤተ ክርስቲያኗ . . . የሚከለክላት ሳይኖር ቀስ በቀስ እየተንሸራተተች . . . በኒቂያ ጉባኤ ወደ ድምዳሜው ላይ ወደ ደረሰበት ደረጃ መግባቷን ተገነዘበች። በኒቂያ ጉባኤ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቀዥቃዦች መናፍቅነታቸውን በለዘብተኝነት በተቀበላቸው ብዙኃን ላይ አስርገው አስገቡና በስተ ጀርባቸው በነበሩት የፖለቲካ ባለሥልጣኖች አማካኝነትም የእምነታቸውን ንጽሕና ሳይበከል እንዳለ ጠብቀው ለማቆየት የሚጥሩ ሰዎችን ያስገድዱ፣ ይደልሉና ያስፈራሩ ነበር።10
የቁስጥንጥኒያው ጉባኤ
በ381 እዘአ የቁስጥንጥኒያው ጉባኤ በኒቂያ ጉባኤ የተደነገገውን ቀኖና አጸደቀው። ሌላ ነገርም ጨመረበት። መንፈስ ቅዱስን “ጌታ” እና “ሕይወት ሰጪ” በማለት ጠራው። በ381 እዘአ የተስፋፋው እምነት (ይህም በመሠረቱ የዘመናችን አብያተ ክርስቲያናት እየተጠቀሙበት ያለውና “የኒቂያ ድንጋጌ” በመባል የሚጠራው ነው) ሕዝበ ክርስትና ሁሉን አቀፍ የሥላሴ ቀኖና ለመደንገግ በምትችልበት ደረጃ ጠርዝ ላይ እንደደረሰች አሳይቷል። ሆኖም ይህ ጉባኤም ቢሆን መሠረተ ትምህርቱን የተሟላ አላደረገውም። አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ ይህን አምኖ በመቀበል የሚከተለውን አስፍሯል፦
“ከመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ በኋላ 60 ዓመታት ቆይቶ የተደረገው የመጀመሪያው የቁስጥንጥኒያ ጉባኤ [381 እዘአ] የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊነት ሲገልጽ ሆሙዎሲዮስ የሚለውን ቃል ማስወገዱ ትኩረትን የሚስብ ነው።”11
“ምሁራን በዚህ ድንጋጌ ቃላት ላይ በሚታየው ለዘብተኝነት ተገርመዋል። ለምሳሌ ያህል መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር የባሕሪ አንድነት አለው ለማለት ሆሙዎሲዮስ የሚለውን ቃል ሳይጠቀም መቅረቱ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል።”12
ይኸው ኢንሳይክሎፒድያ “ሆሙዎሲዮስ የሚለው ቃል በቅዱስ ጽሑፍ ውስጥ አይገኝም”13 በማለት አምኖ ተቀብሏል። አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስም ሆነ ወልድ ከአብ ጋር በባሕሪ አንድ ናቸው ለማለት በዚህ ቃል አይጠቀምም። ይህ ቃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወዳልሆነ፣ እንዲያውም ፀረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወደሆነ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ለመምራት የረዳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አገላለጽ ነው።
ከቁስጥንጥኒያው ጉባኤ በኋላም እንኳን የሥላሴ ትምህርት በሕዝበ ክርስትና በሙሉ ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ “በምዕራቡ ዓለም . . . በመጀመሪያው የቁስጥንጥኒያ ጉባኤ በተላለፈው ድንጋጌ ረገድ አጠቃላይ ዝምታ የሰፈነ ይመስላል”14 ይላል። ይኸው ኢንሳይክሎፒድያ የጉባኤው [የቁስጥንጥኒያ] ድንጋጌ እስከ ሰባተኛው ወይም እስከ ስምንተኛው መቶ ዘመን ድረስ በምዕራቡ ዓለም በሠፊው ዕውቅና እንዳላገኘ ይገልጻል።
ምሁራንም ለሥላሴ እንደ መደበኛ ፍቺና ድጋፍ ተደርጎ ዘወትር የሚጠቀሰው የአትናቴዎስ ቀኖና የተጻፈው በራሱ በአትናቴዎስ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ብዙ ቆይቶ በአንድ ያልታወቀ ደራሲ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦
“ድንጋጌው እስከ 12ኛው መቶ ዘመን ድረስ በምሥራቃዊው ቤተ ክርስቲያን ዘንድ አይታወቅም ነበር። የአትናቴዎስ ድንጋጌ (በ373 በሞተው) በአትናቴዎስ እንዳልተጻፈና ምናልባት በ5ኛው መቶ ዘመን በደቡባዊ ፈረንሳይ የተጠናቀረ ሳይሆን እንደማይቀር ከ17ኛው መቶ ዘመን ወዲህ ያሉ ምሁራን ባጠቃላይ ተስማምተዋል። . . . በ6ኛውና በ7ኛው መቶ ዘመናት ይህ ድንጋጌ መጀመሪያ ተጽእኖ የነበረው በደቡባዊ ፈረንሳይና በስፔይን ይመስላል። ድንጋጌው በ9ኛው መቶ ዘመን በጀርመን፣ ጥቂት ቆይቶም በሮም ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ ተሠርቶበታል።”15
እንዴት ተስፋፋ?
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አዝጋሚ ዕድገቱን ያገኘው በመቶ በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ ነው። ከክርስቶስ በፊት አያሌ መቶ ዓመታት አስቀድሞ እንደኖረው እንደ ፕላቶ የመሳሰሉት የግሪክ ፈላስፋዎች የሥላሴ ጽንሰ ሐሳቦች ቀስ በቀስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ሾልከው ገቡ። የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል፦
“የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ቀስ በቀስና ከጊዜ አንፃርም በኋላ የተፈጠረ እንደነበረ እናረጋግጣለን፤ መነሾውን ወይም መሠረቱን ያገኘው በአይሁድና በክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ዘንድ ሙሉ በሙሉ ከማይታወቁ ምንጮች መሆኑን፤ ክርስትናን ከፕላቶ ትምህርት ጋር ለማዋሃድ በሚጥሩ አበው አማካኝነት እንዳደገና በክርስትና ላይ ተጣብቆ እንደተዳቀለ፤ በጀስቲን ዘመንና ከዚያም በኋላ ብዙ ቆይቶ ወልድ ከአብ የተለየና የበታች መሆኑ በሁሉም ዘንድ የሚሰጥ ትምህርት እንደነበረና ከዚያም በኋላ መጀመሪያ ብቅ ብሎ የነበረው ያልተነቃበት የሥላሴ ንድፈ ሐሳብ ጥላ ብቻ እንደነበረ እናረጋግጣለን።”16
ከፕላቶ አስቀድሞ በባቢሎንና በግብፅ በሦስት በሦስት ቡድን የሚመለኩ አማልክት ወይም ሥላሴዎች የተለመዱ ነበሩ። የቤተ ክርስቲያን ሰዎች በሮማው ዓለም የነበሩ የማያምኑ ሰዎችን ለመማረክ ያደረጉት ጥረት የእነዚያ [ባቢሎናዊና የግብፅ] አስተሳሰቦች ቀስ በቀስ ወደ ክርስትና እንዲገቡ አድርጓል። ይህም የኋላ ኋላ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር እኩል ናቸው የሚለው እምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል።a
“ሥላሴ” የሚለው ቃል ራሱም ተቀባይነት ያገኘው ቀስ በቀስ ነበር። በሶርያ አንጾኪያ አቡን የነበረው ቴዎፍሎስ ትርጉሙ ሦስትነት ወይም ሥላሴ ማለት የሆነውን ትሪያስ የሚል ቃል በግሪክኛ ጽፎ ያስተዋወቀው በሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ነበር። ከዚያም በሰሜን አፍሪካ የምትገኘው የካርቴጁ የላቲን ጸሐፊ፣ ተርቱልያን በጽሑፎቹ ውስጥ “ሥላሴ” የሚል ትርጉም ያለውን ትሪኒታስ ወደ ጽሑፎቹ አስገባ።b ይሁን እንጂ ትሪያስ የሚለው ቃል በመንፈስ በተጻፉት የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያልተገኘ ሲሆን ትሪኒታስ የሚለው ቃል ደግሞ ቩልጌት ተብሎ በሚጠራው የላቲን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ አልተገኘም። ሁለቱም አገላለጾች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አልነበሩም። የሆነ ሆኖ “ሥላሴ” የሚለው በአረማዊ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ቃል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፎች ሾልኮ ገባና ከአራተኛው መቶ ዘመን በኋላ የቀኖናቸው ክፍል ሆነ።
ስለዚህ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖር አለመኖሩን ምሁራን በጥንቃቄ መርምረው ያገኙት ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለመሠረተ ትምህርቱ ከፍተኛ ግፊት ያደረጉት ዓለማዊና የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ናቸው። ዘ ክርስቲያን ትራዲሽን (የክርስትና ባሕል) በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ደራሲ ጃሮስላቭ ፔሊካን “እነርሱን ራሳቸውን በሚመስሉ ኃይሎች ተገሰጹ እንጂ በክርክሩ የሚነሱት መንፈሳዊ ጉዳዮች የማይጠቅሳቸው ሰዎች የክርክሩን ውጤት ለመወሰን ሲያሰፈስፍ ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ታይተዋል። ብዙውን ጊዜ መሠረተ ትምህርቱ የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካና የታላላቅ ሰዎች ግጭቶች ሰለባ ወይም ውጤት ይመስላል” በማለት ያሳስባሉ።17 የየል ፕሮፌሰር ኢ ዎሽበርን ሆፕኪንስ “የመጨረሻው ተቀባይነት ያገኘው የሥላሴ ፍቺ ጉዳይ በአብዛኛው የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ጉዳይ ነበር” በማለት ገልጸውታል።18
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አምላክ ከሁሉም የበላይና አቻ የሌለው ነው ከሚለው ቀላል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ሲወዳደር ምክንያተ ቢስ ነው! አምላክ ራሱም “በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?” ብሏል።—ኢሳይያስ 46:5
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ምን ያመለክታል?
የሥላሴ መሠረተ ሐሳብ ቀስ በቀስ እያደገ መምጣቱ ምን ያመለክታል? ኢየሱስ በእውነተኛው ክርስትና ላይ እንደሚመጣ የተነበየው ክህደት ክፍል እንደነበር ያመለክታል። (ማቴዎስ 13:24-43) ሐዋርያው ጳውሎስም የክህደትን መምጣት እንደሚከተለው በማለት ተንብዮአል፦
“ሰዎች ንጹሑን ቃል ለመስማት የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን [ለአዲስ ወረት በመጎምጀት የካቶሊክ ጀሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ] እነርሱ ራሳቸው የሚወዱትን ነገር የሚነግሩአቸውን አስተማሪዎች ይሰበስባሉ። እውነትን መስማት ትተው [ወደ ተረት ይመለሳሉ የካቶሊክ ጀሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ]”—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4
ከእነዚህ ተረቶች አንዱ የሥላሴ ትምህርት ነው። ለክርስትና ባዕድ የሆኑና ቀስ በቀስ የተስፋፉ ሌሎች ተረቶችም የሰው ነፍስ ያለመሞት ባሕሪ አላት የሚለው ትምህርት፣ መንጽሔና የክርስትና ጥምቀት ባለመቀበላቸው ምክንያት ወደ ሰማይ እንዳይገቡ የታገዱ ነፍሳት መኖሪያ ተብሎ የሚታመን ሥፍራና በሲኦል እሳት ለዘላለም መሠቃየት ናቸው።
ስለዚህ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ምንድን ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ክርስቲያን መስሎ የቀረበ አረማዊ መሠረተ ትምህርት ነው። እሱም ሰዎችን ለማሳሳት፣ አምላክ ለሰዎች ግራ የሚያጋባና ሚስጥራዊ እንዲሆንባቸው ለማድረግ ሰይጣን ያመነጨው ነው። ይህም ሰዎች ሌሎች የሐሰት ሃይማኖት አስተሳሰቦችንና የተሳሳቱ ተግባሮችን ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኞች እንዲሆኑ አመቻችቶአቸዋል።
“በፍሬያቸው”
ኢየሱስ በማቴዎስ 7:15-19 ላይ ሐሰተኛ ሃይማኖትን ከእውነተኛ ሃይማኖት ለይታችሁ ለማወቅ የምትችሉበትን መንገድ እንዲህ ብሎ ገልጾአል፦
“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ (የተበላሸ) ፍሬ ያደርጋል። . . . መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።”
አንድ ምሳሌ ተመልከቱ። ኢየሱስ በዮሐንስ 13:35 ላይ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። በተጨማሪም በ1 ዮሐንስ 4:20 እና 21 ላይ አምላክ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈው ቃሉ እንደሚከተለው ይናገራል፦
“ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትዕዛዝ ከእርሱ ዘንድ አለችን።”
እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ፍቅር ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚገልጸውን መሠረታዊ ደንብ በዚህ ምዕተ ዓመት በተደረጉት በሁለቱም የዓለም ጦርነቶችና በሌሎቹም ውጊያዎች ላይ ከደረሰው ነገር ጋር አነፃፅሩት። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ አንድ ዓይነት ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች በብሔራዊ ልዩነቶች ምክንያት በጦር ሜዳ ላይ ተጋጥመው እርስ በርሳቸው ተራርደዋል። በሁለቱም ተቃራኒ ወገኖች መሃል ያሉት ክርስቲያን ነን ባዮች ከመሆናቸውም ሌላ እያንዳንዱ ወገን አምላክ ከጎናችሁ ነው ብለው የሚነግሯቸው የካህናቶቻቸው ድጋፍ ነበራቸው። ይህ “የክርስቲያን” “ለክርስቲያን” መተራረድ የተበላሸ ፍሬ ነው። የክርስትናን ፍቅር የሚፃረርና የአምላክን ሕጎች መካድም ነው።—በተጨማሪም 1 ዮሐንስ 3:10-12ን ተመልከት።
የመጨረሻው ዋጋ መቀበያ ቀን
ስለዚህ ክርስትናን መካድ እንደ ሥላሴ ወደመሳሰሉት አምላካዊ ያልሆኑ እምነቶች ብቻ ሳይሆን አምላካዊ ወዳልሆኑ ተግባሮችም መርቷል። ሆኖም ኢየሱስ “መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል” ብሎ ስለተናገረ የመጨረሻውን ዋጋ መቀበያ ቀን የሚመጣበት ጊዜ አለ። ለዚህም ነው የአምላክ ቃል እንደሚከተለው በማለት አጥብቆ የሚያሳስበን፦
“ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ [ከሐሰት ሃይማኖት] ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።”—ራእይ 18:4, 5
በቅርቡ አምላክ የፖለቲካ ባለሥልጣኖች በሐሰት ሃይማኖት ላይ እንዲዞሩባት ‘አሳቡን ወደ ልባቸው ያስገባል።’ እነሱም “ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሏታል።” (ራእይ 17:16, 17) የሐሰት ሃይማኖት ስለ አምላክ ከሚያስተምረው አረማዊ ፍልስፍና ጋር ለዘላለም ይጠፋል። ኢየሱስ በዘመኑ “እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ብሎ እንደተናገረው ሁሉ አምላክም ለሐሰት ሃይማኖተኞች እንዲሁ እንደሚላቸው ያህል የሚቆጠር ነው።—ማቴዎስ 23:38
በመጨረሻው ማንኛውም ክብርና ውዳሴ ኢየሱስ “ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንህ” በማለት ለጠራው አምላክ ይሰጥ ዘንድ እውነተኛ ሃይማኖት ከአምላክ የጥፋት ፍርድ ይተርፋል። “ስምህ ይሖዋ የሆንከው በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል ነህ” ብሎ በተናገረው መዝሙራዊ ተለይቶ የተጠቀሰውም እርሱ ነው።—ዮሐንስ 17:3፤ መዝሙር 83:18
ማጣቀሻዎች
1. Encyclopædia Britannica, 1971, Volume 6, page 386.
2. A Short History of Christian Doctrine, by Bernhard Lohse, 1963, page 51.
3. Ibid., pages 52-3.
4. New Catholic Encyclopedia, 1967, Volume VII, page 115.
5. A Short History of Christianity, by Martin E. Marty, 1959, page 91.
6. A Select Library of Nicene and Post-Nicene Fathers of the Christian Church, by Philip Schaff and Henry Wace, 1892, Volume IV, page xvii.
7. A Short History of Christian Doctrine, page 53.
8. A Short History of Christianity, page 91.
9. The Church of the First Three Centuries, by Alvan Lamson, 1869, pages 75-6, 341.
10. Second Century Orthodoxy, by J. A. Buckley, 1978, pages 114-15.
11. New Catholic Encyclopedia, 1967, Volume VII, page 115.
12. Ibid., Volume IV, page 436.
13. Ibid., page 251.
14. Ibid., page 436.
15. The New Encyclopædia Britannica, 1985, 15th Edition, Micropædia, Volume 1, page 665.
16. The Church of the First Three Centuries, page 52.
17. The Christian Tradition, by Jaroslav Pelikan, 1971, page 173.
18. Origin and Evolution of Religion, by E. Washburn Hopkins, 1923, page 339.
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሥላሴ ልታምን ይገባሃልን? በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር የታተመውን ብሮሹር ተመልከቱት።
b በዚህ በተከታታይ በቀረበ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባለፉት ርዕሰ ትምህርቶች ላይ እንደተገለጸው ቴዎፍሎስ ተርቱልያን በእነዚህ ቃላት ቢጠቀሙም ዛሬ በሕዝበ ክርስትና የሚታመነው ሥላሴ በሐሳባቸው አልነበረም።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የፖለቲካ ባለሥልጣኖች በሐሰት ሃይማኖት ላይ እንዲዞሩባት ያደርጋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛው ሃይማኖት ከአምላክ ፍርድ ይድናል